| ድሬዳዋን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ |
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
የድሬዳዋ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ የድሬዳዋ መቶ አምስተኛ ዓመት በዋነኝነት የሚከበረው ከተማዋ በዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብ ለማስቻል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የከተሞች እድገት ታሪክ ድሬዳዋ በፕላን ከተመሰረቱ ቀደምት ከተሞች አንዷ መሆኗን የገለፁት አቶ አብዱልአዚዝ ከተማዋ በታሪካዊ መስህብነታቸው የሚታወቁ የፓርክ ኤፒክ፣ ለገኦዳ፣ ጎዶ አጀዋ፣ እንቁፍቱና ሌሎችም ታሪካዊ ቅርሶች መገኛ መሆኗን አመልክተዋል፡፡
ከረጅም ዓመታት በፊት በከተማዋ ይኖሩ የነበሩ የውጭ አገር ዜጎች ይኖሩባቸው የነበሩ አካባቢዎች ዛሬም በውጭ አገር ዜጎች የተሰጣቸውን ስያሜ ይዘው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ከተማዋ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባሻገር የውጭ ዜጎችም በመቻቻልና በመከባበር ይኖሩባት እንደነበር ያመለክታሉ፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡና ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ተሰልፈው የተዋጉ አፍሪካውያን መታሰቢያ መቃብር (የአፍሪካ መቃብር) በከተማዋ ውስጥ ነምበር ዋን እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ መቶ አምስተኛ ዓመት መከበር ከተማዋ በዓለም ቅርስነት እንድትመዘገብ ከማድረግ ባሻገር የተጀመረው የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ጭምር መሆኑንም ከንቲባው አስረድተዋል፡፡ ይኸውም የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ፣ የጤና አገልግሎትንና የትምህርት ሽፋንን (በብዛትና በጥራት) ለማስፋፋት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው ብለዋል፡፡ እንደ ከንቲባው ገለፃ፣ በከተማዋ አንድ ዘመናዊ ሪፈራል ሆስፒታልና ትልቅ የስብሰባ ማዕከል ለመገንባት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅና ውጤታማ ለማድረግ በዓሉ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የኦሮሚያና የሶማሌ ብሔራዊ ክልሎች በሚያዋስኗት ድሬዳዋ የሚገነባው ሪፈራል ሆስፒታል ከከተማዋ ኗሪዎች ባሻገር ለአጎራባች ክልሎችም ከፍተኛ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡ አቶ አብዱልአዚዝ አክለውም "መንግስት ለከተማዋ እድገት በሰጠው ትኩረት የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማስፋፋት በተለይም በክረምት ወቅት በተደጋጋሚ የሚከሰተው ጎርፍ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ለመከላከል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው" ብለዋል፡፡ በከተማዋ ያለው የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው የከተማዋ መስተዳድር ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማስፋፋት መቶ አርባ ሔክታር መሬት ለባለሃብቶች ማዘጋጀቱን ተናገረዋል፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቶች በዚህ እድል በመጠቀም ከተማዋን፣ አገሪቱንና ራሳቸውን ለመጥቀም፣ ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ሐዲድ መዘርጋት ለመቆርቆሯ ምክንያት የሆነው የድሬዳዋ ከተማ በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ታሪክ የጨርቃ ጨርቅና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቀደም ብለው የተቋቋሙባት ሲሆን እነዚህ ቀደምት እንቅስቃሴዎች ለከተማዋ የንግድና ኢንቨስትመንት መሰረት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በከተማዋ የተለያዩ በፕላን የተሰሩ መኖሪያ ሰፈሮችና ዘመናዊነትን የተላበሱ መንገዶች እንዲሁም ሌሎች ታሪካዊ እሴቶች መኖራቸው የቱሪስት መስህብ እንዲኖራት ማድረጋቸውን በመጥቀስ ከተማዋ ከታሪካዊ ቅርሶች ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የከተማዋ መስተዳድርና ኗሪው ጥረት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ..በዓላችንን የምናከብረው የከተማችንን ገጽታ በመቀየር፣ ምቹ የልማት እንቅስቃሴ በመቀየስና የተቀረፁ ፕሮጀክቶችን በመፈጸም ነው፡፡ ካስቀመጥናቸው የበዓሉ አከባበር ዓላማዎች በመነሳት የምናከናውናቸው ተግባራት መልካም እሴቶቻችንን፣ ታሪካችንንና ባህላችንን በማስተዋወቅ ወደ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው.. በማለት የድሬዳዋ መቶ አምስተኛ የምስረታ በዓል አካል የሚሌኒየም በዓል እንደሆነና የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ይሳኩ ዘንድም መንገድ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የከተማዋ ጊዜያዊ አስተዳደር ለኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታን በመፍጠር ባለሃብቶች በከተማዋ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ለዚህም መስተዳድሩ መሬትና የሥራ ፈቃድ መስጠት በኩል እያደረገ ባለው በጎ ምላሽ የተጀመሩ ፋብሪካዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Forums |
| Contact Us |