| የሴት ማሳጅ ሠራተኞች ፈተና |
|
|
| Sunday, 22 June 2008 | |
![]() ቤዛ ገረመው ![]() ራሔል ሙሉቀን ስለማሳጅ ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማችው ከአዲስ አበባ ወደ አዋሳ ስትጓዝበት በነበረ መኪና ውስጥ እንደሆነ ታስታውሳለች፡፡ አጠገቧ የተቀመጠችው ልጅ የማሳጅ ባለሙያ ነበረችና ስለ ሥራዋ በዝርዝር አጫወተቻት፡፡ ራሔል ሙሉቀን እንደምትለው ባጋጣሚ ያገኘቻትና በኋላም በተደጋጋሚ አግኝታት ስለማሳጅ ያጫወተቻት ወጣት ባለሙያ ስለሥራው ጥሩነት ብቻ አልነበረም የነገረቻት፡፡ በሥራው ስትሰማራ ሊገጥማት የሚችለው ፈተና አስረድታታለች፡፡ "ሙያው አዲስ እንደሆነና ብዙ ሰው ስላልተሰማራበት በደንብ ገንዘብ ላገኝ እንደምችል ነገረችኝ፡፡ እንዲያውም እሷ እንደነገረችኝ አንዳንድ የውጭ ዜጎች ከመደበኛ ክፍያው ውጭ እስከ 500 ብር ድረስ ጉርሻ ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን ሥራው ሴትነትን የሚፈትን እንደሆነና ከፈተናውም ለማምለጥ ብልህና ጠንካራ መሆንን እንደሚጠይቅ መከረችኝ፡፡" ባለሙያዋ ለእማኝነት የታወቁ ዘፋኞችንና ባለሥልጣናትን ስም እየጠራች ማሳጁ ከተሰራላቸው በኋላ የወሲብ ጥያቄ እንደሚጠይቋትም አልደበቀቻትም፡፡ በመሆኑም ራሔል ወደ ሥራው ስትገባ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ቢገጥማት ተራና የተለመዱ መሆናቸውን በማሰብ የራሷን አቋም እንድትወስድ መክራታለች "መቶና ሁለት መቶ ብሮች እንዳያታልሉሽ ገላውን ካሸሽለት ወንድ ጋር እንኳን መውጣት ብትፈልጊ ከአበሻ ወንድ ጋር እንዳትወጭ፡፡ አበሻ ከሆነ ነገ እገሌ ሆቴል ማሳጅ የምትሰራውን ሴት እኮ አውጥቻታለሁ እያለ ያወራል፡፡ ዓላማው እንኳን ቢኖርሽ ደህና ብር ተቀብለሽ ከውጭ ዜጋ ጋር መውጣት ይሻልሻል ብላ መከረችኝ፡፡" ራሔል በወቅቱ የፍቅር ጓደኛ ነበራት፡፡ የማሳጅ ሙያውን ተምራ ወደ ሥራው ብትገባም ከሥራዋ ውጭ የወሲብ ጥያቄ ከሚያቀርብላት ወንድ ጋር እንደማትወጣ ለራሷ ቃል ገብታ ትምህርቷን ጀመረች፡፡ በወር 300 ብር እየከፈለች ለወራት ትምህርቷን ተከታትላ አጠናቀቀች፡፡ አንዳሰበችው ግን በሙያው ተሰማርታ ገንዘብ ልታገኝበት አልቻለችም፡፡ ገና ትምህርቱን ስትጀምር "ለዕውቀት ያህል ተማሪው እንጂ አትሰሪበትም" ይላት የነበረው የፍቅር ጓደኛዋ ወደ ሥራው እንዳትገባ ከለከላት፡፡ "የሱን ገላ ሳሸው ደስ ይለዋል፤ እንኳን ተማርሽ ይለኛል፡፡ በሙያው ተሰማርቼ የሌላ ወንድ ገላ እንዳሽና የገቢ ምንጬ እንዲሆን ግን በጭራሽ ሊፈቅድልኝ አልቻለም፡፡ ወይ ሥራውን፣ ወይ እኔን ምረጭ አለኝ፡፡ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ሂደት ላይ የነበርኩና ምናልባት ከተሳካልኝ ሙያው እዚያ እንደሚጠቅመኝ ብዙዎች ይነግሩኝ ነበር፡፡ ይሁንና ወደ ውጭ መውጣቱም ስላልተሳካ እዚህ መሥራቱንም ጓደኛዬ ስለተቃወመኝ ተውኩት"፡፡ በፍቅረኛዋ ተቃውሞ ምክንያት ወደማሳጅ ሥራው ለመግባት ያልቻለችው ራሔል ዛሬ ሙያዋ ለባሏ ብቻ ደስታ መፍጠሪያ መሆኑን ወልዳ በተኛችበት ሆስፒታል አግኝቼ ባናገርኳት ወቅት ገልፃልኛለች፡፡ ሌላዋ ያነጋገርኳት ወይዘሪት ሔለን በቀለ ግን ፈተናዎቹን ሁሉ አልፋ የራሷ የማሳጅ መሥሪያ ማዕከል ለመክፈት የበቃች ሴት ሆናለች፡፡ ትኖርበት በነበረው አዋሳ ከተማ ዋቢሸበሌ ሆቴል ውስጥ በሱቅ ሻጭነት ትሰራ ነበር፡፡ ስለማሳጅ ያወቀችውም እዚያ ሆቴል ውስጥ የማሳጅ አገልግሎት ከምትሰጥ ብቸኛ ሴት ነበር፡፡ በሆቴሉ የመዋኛ ገንዳ አጠገብ ትሰራበት ወደነበረው ሱቋ ብዙ ሊዝናኑ የሚሄዱ የውጭ ዜጎች የማሳጅ ሠራተኛዋን እንድታገናኛቸው ይጠይቋት ነበር፡፡ በተደጋጋሚም በስልክ እየጠራች ከደንበኞቿ ጋር ለሥራ አገናኝታታለች፡፡ በዚህ አጋጣሚም ጥሩ ገበያ እንዳለው በማሰብ ወደ ሥራው ለመግባት ወሰነች፡፡ ይሄንን ስትወስን (ከዘጠኝ ዓመት በፊት) ህብረተሰቡ ለሥራው የነበረው አመለካከት በጣም አስፈሪ እንደነበር አስታውሳለች፡፡ "ሥራዋ ምንድን ነው ሲባል፣ ማሸት፡፡ እንዴት ነው የምታሸው ሲባል ልብሱን አውልቆ ተኝቶ፤ አንድ ክፍል ውስጥ ሁለቱ ብቻቸውን፤ የሚለው ነገር ከእኛ ባህል ጋር ሲታይ በጣም ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ ሰው ከሴተኛ አዳሪነት ለይቶ አያየውም፡፡ የምሰማው ነገር ያስፈራኛል፡፡ ልጅቱን ሳነጋግራትም ሰዎች የሚያወሩትን ነገር ደግማ ነበር የምትነግረኝ፡፡ ፣ሰው እንዲህ ታደርጋለች እኮ እያለ ሊያወራብሽ ይችላል፡፡ ነገር ግን እንቺ እነሱ የሚሉሽን ሆነሽ ካልተገኘሽ በህይወትሽ ምንም ነገር ለውጥ አያመጣም፡፡ ለሰው ወሬ አትጨነቂ ብላ መከረችኝ፡፡፣ ስለዚህ ወደ ሙያው ለመግባት ወሰንኩ፡፡" ሔለን እንደምትለው ለመማር በወሰነችበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የማሳጅ ትምህርት የሚሰጥበት ቦታ አንድ ነበር፡፡ በመሆኑም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አሜሪካ ኤምባሲ ጎን ወደሚገኘው እንጦጦ መካነኢየሱስ ት/ቤት በመሄድ ስልጠናውን አገኘች፡፡ ከእሷ ጋር ትምህርቱን ጨርሰው የወጡት አራት ሴቶች ብቻ ነበሩ፡፡ በርካቶቹ ትምህርታቸውን ያቋረጡት ከቤተሰቦቻቸው በነበረባቸው ግፊትና ህብረተሰቡ ለሥራው በነበረው አመለካከት ሊሆን እንደሚችል ትገምታለች፡፡ የስልጠና ጊዜዋን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ አዋሳ ተመልሳ ፒና ሆቴል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የማሳጅ ሥራ ጀመረች፡፡ ከቤተሰቧም ሆነ ከፍቅረኛዋ ተቃውሞ ቢገጥማትም ፣በፈለግሁት ሙያ የመሰማራት መብት አለኝ፣ በሚል ሃሳቧ ፀናች፡፡ የፍቅር ጓደኛዋ በወቅቱ ለማሳመን ከባድ ቢሆንም እንደተሳካላት ትናገራለች፡፡ "የህክምና ባለሙያ ብሆን ወንዶችን አታክሚም አትለኝም አልኩት፡፡ እኔ ጋ መታሸት ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ለመዝናናት ብቻ ሳይሆን የተለያየ በሽታ ያለባቸው እርዳታ ፈልገው የሚመጡ አሉ፡፡ ስለዚህ በስራዬ ሰዎችን እየረዳሁ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ምክንያትህ ለምን ወንድ ልጅ ታሻለሽ የሚል ከሆነ ልንለያይ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም በሁለታችን ግንኙነት መካከል ችግር ሊፈጥር የሚችለው ስራዬ ከወንዶች ጋር የሚያገናኘኝ ስለሆነ መሆኔ እንደሌለበት አምናለሁ፡፡ እኔ ከሌላ ወንድ ጋር መውጣት ከፈለግሁ የሚያግደኝ ነገር የለም፡፡ የቢሮ ሠራተኛ መሆኔ፣ የቤት እምቤት መሆኔ ወይም የማሳጅ ሠራተኛ መሆነ ልዩነት አያመጣም የሚል አስተሳሰብ አለኝ አልሁት፡፡ በመጨረሻ አቋሜን እንደማያስቀይረኝ ሲያውቅ በኔ ሃሳብ ተስማምቶ እስካሁን በጓደኝነት አብረን እንኖራለን" ትላለች፡፡ ከስድስት ዓመት በላይ ኢትየጵያ ውስጥ ከሰራች በኋላ በሙያው የተሻለ ትምህርት ለማግኘት ወደ ጣሊያን ሃገር አምርታለች፡፡ ሔለን እንደምትለው እኛ ሃገር አንድ እንኳን ማሰልጠኛ ባልነበረበት ደረጃ በአውሮፓ ሃገራት ግን የማሳጅ ስልጠና በኮሌጅ ደረጃ ይሰጣል፡፡ እሷ ኮሌጅ ገብታ የመማር እድል አልነበራትም፡፡ በሙያው የተሰማሩ ሰዎች ጋ በመቅረብና ከልምድ ካላት የተሻለ እውቀት ለመቅሰም ሞክራለች፡፡ ጣሊያን ሃገር ተቀጥራ በሰራችባቸው የጂምናዝየም ቦታዎችም ከእኛ ሃገር የሚለዩ በርካታ ነገሮችን እንዳስተዋለች ትናገራለች፡፡ "ውጭ ሃገር ማሳጅ ሠራተኞች ወንዶችም ሴቶችም ናቸው፡፡ ተጠቃሚዎችም ፆታ አይመርጡም፡፡ ከማሳጁ የሚያገኙትን ጥቅም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እኛ ሃገር ግን ብዙ ሰው መታሸት የሚፈልገው በሴቶች ነው፡፡ ወንዶችን ለምን ሴት እንደሚፈልጉ ስትጠይቂያቸው እንዴት ወንድ ገላየን ይነካኛል ይሉሻል፤ እንዲያውም ወንድ ገላየን ቢያሻሸኝ ግብርሰዶማዊ የሆንኩ ይመስለኛል ያለኝም አለ፡፡ ሴቶች ደግሞ የባህሉም ተፅዕኖ ይመስለኛል ልብሳቸውን አውልቀው ወንድ ጋ መቅረቡን አይፈልጉትም፡፡ ስለዚህ እኔም አምስት ሴት ሠራተኞች ሲኖሩኝ ያለኝ ወንድ ሠራተኛ አንድ ብቻ ነው፡፡ እሱም ምናልባት ሴት እንድታሻቸው የማይፈልጉ የእስልምና እምነት ተከታይ ደንበኞቻችን ሲመጡ በቀጠሮ ነው የሚሠራው" ሰዎች ሴት ብቻ ትሸን በሚሉት ሃሳብ ግን ሔለን እንደማትስማማ ትናገራለች፡፡ አንድ ሰው በትክክል በመታሸቱ የሚያገኘውን ጥቅም ብቻ ፈልጎ እስከመጣ ድረስ ፆታ ጥያቄ መሆን የለበትም ባይ ናት፡፡ አንድ ሰው ታሞ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ቢሄድ የሚያክመኝ ዶክተር "ወንድ ነው ወይስ ሴት ናት?" ብሎ አይጠይቅም "የምንፈልገው ሙያውን ብቻ እስከሆነ ድረስ ጥያቄያችን ባለሙያው ምን ያህል ጎበዝ ነው? የሚለውን ነው፡፡ ፆታው ሳይሆን ችሎታው ነው ሊጠየቅ የሚገባው"፡፡ ሲወራ እንደሚሰማው በሥራ ላይ እያለች የወሲብ ጥያቄ ያቀረበላት ሰው ይኖር እንደሆነም ጠይቄያት ነበር፡፡ ትክክለኛና ሙያዊ ማሳጅ ከተደረገለት አንድ ሰው ብልቱ ሊቆምበትና ማሳጁን ከጨረሰ በኋላም ሽንቱ ሊመጣ የግድ እንደሆነ ሔለን ትጠቅሳለች፡፡ ይህ የሚሆነውም ማሳጅ በሰውነት ውስጥ የደም ዝውውርን ስለሚጨምር እንደሆነ ትናገራለች፡፡ "በመሆኑም ሲታሽ ብልቱ የቆመበት ወንድ ወሲብ ፈለገ ማለት ሳይሆን የማሳጁ ውጤት ነው" ትላለች፡፡ ይሁንና አልፎ አልፎ የወሲብ ጥያቄ የሚያቀርቡ ወንዶች እንዳሉ አልሸሸገችም፡፡ "አንዳንድ ጊዜ ከሰሙት ነገርና ያለበት ሁኔታ እሱ ወንድ እኔ ሴት ሁኜ ልብሱን አውልቆ አንድ ክፍል ውስጥ ሆነን ገላውን እያሸሁት በመሆኑ የወሲብ ስሜቱ ተቀስቅሶ ሊሆን ይችላል ጥያቄውን የሚያነሳልኝ፡፡ ያኔ ግን ደንበኛየን አላስደነግጥም፡፡ አስረዳዋለሁ፡፡ ለሰኮንዶች ደስታ ተብሎ በኋላ የሚመጣውን የህይወት መከራ መርሳት እንደሌለበት፣ ይሄንን እንዳያደርግ ጊዜው ራሱ እንደሚያስገድደውና ከሴት ጋር መውጣት ከፈለገ ደግሞ ቦታው ሌላ እንደሆነ እነግረዋለሁ፡፡" የሚል ምላሽ ሰጥታኛለች፡፡ ሔለን እንደምትለው ጌቱ ህንፃ ላይ በባለቤትነት በምትሰራበት ሮዛ ማሳጅ ሴንተር ውስጥ በብዛት የሚስተናገዱት ደንበኞቿ ወንዶች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎም ሴቶችና እርጉዝ ሴቶችም ጭምር ለመታሸት እንደሚመጡም ገልፃለች፡፡ በእርግዝና ወቅት ሴቶች ስቲም መጠቀም አይፈቀድላቸውም፡፡ በሌላ በኩል ግን ማሳጅ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ሳይንሱ እንደሚያዝ ሔለን ትናገራለች፡፡ "ነፍሰጡር ሴት ከአራት ወር በፊት (ፅንሱ ሳይረጋጋ) ማሳጅ እንድታደርግ አይመከረም፡፡ ምክንያቱም የደም ዝውውርን ስለሚጨምር ውርጃ ሊከሰት ይችላል፡፡ ከአራት ወሯ በኋላ ግን ብትታሽ እንዲያውም በእርግዝና ጊዜ በሚኖር የሆርሞን ለውጥ ምክንያት የሚከሰትባትን ድካም፣ የመንፈስ አለመረጋጋት፣ ጥሩ እንቅልፍ አለማግኘትና የምግብ አለመፈጨት ችግር ተቋቁማ እንድታልፍ ይረዳታል" ማሳጅ መሥራት ጉልበት እንደሚጠይቅ የምትናገረው ሔለን ሥራውን በጀመረችባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት እስከ ስምንት ሰው ማሸት ትችል የነበረ ሲሆን አሁን ግን በቀን ከስድስት ሰው በላይ ማሸት እንደሚከብዳት ትናገራለች፡፡ አካላዊ ጥንካሬዋን ለማጎልበትም ጉልበት ሰጭ ምግቦችና ወተት እንደምትመገብ ገልፃልኛለች፡፡ ይህም ሆኖ ግን ማሳጅ ከጉልበት ይልቅ ቴክኒክን መጠቀም እንደሚፈልግ ባለሙያዋ ትናገራለች፡፡ "ጉልበት የሚያስፈልገው ሥራው ለረዥም ሰዓት ተቁሞ የሚሰራ በመሆኑ ነው" በመጨረሻ ያነጋገርኳት ከቤት እመቤትነት ወጥታ ወደ ማሳጅ ሥራ የገባችውን ቤዛ ገረመውን ነው፡፡ ትዳር መስርታ የሁለት ልጆች እናት ከሆነች በኋላ በሙያው ሰልጥና ተቀጥራ መሥራት እንደጀመረች ገልፃልኛለች፡፡ ቤት ውስጥ ቁጭ ብላ ከምትውል ሙያውን ተምራ ወደ ሥራው እንድትገባ የባሏም ማበረታቻ እንደነበረበት ታስታውሳለች፡፡ ባለቤቷ እንደሌሎቹ ሴቶች ወደሙያው እንዳትገባ ያልተቃወማት ምናልባት የሙያው ባለቤት የሆነችው ዘመዷ ዘወትር ቤታቸው ስትሄድ ስለሙያዋ ስለምታወራላቸውና ገንዘብም እንደሚገኝበት ስለምትነግረው ሊሆን እንደሚችል ትገምታለች፡፡ ቤዛ እቤት ውስጥ ከመዋል ሥራ ላይ ወደመዋል ከተሸጋገረች ሁለት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ ለሥራ ወጥቶ ወደ ቤት መመለሱ የአዕምሮ እረፍት እንደሚሰጥ ገልፃ የማሳጅ ሥራ ጉርሻ ያለው በመሆኑም ለቤቷና ለልጆቿ የፈለገችውን እንድታደርግ የሚያስችላት ገንዘብም ታገኛለች፡፡ እንደ ቤዛ አገላለፅ አንድ ሰው ከመደበኛ ክፍያው ውጭ እስከ ሁለት መቶ ብር ድረስ ይሰጣል፡፡ ባለቤቷን በዕረፍት ጊዜዋ እንደምታሸውና ደስተኛም እንደሚሆን የምትናገረው ቤዛ ሴት ልጅ ለባሏም ሆነ ለልጆቿ እውቀቱ ቢኖራት አስፈላጊ እንደሆነ ትመክራለች፡፡ "ማሳጅ እየተደረገ ያደገ ልጅ ከሌሎች በእድገት ፍጥነቱ፣ በሰውነት ቅርፁ የተለየ ይሆናል፡፡ የአእምሮው እድገትም ፈጣን እንደሚሆንም ሳይንሱ ይገልፃል፡፡ ባለቤትሽንም ብታሽው ደስተኛና ጤነኛ እንዲሆን ትረጂዋለሽ" ትላለች፡፡ ቤዛ፣ እናቷ ፀጉሯን እያሻሸች ታስተኛት እንደነበር ታስታውሳለች ለእሷ ልጆች ይሄንን አታደርግም፡፡ የነርቭ መጨረሻዎች የሚገኙበትን ውስጥ እግራቸውን እያሻሸች በቀላሉ እንቅልፍ እንዲወስዳቸው ታደርጋለች፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |