Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow “የክልሉን ገጽታ የሚያበላሽ አንድ...
“የክልሉን ገጽታ የሚያበላሽ አንድ... Print E-mail
Sunday, 22 June 2008
Image“የክልሉን ገጽታ የሚያበላሽ አንድ የቀረን የድለላ እንቅስቃሴን ማስወገድ ነው”
 
አቶ ዓለሙ ስሜ
የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮምሽነር

አቶ ዓለሙ ስሜ የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮምሽነር ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በልማት አስተዳደር ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ወስደዋል፡፡ ከባህርዳር የመምህራን ኮሌጅ በሒሣብ ዲፕሎማ አላቸው፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በክልሉ የኢንቨስትመንት ጉዳዮችና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል፡፡ 
ሪፖርተር፡- ትክክለኛ ባለሃብት ማን ነው?

አቶ ዓለሙ፡-
ትክክለኛ ባለሃብት ማለት ለራሱም ሆነ ለአገሪቷ እሴት የሚጨምር ሥራ የሚሠራ ማለት ነው፡፡ እሴት የሚጨምር ማለት ከምርት አንፃርም እሴት የሚጨምር እድገት የሚያመጣና ለአገር ለዜጋና ለራሱም የሚጠቅም ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለኢንቨስትመንት ከሚቀርበው ጥያቄ አንፃር እንዲህ ዓይነቱን ባለሃብትና ሌሎችን እንዴት ትለያላችሁ?

አቶ ዓለሙ፡-
ባለሃብቶችን በተለይ በቅድመ ኢንቨስትመንት ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ችግርም ነው እየገጠመን ያለው፡፡ ልማታዊና ልማታዊ ያልሆነውን ባለሃብት በተጨባጭ የምትለየው በሥራ ውስጥ ነው፡፡ በቅድመ ኢንቨስትመንት ለማጣራት ብዙ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ሙሉ ለሙሉ ግን በዚያ ሂደት ለመቆጣጠር አልተቻለም፡፡ ይህንን ለመቆጣጠር ስንጠቀምበት የነበረው በመጀመሪያ አካባቢ የባንክ ስቴትመንት ነው፡፡ የባንክ ስቴትመንት ማየት ከመጀመራችን በፊት ከባንክ የሚፃፍ ደብዳቤም ስናይ ነበር፡፡ አካውንቱ ውስጥ ገንዘብ አለው ወይ? መሥራት የሚችል ነው ወይ? በሚል ደብዳቤ ስንቀበል ነበር፡፡ በዚህ በአንድ ቀን ደብዳቤ ማንኛውም ሰው ገንዘብ ከየትም አምጥቶ አካውንቱ ውስጥ ያስገባና ደብዳቤውን ካስፃፈ በኋላ ገንዘቡን ወደወሰደበት ይመልሳል፡፡ በዚህ መቆጣጠር ስላልቻልን እንደገና ሌላ ብልሃት ምንድነው ብለን የተለየ መሠረታዊ የሥራ ሂደት ማሻሻያ በምንሠራበት ጊዜ ሌላ መፍትሔ ፈለግን፡፡ የተሻለ መፍትሔ ብለን የወሰድነው በተቻለ መጠን የእያንዳንዱን ሰው የኋላ ታሪክ ለማወቅ ሞከርን፡፡ ሁለተኛ ከባንክ ቤት የሚመጣው የአንድ ቀን መረጃ የስድስት ወርና ከዚያም በላይ ያለውን የገንዘብ እንቅስቃሴ (የገንዘብ ስቴትመንት) የሚያሳይ እንዲሆን አደረግን፡፡

የኋላ ታሪኩን ማጥናት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ካለን የሰው ኃይል፣ ካለን ሎጅስቲክ አንፃር እያንዳንዱን ባለሃብት ቤቱና የሥራ ድርጅቱ ድረስ በመሄድ ይሄ ሰው ምንድነው ብሎ ማጥናት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን የተቻለንን ያህል እንሄድበታለን፡፡ በተቻለ መጠን ሪፈረንሶችን እየወሰድን እናያለን፡፡ በተለይ በትልልቅ ነገሮች ላይ ግን ከባለሃብቱ ብዛት አንፃር አልተቻለም፡፡ ይህ የሚሆነው ለማናውቃቸው ባለሃብቶች ነው፡፡ ለሁሉም አናደርግም፡፡ ሁለተኛ የባንክ ስቴትመንት ማየት ጀመርን፡፡ እዚያ ላይ አሁንም ችግር ተፈጠረ፡፡ ከዚህ ተያይዞ የመጣው ችግር የውሸት መረጃ ማምጣት ነው፡፡   
   
ሪፖርተር፡- ይህ መረጃ የሚመጣው ከየት ነው? ከባንኮች ነው?

አቶ ዓለሙ፡-
ከባንኮች አይመስለኝም፡፡ የባንኮችን አስመስሎ ሄዲንግ ሌተር ይዘጋጃል፡፡ ስቴትመንት ይዘጋጃል፡፡ ፎርጅድ ከሚሠሩ አካላት ይመስለኛል፡፡ ምንጮቹን ፖሊስ የሚደርስበት ይሆናል፡፡ ባንኮች አለመሆናቸውን ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ በማጣራቱ ሂደት ባንኮች እየረዱን ስለሆነ ይሄ መረጃ ከእኛ መሥሪያ ቤት የወጣ አይደለም የቀረበላችሁ የውሸት መረጃ ነው በማለት እየነገሩን ያሉት ባንኮች ስለሆኑ ከባንኮች ይወጣል ማለት እቸገራለሁ፡፡ የግለሰቦች እጅ ሊኖርበት ይችላል፡፡ እስካሁን ባደረግነው ማጣራት ከ30 በላይ የውሸት መረጃዎችን ይዘናል፡፡ ይህ በኮሚሽኑ ደረጃ የተያዘ ነው፡፡ በከተማ በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚታይ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ሲጠቃለል ምን ያህል ሊሄድ እንደሚችል ማየት ይቻላል፡፡ በዚህ ስቴትመንት የውሸት መረጃ እየመጣ መሆኑን ከደረስንበት በኋላ ባደረግነው ጥረት ነው እነዚህን 30 የውሸት ማስረጃዎችን ያገኘነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ እርምጃ በፊት ብዙ ሕገ ወጦች አምልጠዋል ማለት ነው?

አቶ ዓለሙ፡-
በፊት ብዙ አምልጧል ማለት ነው፡፡ በክትትል የምንደርስባቸው ይኖራሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ችግር ከተከሰተ ዞሮ ዞሮ እነኚህ ለልማት ያልቆሙትና መሬትን ለሌላ ዓላማ ለመውሰድ የሚጥሩትን ሃይሎች ተቆጣጥረናል ማለት አንችልም፡፡ እኛ አንድ መፍትሔ ስናመጣ የእነሱም ሌብነት የዚያን ያህል እያደገ ነው፡፡ ዋናው ነገር የመቆጣጠሪያውና የኢንቨስትመንት የክትትል ዘርፎችን ማጠናከር ነው፡፡ የክትትል ዘርፋችንን አጠናክረን መሬት ከወሰዱበት ቀን ጀምሮ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸውን እየተከታተልን ምንም የማይንቀሳቀሱ ከሆኑ በተግባር ስለሚታዩ ከዚያ እርምጃ ለመውሰድ ነው ያቀድነው፡፡ እስካሁን ያገኘናቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ለተለያዩ አካላት (ለፀረ ሙስና ኮሚሽን) ፅፈናል፡፡ ፀረ ሙስናም ይህ በግለሰቦች የተፈፀመ ደረቅ ወንጀል ስለሆነ ፖሊስ ነው የሚመለከተው ብሎን ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፅፈናል፡፡ እስካሁን ግን አልቆመም፡፡ አሁንም እየመጣ ነው፡፡ ይመጣል ብቻ ሳይሆን መረጃው ትክክለኛ ባለመሆኑ አንደኛ ይህንን መረጃ የሚያጣሩ ሠራተኞችን እያስፈራሩ ነው፡፡ ሁለተኛ ከባንክ ቤት የሚተባበሩ የባንክ ኃላፊዎችን እየደወሉ እያስፈራሩ ነው፡፡ ኮሚሽኑንም ባንክ ቤት ያሉ ተጠሪዎችንም እያስፈራሩ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የመንግሥትም ሆነ የግል የባንክ ኃላፊዎችን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ በጣም ፈጣን ምላሽ ይመልሳሉ፡፡ ትብብራቸውም ቀና ነው፡፡ በእነሱ ሥም የሚነገደውን ለእነሱም ጥሩ አለመሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም በአገር ልማት ላይ የተቃጣ አደጋ መሆኑን በመገንዘብ እየተባበሩን ነው፡፡ ኮሚሽኑ ከሌሎች አካላት ጋር ካለው የሥራ ትብብር በላቀ ደረጃ ባንኮች እየተባበሩት ነው፡፡ የጠየቅነውን መረጃ ወዲያው በፋክስ ይሰጡናል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ባለሃብት ውል ገብቶ መሬት ከተረከበ በኋላ በአብዛኛው የምንመለከተው መጋዘን ሠርቶ ማስቀመጥ ነው፡፡ ይህንንስ ከማጭበርበር ጋር ያያይዙታል?

አቶ ዓለሙ፡-
እሴት ያልጨመረ በሙሉና ፈቃድ የወሰደበትን ፕሮጀክት ያልሠራ ያው አልሠራም ማለት ነው፡፡ ከማጭበርበር አይለይም፡፡ ፋብሪካ እሠራለሁ ብሎ መጋዘን ከሠራ መዋሸት ነው፣ ማጭበርበር ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ማከራየት ነው የተያዘው፡፡ በሬዲዮ ፋና በተደረገ የቀጥታ ውይይት ህብረተሰቡ ይህንን አንስቷል፡፡ እኛም በክትትል ደርሰንበታል፡፡ ይህ ጉዳይ በሚበዛባቸው ለገጣፎ ሰበታ እና ዱከም አካባቢ ጥናት አድርገን ሰዎቹን ለይተናል፡፡ ለጊዜው በእነዚህ አካባቢዎች 16 ሰዎች ሠርተው የሚያከራዩ አግኝተናል፡፡ ጋርመንት ብለው ወስደው መጋዘን ሠርተው ያስቀመጡ አሉ፡፡ አንዳንድ ሳልፍ ሳገድም መንገድ ላይ የማያቸው አዲስ አበባ ላይ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች አቃቂና ዱከም አካባቢ ደግሞ መጋዘን ሠርተው ማዳበሪያ ይቀመጥበታል፡፡ ቦታው የተወሰደው ለመጋዘን አይደለም፡፡ ለመጋዘን የሚሆን ቦታ ካለን እንሰጣለን፡፡ ለሌላ ፕሮጀክት ተብሎ ተወስዶ ዝም ብሎ ማስቀመጥ ሌላው ቢቀር አስበው የተነሱበት ጉዳይ እንኳን ከተቀየረ ኮሚሽኑን አስፈቅዶ መቀየር ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች በአካል ጠርቼ አነጋግሬ ጥፋታቸውን አምነዋል፡፡ አንዳንዱ በግልፅ በማስታወቂያ የሚከራይ መጋዘን አለኝ ይላል፡፡ ለእነርሱም ማስጠንቀቂያ ፅፈናል፡፡ ለ16 ሰዎችም ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል፡፡ ከዚህ በኋላ በማይሠሩ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ መጋዘን ሰርተናል አይወሰድብንም ብለው አስበው ከሆነ ካሣቸው ተከፍሎ ለሌላ ባለሃብት ይሰጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ብዙ መክሮበታል፣ አቋምም ተወስዷል፡፡ ከገበሬ ካሣ ከፍለን እንደምንወስድ ሁሉ አጥጋቢ ሥራ ላልሠሩ ካሣ ከፍለን እናስለቅቃለን፡፡ ይህም ካሣ አይደለም ያወጡትን ወጪ ነው፡፡ ይህንንም ሕጉ ይፈቅድልናል፡፡ እንዲያውቁት እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለማልማት ቦታ ከወሰዱት መካከል ሜድሮክ ይገኝበታል፡፡ ሜድሮክ የወሰዳቸው ቦታዎች በአብዛኛው ለዓመታት ታጥረው ቁጭ ብለዋል፡፡ ወይም ደግሞ ከመጋዘን አላለፉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይታችኋል? ምን እርምጃ ወሰዳችሁ?

አቶ ዓለሙ፡-
ሁሉንም ባለሃብት እኩል ነው የምንመለከተው፡፡ ከሜድሮክ ጋር ባለው ጉዳይ እኔ የማውቀውና ባለፉት ሁለት ዓመታትም አብሬ ሥሰራ የነበረው በአብዛኛው የመንግሥት የልማት ድርጅት የነበሩና ሜድሮክ የገዛቸው ናቸው፡፡ ይህንን በተመለከተ የዛሬ ሁለት ዓመት የድንበር ችግር ነበር፡፡ በግልፅ ተከልሎ ለሜድሮክ ያለማስተላለፍ ችግር ነበር፡፡ ይህንን ከፕራይቬታይዜሽን፣ ከኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት የተውጣጣ ቡድን ሄዶ ለመለየት ሞክሯል፡፡ እስካሁን ያላለቁ ነገሮች አሉ፡፡ የሜድሮክ ቺፍ ኤክስኩዊቲቭ ዳይሬክተርን አግኝቼ አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡ ርክክቡን በተመለከተ ያላለቁና አንዳንድ የድንበር ጉዳዮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ምንድነው የድንበር ጉዳይ?

አቶ ዓለሙ፡-
ከዚህ እስከዚህ ተብሎና ተለይቶ ከፕራይቬታይዜሽን ሽያጭ ተከናወነ እንጂ በካርታ በዶክመንት መሬት ላይ ሆኖ ያለመካለል ችግር አለ፡፡ ያላለቀ ጉዳይ አለ፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ቁጭ ብለን አብረን ወይም አንድ ቡድን አቋቁመን ጨርሰን ወደ ሥራ ይገባሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ችግር ካለቀ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ቃል ገብተውልኛል፡፡ እነሱንም ዝም ብለን አላየናቸውም ማለት ነው፡፡ ችግራቸውንም በተደጋጋሚ ገልፀውልኛል፡፡ ሰርቬ ተደርጓል፡፡ የሰርቬው ሥራ ካለቀ በኋላ ካርታው በእጃቸው አልገባም፡፡ ይህ ጉዳይ ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ጋር ይያያዛል፡፡ ከአካባቢ መሬት አስተዳደሮች ጋር የሚያያዝም ነገር አለው፡፡  ከገበሬም ጭምር፡፡

ሪፖርተር፡- ከርክክብ ጋር በተያያዘ የካርታ ችግር ነው ያለባቸው ማለት ነው?

አቶ ዓለሙ፡-
በአጠቃላይ ከፕራይቬታይዜቭን ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ይሄ ነው፡፡ ሌላው ከኢንቨስትመንት የወሰዱትና ገና ሂደቱ ያላለቀ አለ፡፡ የአትክልትና ፍራፍሬ መሬት ጠይቀው ውል ያልተፈረመበት አለ፡፡ ከሙስና ግን በአብዛኛው የሚድሮክ እኔ የሚጠቀሙ ሻሸመኔ ያለውና ከመቂ ወደ አርሲ መሄጃ ያለው ቢሾፍቱ አካባቢ ሆራ ላይ አለ፡፡ የፕራይቬታይዜሽን ጋር ነው ያለው፡፡ የሆራው ባለፈው ዓመት ተነጋግረን ወደ ሥራ እንደገቡ ነው ያለኝ መረጃ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንም ግን ታሽጐ ነው ያለው፤ ሥራም እየተሠራበት አይደለም፡፡

አቶ ዓለሙ፡-
በአጠቃላይ ያሉትን ችግሮች አይተን ከእኛ ችግር ካልሆነና ከባለሃብቱ ችግር ካልሆነ የምንወስደው እርምጃ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፡፡ የእኛ ችግር ከሆነ ደግሞ የእኛን ችግር ወደ መፍታት ነው የምንሄደው፡፡

ሪፖርተር፡- ለሌሎች የተቀመጠው የጊዜ ገደብ እነርሱም ላይ ይሠራል?

አቶ ዓለሙ፡-
አዎ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- በመሥሪያ ቤታችሁ ቢፒአር አጥንታችሁ ነበር፡፡ አጭበርባሪዎችን ለመያዝ ምን እያደረጋችሁ ነው? በአሁኑ ሰዓት ያስቸገረው የደላሎች እንቅስቃሴ ነው፡፡ ደላሎች ለገበሬ ገንዘብ ይሰጡና ውክልና ይወስዳሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ምን አድርጋችኋል?

አቶ ዓለሙ፡-
ከመሠረታዊ የሥራ ሂደት ማሻሻያው ጋር ተያይዞ ባለሃብቱ እንዴት በቅድሚያ መለየት እንዳለብን ስልት አስቀምጠናል፡፡ እያሻሻልን መጥተናል፡፡ የስድስት ወር የፋይናንሻል ስቴትመንት እናያለን፡፡ የውጭውን ተሞክሮ ከኢንተርኔትም ለማየት እንሞክራለን፡፡ የአገር ውስጡንም ፕሮፋይል በማጥናት በሰፊው እየሄድንበት ነው፡፡ ሌላም አዳዲስ ሃሳቦችን እየጨመርን መሄድ ነው፡፡ ሁለተኛው የሚሆነው ደግሞ መሬት ከወሰዱ በኋላ የሚደረገው ክትትል ነው፡፡ ይህንን በሰው ሃይልና በሎጀስቲክ እያጠናከርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መከታተል ማለት ምንድነው?

አቶ ዓለሙ፡-
መከታተልና ድጋፍ ማለት ለአንድ ባለሃብት መሬት ሰጥተን አናቆምም፡፡ ተከታትለን ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ ቶሎ ወደ ሥራ ገብቶ ሕዝብንና አገርን እንዲጠቅም ለማድረግ ነው፡፡ ኢንቨስትመንትን ስናስፋፋ ባለሃብቱን ለመጥቀም ብቻ ሳይሆን ባለሃብቱ ራሱም ተጠቅሞ አገርን ስለሚጠቅም ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ነው ባለሃብቱን የምንደግፈው፡፡ ይህም ስለሆነ ከፍቃድና መሬት መስጠት በኋላም ክትትል አለ ማለት ነው፡፡ ስንደግፍና ስንከታተል የሚሠራውና የማይሠራው ይታወቃል፡፡ ከማይሠራው ላይ መሬቱን ወስደን ለሚሠራው እንሰጣለን፡፡ የሚሠራው ደግሞ የበለጠ እንዲሠራ መልሶ ኢንቨስት እንዲያደርግ ኢንቨስትመንቱን እንዲያስፋፋ የማድረግ ሥራ እንሠራለን፡፡ ይህም በቢፒአር የተጠና ነው፡፡

ሌላው ደላሎችንና ጥገኛን መዋጋት በጣም ሰፊ ሥራ ነው፡፡ የብዙዎችን ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡ ዘመቻ የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ በጣም ተስፋፍቷል፡፡ አርሶ አደሩን ራሱ እስከ ማበላሸት የደረሰ ነው፡፡ ይህ ችግር ደግሞ ከእድገት፣ ካለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር እንደሚመጣ የታወቀ ነው፡፡ ለማስወገድም ያን ያህል ጠንካራ ትግል ነው የሚጠይቀው፡፡ ደላላ በዚህ ምክንያት እዚህ ቢሮ የሚውልበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አሁን ያንን ማስቀረት ችለናል፡፡ ግን እታች አለ፡፡ ይሄ አዝማሚያ ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት መጥፎ አዝማሚያ ነው፡፡ የክልሉን የኢንቨስትመንት ገፅታ የሚያበላሽ አንድ የቀረን የድለላ እንቅስቃሴን ማስወገድ ነው፡፡

የድለላ ሥራ እየተሠራ ያለው የተዘጋጀ የኢንቨስትመንት መሬት ስለሌለ ባለሃብት መሬት ስለሚፈልግ ነው፡፡ ይህንን ለማስቀረት ቢፒአር በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ይህንን ለማስቀረት የከተማና የገጠር መሬት ይዘጋጃል፡፡ ይዘጋጃል ብቻ ሳይሆን መረጃው ማንም ሊያየው በሚችልበት መልኩ ይቀመጣል፡፡ ዌብ ሳይት ላይ ይጫናል፡፡ ከዚያ ላይ የተሰጠ መሬት ካለ ያ መሬት ይቀነሳል፡፡ ግልፅ የሆነ አሠራር ይኖራል፡፡ ደላላና መሬት ጠያቂም አይገናኝም፡፡ መሬት የሚሰጥ አካልና መሬት ጠያቂ ብቻ ነው የሚገናኘው፡፡

ይሄ አሠራር ሥራ ላይ ሲውል ይህንን ሙሉ በሙሉ ባናስቀረውም ብዙ መንገድ ያስኬደናል፡፡ ከዚህ አንፃር የገጠር መሬት ብዙ ሄደንበታል፡፡ ቢፒአሩ የገጠር መሬትን ማን እንደሚያዘጋጅ የከተማ መሬትን ማን እንደሚያዘጋጅ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ የገጠር መሬትን የኦሮሚያ የገጠርና የግብርና ልማት ቢሮ እንዲያዘጋጅ፡፡ መረጃውንም ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሰጥ፡፡ የከተማ መሬትን የሥራና ከተማ ልማት ቢሮና የከተማ አስተዳደሮች እንዲያዘጋጁ መረጃውን ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሰጡ፡፡ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ደግሞ አስተዋውቆ ጠያቂ ከመጣ ጠያቂው ቦታ የሚያገኝበትን ሁኔታ እንዲያመቻች በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በያዝነው ዓመት ብቻ ከአንድ ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ችግሩ ወደተዘጋጀው መሬት መሄድ አለመፈለግ ነው፡፡ በተለይ የአገር ውስጥ ባለሃብቱ ወይም ደግሞ ከአገር ውስጥ ባለሃብት ጋር የሚሠራ የውጭ ባለሃብትም ይሰረዛል፡፡ ከአዲስ አበባ ርቀው መሄድ አይፈልጉም፡፡ ከዚያ በተረፈ የመከናይዝድ እርሻ መሬት ከአንድ ሚሊዮን ሔክታር በላይ ተዘጋጅቷል፡፡ የሚቀረን አሁን ከተሞች ላይ ነው፡፡ ከተሞች ከማስተር ፕላን ክለሳ ጋር በተያያዘ ቢ.ፒ.አሩን ከመሠረቱ ሥራ ላይ ከማዋል ጋር በተያያዘ የመሬት ዝግጅቱን አልሄዱበትም፡፡ ይህንን ጉዳይ በቦርድ አይተን ደካማ አሠራር እንዳለ ተረድተን መስተካከል እንደሚኖርበት ተረድተናል፡፡ ገላን አዲስ ከተማነት ማስተር ፕላኑ በቅርቡ ነው ያለቀው በቅርቡ ባለቀው ማስተር ፕላን የነበሩትን በፊት የተሰጣቸውን ኢንቨስትመንቶች ፕሮጀክቶች አሁን ገና በማስተር ፕላኑ የማስተናገድ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ወደ አዲስ ቦታ ዝግጅት ከመግባት በፊት ለገጣፎም አዲስ የታወቀች ከተማ ነች፡፡ ማስተር ፕላኑ እንዳለቀ ያለው የኢንቨስትመንት ቦታ አልቋል ገና የማስፋፊያ ማስተር ፕላን ካልተሠራ በዚህ ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ሱሉልታም ተመሳሳይ ችግር አለ፡፡ ቡራዩ የተዘጋጀ የኢንዱስትሪ መንደር ስላለው እዚያ ችግር የለም፡፡ እነሰበታ ቢሾፍቱ አዳማ እያዘጋጁ ነው፡፡ እንደግብርና ቢሮ የተፋጠነ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ክልሉ ላይ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የዴቨሎፕመንት ማስተር ፕላን ለማዘጋጀት እየተሠራ ነው፡፡ እሱንም ጀምሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ማዘጋጃ ቤቶች በተለይ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ተባብረናቸው አንዳንድ ጊዜ የሚታዩ ችግሮች አሉ በተለይ ለእናንተ ትእዛዝ በአስቸኳይ መልስ አለመስጠት ማንዴት አለን ይላሉ፡፡

አቶ ዓለሙ፡-
ይህ ችግር የሥርዓት ችግር ነው፡፡ የሥርዓት ችግር ስልህ ሰንሰለት የለንም፡፡ በፊት ከተሞች በዞን ሥር ነበሩ፡፡ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በዚህ ሥርዓት ሲዋቀር በፊት በክልል ደረጃ ነበር የተዋቀረው፡፡ ከዚያ በ8 ዞን ብቻ ተዋቅሮ ነበር፡፡ በ17 ዞን የተዋቀረው በ1999 ዓ.ም ነው፡፡ ከተማ ላይ እስካሁን የለንም፡፡ የግንኙነት ችግር ነው፡፡ ግልፅ የሆነ ከኢንቨስትመንት ኮምሽን ጋር ከተሞች በኢንቨስት ጉዳይ ላይ እንዴት ይገናኛሉ የሚል በስትራክቸር የተሳሰረ ግንኙነት የለንም፡፡ ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ ወይ ደግሞ ለፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ስለምንጠራ ሪፖርት የምናደርገው በዚያ በኩል ነው፡፡ በሚል አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች አልፎ አልፎ ከአንዳንድ አካላት ላይ ይንፀባረቃሉ፡፡ ይሄ በስርዓት እንመልሰዋለን ብለን መዋቅር ዘርግተናል፡፡ መዋቅሩ አልቆ ለከተሞች ተልኳል፡፡ ይሄ መዋቅር ካለቀ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ከተሞች መስተዳድሮች ጋር የሚመራው የኢንቨስትመንት መዋቅር ይሆናል፡፡ በእርግጥ የከተማው መስተዳድር ይቆጣጠረዋል፡፡ እዚያ ያለው የመንግሥት አካል ነው፡፡ ከተማውን የሚያስተዳድረው የከተማው አስተዳደር ግን ቀጥታ ግንኙነት ይኖረናል፡፡ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ መረጃ የመለዋወጥ ሪፖርት የማድረግ መመሪያ የመቀበል ግንኙነት ይኖረናል፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ማዘጋጃ ቤቶች ስመለከት የእናንት ኢንቨስትመንት ዴስክ ተጠሪዎች አሉ፡፡ ከማሀንዲሶች ጋር እንኳን ቴክኒካል ሥራ ለመሥራት የሥራ ግንኙነት ያላቸው አይመስልም፡፡ ይህ ትልቅ ጉዳይ የያዘ ጉዳይ እንዴት እንደዚህ ይሆናል? መዋቅሩ ይህንን ነገር ያስተካክላል ወይ?

አቶ ዓለሙ፡-
እዚያ ያለው ዴስክ መስተዳድሩ ራሱ የፈጠረው ነው እንጂ በስትራክቸር ኮሚሽኑ የፈጠረው አይደለም፡፡ ዴክስ ተብሎ የተፈጠረው ከተሞች አስተዳደር ይህንን ሥራ ማን ይሠራልኛል የኢንቨስትመንቱን ችግር ማን ይከታተልልኛል በሚል ዴስክ ይከፍታሉ፡፡ የችግሩ ምንጭ ይሄ ነው፡፡ የሚያያዝ ነገር አለመኖር ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ አንዳንድ ሰዎች በስሜት የሚናገሩት ነገር ይኖራል፡፡ የግንዛቤ ችግር አለ፡፡ እንደ ኢንስቲቱዩሽን አብረው እየሠራ ያለ ነው፡፡

ባለሃብቶች ከዚህ እንልካለን ያስተናግዳሉ በከተማ ደረጃ የሚወሰን ውሣኔ አለ፡፡ ማንዴት ተሰጥቷቸው ይወስናሉ፡፡ ለቦርድ የሚላክ አለ ይልካሉ፡፡ ሲሪየስ ችግር ያለው ሪፖርት ላይ ነው፡፡ ሪፖርተር ላይ የሠሩን ሥራ ሪፖርት አንድም የሪፖርቱን ሲስተም የማድረግ ልምድ ችግር ያለም ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ቻይናዎች በኦሮሚያ በምን በምን ዘርፍ ተሰማርተዋል?

አቶ ዓለሙ፡
- አሁን ቁጥሩን አላስታውስም፡፡ ግን በአጠቃላይ የክልላችን ኢንቨስትመንት ጉዳይ የቻይናና የህንድ ኩባንያዎች ይበዛሉ፡፡ የቻይናና ህንድ ኩባንያዎች እንደ ክልል የኢንቨስትመንት ታርጌታችን ስናወጣ ፕሮሞሽን ላይ ታርጌት አድርገናል፡፡ ታርጌት ስናደርግ የት አካባቢ ላይ ነው ማተኮር ያለብን ብለን አስቀምጠናል፡፡ ማተኮር አለብን ብለን አንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጥነው የቻይናና ህንድን ነው፡፡ ቀጥሎ መካከለኛው ምሥራቅ ነው በሶስተኛ ደረጃ አውሮፓና አሜሪካን ነው፡፡

ይህም የሆነበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ አንደኛ ህንድና ቻይና በቅርብ ጊዜ ከእኛ አገር ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ደረጃ ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ ብዙ የእኛን አገር ሁኔታን ያልረሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ እዚህ አገር መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ባለሃብቶች ሁኔታዎች ብዙ የማይመቻቸው አይደለም፡፡

የአውሮፓና የአሜሪካ ባለሃብቶችን ብትወስድ ግን መሠረተ ልማታችን ላይመቻቸው ይችላል፡፡ አስፓልታችን ሆቴላችን ላይመቻቸው ይችላል፡፡ ቻይናና ህንድ ግን በቅርብ እንደዚህ ዓይነት መንገድ ላይ ሲሄዱ የነበሩ ናቸው፡፡  አሁንም ደሳሳ ጐጆ ያለባቸው አገሮች ናቸው፡፡ደሃ ሕዝብንም ለማየት የሚጠየፉ አይደሉም፡፡ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ዲስ ኮንፎርት የሚሰማቸው አይደለም፡፡ የወደፊት የዓለምን ሚዛን ወደእጃቸው እያስገቡ ያሉ ኃይሎች በመሆናቸው በቀላሉ ፕሮሞት አድርገን ልንወስዳቸው የሚችሉ ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ በቀላሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡ እኛም ለእድገታችን የእነሱን ተሞክሮ እየወሰድነው ያለነው፡፡ እስካሁን ያለው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም እነዚህን አገሮች ታርጌት እናደርጋለን፡፡

ያለፈውን ስናይ ቻይናዎች በኮንስትራክሽን በሲሚንቶ በፕላስቲክ በመሳሰሉት ላይ አሉ፡፡ በኢንዱስትሪና በኮንስትራክሽን ይሠራሉ በሪል ስቴት ጭምር በክልላችን አሉ፡፡
የህንዶችን ስናይ በአብዛኛው እርሻ ላይ አሉ፡፡ ጥቂቶችም በኢንዱስትሪም ላይ ይሳተፋሉ፡፡ የአበባ እርሻ ፓልም ላይ መሬት እየወሰዱ ነው፡፡ ሩዝም ለማልማትም በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ አሉ፡፡ መሬት የወሰደ የህንድ ባለሃብት አለ፡፡

ሌላው ታርጌታችን መካከለኛው ምሥራቅ ነው፡፡ የውጭ ገበያችንም እዚያ አካባቢ አለ፡፡ እነሱም ለአገራቸው የሚሆን ምርት ማምረት ይፈልጋሉ፡፡ ወደ አፍሪካ ኢንቨስትመንት ሲገቡ ኢትዮጵያን እንደዋነኛ መዳረሻ ስለሚቆጥሩ ይመጣሉ፡፡

በአጠቃላይ ሁሉም የዓለም ኢንቨስትመንት እንዲመጣ ነው የምንፈልገው ግን ሁለም ላይ ያለውን ሪሶርስ ከምናባክን በታርጌት መውሰን በደረጃ መምረጥ ስላለብን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአብዛኛው ከእህል እጥረት ጋር በተያያዘ ሰፋፊ ሜካናይዝድ የሆኑ የእርሻ ተቋሞች መሠራት አለባቸው በሚል የእርሻ ባለሙያዎች አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡ መንግሥትም በምግብ ራስን ለመቻል በሰፊው እንደ”ንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ምን ታስቧል፡፡ መካናይዝ የሆኑ እርሻዎችን ለማካሄድ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ዓለሙ፡- እንደ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊነቴ በተለይ የዓለም የምግብ ጥረት ለኢንቨስትመንት እንደ እድል ነው ያየሁት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እየመጡ ስለሆነ ጥሩ እድል ነው፡፡ እህል በመወደዱ ደስተኛ ባልሆንም ለኢንቨስትመንቱ ጥሩ ነው፡፡

ይህንን እድል ለመጠቀም ተዘጋጅተናል፡፡ በእርሻ ላይ የምናካሂደው ኢንቨስትመንት ምን ዓይነት እርሻና በምን ዓይነት ደረጃ እርሻ የሚለውን እናያለን፡፡ ትልቅ እርሻ መሆን ይኖርባቸዋል ብለን መሬትን ቆራርሰን ለብዙ ባለሃብቶች ከምናዳርስ አቅም ያለው መሥራት የሚችል ባለሃብት ከመጣ እንስጥ ብለን ድሮ በ200 ሔክታር በተለይ አምስት መቶ ሔክታር በዞንም በወረዳም መሬት ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ለእርሻ የሚሆን ሰፊ መሬት እንሰጣለን፡፡

ይህንን በሚመለከት ቦርድ ወስኖ ሰርኩላር አስተላልፈን መሬት ተበጣጥሶ እንዳይሰጥ እንዲሁም በወረዳና በዞን ደረጃ ቦርድ ሳያውቅ የእርሻ መሬት እንዳይሰጥ መመሪያ ተላልፏል፡፡ ይሄ ማለት መሬት ሳይበጣጠስ እንዲሰጥ ያለንን መሬት ለይተን ከአንድ ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ ተዘጋጅተዋል፡፡ የስንዴ የሩዝ የሸንኮራ የጥጥ የሻይና የመሳሰሉትን መሬት ለይተናል ለምሳሌ በባሌ አካባቢ ከ30 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ ለጥጥ የሚሆን መሬት ሆረጉድሩ ውስጥ ለሩዝ ምርት የሚሆን 30 ሺህ ሔክታር የሚሆን መሬት ተዘጋጅቷል፡፡

ስለዚህ ሰፋፊ እርሻዎችን እናበረታታለን፡፡ ሪሶርስ እያላት በምግብ የምትራብን አገር የእህል የዳቦ ቅርጫት እንድትሆን የሚያደርጉ ባለሃብቶች እየጠበቅን ነው፡፡

እስካሁን ከብራዚል ስንዴ ምርት ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ እየመጡ ያሉ አሉ፡፡ ከህንድ ሩዝ ላይ ለመሥራት የሚመጡ አሉ፡፡ እስራኤሎች ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ ለመሥራት ተዘጋጅተዋል፡፡ ሰፋፊ እርሻዎችን የሚያስተናግድ መሬት አለ፡፡
 
< Prev   Next >