| በዲያስፖራ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሴቶችም... |
|
|
| Sunday, 13 January 2008 | |
|
በዲያስፖራ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሴቶችም በአደባባይ ሕይወት አይሳተፉም በኢትዮጵያ ያደጉበት ማኅበረሰብ ለሴቶች አደባባይ መውጣትና ድምጽ ማሰማት እንዲሁም በህዝባዊ እንቅስቃሴ መሳተፍ አለመቻል በዲያስፖራ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ ተጽዕኖ እያስከተለ መቆየቱን ፣አድባር የኢትዮጵያውያት ሴቶች፣ የተሰኘ ማህበር ገልጿል፡፡ ማኅበሩ በቅርቡ በድረ ገፁ አማካኝነት ይፋ ባወጣው መልዕክት ኢትዮጵያውያት በዲያስፖራ የሚገኙ ሴቶች በሲቪክ እንቅስቀሴዎች ሊሳተፉ እንደሚገባ ለዚህም እንዲረዳቸው እርስ በርስ የመደጋገፍን የኢትዮጵያዊነታቸውን ባህል ሊያስታውሱ ግድ እንደሆነ ገልጿል፡፡ "አድባር የኢትዮጵያውያት ሴቶች ትብብር" ይህንኑ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ሴቶች በአደባባይ ህይወት መሳተፍና ድምፃቸውን ማሰማት አለመቻል ለማስቀረት 1993 (እ.ኤ.አ) በአሜሪካ የተቋቋመና መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅትነት የተመዘገበ ተቋም ነው፡፡ ..በአብዛኛው ኢትዮጵያውያት ሴቶች የተሻለ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የአገራቸው ሴቶች የተሸከሙትን ቀንበር ለማንሳት የሚያስችል እንቅስቃሴና ጥረት ለማድረግ ብዙም ሲፈልጉ አይታይም.. ያለው ሪፖርቱ ይህ ምናልባት በተጨቆኑ ሴቶች ማኅበረሰብ ውስጥ የማደግና አሁንም ያልጠፋ በማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ሚና የለንም የሚል አስተሳሰብ ውጤት ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች በቤት ውስጥ ብቻ ሚና ያላቸው እንዲሆኑ ተደርጎ የተቀረፀባቸው አስተሳሰብ ሴቶች በራሳቸው እንዳይተማመኑና ለውጥ ለማምጣት የሚችሉ አድርገው ራሳቸውን እንዳያስቡ ማድረጉም ነው በሪፖርቱ የተጠቆመው፡፡ ከላይ የተገለፀው ትብብር ይህንኑ ኢትዮጵያ ሴቶችን የመርዳትና የማጠናከር ሚናውን የሚወጣው የተለያዩ አገልግሎቶችን በዲያስፖራ ለሚገኙ ሴቶች በመስጠት ነው፡፡ ሪፖርቱ እንዳለው "አድባር" በተቋቋመበት ቦስተን ግዛት አካባቢ 15ሺህ ኢትዮጵያውያን ሲኖሩ ከነኝህ ግማሹ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 50 ዓመት የሚሆን ሴቶች እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ድርጅቱ በቦስተን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ከቦታ ቦታ በመዘዋወር በካምብሪጅ፣ ሮክስበሪ፣ ዶርቸስተር፣ ቼልሲ፣ ብሮክሊን፣ አርሊንግተን፣ ፍለሚንግሀም የሚኖሩትን ጭምር የሚያካትት ነው፡፡ ከአድባር ፕሮግራሞች ዋና ዋናዎቹ የሴቶች እገዛና መረጃ ፎረም፣ አድቮኬሲ፣ የመራጭነት ምዝገባና የሲቪክ ተሳትፎ፣ ትምህርት ይገኙበታል፡፡ የመጀመሪያው ፕሮግራም ለሴቶችና ለልጃገረዶች በተወሰነ ጊዜያት የሚካሄዱ ባህላዊ ፎረሞች የሚያካትት ሲሆን በኢትዮጵያዊ ባህላቸው እርስ በርስ ለመረዳዳትና ኢኮኖሚ አቅማቸውን ለመገንባት እንዲችሉ ለማድረግ ይሰራል፡፡ የቅስቀሳ/አድቮኬሲ ፕሮግራሙ በሴቶች ግርዛት፣ በስደተኛ ሴቶች፣ በአዕምሮ ህመም፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ የተለያዩ ቤተሰቦችን የመገናኘት፣ የቤት ማግኘት ሁኔታዎችን የሚመለከት ነው፡፡ የመራጭነት ምዝገባ ከላይ የተቀመጠውን የሴቶችን በሲቪክ እንቅስቃሴዎች የመሳተፍ ችግር ለማስወገድ የመራጭነት ትምህርት በመስጠት ላይ ጭምር ያተኮረ ነው፡፡ የትምህርት ዘርፉ እንግሊዝኛ መናገር ለማይችሉ ኢትዮጵያውያት የቋንቋ ትምህርት ለመስጠት ያለመ ሲሆን ማንበብና መፃፍ ለማይችሉ አዋቂዎች ትምህርት መስጠትን የሚያካትት ነው፡፡ በተጨማሪም "አድባር" አዲስ ለሚመጡ ሴት ስደተኞች ገለፃ ማድረግ፣ ሥራ ማፈላለግ፣ የትርጉም ሥራ፣ የማህበራዊ ኑሮና ባህላዊ መገናኛ መድረኮችን ማመቻቸት፣ የሕግ ድጋፍ መስጠት ያሉትን አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ ቤት ማፈላለግና መረጃ በመስጠት በኩል ትብብት ማድረግም የ"አድባር" ሌሎች ተግባራት ናቸው፡፡ አድባር ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያት መብቶቻቸው ተከብረው እንዲኖሩ በማመቻቸት፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከአዲሱ ኑሮ ጋር በተሻለ ሁኔታ እንዲላመዱ፣ ኢኮኖሚያዊ ነፃነት እንዲያገኙ ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲኖሩ ለማድረግ ይሰራል፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |