| ድጋፍ ሲቋረጥ፣ ድጋፍ ፍለጋ |
|
|
| Sunday, 22 June 2008 | |
![]() ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ሜሪ ጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅት "ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን" በሚል ስያሜ አዲስ የጀመረው አገር አቀፍ ኘሮግራም በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና በትምህርት ተቋማት ዘንድ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል፡፡ ድርጅቱ ይህን ኘሮግራም ሊጀምር የቻለው በውጭ አገር ከሚገኙ ለጋሾች መካከል አንዳንዶቹ ድጋፋቸውን በማቋረጣቸው ምክንያት መሆኑን ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ የድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ገልፀዋል፡፡ ዋና ሥራ አስከያጇ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳብራሩት፣ ከሦስት ዓመት በፊት በተጀመረው በዚህ ኘሮግራም ከሁለት ሺህ በላይ የሚሆኑ ወላጅ አልባ ሕፃናት በኢትዮትዮጵያውን እየተረዱ ይገኛለ፡፡ በአንድ ሕፃን እስከ 12ዐ ብር ነው ከግለሰቦች የሚጠየቀው፡፡ አቅም ያለው እስከ 2ዐ ሕፃናት፣ አቅም የሌላቸው ደግሞ በቡድንና በመሥሪያ ቤት ደረጃ እየተሰባሰቡ አልባሳት፣ ደብተርና እርሳስ በመስጠት ሕፃናቱን እያሳደጉ ናቸው፡፡ ድርጅቱ በውጭ አገር የሚገኙ ለጋሾች በአንድ ወቅት እርዳታቸውን ሊያቋርጡ ይችሉ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ቀደም ሲል አላደረበትም ነበር? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ "እርዳታውን ያቆማሉ ብለን አላሰብንም፡፡ ልምድም አልነበረንም፡፡ ወደ ውስጥ እየገባን ስንሄድ ግን እየነቃን መጣን፡፡ በዚህም የተነሳ የኘሮግራማችንን ቀጣይነት ወይም ዘላቂነት አስተማማኝ ለማድረግ ሕብረተሰቡን፣ ድርጅቶችንና የትምህርት ተቋማትን ማስተባበር ጀመርን" ብለዋል፡፡ ለጋሾች ድጋፋቸውን ከማቋረጣቸውም በላይ ባንክ ውስጥ ያለውንም ገንዘብ ሁሉ አውጥተው የሚወስዱበት ጊዜ አለ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ለሌላው ቅድሚያ በመስጠት ነው፡፡ "የገንዘብ ችግር ስላለብን ባንክ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በአስቸኳይ መልሱልን" ብለውም ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ ባለፈው ዓመት ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ ወጥቶ ተመላሽ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ እርዳታውን ካቋረጡት ለጋሾች መካከል ዋንኛውና ትልቁ "ሆኘ ፎር አፍሪካን ችልድረን" የተባለው ይገኝበታል፡፡ ሰባት ሺህ ወላጅ አልባ ሕፃናት ለሦስት ዓመት እንዲገለገሉበት ቀደም ሲል የለገሰውን አምስት ሚሊዮን ብር አቋርጧል፡፡ ገንዘቡንም ያቋረጠው ብዙ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ውስጥ ያለና የተለመደ ነው፡፡ ሲፈልጉ ይሰጣሉ፤ ሲፈልጉም ይነሳሉ፡፡ ሆኘ ፎር አፍሪካን ችልድረን እርዳታውን ሲያቋርጥ ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ሕፃናት ለችግር ተዳርገዋል፡፡ የትምህትርና የምግብ ክፍያ በመቋረጡም በአንድ ጊዜ ወደ ጎዳና ወጥተዋል፡፡ ነገር ግን ወዲያውኑ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሚለው አገር አቀፍ ኘሮግራም ላይ ያተኮረ ቅስቀሳ በስፋት ተካሂዷል፡፡ ቅስቀሳውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና መዋእለ ሕፃናት የትምህርት እድሎችን እንዲሰጡ በማድረግ በጎ ምላሽ አስገኝቷል፡፡ ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩት በተገኘው እድል ተጠቅመው ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ በቅተዋል፡፡ አንዳንድ የውጭ ለጋሾች በሚፈልጉት አቅጣጫ ብቻ ለማይንቀሳቀሱ ድርጅቶች ድጋፍ ከማድረግ ይቆጠባሉ ወይም ድጋፋቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሲስተር ዘቢደር ገልፀው፣ "እኛ በምንፈልገው አቅጣጫ ብቻ ሂዱ" የሚሉትን ሜሪ ጆይ እንደማይቀበላቸው፣ በዚህም የተነሳ አልቀበልም ብሎ የመለሰው ብዙ ገንዘብ እንዳለና ዓላማቸው ከድርጅቱ ዓላማ ጋር አንድ የሆኑት ለጋሾች የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ እየተቀበለ ሥራ ላይ እንደሚያውል አስረድተዋል፡፡ ሲስተር ዘቢደር እንዳመለከቱት የውጭ ለጋሾች በአገራቸው፣ ወይም በእስያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ መግባት ሲፈልጉ እዚህ ያለውን ገንዘብ ያቋርጣሉ፡፡ ወደሞቀበት ነው የሚሄዱት፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያድ) የገቢ ምንጫቸው 9ዐ ከመቶ ከአገር ውስጥ የቀረውን አሥር ከመቶ ከውጭ ለጋሾች ማግኘት ይኖርባቸዋል የሚለው የሚቀበሉም እንደሚኖሩ አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ዓይነት በጎ ሥራ የመስጠት ባህሉ ገና ጥንስስ ላይ እንደሆነ፣ ምን ያህል ይሰጣል የሚለው ገና አዲስ ልምድ እንደሚሆንበት፣ ነገር ግን ልምዱ ዳብሮ ቢሆን ለማግኘት ይቻል እንደነበር ዋና ሥራ አስኪያጇ አስረድተዋል፡፡ በሌላው አገር የንግዱ ሕብረተሰብ እንደ ሜሪ ጆይ ላሉ ዓይነት ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ካደረገ ከታክሳቸው ላይ ይቀነሳል፡፡ ከዚህ አንጻር የንግዱ ሕብረሰብ እርዳታ ሲሰጡ መንግሥት ታክሱን ቢቀንሰላቸው ሕብረተሰቡ የመስጠት ባህሉ ይዳብራል፡፡ የገቢ ምንጭም ከአገር ውስጥ እንዲገኝ ለማድረግ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት "መያዶች የገቢ ማስገኚያ ማመቻቸት ይችላሉ" ይላል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ "ታክስ መክፈል አለባቸው" ይላል፡፡ ከዚህ አኳያ ፖሊሲው የተቃረነ ይመስላል፡፡ መንግሥትም እንደ መንግሥት ፖሊሲውን በሚገባ ካየው ጥሩ ነው፡፡ ግን አሁን ባለው ደረጃና ሕብረተሰቡ የመስጠት ልምዱ ባልዳበረበት ሁኔታ 9ዐ ከመቶ ያህሉ ከአገር ውስጥ መገኘት አለበት የሚለው ይከብዳል፡፡ ሜሪ ጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅትን የቦትስዋና ኘሬዚዳንት፣ የኬንያ ቀዳማይ እመቤትና የዓለም ባንክ ኃላፊዎች ጎብኝተውታል፡፡ "የቦትስዋና ኘሬዚዳንት አገራቸው ሄደን እንድንሠራ ጋብዘውናል፡፡ እኛ ግን የኢትዮጵያን ችግር ሳንፈታ ሌላው አንሄድም ብለን ነው የተቀበልነው" ይላሉ ሲስተር ዘቢደር፡፡ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮችም የመያዶችን የሥራ እንቅስቃሴ ወረድ ብለው ቢያዩ የበለጠ ያበረታታል፡፡ ይህም ማለት በአጠቃላይ መያዶች ጥሩዎች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ገንዘብ የሚያመልኩ እንዳሉ ሁሉ መያዶች ውስጥም ገንዘብ አምላኪ አሉ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ለብቻ መያዶችም ለብቻቸው ዳር ቆመው እርስ በርሳቸው በጥርጣሬ አይን እየተያዩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በልማት መስክ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ለውጥ ማምጣት የሚችለውም እንደ ሜሪ ጆይ የመሳሰሉ የልማት አጋር ድርጅቶችን በመሰብሰብ ነው፡፡ አሁን ያለው መራራቅ የልማቱን እንቅስቃሴ አያሳካም፡፡ ከድህነትም ለመላቀቅ የሚያስችለው መፍትሄም አይመስልም፡፡ የተጠያቂነትና የግልጽነት ችግር በሁሉም ወገን ይታያል፡፡ መንግሥት ፖሊሲውን ቀርፆ አፈጻጸሙ ላይ ክትትል እያደረገ መያዶች ደግሞ በራቸውን ከፍተው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የተለበሰ እንቅስቃሴ በማድረግ ከሕብረተሰቡ ጋር በጋራ ከተሠራ ድህነትንና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመቅረፍ ይቻላል፡፡ "ከመንግሥት ጋር የአምስት ዓመት ውል እንፈራረማለን፡፡ ውሉ እንዳበቃም የሚመለከተው አካል መጥቶ ክትትልና ግምገማ ያካሂዳል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ግን ስህተትን (ፎልት ፋውንደር) ፍለጋ ዓይነት ነው፡፡ መሆን ያለበት ከመጀመሪያው ጀምሮ እቅዱ ምንድነው? እንዴት ነው እየሠራችሁ ያላችሁት? አካሄዱ ትክክል ነው ወይ በሚለው ዙሪያ ከመንግሥት ጋር አብረን መሥራት አስፈላጊ ነበር፡፡ ይህም ባለመሆኑ ከመንግሥት ጋር በጣም ተራርቀናል፡፡ ዘንድሮ ፖሊሲ አውጥተንና ኤጀንሲ አቋቁመን አብረን እንሠራለን ብለዋል፡፡ ኤጀንሲ መኖሩ በጣም ጥሩ ነው፡፡ መያዶችን ያበረታታል" የሚል እምነት እንዳላቸው ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ከመያዶች ጋር አብሮ ለመሥራት ያልቻለው የአቅም ውስንነት ስላለበት ነው፡፡ ቀደም ሲል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ቀጥሎም እርዳታና ማስተባበሪያ አሁን ደግሞ ሲቪልና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ነው መያዶችን የሚከታተለወ፡፡ በመምሪያው ይህንኑ የሚከታተሉ ሦስትና አራት ሰራተኞች ቢኖሩ ነው አዲስ አበባ ውስጥ ያለት መያዶች ደግሞ በሺህ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ተከታትሎና ገምግሞ ለመሥራት ያስቸግራል፤ አቅምም የለም፡፡ ቶሮንቶ ካናዳ በተካሄደው 16ኛው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዓመታዊ በዓል ላይ ከ547 ኢንተርናሽናል ድርጅቶች ጋር ሜሪ ጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅት ተወዳድሮ ተሸላሚ ሆኗል ያሉት ሲስተር ዘቢደር፣ ድርጅቱ በድህነት ቅነሳ ሂደት ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዳመጣ አስረድተዋል፡፡ ይህም ሲባል ይቻላልን ተግባራዊ በማድረግ፣ ከሌላው ልምድ በመማር፣ እንዲሁም የመፈቃቀርና የመቻቻል ባህልን እያዳበሩ በመንቀሳቀሱ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ሜሪ ጆይ የልማት ተራድኦ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባና በአዋሳ ከተሞች በሚገኙ 34 ቀበሌዎች ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ አገልግሎቱን እያበረከተ ያለው በጉለሌ፣ በኮልፌ ቀራኒየና በየካ ክፍለ ከተሞች ሲሆን አዋሳ ላይ ደግሞ በሁሉም ቀበሌዎች ነው፡፡ ከ1ዐዐ በላይ ቋሚ ሰራተኞች፣ የኪስ ገንዘብ የሚከፈላቸው ከ4ዐዐ የሚበልጡ በጎ ፈቃደኞች እንዳሉትና ከ32 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሕፃናትም ሁለገብ ድጋፍ እየሰጠ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ውጭ የአረጋውያን ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችለውን እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ ነው፡፡ ይህም ሞዴል ማዕከል ለአረጋወያኑ የሚውል የማረፊያ ቦታ፣ የገቢ ማስገኛ ሱቆች፣ ካፊቴሪያና አዳራሽ፤ አረጋውያኑ ለወጣቱ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይ.ቲ) ማዕከላት ይኖሩታል፡፡ ይህንንም ተከታትሎ የሚያስፈጽም አርቲስቶችን ደራሲያንና ጋዜጠኞችን ያካተተ የበጎ ፈቃደኛ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |