| "ገንዘብ የጠየቀንም ሆነ የምንጠይቀው አካል የለም" |
|
|
| Wednesday, 25 June 2008 | |
ዶ/ር ሃይሉ አርአያዶክተር ሃይሉ አርአያ በመቋቋም ላይ ያለውና በቅርቡ መስራች ጉባኤውን ያካሄደው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የብሔራዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እንዲሁም ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው፡፡ ሰለሞን ጎሹ በፓርቲው ወቅታዊ ሁኔታና ተዛማጅ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ መስራች ጉባዔ እንዴት ነበር? ምን ምንስ ጉዳይ ፈፀመ? ዶ/ር ኃይሉ፡- መስራች ጉባዔው በጥሩ ሁኔታ ነው የተከናወነው፡፡ የሰው ብዛት ስለነበር የቦታ ጥበት ነበር፡፡ ከሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የመጡ ተወካዮች በከፍተኛ ንቃት ነበር ጉባዔውን የተከታተሉት፡፡ ከ3ዐዐ በላይ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ ከ7 ክልሎችና ከአዲስ አበባ ነው የመጡት፡፡ ጉባዔው ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ፣ ኘሮግራምና አርማ አፅድቋል፡፡ መዝሙራችንም እንዲሁ ፀድቋል፡፡ እነዚህ ነገሮች የተሟሉ ናቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ነገር ግን የመጨረሻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሊሻሻሉ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ጉባዔው ሊካሄድ የነበረው በኤምፔሪያል ሆቴል ነበር፡፡ ሆኖም በአንዳንድ ችግሮች ሳይካሄድ በመቅረቱና ወደ ሌላ ቀን በመተላለፉ ከክልል የመጡ ተወካዮች የነበራቸው አማራጭ ወይ መመለስ አሊያም ተቸግረው መቆየት ነበር፡፡ ተሳታፊዎቹ ግን ተቸግረንም ቢሆን ቆይተን ጉባዔውን ማካሄድ አለብን ብለው ወሰኑ፡፡ ለኤምፔሪያሉ ስብሰባ ከተገኙት 4ዐዐ የሚያህሉ ተሳታፊዎች መካከል 3ዐዐቶዎቹ ብቻ የተገኙት የተቀሩት ከነበራቸው የመንግሥት ሥራና የቤተሰብ ኃላፊነት አንፃር መቆየት የማይችሉ ስለነበሩ ነው፡፡ በእለቱ ጉባኤው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በደቡብ አሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በአውስትራሊያ በቴሌቪዥንና በቴሌፎን ቀኑን ሙሉ ሲሰራጭ እንደዋለ ነው የተነገረን፡፡ ሪፖርተር፡- በመስራች ጉባዔው በጉልህ የተደመጠው ነገር አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ወራሽ መሆኑ ነው፡፡ የቀድሞው ቅንጅት የራሱ ደካማና ጠንካራ ጎኖች ነበሩት፡፡ አንድነት ከቅንጅት በምን መልኩ ይለያል? ዶ/ር ኃይሉ፡- በመሠረቱ በአንድነትና በቀድሞው ቅንጅት መካከል መሠረታዊ ልዩነት የለም፡፡ አንድነት የቅንጅት ወራሽ ነው፡፡ በመንፈስም በዓላማም ከቅንጅት ጋር አንድ ነው፡፡ ነገር ግን ስያሜው ለሌላ አካል ስለተሰጠ በቅንጅት ስም መቀጠል አልተቻለም፡፡ የቀድሞው ቅንጅት የቆመላቸው አላማዎች መስራት ስነበረባቸውና ለህዝቡ የተገባውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል ለዚች ሃገር ያለንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ሲባል በሌላ ስም ለመቀጠል አቅደናል፡፡ ህገ ደንቡ አሁን ላለንበት ሁኔታ እንዲስማማ ተደርጎ ተሻሽሏል፡፡ ኘሮግራሙም ራሱ ባገኘነው ትምህርትና ተሞክሮ በመነሳት አንዳንድ ነገሩ እንድስተካከልና አዳዲስ ነገሮች እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ አዲስ ገፅታ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የቀድሞው ቅንጅት መተዳደሪያ ደንብ አንዳንድ አንቀፆች ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮችን በትርጉም ልዩነት የተነሳ አለመግባባት የዳረጉበት ሁኔታ ነበር፡፡ በአንድነት መተዳደሪያ ደንብ አምታችና አሻሚ አንቀፆችን ግልፅና ቀላል በሆኑ አንቀፆች ለመለወጥ ጥረት አድርጋችኋል? ዶ/ር ኃይሉ፡- የትኛውን አለመግባባት ነው የምታወራው? ሪፖርተር፡- ኢንጂነር ኃይሉ የሥራ አስፈፃሚዎችን ከፓርቲው ለማገድ መተዳደሪያ ደንቡ ይፈቅድልኛል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ለአቶ አባይነህ ብርሃኑ ውክልና ለመስጠት በተመሳሳይ መተዳደሪያ ደንቡን ጠቅሰዋል፡፡ በተቃራኒ እርስዎን ጨምሮ እነ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የኢንጂነሩን ተግባር ለመቃወም ተመሳሳይ አንቀጽ ነው ያነሱት፡፡ በምልዕተ ጉባዔ ጉዳይም ተመሳሳይ ነገር ተፈጥሯል፤ ዶ/ር ኃይሉ፡- አንድ ነገር ግልፅ መሆን አለበት፡፡ በደንቡ ላይ አሻሚ ነገር አልነበረም፡፡ የተፈፀመው የህግ ጥሰት ነው፡፡ የቀድሞው ቅንጅት ሊቀመንበር በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በጥቁርና በነጭ በግልፅ የተቀመጡ ህጎችን ነው የጣሱት፡፡ አሁን አንድነት መተዳደሪያ ደንቡን ሲቀርፅ ባደረገው ውይይት እነዚህ የህግ ጥሰቶች እንዳይደገሙ እንዴት መጠናከር አለባቸው ብሎ አንስቷል፡፡ ለአንባገነንነት ህገ ደንቡ ክፍተት እንዳይፈጥር ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ክፍተት እንዳይፈጥር ማለት ግን ክፍተት ነበረ ማለት አይደለም በአሁኑ ውይይት ካለፈው ተምረን ህገ ደንባችን ለዚህ ዓይነት አካሄድ በር የሚከፍት እንዳይሆን የመጠንቀቅ ነገር ነው ያነሳው፡፡ ሪፖርተር፡- ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ በአሁኑ ወቅት በአቶ አየለ ጫሚሶ ይመራል፡፡ አንድነትን ጨምሮ በርካታ የቀድሞው ቅንጅት አካል የነበሩ ኃይሎች የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡ ነገር ግን ተቃውሞአቸውን ለመደበኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ መልክ የወሰዱት ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ብቻ ናቸው፡፡ አንድነት ይህን ያላደረግሁት ፍርድ ቤቱ የሚወስነውን ስለማውቅ ነው ብሏል፡፡ በህጋዊ መልኩ ለመንቀሳቀስ እየተቋቋመ ያለ ፓርቲ በፍትህ ስርዓቱ እንዴት እምነት ያጣል? ዶ/ር ኃይሉ፡- ንትርክና መጓተት ውስጥ መግባቱ እንዲሁም ጊዜ ማጥፋቱ ጠቃሚ መስሎ ስላልታየን ነው፡፡ የፍትህ ሒደቱን በተለያየ መንገድ ከዚህ ቀደም አይተነዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ፍትህ እናገኛለን ብለን አላመንም፡፡ ዋናው ነገር አላማውንና ራዕያችንን ተግባራዊ ማድረግ፣ ቃላችንን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ፍርድ ቤት መጨቃጨቁ ያን ያህል ጠቃሚ መስሎ አልታየንም፡፡ የዚህ ሃገር ዋነኛ ችግር የፍትህ ስርዓቱ ነው፡፡ ደግሞ እስከሰራን ድረስ ስም ያን ያህል ወሳኝ ነገር አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- የቀድሞውን ቅንጅት የፈጠሩት አራት ፓርቲዎች በተናጠልና በቅንጅት ስም ንብረት ያፈሩበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የኦዲት ሪፖርትን አስመልክቶ በየጊዜው የምንሰማቸው ነገሮች እርስ በርስ ይጋጫሉ፡፡ የአንድነት አቋም ምንድን ነው? ዶ/ር ኃይሉ፡- ስለገንዘብና ንብረት እኔም የተለያዩ ወሬዎች ሲወሩ እሰማለሁ፡፡ እኔ ግን ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ሌሎች የሚናገሩት ነገር ካለ ነገሩን በግልፅ ይዘው ይውጡ፡፡ ያኔ መልስ መስጠት ይቻል ይሆናል፡፡ ሪፖርተር፡- ስለዚህ አንድነት ከቀድሞው ቅንጅት ከወጡ ፓርቲዎች ገንዘብ አልተጠየቀም እሱም ከእነሱ አልጠየቀም እያሉኝ ነው? ዶ/ር ኃይሉ፡- አዎ የጠየቀንም የለም፡፡ የምንጠይቀውም አካል የለም፡፡ ሪፖርተር፡- አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚሰራው? የሚኖረውስ ግንኙነት በቀድሞው ቅንጅት ሁኔታ ተፅእኖ ይፈጥርበታል? ዶ/ር ኃይሉ፡- ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት እኛን አያሳስበንም፡፡ ዋነኛው ሥራችን እራሳችንን ማጠናከር ነው፡፡ በጥንካሬ ቆመን መስራት የሚጠበቅብንን መስራት ነው የምንፈልገው፡፡ ከዛ በኋላ ሥራችንን ስንሰራ ጉዳዩን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ ብንሰራው የተሻለ ውጤት ልናገኝ እንችላለን የምንልበት ሁኔታ ከተፈጠረ ያን ጊዜ ትኩረት እንሰጠዋለን፡፡ በመርህ ደረጃ ከሌሎች ጋር ተባብሮ መስራት ቋሚ መመሪያና እምነታችን ነው፡፡ እኛ ከምንከተለው መስመር ጋር ተመሳሳይነት ያለውና ጠንካራ የሆነ ድርጅት ካለ አብሮ የመሥራቱ ጉዳይ በቀድሞው ቅንጅት ጊዜ እንደነበረው ሁሉ አሁንም አለ፡፡ አሁን እየሰራን ያለነው በማዕከል፣ በክልል፣ በወረዳ፣ በቀበሌ እራሳችንን ማደራጀት፤ በሰው ኃይል መጠናከር፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ማውጣትና ያን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ፓርቲያችሁ በርካታ አካዳሚያዊ ልሂቃንን እንደማቀፉና የጥናትና ምርምር ቡድን እንደማደራጀቱ አማራጭ ኘሮግራሞችንና የውይይት መነሻ ሃሳቦችን በማዘጋጀት በኩል ምን እየሰራችሁ ነው? ዶ/ር ኃይሉ፡- ጥናትና ምርምር ለፓርቲያችን ወሳኝ ነው፡፡ በድርጅታችን ውስጥ በትምህርት የበሰሉ፣ ልምድ ያካበቱ ሰዎች መኖር አለባቸው፡፡ እነሱን በመጠቀምም ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ አማራጭ ውጤቶችን እናስገኛለን ብለን ነው የምናምነው፡፡ የጥናት ምርምር ኮሚቴው በሃገራችን ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል በሚላቸው አካባቢዎች ሃገሪቱ የገጠማትን ችግር በማጥናት መፍትሔ የሚላቸውን ነገሮች ለመስጠት ጥልቀትና ሥፋት ያለው ምርምር ያደርጋል፡፡ ለዚህ ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው ይሆናል፡፡ ሪፖርተር፡- አካዳሚያዊ ልሂቃኖች በፓርቲያችሁ መሰብሰባቸው ቀደም ብሎ ገዢው ፓርቲ የልሂቃን ቡድን በመሆኑ በከተማ ላይ የተመሰረተና የገጠሩ ህዝብ ድጋፍ የሌለው በማለት ቅንጅት ላይ ያሰማ የነበረው ትችት አሁንስ አንድነት ላይ አይደገምም? ዶ/ር ኃይሉ፡- ልሂቃንን መሰባሰባቸው እንደድክመት ነው በመንግሥት የሚወሰደው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ልሂቃን ከሌሉ "የመሐይም ቡድን" የሚልበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ፈረንጆቹ "You are damn if you do; You are damn if you don't" የሚሉት ዓይነት ነው፡፡ በዚህም ብትሄድ ትወቀሳለህ በዚያም ብትሄድ ትወቀሳለህ፡፡ ነገር ግን በድርጅታችን ልሂቃን ቢኖሩም ልሂቃን የማይባሉትም ቢሆን የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በልምድ፣ በተሞክሮ፣ በተፈጥሮ ባለ ችሎታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ ምሁራኑም በትምህርታቸው በእድሜ ብስለታቸው፣ ባካበቱት ልምድ አስተዋፅኦዋቸው የጎላ ነው፡፡ አንድነት የሁለቱ ቅንጅት ነው፡፡ የአቅም ግንባታ ኘሮግራምም አለን፡፡ በሌላ መልኩ ድጋፋቸው በከተማ ነው የሚለው ጉዳይ ተደጋግሞ የተሰማ ነው፡፡ በምርጫ 97 ቅንጅት እንዲሁ ድጋፍ በከተማ ነው ሲባል ቆይቶ በገጠር ምን ዓይነት ድጋፍ እንዳለው በግልፅ ታይቷል፡፡ አንድነትም እንደዛ ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን 60 በመቶ የሚሆኑት የመሥራች ጉባዔው አባላት ከገጠር ነው የመጡት፡፡ አንድነት የገጠርም ሆነ የከተማ መሰረት እንዳለው ወደ ፊትም እናረጋግጣለን፡፡ ይህ እንዳይሆን ችግሮች ልንጋፈጥ ብንችልም ለህዝቡ እያጋለጥን እንቀጥላለን፡፡ ሪፖርተር፡- የቀድሞው ቅንጅት በገጠር ድጋፍ ያገኘው ህዝቡ ለውጥ ስለፈለገ ነው እንጂ ቅንጅትን አውቆት ወዶት አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ቅንጅት አግኝቶት የነበረውን ድጋፍ አንድነት በቀላሉ አያገኝም፡፡ በርካታ ሥራዎች ከፊት ለፊቱ ይጠብቁታል የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች አሉ፤ ዶ/ር ኃይሉ፡- የአንድ ፓርቲ አላማና ራዕይ እንጂ ስሙና ምልክቱ አይደለም ጠቃሚው ነገር፡፡ የሕዝባችንን የማሰብ ችሎታ የተረዳነው አልመሰለኝም፡፡ ህዝቡ ድጋፍ የሚሰጠው ምልክት አይቶ አይደለም፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር ያለው ህዝብ የአንድን ፓርቲ አላማና ራዕይ ይጠይቃል፡፡ የሚሰሩት ምንድነው? የሚያመጡት ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ሕዝቡ ይጠይቃል፡፡ ሕዝቡ እኮ ቀድሞ ሄዷል፡፡ ስለዚህ ዓላማችን ሀገርና ሕዝብን የሚጠቅም ከሆነ፣ ከኋላቀርነቷና ከድንቁርናዋ የሚገላግላት ከሆነ ይደግፈናል፡፡ አንድነት ከፍተኛ ስራና ፈተና ይጠብቀዋል የሚለው አስተያየት ትክክለኛ ነው፡፡ ቢደክምም ቢጠናከርም በራሱ ሥራ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በምርጫ 97 ሰው ቅንጅትን የመረጠው ኢሕአዴግን ስለጠላ ነው እንጂ ቅንጅትን ስላወቀና ስለወደደው አይደለም ይል ነበር፡፡ መጠላቱን ማመኑ ራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እውነታው ግን እሱ አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ፣ተሸንፈናል ታማኝ ተቃዋሚ ሆነን እንቀጥላለን፣ ያሉትን ሌላውም ላይ መድገም ነበረባቸው፡፡ እኛ ከእንግዲህ ጥሩ ወጤት ባናስመዘግብ የምንሸነፈው በራሳችን ድክመት ነው፡፡ እኛ ግን አቅማችን በፈቀደው መጠን እንሰራለን ብለን ነው እየተዘጋጀን ያለነው፡፡ አሁን የመጀመሪያው ሥራችን ያለፍንበት መንገድ ምን ይመስላል? ደካማና ጠንካራ ጎናችን ምን ነበሩ? ደካማ ጎናችንን እንዴት ነው የምናስወግደው? ጠንካራ ጎናችንንስ እንዴት ነው የምናጎለብተው? ብለን እንወያያለን፡፡ ይህን ካላደረግን ከዚህ በፊት የሰራናቸውን ስህተቶች መድገም የሆናል፡፡ ከእነዚህ ስህተቶች ፀድተን ነው የአዲሱን ፓርቲ ሥራ የምንጀምረው፡፡ ሪፖርተር፡- የአሁኑ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ የቅንጅት ፣ህጋዊ ወራሽ፣ ነኝ የሚሉ አካላትን ህገ ወጥ ናቸው ይላሉ፡፡ ምርጫ ቦርድ ስያሜውን ለእሳቸው እንደመወሰኑና አንድነትም ይህንን ቃል ስለተጠቀመ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን የሚሉን ነገር ይኖራል? ዶ/ር ኃይሉ፡- በጣም አብዛኞቻችን በምርጫ 97 የነበርንበት ፓርቲ እኮ ቅንጅት ነው ይባል የነበረው፡፡ "የቀድሞው ቅንጅት" የምንለው እኮ እኛ የነበርንበት ቅንጅት ለማለት እንጂ የአቶ አየለ ጫሚሶ ቅንጅትን ህልውና ለመካድ አይደለም፡፡ የአቶ አየለ ቅንጅት ምን እንደሆነ እኛም ህዝቡም በሚገባ ያውቃል፡፡ ብንስማማበትም ባንስማማበትም የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እናከብራለን፡፡ ሪፖርተር፡- በቅርቡ ፓርላማው ያፀደቀው የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ፓርቲዎች ስለሚያገኙት ገቢና መዋጮና እርዳታ ስለሚያደርጉ ግለሰቦችና ድርጅት ምርጫ ቦርድ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ ይፈቅዳል፡፡ የረቂቁ ማብራሪያ ደግሞ ህጉ ይህን ያደረገው አንዳንድ ፓርቲዎች ከውጭ በሚያገኙት እርዳታ በጥቅም ግጭት ላለመግባባት ስለተዳረጉ እንደሆነ ይገልፃል፤ ዶ/ር ኃይሉ፡- አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ሲታተም ቁጭ ብለን የምንመረምረው ይሆናል፡፡ ገንዘቡን በተመለከተ ህጉን አክብረን ነው የምንሰራው፡፡ እርዳታ የሚሰጡ ሰዎች ስማቸውን ማሳወቅ እንዳለባቸው ህጉ ያዛል፡፡ ሕዝቡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፍ መስጠት ይፈራል፡፡ የሚፈራው ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ተነስቶ ነው፡፡ ሕዝቡ ሲደግፍ የሚፈልገውን ፓርቲ በግልፅ መደገፍ መቻል አለበት፡፡ ፍርሃቱ አንዳንድ ጊዜም የሕዝቡ ድክመት ነው፡፡ ለመርዳት እየፈለገ ከደገፍኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጎዳለሁ የሚል ሃሳብ ያለው ይመስለኛል፡፡ ገዢው ፓርቲም ይሄን የሕዝቡን ፍርሃት ሊጠቀምበት የፈለገ ይመስለኛል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የገንዘብ አቅም እንዲዳከም መንግሥት ይፈልጋል፡፡ እኛ የምንቀሳቀሰው በትክክለኛ መንገድ ባገኘነው ድጋፍ ነው፡፡ ሕዝቡም ቢሆን እየዋለ እያደረ የሚደግፈውን ፓርቲ በግልፅ ሊደግፍ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለን ነው የምናምነው፡፡ ህጉ የወጣው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሽኩቻ ለማዳን ነው ማለቱ አስቂኝ ነወ፡፡ "አዛኝ ቅቤ አንጓች" የሚለው ዓይነት ነገር ነው፡፡ ቅንጅት በገንዘብ የጥቅም ግጭት አልነበረበትም፡፡ አንድነትም ይህ ችግር የለበትም፡፡ አዋጁን በጥንቃቄ አይተን የማንስማማበትና ጉድለት የምንለው ነገር ካየን ግን መስተካከል እንዲችሉ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት ጥረታችን ይቀጥላል፡፡ የኘሬስ ሕግ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የፓርቲዎች ምዝገባ ሕግ ያሳስበናል፡፡ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብትን የሚያጠቡ ናቸው፡፡ በሕግነታቸው ተቀብለን እንዲሻሻሉ ግን ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ ሪፖርተር፡- ቅንጅትን ለውድቀት የዳረገው የሥልጣን ሽኩቻ በአንድነት ፓርቲ ውስጥም እንዳቆጠቆጠ ከመስራች ጉባኤው በፊት አንዳንድ ጋዜጦች ዘግበው ነበር፤ ዶ/ር ኃይሉ፡- የመገናኛ ብዙሀን ሰዎች ይህንን ችግር ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጋችኋል፡፡ አግባብ የሌላቸው ቃላትን ትጠቀሙ ነበር፡፡ ሽኩቻ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ፉክክር ግን ነበረ፡፡ ይሄ ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ እንደውም ባለመታደልና ብስለት ደረጃ ላይ ለመድረስ ባለመቻላችን ነው እንጂ ለአንድ ቦታ ብቃት አለኝ የሚሉ ሰዎች በግልፅ ወጥተው የተወሰነ ጊዜ ተሰጥቷቸው ተወዳድረው የምረጡኝ ዘመቻ አድርገው አባላቱም የእጩዎቹን ችሎታ ገምግመው ነበር መምረጥ የሚኖርባቸው፡፡ ለወደፊት ግን ወደዛ እንሄዳለን፡፡ የአንድነት ፉክክር የፈለግነውን ያህል አልወጣም፡፡ መጠነኛ የውድድር ስሜት ነበር፡፡ ብዙዎች በመስራች ጉባዔው ራሳቸውን የጠቆሙበት ሁኔታ ነበር፡፡ መገናኛ ብዙሀን ግን ይህን ውድድር ሽኩቻ አስመሰለው ሕዝቡን ግራ አጋብተዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የቅንጅት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጭ ጋር አንድነት ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል? ዶ/ር ኃይሉ፡- በውጭ ሀገር የሚኖሩ በሃገራችን በሰላማዊ መንገድ ትግሉ ተካሂዶ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን መደራጀት ነበረባቸው፡፡ የቅንጅት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጭ አባላት በሹመት ነበር የተደራጁት፡፡ የአንድነት ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ከስር ጀምረው በዲሞክራሱያዊ ምርጫ ነው የተቀናጁት፡፡ ከዚህ በፊት ለቅንጅት ድጋፍ ይሰጡ የነበሩት አሁን ሙሉ በሙሉ የአንድነት ድጋፍ ሰጭ ናቸው፡፡ የሚከተሉትም አንድነት የሚሰጣቸውን መመሪያ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አንድነት ለአንዳንድ ይደግፉኛል ለሚላቸው ሚዲያዎች መግለጫና መረጃ ሲሰጥ የእኔ ተቃዋሚ ናቸው ለሚላቸው ግን በሩን ይዘጋል በመባል እየተተቸ ነው፡፡ ይህ ከምትታገሉት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ጋር አይጋጭም? ዶ/ር ኃይሉ፡- የሆነ ጊዜ ላይ የሚሰሩት ሥራ ጫና ካሳደረብንና ቁስሉን ካበረቱብን ጋዜጦች ጋር የነበረን ግንኙነት ጥሩ አልነበረም፡፡ ሪፖርተር፡- ስም ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ? ዶ/ር ኃይሉ፡- ለምሳሌ ሪፖርተር ጋዜጣን መውሰድ ትችላለህ፡፡ ሪፖርተር፡- ሪፖርተር ጋዜጣ ምን አደረጋችሁ? ዶ/ር ኃይሉ፡- በርዕሰ አንቀጹ እኮ "ቅንጅትን ከመሳሰሉ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን ጠብቃት" ብሎ ፀሎቱን ነግሮናል፡፡ ቅንጅት ምን አጠፋ? ይሄ አፍራሽ ነው፡፡ ቅንጅት ኢትዮጵያን የሚጎዳ አልነበረም፡፡ ሪፖርተር፡- አንድ ፓርቲ ደጋፊም ተቃዋሚም አለው፡፡ ሪፖርተር ስለቅንጅት ብዙ በጎ ነገሮችም ፅፏል . . ዶ/ር ኃይሉ፡- አሁን እኮ ሁሉም ነገር ቀርቷል፡፡ አሁን ድርጅታችን ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡ አንዱን የማቅረብና አንዱን የማግለል ነገር የለንም፡፡ ድክመታችንን የሚጠቁመን እንፈልጋለን፡፡ "አጥፋቸው" ብሎ ለሚፀልይ ድጋፍ ባንሰጥም ቢሯችን ለሁሉም ክፍት ነው፡፡ ሕዝቡ አሁን ሁሉንም የተሻለ ይረዳል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |