| ድርቅ ማለት ረሃብና ሞት መሆን የለበትም! |
|
|
| Wednesday, 25 June 2008 | |
እስከ አሁን ባለው ታሪካችን ድርቅ ማለት ረሃብ፣ ረሃብ ማለት ሞት እየሆነ መጥቷል፡፡ በሌሎች አገሮች ግን ድርቅ ማለት ረሃብና ሞት ማለት አይደለም፡፡ ዝናብ ባይዘንብም ረሃብ አይኖርም፡፡ እንዲያውም ድርቅ የተለመደ ክስተት ስለሚሆን ረሃብና ሞት አጀንዳ የማይሆንበት ሁኔታ አለ፡፡እኛ ግን ሁሉም ነገራችን በዝናብ ብቻ የሚተማመን ስለሆነና በአንድ የዝናብ ወቅት የሚገኘው የእህል ምርትም ከዚያው ዓመት ውጭ በዘለለ ተቆጥቦ ዓመት ሊዘልቅ ስለማይችል ድርቅ ይሆናል፡፡ የዓለም መገናኛ ብዙሃንም የዝናብ እጥረት አለ ሲባል ረሃብና ሞት መኖሩ አይቀርም ብለው አጥንቱ የወጣ የሕፃን ፎቶግራፍ ፍለጋ ይወጣሉ፡፡ ዝናብ ሳይዘንብልን ጠግበን አይተውን አያውቁምና፡፡ በአሁኑ ወቅትም የድርቅ፣ የረሃብና የሞት አጀንዳ እንደገና በአገራችን ላይ እያንዣበበ ነው፡፡ የዓለም ካሜራዎችም እንደገና ማንዣበቡን ተያይዘውታል፡፡ ይህ ሁኔታ በሕዝብም በመንግሥትም ዘንድ የሚፈጥረው ጫናና አሉታዊ መንፈስ አለ፡፡ መጠሪያችንና መለያችን ያ ፊልምና ያ ፎቶግራፍ ነው ወይ የሚል ጥያቄም ያስነሳብናል፡፡ ይህን እንዴት ነው ማየት ያለብን? ሕዝብም ሆነ መንግሥት በተለይም ደግሞ መንግሥት ችግሩን ሊከታተል የሚገባው የዓለም መገናኛ ብዙሃን ምን አሉ? ምን ፎቶግራፍ አወጡ? ምን ፊልም አስተላለፉ? በሚለው ላይ ተመስርቶ መሆን የለበትም፡፡ በዚህ መንገድ ቢሞክሩት መፍትሔና ማቆሚያ አይገኝለትም፡፡ መንግሥት ማተኮር ያለበት ያለውን የድርቅና የረሃብ ችግር በትክክል ስፋቱንና ጥልቀቱን ማወቅና ለችግሩ ተመጣጣኝ መፍትሔ ፈልጐ ድርቅ ማለት ረሃብና ሞት እንዳልሆነ ማረጋገጥ ነው፡፡ የአሁኑ ድርቅ ካለፈው ድርቅ ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው፤ የከፋ ነው፣ የተጋነነ ነው፣ ያልተጋነነ ነው በሚል ንትርክና መተራረብ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ በተጨባጭ ለችግሩ አፋጣኝ መልስና መፍትሔ መስጠት ነው፡፡ ልዩና ቀልጣፋ ትኩረትም ያስፈልገዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የችግሩ መጠን ካለፈው ጋር እያወዳደሩ የቁጥር ብዛት እያስተባበሉ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ከሚያወሩት ጋር እያነፃፀሩ የሚያሰራጩት መነታረክ መቆም አለበት፡፡ ስላለው ሁኔታ ዓለም ማወቅ ያለበትን ማሳወቁ ተገቢ ነው፡፡ ችግር እስካለ ድረስ ደግሞ ለችግሩ ተመጣጣኝ መፍትሔ መስጠት እንጂ ካለፈው የባሰ ነው ሲባል መስጋት፣ ካለፈው የተሻለ ነው ሲባል መረጋጋት አይደለም፡፡ ስላለው ችግር በግልፅ እናውራ፤ ላለው ችግር ደግሞ ተመጣጣኝ መፍትሔ ይሰጥ፡፡ ድርቅ ሲከሰት ለምን ረሃብና ሞት ይከተላል? ድርቅ ማለት ውሃ የለም ማለት ነው? ውሃ የለም ማለት ምግብ የለም ማለት ነው? ምግብ የለም ማለት ረሃብና ሞት ነው ተብሎ ሊደመደም ይችላል፡፡ መሆን ያለበት ግን ይህ ቀመር አይደለም፡፡ ዝናብ ባይዘንብ በሌላ መንገድ ምግብ ማምረት አይቻልም ወይ? መስኖ መጠቀም አይቻልም ወይ? በአንዳንድ አካባቢዎች ዝናብ ባይኖር፣ ዝናብ ባለባቸው አካባቢዎች በቂ እህል አምርቶ ከምግብ እጥረት መገላገል፣ ረሃብና ሞትን ማስወገድ አይቻልም ወይ? ብዙ ምርት እያመረቱ ማከማቸትና በችግር ጊዜ መጠቀም አይቻልም እያልን ነው ወይ? የምናስተካክለውና የምንቀይረው ፖሊሲ የለም ወይ? በእንዲህ ዓይነቱ ቁልፍና ዓበይት ነጥቦች ላይ አትኩረን ነው መንቀሳቀስ ያለብን፡፡ እንዲህ ስናደርግም ነው የዓለም ሚዲያዎች ከጐናችን እንዲቆሙ ማድረግ የሚቻለው፡፡ አገር ላይ ችግር ሲከሰት ሁሉም ወገን ችግሩን ለመፍታት መረባረብ አለበት፡፡ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ችግሩን ለመፍታት መረባረብ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ችግራ ለመፍታት በጋራ የምንቀሳቀስ መሆናችንን ስናሳይ ነው ዓለምም ከጐናችን የሚሰለፈው፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ የአገር ችግር ጊዜ የግልና የፓርቲ ፍላጐትን ወደ ጐን ትተን ቅድሚያ የሕዝብን ችግር ለመፍታት መረባረብ መቻል ይኖርብናል፡፡ የአሁኑ የምግብ እጥረት ከሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ የመጣ ስለሆነ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ በናረበት፣ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች በተወደዱበት፣ በዓለም ደረጃ የምግብ ነገር ከፍተኛ አጀንዳ በሆነበት ወቅት የተከሰተ በመሆኑ እርዳታ ለማሰበሰብና ለማሰራጨትም ቀላል አይሆንም፡፡ ይህ ስለሆነም ነው ልዩ መተሳሰብና መረባረብ የሚያስፈልገን፡፡ መድረኩን ታሪክ የምንለውጥበት መድረክ እናድርገው፡፡ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ድርቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለዓለም የምናሳይበት አጋጣሚ እናድርገው፡፡ ምግብ ለማምረትና ሕይወት ለማዳን ብዙ መንገዶች እንዳሉ የምናሳይበት ወቅት እናድርገው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካልዘነበም መኖር የሚችል መሆኑን ከማንም በላይ ማረጋገጥ ያለብን እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ በዚህ መንገድ ካካሄድነው ወቀሳ አይኖርም፤ ካለም ወቃሹ ራሱ ያፍርበታል፡፡ በጋራ ተባብረን ችግሩን መፍታት ካቃተን ግን ብንወቀስም አናማርር፡፡ ለኢትዮጵያ ድርቅ ማለት ረሃብና ሞት መሆኑን እናስቁም! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |