| በገበሬዎች ላይ ያነጣጠረው የማዳበሪያ ችግር |
|
|
| Wednesday, 25 June 2008 | |
በዳዊት ታዬአቶ አለማየሁ ጉሜ የ34 ዓመት ጐልማሳ ነው፡፡ በአደአ ወረዳ ቀምቡርሳ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ነው፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን የገብርና ሥራን ከወላጆቹ የወረሰው መሆኑን ይናገራል፡፡ ከሚኖርበት ግቢ ውጪ የእርሻ መሬት የለውም፡፡ ግን በየዓመቱ መሬት ተከራይቶ ያርሳል፡፡ በኪራይ አርሶ የሚያገኘው ምርት ቤተሰቡን የማያስተዳድርለትና የማይበቃው በመሆኑ እንደምንም ብሎ ጋሪ ገዝቶ ለመስራት ተገድዷል፡፡ አለማየሁ እንደሚለው፣ ቀደም ባሉ ዓመታት አንድ ሔክታር መሬት 3200 ብር ለአንድ ዓመት ይከራይ ነበር፡፡ አሁን ግን የመሬት ዋጋ በመጨመሩ የአንድ ሔክታር መሬት ኪራይ አራት ሺህ ብር ደርሷል፡፡ "በኪራይ አርሰህ የምታገኘው ምርት ብዙ ውጤት የለውም፡፡ የማገኘው ትርፍ ከዘራሁት ጤፍ የማገኘው ጭድ ነው፡፡ ጭዱን ደግሞ ለጋሪዬ ፈረሶች ቀለብ ስለማደርገው ይጠቅመኛል፡፡ ከዚያ ውጪ ምንም ትርፍ የለውም" ይላል፡፡ ለመሬት ኪራይና ለማዳበሪያ የሚከፍለው ብዙ ስለሆነ ለቀለብ የሚሆን ትንሽ ካገኘ እድለኛ ነው፡፡ ዘንድሮ የመሬት ዋጋና በተለይም የማዳበሪያ በእጥፍ መጨመር ገበሬውን አሳስቦታል፡፡ ስጋቱ የማዳበሪያ ዋጋ በእጥፍ ማደግ ብቻ ሳይሆን የማዳበሪያ እደላ አሠራር መቀየሩም ነው፡፡ እያንዳንዱ ገበሬ በልምድ ለአንድ ሄክታር መሬት 15ዐ ኪሎ ግራም ዩሪያና ዳኘ የተባሉትን የአፈር ማዳበሪያ ይጠቀማል፡፡ ባለፈው ዓመት ለዚህ 15ዐ ኪሎ ግራም የነበረው በቅድሚያ ይከፈል የነበረው 355 ብር ሲሆን ቀሪውን ከ3ዐዐ ብር በላይ የሚሆን ክፍያ ደግሞ ምርቱ ሲደርስ ይከፈል ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ይህ ዋጋ 1 ሺህ አንድ መቶ 9ዐ ብር ደርሷል፡፡ በዱቤ ይወሰድ ቢባል እንኳን በቅድሚያ ከ760 ብር በላይ መከፈል እንደሚኖርበት ይገልፃል፡፡ የአድአ ወረዳ ከማዳበሪያ አጠቃቀም ጋር ቀዳሚ ስም አላት፡፡ በዚህ ወረዳ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቀበሌ ገበሬ ማህበራት ውስጥ ያነጋገርናቸው ገበሬዎችና የግብርና ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ኢትዮጵያ ወስጥ በማዳበሪያ ማምረት የተጀመረው በዚህ አካባቢ ነው፡፡ ከ60 ዓመታት በፊት በዚህ አካባቢ ይንቀሳቀስ ለነበረ አንድ የውጭ ተራድኦ ድርጅት የአካባቢውን ገበሬዎች በማዳበሪያ ማምረት እንዳስለመደና ከዚህ በኋላ እየተስፋፋ እንደመጣ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በዚህ አካባቢና በሌላው የአገሪቱ ክፍል ያሉ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ መጠቀም እርሻ ጀመሩ፡፡ መሬቱ ያለማዳበሪያ ማፍራት አቁሟል፡፡ የአድአ ወረዳ ጉሜ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ቁንቡርሣ ገበሬ ማህበር እየተባለ በሚጠራው መንደር ውስጥ ያገኘናቸው የ46 ዓመቱ አርሶ አደር አቶ ሲሣይ አስማማው እንደገለፁት ከሆነ ደግሞ፣ በዚህ አካባቢ ማዳበሪያ ከሌለ ምርት የለም፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ማዳበሪያን ለማስገባት በአገር ውስጥ የሚካሄደው ጨረታ በየጊዜው እዚህ ወረዳ በዚህ ዓመት ምርት የሚሆነው የማዳበሪያ ጨረታ ሽያጭ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ3ዐዐ ዶላር በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህ ዋጋ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ የጨረታ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ መጨመሩን ያመለክታል፡፡ ባለፈው ዓመት የአንድ ቶን የማዳበሪያ የጨረታ ዋጋ ከ366 እስከ 400 ዶላር ነበር፡፡ የዘንድሮው የዋጋ ጭማሪ በቀጣይ ሊኖር ከሚችለው ጋር ሲነፃፀር አስጊ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ለ2000/2001 የምርት ዘመን የሚሆነው ማዳበሪያ ቀድሞ በመግባቱ እንጂ የአንድ ቶን ማዳበሪያ ዋጋ እስከ አንድ ሺህ ዶላር በቀጣዩ ዓመት ስለሚደርስ እጅግ ይጨምራል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ከ1997 እስከ 2000 ባለው ጊዜ ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ 14ቱ ዩኒየኖች ማዳበሪያ አስገብተዋል፡፡ እነዚህ 14 ዩኒየኖች በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ 6 መቶ 77 ሺ 45ዐ ሜትሪክ ቶን ዳፕና 228 ሺህ 75ዐ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ለአባሎቻቸው ሸጠዋል፡፡ ዩኒየኖቹ ማዳበሪያ የማስገባት 62 በመቶ መሸፈን ችለዋል፡፡ እነዚህ ዩኒየኖች ማዳበሪያ ለማስገባት እንዲችሉ መንግሥት ከ1997 እስከ 2ዐዐዐ ባለው ጊዜ ውስጥ ከ4.18 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር እንዳገኙ ይገልፃል፡፡ ከፌዴራል የህብረት ሥራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የህብረት ሥራ ማህበራት ቁጥር ከ23 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡ እነዚህ ማህበራትም ከ4.6 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን ይዘዋል፡፡ በዩኒየን ደረጃም አንድ መቶ አርባ ሦስት የሚሆኑ ናቸው፡፡ ከትናንት በስቲያ የተላለፈው መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት እያሻቀበ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ ተከትሎ ለከፍተኛ ወጪ ከተዳረጉና በምርታቸው ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ላይ ከሚገኙት ኩባንያዎች መካከል የማዳበሪያ አምራች ኩባንያዎች ቀዳሚ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ የማዳበሪያ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሊመጣ የቻለው የህዝብ ቁጥር እድገት አንዱ ምክንያት መሆኑንም ገልጿል፡፡ በዓለም ላይ የማዳበሪያ ዋጋ ማሻቀብ ችግር እየፈጠረባቸው ካሉ አገራት መካከል አንዷ ቻይና ናት፡፡ ቻይና ይህንን ችግር ለማቃለል በመፍትሔነት የወሰደችው ማዳበሪያን ከሌሎች አገሮች ጋር በሽርክና መስራትን ሲሆን ይህንኑ ወደ ተግባር ለመለወጥ በእንቅስቃሴ ላይ ነች፡፡ ለማዳበሪያ ምርት ወሳኝ ከሆኑ ግብአቶች መካከል አንዱ የሆነው ፖታሺየም ሲሆን አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የአንድ ቶን ዋጋ 1ዐዐዐ ዶላር በመድረሱ ለማዳበሪያ አምራቾች የራስ ምታት ሆኗል፡፡ በአድአ ወረዳ ያነጋገርናቸው ገበሬዎች እንደገለፁት በአንድና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደማዳበሪያ ዋጋ የናረ ነገር እንዳላጋጠማቸው ነው፡፡ ማዳበሪያ በእጥፍ ጨመረ ማለት ገበሬው ትልቅ ችግር ውስጥ እንደገባ ይቆጠራልና መንግሥት ይህንን ጉዳይ ሊያስብበት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በአደአ ወረዳ የአጼ ገበሬ ማህበር ውስጥ ያገኘናቸው የ3ዐ ዓመቱ አርሶ አደር አቶ ደሜ ገረመው በበኩሉ ለዘንድሮው እርሻ መሬቱን ቢያዘጋጅም የማዳበሪያ ጉዳይ ግን ሥጋት ወስጥ እንደከተተው ይገልፃል፡፡ "እኔ ሦስት ቀርጥ አለኝ (የአንድ ሔክታር ሦስት አራተኛው እጅ ማለት ነው) ከዚህ ከምዘራው ቀይ ጤፍ 7 ኩንታል ገደማ አገኛለሁ፡፡ ለዘር የሚሆነኝ ጤፍ አለኝ፡፡ የማዳበሪያ ዋጋ ስለጨመረና ቅድሚያ ከፊሉ ሰዓት ባለ የማደርገው ያሉኝ ከብቶች መሸጥ ነው፡፡ የግድ ማምረት ስላለብኝ የማደርገው ይህንኑ ነው፡፡ አማራጭ ካገኘሁ ልበደርም እችላለሁ" ብሏል፡፡ አቶ ሲሳይ ግን የተለየ አመለካከት አላቸው፡፡ መንግሥት አቤቱታችንን ሰምቶ መፍትሔ ካልፈለገልን አቅማችን በሚፈቅደው መጠን ማዳበሪያ እንገዛለን፡፡ ማምረት ይገባን የበረውን ምርት ስለማናመርት እኛም አገርም እንቸገራለን፡፡ አሁን እንደሚወራው ገበሬው ገንዘብ አለው ተብሎ ከሆነ እኛ የለንም፡፡ ቢኖረን እኛም በካሽ ብንገዛ ደስ ይለን ነበር፡፡ በአንዴ ግን የሚሆን ነገር ስለሌለ ቅድሚያ ክፈሉ የተባለውን ነገር ቢቆይ ይመረጣል" ብለዋል፡፡ አርሶ አደር ሲሳይ አስማማውን በወቅታዊ የማዳበሪያ ጉዳይ ላይ አነጋግረናቸው የሚከተለውን መልስ ሰጥተውናል፡፡ የማዳበሪያ ዋጋ ምን ያህል ደረሰ? በፊት ከነበረበት ዋጋ በእጥፍ ጨምሮብናል፡፡ የራስዎ መሬት አለዎት? ሁለት ሔክታር አርሳለሁ፡፡ ለሁለቱ ሔክታር ምን ያህል ማዳበሪያ ይጠቀማሉ? በፊት ማዳበሪያውን በዱቤ እንወስድና ግማሹን በአመት ነበር የምንከፍለው፡፡ አምና ለአንዱ ሔክታር ማዳበሪያ ቀብድ 355 ነበር የከፈልነው፡፡ አሁን በቀብድ የምትወስዱ ከሆነ 760 ብር ትከፍላላችሁ ብለውን ነበር፡፡ ነገር ግን ይህም ቀርቶ ሙሉ በሙሉ ካልከፈላችሁ አትወስዱም አሉን፡፡ እጥፍም ጨምሮ ጭራሽ በካሽ ካልከፈላችሁ አትወስዱም እየተባልን ነው፡፡ ማዳበሪያውን ማነው የሚሰጣችሁ? ዩኒየኑ ነው የሚሰጠን፡፡ እርስዎ በመሬትዎ ላይ ምንድ ነው የሚዘሩት? ስንዴና ጤፍ ነበር የምዘራበት፡፡ አሁን መዝራት የምችለው ማዳበሪያውን ሳገኝ ነው፡፡ ማዳበሪያው ከሌለ ምን እዘራለሁ ብለህ ነው ገና ነው፡፡ ማዳበሪያውን ካላገኘን ቁጭ ነው፡፡ ማዳበሪያው በምን መልኩ እንዲሰጣችሁ ነው የምትፈልጉት? ማዳበሪያው እንደቀድሞው ይሰጠን ነው የምንለው፡፡ ምንም እንኳ የዋጋ ንረቱ ቢኖርም የማዳበሪያ ዋጋ እጥፍ መጨመር የለበትም፡፡ ጭማሪው ብዙ ነው፡፡ ይህንን ያህል ዋጋ መጨመሩና በዱቤ አትወስዱም መባልን እንደሰማን ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታችንን አድርሰናል፡፡ እስካሁን ግን መፍትሄ አልተገኘም፡፡ ለማን አቤት አላችሁ? ለግብርናም አቤት ብለናል፡፡ ለሚመለከተው ሁሉ ግልባጭ አድርገናል፡፡ አገልግሎትም ዝም ብሎ ቁጭ ብሏል ገበሬውም በገንዘብ አንወስድም ብሎ ቁጭ ብሏል፡፡ ያለ ማዳበሪያ ብትዘሩ ምን ችግር ያመጣል? ኪሣራ ነው፡፡ መሬቱ ያለማዳበሪያ አይሰጥም፡፡ ማዳበሪያ ተጠቅመው ቢዘሩ ምን ያህል ምርት ያገኛሉ? እንደ ዘመኑ ነው፡፡ ውሃ ካልበዛ በሔክታር እስከ 15 ኩንታል ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ሃያ ኩንታልም የሚደርስበት ጊዜ አለ፡፡ ማዳበሪያ ከሌለው መሬቱ አይሰጥም፡፡ ማዳበሪያ ከሌለ ከብትም የለም፡፡ ዋናው ማዳበሪያ ነው፡፡ ይህንን መንግሥት ማስተካከል አለበት፡፡ መንግሥት ምን ያድርግ? መንግሥት የማዳበሪያ እደላውን እንደ ቀድሞው አድርጎ ምርታችንን አሳድገን እኛም መንግስትም እንዲጠቀም ነው የምፈልገው፡፡ ምርቱ ካለ እናድጋለን፣ መንግሥትም ያድጋል፡፡ ልማቱም ጥሩ ይሆናል፡፡ በተለይ በአድአ መሬቱ ማዳበሪያ ለምዷልና ያለ ማዳበሪያ ምንም የምናደርገው ነገር የለም፡፡ ማዳበሪያ እዚህ አካባቢ ነው የተጀመረው የሚሉ አሉ እዚህ አካባቢ ነው የተጀመረው፡፡ ከዱሮም ጀምሮ የዚህ አካባቢ ገበሬ በማዳበሪያ ይጠቀማል፡፡ ያለ ማዳበሪያ አይበቅልም፡፡ ይጠፋብናል፡፡ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ የማዳበሪያ እጥረት አለ? ማዳበሪያ መወደድ የጀመረው አምና ነው፡፡ ብዙ እየጨመረብን ነው፡፡ አሁን ገበሬው መልሶ ወደ ቁጠባ ገብቷል፡፡ በዚህ ዋጋ ገዝቶ ለመጠቀም አቅሙ አይፈቅድለትም፡፡ ጠንካራ የሚባሉት ገበሬዎች እንኳን አይችሉም፡፡ 8 ሔክታር መሬት ያለው በአዲሱ ታሪፍ መወሰድ የሚቻለው ለአራቱ ቢሆን ነው፡፡ ማዳበሪያ ርካሽ ገዝተናል የምትሉት መቼ ነው? በደርግ ዘመን አንድ መቶ ብር ነበር፡፡ አሁን እያደገ መጥቶ እዚህ ደረሰ፡፡ አሁን ዱቤ ስለማይሰጥ ለአንዱ ሔክታር 1ሺህ 90 ብር ገብቷል ተብለናል፡፡ አኛ ይህንን አንችልም ነው የምንለው፡፡ ያለ ማዳበሪያ የሚዘራ ዘር የለም? ሽንብራ ሊዘራ ይችላል፡፡ ሽንብራ ምን ይሆናል እንጀራ አይሆን፡፡ ጤፍ ብንዘራ ግን ምርቱን ሸጠን ጭዱን እንጠቀምበታል፡፡ ጭድ ይህን ያህል ዋጋ አለው? አዎ፡፡ ጭድ እያሰርን እንሸጣለን፡፡ እስከ ጅቡቲ ድረስ እየተላከ ነው፡፡ ምን ያደርጋል? ለከብቶች ይሰጣል አሉ፡፡ አሁን በደላላ በመኪና እየዞሩ እየወሰዱ በማሽን አስረው ይሸጣሉ፡፡ ይችን ክምር (ክምሩን እያሳዩ) አሁን ከሁለት ሺህ ብር በላይ ይሸጣል፡፡ አምና እንዴት ነበር ምርቱ? ባለፈው ምርታችን ወቅት ዝናብ በዝቶ ብዙ ምርት አላገኘንም፡፡ ቀንሶብናል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ገንዘብ የለንም ማዳበሪያ ከፍለን አንገዛም ያልነው፡፡ ዘንድሮስ እንዴት ነው? አገባቡ ጥሩ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |