| ማመስገን ያለበት ሰጪው ነው |
|
|
| Wednesday, 25 June 2008 | |
|
"ይህቺ የሱፊዎች ናት፡፡ እንደ ፈላስፋም እንደ ባህታዊም ያረጋቸዋል ሱፊዎች፡፡ እቻትልህ፡- አሊ መጣና ፣እባክህን ያ እንትና ችግር ደረሰበት መቶ ዲናር ስጠኝ እስኪ?፣ አለው፡፡
ከቦርሳው አውጥቶ ሰጠው፡፡ ተቀብሎት ሄደ፡፡ በሳምንቱ አሊ ተመልሶ መጣ፡፡ ፣ባይገርምህ ያ ወዳጃችን ችግሩ ጠናበት፡፡ ዛሬም መቶ ዲናር አምጣ፣፣ አለው፡፡ ፣እሺ ቆየኝ፣ አለና ፈላልጎ፣ የጐደለውንም ሞላልቶ ሰጠው፡፡ አሊ ተቀብሎት ይሄዳል፡፡ ከሳምንታት በኋላ ይመለሳል፡፡ አሁንም ያ ችግር ስላልተወገደ መቶ ዲናር እንደሚፈልግ ይነግረዋል፡፡ ቢፈላልግ የለም፡፡ ፣ቆየኝ ብሎ፣ ከጐረቤት ተበድሮ ሰጠው፡፡ አሊ ገንዘቡን ተቀብሎ ሲጣደፍ ፣አንዴ ቆየኝ"፣ አለው ሰጪው፡፡ መጀመሪያ ስትመጣ መቶ ዲናር ሰጠሁህ፡፡ ቀጥሎ መጣህ አሟልቼ ሰጠሁህ፡፡ አሁን ባሰና ተበድሬ ሰጠሁህ፡፡ እንዲያው ይህንን ያህል ስለግስህ አላህ ይስጥልኝ ማለትን ማንን ገደለ?፣ ሲለው፣ ጥቂት አስቦ፣ ፣አላህ ይስጥልኝ ማለት ያስፈልጋል እንዴ? አለው፡፡ ካስፈለገማ አላህ ይስጥልኝ ብሎ ማመስገን ያለበት ሰጪው ነው፡፡ አስቀድሞ አላህ ሲሰጠው ነዋ እሱ ለሰው መስጠት የቻለው፡፡፣ (ዘነበ ወላ፣ ማስታወሻ፣ 1993) ሦስቱ ዓሦች ሦስት ዓሦች ያሉበት የጠራ ትልቅ ባሕር ነበር፡፡ ከነዚያም ከሦስቱ ዓሣዎች አንዲቱ አእምሮ ያላት ብልኅ ነበረች፡፡ ሁለተኛዋ ከሷ የበለጠች ዕውቀት ያላት ብልኅ የብልኅ ብልኅ ነበረች፡፡ ሦስተኛዋ ግን ዕውቀት የሌላት ሰነፍ ነበረች፡፡ ያም ትልቅ ባሕር ከፍ ያለ በገለልታ ቦታ ነበረ፡፡ አንድ ሰው ስንኳ የማይደርስበት ካጠገቡም ፈሳሽ ውሃ ያለበት ነበረ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ዓሣ አጥማጆች በፈሳሹ አጠገብ ሲያልፉ ያንን ጥልቅ ባሕር አዩና ወደዚያ ባሕር ተመልሰው መጥተው በሱ ውስጥ ያለውን ለማደን ተቃጠሩ፡፡ ዓሣዎቹም የአዳኞቹን ነገር ሰምተው አሳባቸውን አወቁ፡፡ ዕውቀት ያደረባት የብልኅ ብልኅ ያልናት የአዳኞቹን ንግግር በሰማች ጊዜ ጠርጥራ ፈርታ ዛሬ ነገ ሳትል ወዲያው በፍጥነት ተነሥታ በጣም ጥልቅ ወደ ሆነው ክፍል ሸሽታ ዳነች፡፡ (ከበደ ሚካኤል፣ ታሪክና ምሳሌ፣ 1966) መጭ ብየ መጣሁ ላፈ ንጉሥ አንድ ሰው ነገሩ እንዲቃናለት ሲል ብር ሰጠ፡፡ አሥርም ሃያም ይሁን አናውቅም፡፡ ባላጋራው ብር መስጠቱን ቢሰማ በቅሎ ይዞ መጣ፡፡ የመጣው ላፈ ንጉሥ ብር ብየ መጣሁ አላቸው ልብ እንዲያረጉት ነው፡፡ በቅሎ ይዞ የመጣው መጭ ብየ መጣሁ አላቸው፡፡ ቀልደኛ አቶ አማ የሚባል ኃብታም ጌታ ነበር፡፡ እጅግ አጥብቆ ቀልድ ወዳጅ ነበረ፡፡ አጋፋሪውም እንደ ጌታው ቀልድ ወዳጅ ነበረ፡፡ እንደዚሁ ሁነው ሲኖሩ አንድ ቀን አቶ አማ ጥሩ በቅሎ ጫንና መንገድ አሳያት ብሎ አዘዘው፡፡ እሺ የኔታ ብሎ በቅሎዋን ጭኖ ተቀምጦባት ሔደ፡፡ ሁለት መንታ መንገድ ሲደርስ ዱብ ብሎ ወርዶ ያውልሽ እንግዴህ የሸዋ መንገድ ይህ ነው፡፡ የጐጃምም መንገድ ይህ ነው፡፡ የጐንደርም መንገድ ይህ ነው፡፡ የትግሬም መንገድ ይህ ነው ጌታሽ መንገድ አሳያት ብሎኛልና የወደድሽውን መንገድ ይዘሽ ሒጂ ብሎ እንደተጫነች ለቀቃትና ወደ ቅልውጡ ውሎ ወደ ማታ ኸጌታው ተመለሰ፡፡ እጅ ተነሣ በኋላ አቶ አማ ጌታው በል አንተ ለበቅሎዋ መንገድ አሳየሀትን ብሎ ጠየቀው፡፡ አዎን የኔታ የአራቱን አገር መንገድ አሳየኋት፡፡ የወደድሽውን ያዥና ሒጂ ብየ ለቀቅኋት አለ፡፡ ጌትዮም ተናዶ መቼም መሽቷልና አድረው በነግህ ተነሱ፡፡ በቅሎዋን እንፈልግ ብሎ አቶ አማ አሽከሮቹንና አጋፋሪውን አዘዘ፡፡ ተነስተው ፍለጋቸውን ያዙ፡፡ ሲፈልጉ ሲፈልጉ በቅሎዋ ድምጥማጥዋ ጠፋ፡፡ በመጨረሻ የጣላት አጋፋሪ ያቶ አማ አሽከር አገኛት፡፡ ዳሩ ግን ገሚስ ጐንዋን ጅብ ተጋበዛት፡፡ የኔታ በቅሎዋን አገኘኋት ዳሩ ግን ጅብ በልቷት፤ ጌትዮው አማ አለ አጋፋሪ አላማም አመስግኖ በላ እንጂ፡፡ (ማጆር ጄ.አይ.ኢዲ፣ የአማርኛ መድበለ ምንባብ፣ 1993) ህሊና ሲናገር አልቅሰሻል አሉኝ እርርን ድብንን፡፡ ስለምን አለቀስሽ"? አልቆረጥሽም እንዴ? . . . እንባ ማቆሚያ አለው የቆረጡ ለታ፣ አለሁኝ እንጂ እኔ አልቅሼው አይወጣ ሞቼው አይረታ፡፡ ነፍሰ ገዳይ እኔ አንቺ ምን ሆንሽና እኔው ለኔ ላልቅስ እሽሩሩ ቢሉት አይተኛ ህሊና፡፡ (ወንድዬ አሊ፣ ውበት እና ህይወት፣ 1998) ሲኒማ ቻርልስ ሚኬል እንደጻፈው ምኒልክ ከእስቴቬኒን ጋር ሲጫወቱ እስቲቬኒን የሲኒማን መኖር አጫወቷቸው፡፡ "ሲኒማ ምንድነው እሱ?" ብለው ጠየቁ፡፡ እስቲቬኒንም የሲኒማን ታሪክ ዘርዝሮ ካስረዳ በኋላ ለማስመጣት ፈልጐ ቄሶችን ፈርቶ መተዉን ነገራቸው፡፡ ምኒልክም "ቄስ ይኑር አይኑር እሱን ተወውና ይሄን ነገር ለማየት ቶሎ ብለህ አስመጣ" ብለው አዘዙት፡፡ በ1889 ዓ.ም. ኘሮጀክተር ከነ ፊልሙ መጣ፡፡ ምኒልክም መኳንንቶቻቸውን ይዘው ሚያዚያ 1 ቀን ፊልሙን ለመመልከት ከእልፍኝ ተገኙ፡፡ ፊልሙ ሃይማኖት ነክ ሆኖ የሚያሳየው የክርስቶስን ታሪክ ነበር፡፡ ክርስቶስ በባህር ላይ እየተራመደ በእግሩ ሲሄደ በታየበት ወቅት መኳንንቱም ሁለም ተነስተው እጅ ነሱ፡፡ ፊልሙ አልቆ ከራስ ጋር በሚጨዋወቱበት ጊዜ ምኒልክ " . . . እነኚህ ፈረንጆች ማይሠሩት ነገር የለም፡፡ ሁሉንም ነገር ሲሰሩ የሰው ነፍስ ብቻ መስራት አልቻሉም" ብለው ተናገሩ፡፡ የመጀመሪያው የሕዝብ ሲኒማ ቤት በ1890 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተከፈተ፡፡ ሲኒማ ቤቱን የከፈተው አንድ ከአልጄሪያ የመጣ ፈረንሣያዊ ነው፡፡ ይህን በዘመኑ የማይታመን ምትሀት መሰል ነገር የሚያየው ሕዝብ የሲኒማ ቤቱን ሰይጣን ቤት ብሎ ሰየመው፡፡ በተለይ ቀሳውስቱ ሕዝቡ ከሰይጣን ቤት እየሄደ ሰይጣን እንዳያይ እያሉ ስላወገዙ ሲኒማ ቤቱ ከሰረ፡፡ ባለቤቱም የሲኒማ ማሳያውን እቃ አዲስ አበባ ከነበረው የኢጣሊያ ሚኒስትር ለቺኮዲኮላ ሸጦ አገር ጥሎ ወጣ፡፡ የኢጣሊያኑ ሚኒስትር ያን ኘሮጄክት ለአጤ ምኒልክ በስጦታ ሰጠ፡፡ ምኒልክም በቤተ መንግሥታቸ አዳራሽ ከመኳንንቱና ከቀሳውስቱ ጋር መንፈሳዊ ፊልሞችን በማየት እንዲለመድ ካደረጉ በኋላ እዚያ እንደሚገኝ እምነት ተጥሎ በ1901 ዓ.ም. ወንድማማቾቹ እነ ዛይኮቢች ለሕዝብ የሚሆን ሌላ ሲኒማ ቤት በምኒልክ አበረታችነት ከፍተው ነበር፡፡ የህም ሲኒማ ቤት አንድ ዓመት ያህል ከሠራ በኋላ በኀኘሮጀክተሩ መበላሸት ምክንያት ተዘጋ፡፡ ከዚህ በኋላ የተሳካ ሥራ የተጀመረው ድሬዳዋ ውስጥ ነው፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ፣ አጤ ምኒልክ፣ 1984) የኔውትሮን ቦምብ የኔውትሮን ቦምብ በጣም ከፍተኛ ራዲኤሽን የሚያስከትል እጅግ አረመኔያዊ ዓይነት የኒክሌየር መሳሪያ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ሕንጻዎችንና መኖሪያ ቤቶችን እጅግም ሳይነካ በሕያው ነገሮች ሁሉ ከፍተኛ እልቂት እንዲያደርስ የተፈለሰፈ መሳሪያ ነው፡፡ ከሌላ ዓይነት ራዲኤሽን (ጨረር) ጋር ሲነጻጸር የኔውትሮን ራዲኤሽን ኃይል በአሥር እጅ የበለጠ ነው፡፡ ኔውትሮኖች በሰው ልጅና በእንሰሳት የአካል ክፍሎች ውስጥ ገብተው ሕዋሶችን ያፈርሳሉ፡፡ የኔወትሮን ራዲኤሽን አሰቃቂነቱ በቀጥታ በመግደሉ ብቻ ሳይሆን ሕያው ነፍሳትን በመመረዝ ለሚመጡት ትውልዶች ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት በኔወትሮን ራዲኤሽን የተመረዘ ሰው የኋላ ኋላ ይሞታል፣ ልጆች ቢወልድም ልጆቹ ይሞታሉ ወይም አካለ ጎዶሎዎች ይሆናሉ፡፡ (የኖቨስቲ አገልግሎት ማተሚያ ቤት፣ 100 ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፣ ሞስኮ 1983) ገራገር ወሬዎች ፖሊሱን አሳማ ብሎ የጠራው ተቀጣ ፖሊሱን አሳማ በማለት የጠራው የ22 ዓመቱ የኒውዚርላንድ ወጣት ለአንድ ቀን በአሳማ እርባታ ግቢ ውስጥ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ ዘ ቤይ ኦፍ ኘሌንቲ ታይምስ እንዳስታወቀው በፖሊስና በአሳማ መካከል ያለውን ልዩነት አስመልክቶም አጠር ያለ ጥናታዊ ፅሁፍ እንዲፅፍ የአካባቢው ፍርድ ቤት ወስኖበታል፡፡ "በጣም ሰክሬ ነበር፤ አሁን በተፈጠረው አጋጣሚ ምክንያት መጠጣት አቁሜያሁ፡፡ የኔንም ሆነ የፖሊሱን ሰዓት አጥፍቻለሁ" ሲል ወጣቱ ተናግሯል፡፡ ወጣቱ የተቀጣው አግባብ ያልሆነ ቃል በመጠቀም ፖሊሱን ጠርቷል በሚል ነበር፡፡ ወጣቱ "በፖሊስና በአሳማ መካከል ምንም አንድ የሚያደርግ ባህሪ እንደሌለ ተገንዝቤያለሁ" ብሏል፡፡ ወፍራሟ ሕፃን ከእድሜ እኩዮቿ በክብደቷ ምክንያት የምትለየው ጀሲካ ከአራት ዓመታት በፊት ዶክተር ፊት ስትቀርብ 110 ኪሎ ትመዝን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ 222 ኪሎ ግራም ትመዝናለች፡፡ በየቀኑ ከምትጠጣው ኮካ ኮላ 1ዐ ሺህ ካሎሪ ታገኛለች፡፡ 15 ሃምበርገርና በብዙ ኪሎ ግራም የሚገመት ቸኮሌት የአንድ ቀን ምግቧ ነው ሲል ፈን ኒውስ ዘግቧል፡፡ በቀን የምትመገበው ምግብ ለአንዳንድ የእድሜ እኩዮቿ ህፃናት የግማሽ ዓመት ቀለብ ነው፡፡ የጀሲካ አናት ካሮሊን እንደገለፀችው "ጠዋት ቁርስ ብቻ 2 ሊትር ኮካ፣ ነጭ ዳቦና የተጠበሰ ድንች በብዛት ተመግባ ተጨሪ ትፈልጋለች" ጀሲካ ከክብደቷ የተነሳ መሮጥም ሆነ መራመድ አትችልም፡፡ ሰውነቷን መሬት በመጐተት ነው የምትንቀሳቀሰው፡፡ "ሕፃኗ እንደተወለደች ሆዷን አሟት ስታለቅስ እርቧት ይሆናል በማለት በጠርሙስ መገብኳት፡፡ ሆኖም ምግቡን እንድደጋግማት ትፈልግ ነበር፡፡ የሰጠኋት ለሷ በቂ አልነበረም፡፡ እናም በተለጋጋሚ ይርባት ነበር" ስትል ካሮሊን ለፈኒ ኒውስ ገልፃለች፡፡ እገታው በፒዛ አቅርቡልን ተጠናቀቀ በአውስትራሊያ ሬስዶን እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ 2ዐ ታሳሪዎች ጠባቂያቸውን ለሁለት ቀናት ያገቱት በእስር ቤቱ ያለውን ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ በመቃወም ነበር፡፡ የእስር ቤቱ ኃላፊ ግራሚ ባርበር ለአድቮኬት ጋዜጣ እንደገለፁት እስረኞቹ በመጀመሪያ 24 ጥያቄዎችን አንስተው ነበር፡፡ ሆኖም በተከታታይ በተደረገ ድርድር ጥያቄያቸውን "በፒዛ አቅርቡልን" ተክተው የእስር ቤቱን ጠባቂ ለቀዋል፡፡ እንደዘገባው ከሆነ ለታሳሪዎቹ 15 ፒዛ፣ ኮካ ኮላና የነጭ ሽንኩርት ዳቦ እንዲቀርብላቸው ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ለ72 ዓመታት በአንድ መሥሪያ ቤት ያገለገለ በጉዳይ አስፈፃሚነት በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ72 ዓመታት ያገለገለው ሚ/ር ፍሪድ ቡርቶን ሥራ የጀመረው የ15 ዓመት ልጅ እያለ ነበር፡፡ ዴይሊ ሚረር እንደዘገበው ሚ/ር ቡርቶን ዛሬ የ88 ዓመት አዛውንት ሲሆን ጡረታም ወጥቷል፡፡ "ሚስጥሩ እኔ ሥራውን መውደዴ ነው፡፡ በየቀኑ ሥራ መሄድ እወዳለሁ" ብሏል ሚ/ር ቡርቶን፡፡ ሚ/ር ቡርቶን 65ኛ ዓመቱን ካከበረ በኋላ ግን የጉዳይ አስፈፃሚነቱን ሥራ ትቶ በመሥሪያ ቤቱ በሚገኝ ላይብረሪ እንዲያገለግል ተደርጐ ነበረ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |