Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Wednesday
Oct 15th
Home arrow Sections arrow "በየትኛውም ማኅበረሰብ /የሴቶች/፣...
"በየትኛውም ማኅበረሰብ /የሴቶች/፣... E-mail
Sunday, 13 January 2008

"በየትኛውም ማኅበረሰብ /የሴቶች/፣ ውበት፣ ልዩ ቦታ አለው"

ዶ/ር ቴዎድሮስ መሰለ ገደቡ
የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ

አይከን ልዩ የቀዶ ጥገና ሕክምና ማዕከል ደርሼ እንግዳ መቀበያው ውስጥ ስቀመጥ ጠባብ ባዶ ቦታ ነበር ያገኘሁት፡፡ በማዕከሉ ሕክምና ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቁት ሙሉ በሙሉ ሴቶች ነበሩ፡፡

አብዛኞቹ ግንባር፣ ጉንጭ፣ አገጭና እጆቻቸው ላይ ንቅሳት ያለባቸው፣ ሌሎቹ በፊታቸው የተለያየ ክፍል ላይ ጠባሳዎች ያሉባቸው ነበሩ፡፡ ሁሉም በክሊኒኩ የተገኙት ለአንድ ዓላማ ነው፡፡ ንቅሳትና ጠባሳዎችን በሌዘርና በቀዶ ሕክምና ጥበብ ለማስወገድ፡፡

ንቅሳት በተለይ ገጠር ቀመስ በሆኑ አካባቢዎች በስፋት ይከናወን የነበረና አሁን ትንንሽ ከተሞችን ሳይቀር እያዳረሰ በመጣው ዘመናዊ ኑሮ ደግሞ ተቀባይነት እያጣ የሄደ ጉዳይ ነው፡፡

ሴቶች ተደጋግሞ እንደሚገለፀው ለውበት ቦታ እንዲሰጡ ተደርገው በማኅበረሰቡ የሚቀረፁ፣ ሁልጊዜም ውብ ሆነው እንዲታዩ የሚጠበቅባቸው አልያም ሆነው ለመገኘት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይህንን የውበት መስፈርት እንደ ማኅበረሰቡ እሴትና ባህል ለማሟላት ሴቶች በተለያዩ ዘመናት፣ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡

ሴቶች ያላቸውን ገጽታ ለመቀየርና ተቀባይነት ያለው ቅርጽና መልክ ለማምጣት ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ የዘመናዊ ሕክምና ውጤት የሆነው ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አንዱ ነው፡፡ በውጪ አገራት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ የመጨመርና የመቀነስ፣ የሌለን የመሙላት ጥበብን ያካተተው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ለዓመታት ሲሰራበት ቆይቷል፡፡

ዛሬ ደግሞ ይኸው ቴክኖሎጂ አገር ውስጥ ገብቶ ኢትዮጵያውያት ሴቶች ያነሳቸውን እያስጨመሩ፣ የበዛውን እያስቀነሱ መዋብ ጀምረዋል፡፡

በተለያየ መልኩ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና በመስጠት ላይ ያሉት ደግሞ "አይከን ልዩ የቀዶ ሕክምና ማዕከል" የተሰኘ ማዕከል የከፈቱት ዶ/ር ቴዎድሮስ መሰለ ገደቡ ናቸው፡፡ ዶ/ር ቴዎድሮስ የተወለዱት አሜሪካ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኢትዮጵያ በተለያየ ደረጃዎች የተከታተሏቸውን የከፍተኛ ትምህርት ሂደቶች ደግሞ በአሜሪካ እና በታይላንድ ተከታትለዋል፡፡ ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናና ማይክሮ ሰርጀሪ እንዲሁም አጠቃላይ ቀዶ ሕክምና ስፔሻላይዝ ያደረጉባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡

"ዘርፉ በአገራችን ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም በዓለም ላይ ያሉ የሰው ልጆች ፍላጎት ሁሉ ተመሳሳይ ነው፡፡ እንዳየሁት ከሆነ በየአገሩ ሰው ፍላጎቱ አንድ ዓይነት መሆኑን አምኛለሁ፡፡ ብዙ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ፕላስቲክ ቀዶ ጥገና የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለውም፡፡ መልክና ቋንቋ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው ውብ ሆኖ መታየት ይፈልጋል" የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ በዋጋ ደረጃ ምን ያህል የሚቀመስ ነው? ለሚለው ጥያቄ "ዋጋውን በተመለከተ በጣም ቀንሼ ነው የምሰራው በውጪ አገር ዋጋ አይደለም፡፡ የአቅም ጉዳይ ችግር ሊሆንባቸው የሚችል ሰዎች ቢኖሩም የሚኖራቸው ሰዎች ብዙ ናቸው ብዬ እገምታለሁ" የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ ገለፃ ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ሰርጀሪ ብዙ ነገር ያካትታል፡፡ በአጠቃላይ የሚታወቀው በመልክ ላይ የሚደረግ ማስተካከያ ነው፡፡ ይህ የህክምናው አንድ አስረኛ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚታወቀውም ይህ ነው፡፡ በአይከን የልዩ ቀዶ ጥገና ማዕከል በውበት መልክ የሚሠራው ጠባሳ ማስተካከል፣ ንቅሳት ማጥፋት፣ አፍንጫ ማስተካከል፣ ከዕድሜ ጋር የሚመጡ የፊት መሸብሸብ፣ የአይን እብጠት የመሳሰሉትን ማስወገድ፣ ከንፈር መጨመር መቀነስ ጥቃቅን ነገሮች እንደ የተሰነጠቀ ከንፈርና ጆሮ መጠገን የመሳሰሉ ተግባራት ናቸው፡፡

ቁስል ማዳን፣ በቃጠሎ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችን ማከም ሌላው ዓይነት ህክምና ነው፡፡ የነርቭ ህምሞችን፣ የፊት አጥንት ስብራት ማስተካከል የመሳሰሉት በማዕከሉ ይሰጣሉ፡፡

ተገልጋዮችን በተመለከተ ዶ/ር ቴዎድሮስ "ከሚመጡልን ተገልጋዮች አብዛኞቹ ሴቶች ጠባሳና ንቅሳት እንዲጠፋላቸው የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተለያየ ጉዳት ይደርስና ተገቢው ሁኔታ ሳይደረግ የጎላ ጠባሰ ይከሰታል፡፡ ይህንን ለማስወገድ ይመጣሉ፡፡ ንቅሳት የሚጠፋበት ሌላ ጥሩ መፍትሄ ስለሌለ ብዙ ተጠቃሚ አለን፡፡ የምንጠቀመው በዓለም ላይ የተሻለ የሚባለውን ሌዘር ቴክኖሎጂ ነው" ይላሉ፡፡

"ንቅሳት የሚጠፋው በአንድ ጊዜ አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ ነው፡፡ በጣም ጥሩ የሚባል ውጤት ያገኘሁት በአንድ ጊዜ 90 በመቶው የጠፋላት ሴት አስታውሳለሁ፡፡" የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደገለፁት ንቅሳት አብዛኛው ሁለትና ሶስት ጊዜ ተደርጎ ነው የመጥፋት ምልክት የሚያሳየው፡፡ ሌላው አንዳንድ ቦታ ይጎላል ሌላ ቦታ ይጠፋል፡፡

በሕክምናው በምን ያህል ጊዜ፣ በምን ያህል ደረጃ ንቅሳቱ እንደሚጠፋ ዶ/ር ቴዎድሮስ ሲናገሩ በአብዛኛው ከ4 እሰከ 6 ጊዜ በሌዘር ከታከመ በኋላ እንደሚሆንና ይህንኑ ለተገልጋዮቹ አስረድተው ሕክምናው እንደሚጀመር ይገልፃሉ፡፡

በእኛ ማኅበረሰብ ካለው አስተሳሰብ አንፃር ለውበት ትልቅ ቦታ ሰጥቶ ፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ማድረግ እንዴት ይታያል? ለሚለው "በየትኛውም ማኅበረሰብና ባህል ሰው ከሰው ጋር እስከኖረ በተለይ ሰው በአይኑ ለሚያየው ነገር ትኩረት ይሰጣል፡፡ ውበት በማንኛውም ብሔረሰብ ውስጥ ዋና ነገር ነው፡፡ እያንዳንዱ ባህል "ውብ" የሚለው ነገር የተለያየ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰው ለማማር ይፈልጋል፡፡" የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ 

ሰዎች ምን መምሰል አለባቸው ለሚለው በማኅበረሰቡ በተለይ ሴቶች ላይ የሚደረግ ጫና አለ፡፡ ሴቶች የግድ ተውበው መታየት አለባቸው እየተባለ አንድ የጭቆና መንገድ ተደርጎ በሴቶች መብት ተማጋቾች ይነሳል፡፡ ያለው ተቀባይነት እንዴት ነው? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ደግሞ "ፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ብዙ በቆየባቸውና የተለመደ በሆነባቸው አገሮች ሁሉ ጥሩ ተቀባይነት አለው፡፡ በመጀመሪያ ላይ ሁልጊዜ አዲስ ነገር ሲመጣ ሰው ላይቀበለው፣ ልዩ ልዩ አስተሳሰብ (ተቃራኒ) ሊኖረው ይችላል፡፡ በሄድኩባቸው አገሮች ትንሽ ገንዘብ ያላቸው ራሳቸውን ለማሻሻል ይችላሉ" የሚል ነው፡፡

እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ ገለፃ በአሜሪካ ያለው አሳሳቢ ነገር ለምሳሌ ሚዲያ ላይ በጣም ቀጫጭን የሆኑና አንድ አይነት መልክ ያላቸው እየታየ ይሄ ብቻ ነው ቆንጆ እየተባለ ሲሆን ሰዎች ያንን ለመምሰል ሲጥሩ አደጋ አለው፡፡ የሆነ ሆኖ አንድ አካባቢ ውበት ብሎ የሚገምታቸው ነገሮች አሉ፡፡ ያ የሌለው ሰው የሚሰማው ስሜት አለ፡፡ ያንን ለማስተካከል ሲጥርም ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናን ይጠቀማል፡፡

በአሜሪካ ለምሳሌ ውፍረት ለሴቶች እንደ ውበት አይታይም ከወለዱ በኋላ ሆዳቸው መጠኑ ከጨመረ እንዲጠገን ይፈልጋሉ፡፡ በፈረንጆች ዘንድ ለሴቶች ትልቅ ጡት እንደ ውበት መለኪያ ሲታይ ጡታቸው ትንንሽ የሆነ ሰዎች (ኢምፕላንት) ይከተትላቸዋል፡፡ አዕምሮአቸው በራስ መተማመን ሲኖራቸው/ ሲገነባላቸው በግልጽ ይታያል፡፡ ስነ ልቦናዊ ለውጥ በማምጣት ረገድ ጥሩ ይረዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ችግር የሌለባቸው ሰዎች የማይሆን ነገር ለማድረግ ሲሞክሩ ይታያል፡፡ የዚያን ጊዜ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ ራሳቸውን እንዳለ የማይወስዱ ሰዎች አሉ፡፡ እንደዚያ ሲሆን ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና መደረግ የለበትም፡፡

ስለዚህ የተበላሸውን ማስተካከል ነው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ተግባር? "አዎን፡፡ ከመጥፎ ወደ ጥሩ የሚቀይር የሰውን አመለካከት የሚያሻሽል ከሆነ ጥሩ ይሰራል፡፡ በጥሩ ሁኔታ መቀየር ካልቻለ አልያም ቀይሮ ሥነልቦናዊ ለውጥ ለማምጣት የማያስችል ከሆነ ተገቢ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡

ዘርፉ በአገራችን ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ዶ/ር ቴዎድሮስ እንዳሉት ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ሳይሆን ቀዶ ሕክምና በአጠቃላይ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ ዘመናዊ ሕክምና በአገራችን አልተስፋፋም የገባውም ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት ነው፡፡ መሻሻል ጀምሯል ነገር ግን የሚቀሩ አሉ፡፡ በአጠቃላይ እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ በተቻለ መጠን ዘመናዊ ሕክምና አለ ለማለት መሠራት የሚገባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡

ሕክምናው አዲስ ከመሆኑ አንፃር ብዙ ሰው ስለ አገልግሎቱ ያለው አስተሳሰብ ትክክል አለመሆኑን ዶ/ር ቴዎድሮስ ሲገልፁ በሐኪሞች ደረጃ ሳይቀር የዕውቀት እጥረት እንዳለ ይናገራሉ፡፡

ሕክምናን በተመለከተ በውጭ ለምሳሌ ታካሚዎች በራሳቸው መረጃ የመፈለግ፣ የማንበብ ሁኔታ ስላለ አይጠራጠሩም፡፡ የሚነገራቸው ይገባቸዋል፡፡ ካልፈለጉ ሌላ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ እነሱን ብዙ ማስተማር አያስፈልገውም፡፡ እዚህ ብዙ ማስረዳት ይጠይቃል፡፡ ማኅበረሰቡ ከሐኪሙ ይልቅ ጎረቤት የሚለውን ምክር የሚቀበል ነው፡፡ ጥሩ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በሁሉም ደረጃ ፈተናዎች አሉ፡፡

ሊሰራም ላይሰራም የሚችል ከመሆኑ አንፃር ከሰዎች መጥፎ ምላሽ አጋጥሞዎት ያውቃል? ለሚለው ደግሞ "አዎን፡፡ እንደ ሁኔታው ነው ያለመረዳት ችግሮች አሉ፡፡ አንድ ሁለት ጊዜ አሜሪካ መሄድ እንችላለን ግን እስቲ እንይህ ብለን ነው ብለው የመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ሂዱ ማለት ነበረብኝ ግን ፍፁም ካልሆነ አትችለውም አሜሪካ ብቻ ይቻላል አይነት አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል፡፡ ሳያምኑበት ሲመጡ ነው ችግሩ፡፡ ሕክምናዎቹ ምን ጊዜም ያለመስራት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ በጣም ስሜታዊ ሆነው እንዴት አልሰራም? ብለው ሲሉ ያስደነግጣል" ብለዋል ዶ/ር ቴዎድሮስ፡፡

"ላለፈው ስድስት ወር ያልተሳካ ነገር አላጋጠመኝም፡፡ ብዙው ነገር የሚመጣው በማኅበረሰባችን የመጠራጠር ሁኔታ ከመኖሩ አንፃር ነው፡፡ ያለፉበት ልምድ ስለሆነ አይፈረድባቸውም፡፡ አንድ ያልሰለጠነ ሐኪም ያበላሸውን ፊት አይተው ከሆነ ማን ጥሩ ይሰራል/ አይሰራም የሚለውን እስካላዩ ይጠራጠሩ ይሆናል፡፡ ማንንም ቢሆን መቶ በመቶ ጥሩ ነው ብዬ አልገፋፋም የሚፈልጉትን መረጃ እሰጣለሁ ተቀብለውት ከመጡ ጥሩ" የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ በማዕከሉ ስለሚሰጡ ሌሎች አገልግሎቶች ሲናገሩ ከመጠን በላይ ውፍረት የምናስወግድ ሲሆን እንደ ኤሌክትሪክ፣ የሚንቀጠቀጥ ነገር የሚሉት ነገሮች እኛጋ አይሰሩም፡፡ የተለያዩ ነጋዴዎች ይሰራል እያሉ ይሸጣሉ፡፡ በማላብ የተወሰነ የቀነሰ ይመስላል ነገር ግን ተመልሶ ይተካል፡፡ ውፍረት ለመቀነስ እየተባሉ የሚደረጉ ነገሮች ሁሉ ሰው መክሳት እንደሚፈልግ ስለሚታወቅ ብቻ የሚደረጉ ናቸው፡፡ የንግድ ኩባንያዎች ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲሉ የሚፈበርኳቸው ናቸው በታወቁ ባለሙያዎች ተጠንቶ፣ ሊያመጣ የሚችለው ጉዳት ተመዝግቦ፣ ተረጋግጦ ከወጣ በኋላ ነው ትክክለኛ የሚባለው" ይላሉ፡፡

ከተማ ውስጥ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ቦርጭ ማጥፊያ ተብሎ እሱን ተጠቅመው አቃጥሏቸው እዚህ የመጡ ደንበኛ እንደነበሯቸው ሲናገሩ በመድሃኒት ደረጃም ኤፍ ዲኤ ወይም ሲኢ የሚባሉት ዓለም አቀፍ ማረጋገጫ ምልክቶች የሌሉት ከሆኑ ብልቃጡ ሰላማረ ብቻ መታመን እንደሌለበት ዶ/ር ቴዎድሮስ ያስረዳሉ፡፡

በቤተልሔም ነጋሽ

 
< Prev   Next >