Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 08th
Home arrow Sections arrow ትንኝ ያጠራሉ ግመል ይውጣሉ
ትንኝ ያጠራሉ ግመል ይውጣሉ Print E-mail
Sunday, 13 January 2008


የባንኮች ኃላፊዎች "የበልቼው ልሙት" አሠራር


ከውብዳር

የዛሬዩቱ ኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ባመቻቸችላቸው ዕድል በመጠቀም የግል ፋይናንስ ተቋማት ወደ ገበያው ከገቡ ከአንድ አስርት ጥቂት ፈቀቅ ብለዋል፡፡ አሁን ካሉት የግል ባንኮች የመጀመሪያው ከተከፈተ 13 ዓመት አለፈው፡፡ የመጨረሻው የአንደኛ ዓመቱን ሻማ ሊለኩስ ወራት ይቀሩታል፡፡

በቅርቡ እነዚህን ታዳጊ የፋይናንስ ተቋማት በሚመለከት የታዘብኩትን ጽፌ ነበር፡፡ መልዕክቱ አገሪቱና ሕዝቡ በተለይም የንግዱ ኅብረተሰብ ከእነሱ ብዙ እየጠበቀ እያለ ከወዲሁ በአጭሩ እንዳይቀጩ የሚያሳስብ ነበር፡፡ ታዳጊ ናቸውና ጥንቃቄና እንክብካቤ እንደሚፈልጉ ነበር ለማሳሰብ የሞከርኩት፡፡

በተለይም ለባንኮቹ ሊደረግ ስለሚገባው እንክብካቤና ጥንቃቄ በዋናነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም በአንድም ሆነ በሌላ በኩል ኃላፊነቱን የፌዴራል ሥነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ቢጋራው የበለጠ ባንኮቹ ዕድገታቸው አስተማማኝ እንደሚሆን በማመን ነው፡፡ አቀራረቤ የተማፅኖ ያህል ቢሆንም ምክንያት ስላለኝ ነው፡፡

ይህ የመንግሥት ያለህ ጩኸት የሚያስደነግጣቸው ወይም የሚያስፈራቸው እርምጃውን አጉል ተቆርቋሪነት አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ መቼም ያልተነካ ግልግል ያውቃል ነውና ጉዳዩ የገባቸውና ውስጡን የሚያውቁ ከሆነ ግን ከእኔ ሃሳብ ጋር ይበጅ እንደሚሉ ጥርጥር የለኝም፡፡

ለዛሬው ፅሑፌ መነሻ የሆነኝ ፎርቹን ጋዜጣ በዲሴምበር 30 ቀን 2007 እትሙ ላይ ያወጣው ባንኮችን የተመለከተው ዜና ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኃላፊ ከተሰጣቸው ሥልጣን በላይ በመሄድ ብድር አለአግባብ ስለፈቀዱ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሁኔታውን ለማጣራት ጎራ ብሏል፡፡ ውጤቱ ምን እንሚሆን በናፍቆት የምንጠብቀው ነው፡፡ ምክንያቱም የደመና መታየት ሁሌ ዝናም እንዳለ ማረጋገጫ ባይሆንም፣ ጭስ ግን እንደው ከባዶ ተነስቶ እንደማይታይ ግልፅ ነው፡፡ ጭስ ካለ እሳት ነበር አለማለት ነው፡፡

ሌላው ከግል ባንኮች አንዱ የሆነው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቀድሞ ሥራ አስኪያጁንና የቦርድ ሰብሳቢውን (በነገራችን ላይ አንድ ሰው ነበሩ በሁለቱም ሥልጣን ላይ የነበሩት) እንደከሰሰ የሚያወሳው ዜና ነው፡፡ የሚያስገርመው ችግሩ ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ የንብ ባንኩ ሥራ አስኪያጅ የባንኩ ሕገ ደንብ ፈቅዶ ከሰጣቸው ሥልጣን በላይ ሄደው ብድር መፍቀዳቸውን አስመልክቶ ነው የክሱ ጭብጥ፡፡ ይህ ዜና አሁን በሥራ ላይ ለሚገኙት የባንክ ማኔጀሮችም ትልቅ ማስጠንቀቂያ ይመስለኛል፡፡ ተጠያቂነት ከጡረታ ባሻገርም እንደሚዘልቅ ያስገነዝባል፡፡

ለመሆኑ እነዚህና የመሳሰሉት የአሠራር ችግሮችን ከብሔራዊ ባንክ በፊት በቅርብ ሆኖ ሊቆጣጠር የሚገባው ማን ነበር? ሥራ አስኪያጆች የሕዝብን ገንዘብ እንደ ልብ በማን አለብኝነት ለማዘዝ ሲቃጣቸው መገደብ የሚገባው ማን ነበር? ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያግዘኛል ብሎ የሚያወጣውንና የዘረጋውን ሥርዓት በአግባቡ መተርጎሙን ሊታዘብ የሚገባው ማን ነበር? ስርዓቱ ሲፋለስ ተው ልክ አይደለም፤ ማለት የሚችለው ማን ነበር? ሥራ አስኪያጆች የተዘረጋውን ሥርዓት ወደፈለጉበት አቅጣጫ እንደፈለጉት ማጉበጥና ማቅናት ሲሞክሩ ያ እንዳይሆን ማገድ የማን ኃላፊነት ነበር? በየባንኩ የሚዋቀር ዋና ተቆጣጣሪ /ኮንትሮል/ የሚባለው መምሪያ አልነበረምን?

የዚህ መምሪያ ተጠሪነት በጣም ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ብዙዎች ላይ ጥያቄ የሚፈጥር የሚከራከሩበትም ነው፡፡ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ተጠሪነቱን ለዳይሬክተሮች ቦርድ ያደርጋሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ባንኮች ግን የመምሪያውን ተጠሪነት ለሥራ አስኪያጁ ሲያደርጉ ነው የምናየው፡፡ በባንኮች ውስጥ በተለይም በግል ባንኮች ውስጥ የአሠራር ብልሹነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስናና የሥነምግባር መበላሸት፣ ሲታይ የሚስተዋለው የቁጥጥር መምሪያዎቻቸው ጥርሱ የረገፈበት አንበሳ ሆነው እንደ ላንቲካ የመዋቅር ማሳመሪያ ብቻ ሆነው በመገኘታቸውና ምናልባትም የተጠሪነታቸው አወቃቀር ችግር ስላለበት ይመስለኛል፡፡

የባንኮች የቁጥጥር መምሪያ የባንኩን መፃዒ ዕድልና ዕድገቱን እውን ለማድረግ ተገቢውን ሥርዓት ከሚዘረጉ የሥራ ዘርፎች መካከል ዋንኛው ነው፡፡ ያንንም ሥርዓት በትክክል መፈጸሙን የሚከታተሉ፣ ግልፅና ንፁህ አሠራር በባንኩ ውስጥ እንዲሰፍን ተገቢውን ሚና የሚጫወቱ፣ ከበታች ሠራተኞች እስከ ከፍተኛ ሥራ አመራሮች ድረስ የባንኩን ሥርዓትና አሠራር ጠብቀው መሥራታቸውን የሚቆጣጠሩ፣ በመንግሥትም ሆነ በሕዝብ ዘንድ የማይነቀፍ ግልፅና ሃቀኛ የመዝገብ አያያዝ መኖሩን የሚከታተሉና የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

ከዚያ ውጭ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት በአግባቡ ካልተከወኑ፣ ካልተጠበቁ፣ ካልተፈፀሙ፣ ከማንም በፊት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስቡ፣ እንደ አስፈላጊነቱ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት እርምጃ የመውሰድም ኃላፊነት ያለባቸው እነርሱው ናቸው፡፡

በአንድ ባንክ ውስጥ ይህ ትልቅ አደራና ኃላፊነት ነው፡፡ ሆኖም አሁን የሚታየው የብዙ ባንኮች የቁጥጥር መምሪያ ከላይ የተጠቀሱትን አደራዎችና ኃላፊነቶች በአግባቡ እየተወጡ እንዳልሆነ ነው፡፡ ባለፈው ፅሑፌ እንደገለጽኩት የግል ባንኮች ላይ እየታየ ያለው የሥነምግባር ብልሽትና ዓይን ያወጣ ሙስና የዚህ ክስተት ነፀብራቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ዋና ተቆጣጣሪዎች አልሠሩም እንዳይባሉ ጥቃቅን ጉድለቶችን ብቻ ሲከታተሉ በአንፃሩ ደግሞ ትልልቅ ጥፋቶችን አይተው እንዳላዩ ሲያልፉ ትንኝ ሲያጠሩ ግን ግመል ሲውጡ ነው የምናየው፡፡ በቀላሉ በቁጥጥር ሊውሉ የሚችሉ ችግሮች ላይ አስፈላጊ ያልሆነ ጊዜ በመውሰድ ትኩረት ሰጥተው የሚባክኑትን ያህል ከፊሉን እንኳ ባንኩን ወደ አዘቅት ሊያወርደው የሚችለውን ችግር መከታተል ቢችሉ ስንት ሥራ ሰሩ በተባለ ነበር፡፡

የባንኩ ኃላፊዎች አውቀው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ደንብ ሲጥሱ፣ በማን አለብኝነት የተዘረጋውን ሥርዓት ሲያጎብጡና ሲያቀኑ፣ ማንና ምንስ ያስፈራኛል በሚል ስሜት በሕዝብ ገንዘብና ንብረት እንዲሁም ሕይወት ላይ እንደፈለጉት ሲወስኑ፣ በልቼ ልሙት በሚል ደካማ አስተሳሰብ ያለ ይሉኝታ የሕዝብ ገንዘብ ሲመዘብሩ፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ክፉ መንፈስ የባንኮችን የወደፊት ዕድገት የሚያጨልም ውሳኔ ሲወስኑ፣ ሃይ ማለት የነበረባቸው ዋናው ተቆጣጣሪ ተብለው የተሰደሩት መምሪያዎች ነበሩ፤ በነበር ቀረ እንጂ፡፡

ትናንት በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ተፈጽሞ የታየው እውነት ስህተት ተፈጽሟል ተብሎ ለአደባባይ የበቃው ወሬ ክስተቱ በአንድ ቀን ስህተት ብቻ የተፈጸመ እንዳልሆነ እርግጥ ነው፡፡ የብዙ ስህተቶችና የብዙ ቸልተኝነት ድምር ውጤት ነው፡፡

የዋናው ተቆጣጣሪ መምሪያ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ እስከሆነ ድረስ የራሱን እንጀራ ሕልውና ለመጠበቅ ሲል ጆሮውን በቀላሉ ቢጠመዘዝና በባንኩ ምንም ዓይነት የአሠራር ግድፈት ቢፈጠር ምን ይገርማል?

ጊዜውን ትንኝ በማጥራት ግን ግመል በመዋጥ የሚያጠፋ፣ የሹመትና የሽልማት ተስፈኛ ከሆነ ባንኩ በሚያስደነግጥ ደረጃ ሲዘረፍ፣ የሕዝብ ሃብት ሲመዘበር፣ ጉቦ እንደ ነውር ሳይሆን እንደ ተገቢ ስጦታ ተወስዶ ሲሰራ አይቶ እንዳላየ ቢያልፍ ምን ያስደንቃል?

የተቆጣጣሪው ብቃትና ችሎታ እንዲሁም ጥንቃቄው ከዚያም በላይ ለሙያ ሥነምግባሩ ያለው ተገዥነት የማያስተማምን ከሆነ በባንኩ ውስጥ ሥርዓት ቢፋለስ ከፍተኛው የሥራ አመራር አሠራሩን እንደፈለገው ሲያጎብጥና ሲያቀና አይቶ እኔን አያገባኝም ብሎ ቢያልፍ ምን ይገርማል?

ያገሬ ሰው "አጥቃ ያሉት ኮርማ ተንበርክኮ ጠባ" ብሎ እንደሚተርተው ጭራሽ ተቆጣጣሪው ኃላፊነቱን ዘንግቶ እርሱ ራሱ ነቅዞ ቁጥጥር እያስፈለገው ሳለ ለሃቅ ቆሞ ቁጥጥርን ተግባራዊ ያደርጋል ማለትም ዘበት ነው፡፡

በአንዳንድ ባንኮች ውስጥማ የሚታየው ሥራ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ የቁጥጥር መምሪያዎች የግለሰቦች ማፈኛ መሣሪያ እስከመሆን የሚደርሱበት ጊዜ እንዳለ የየባንኮቹ የዕለት ተዕለት ልምድ ሆኖ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰንብቷል፡፡ በግለሰብ ትዕዛዝ ሊመቱ የታቀዱትን አካባቢዎች አስቀድመው በመውረር መረጃ በመሰብሰብ ትጥቅ የማስፈታት ዓይነት ሥራ ሲሰሩ ይታያሉ፡፡ በዛው አንፃር አፍንጫቸው ሥር እጅግ የከረፋውንና የሚሰነፍጠውን የሙስና ሽታ እንደ መልካም መዓዛ ተቀብለው ጎራ ጎራውን በመዞር የአለቆቻቸውን ትዕዛዝ  በየአጋጣሚው ታማኝነታቸውን በማስመስከር ሲፎክሩ ይታያሉ፡፡ ለምን ቢባል ሹመት ሽልማት ማግኛ ዋናው መንገድ ይኸው ሆኖ ተቀነባብሯልና፡፡

አይናቸው ሥር ከዕቃ ግዥ ሕግ እጅግ ያፈነገጠ የሚሊዮን ብሮች ዕቃ ግዥ ሲከናወን የአደባባይ ምስጢር ሆኖ እያለ፣ እነርሱ ግን አላየንም፣ አልሰማንም ይላሉ፡፡ ጣልቃ በመግባት ሊያስተካክሉና ዛሬ ባይሆን ነገ መጠየቅም እንደሚኖር ማሳሰብ የሚችሉበት ወኔ የላቸውም፡፡

አፍንጫቸው ስር አገር ጉድ ያሰኘ ሥርዓት ያልተከተለ የሠራተኛ ቅጥር፣ ምደባ፣ ዕድገትና ዝውውር ሲፈጸም፣ ኧረ ልክ አይደለም፤ ደንብ ፈርሷል፣ ሥርዓት ተዛንፏል፤ ብለው ከሚጠይቁ ይልቅ ዓለም ብታልፍ ይቀላቸዋል፡፡

የብድር አሰጣጡ ሥርዓት በቀጭን ትዕዛዝ የዓይን ቀለም እየታየ ሲሰጥና የሚገባቸው ሰዎች ተከልክለው ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ያንን ሰምተው ጉዳዩን መስተካከል የሚገባበት ቦታ ላይ እንደማስተካከል አይተው እንዳላዩ በማለፍ ጎመን በጤና ማለት አይቸግራቸውም፡፡ ይህ ሁሉ አሉባልታ ሳይሆን በተጨባጭ የተፈፀመ ለመሆኑ ተገቢ መረጃዎችን ይዘን ነው፡፡ እነርሱም ልቦናቸው አይስተውም፡፡

ታዲያ ነገሩ እንዲህ ከሆነ መፍትሄው ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ አስፈላጊ ይመስለናል፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በአንዳንድ ባንኮች ላይ የሚታየው አደባባይ የወጣው እሰጥ አገባ፣ ነገ ወደ ሌሎቹም እንደማይደርስ የምንሰጠው ዋስትና የለም፡፡ የታየው የአሰራር ድክመት በእነዚሁ ባንኮች ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የጊዜ ጉዳይ እንጂ ነገ ይኸው ክስተት በሌሎች ባንኮች ላይ ላለመፈጠሩ የምናረጋግጥበት መንገድ የለም፡፡

ስለዚህ ሁኔታው አሳሳቢ ስለሆነ ባንኮች ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያስፈልጉትን ያህል አሰራራቸው ከመልካም አስተዳደር ውጭ ከሆነ ያንኑ ያህል ጉዳታቸው አመዛኝ ስለሚሆን መንግሥት ይህንን ጉዳይ ትኩረት በመስጠት የፌዴራሉ የሥነ ምግባር ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጣልቃ እንዲገባ ቢያደርግ ያለ በቂ ቁጥጥር የሚደረገውን ልቅ አሠራር ለማረም ዕድል ይገኛል፡፡ እስካሁን ስለተፈጸመው ስህተት መንግሥት በራሱ መንገድና ዘዴ ምርመራውን ቢጀምር ለስህተት የተዘረጉ እጆችን አደብ ያስገዛል፡፡ ለሌሎችም ትምህርት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የሥነ ምግባር ብልሽቱም እንዲቀንስ ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ አጥፊዎች መጠየቅ በሚገባቸው ደረጃ ቢጠየቁ ለመፍትሄው እገዛ ይኖረዋል፡፡

ከዚህም በላይ ብሔራዊ ባንክ ምንም እንኳን የዘገየ ቢሆንም በየደረጃው የሥራውን ውስብስብነት በማየት ቁጥጥርን ለማጥበቅ የሚያስችሉ መመሪያዎችን ማውጣቱ እጅግ አግባብነት ያለው ነው፡፡ መመሪያ ማውጣቱ ብቻም ሳይሆን ተግባራዊነቱንም እግር በእግር መከታተል ለጥሩ ውጤታማነት ትልቅ አስተዋፅዖ አለው፡፡

እነዚህ በአንድ ባንክ ውስጥ ከፍተኛ የኃላፊነት ድርሻና አደራ የተቀበሉት የቁጥጥር መምሪያዎች ከመዋቅር ማሳመሪያነት ወጥተው ሕይወት እንዲዘሩና ትክክለኛ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ብሔራዊ ባንክ አወቃቀራቸውን አስመልክቶ ጥናት በማካሄድ ሁሉም ባንኮች በወጥነት እሚተገብሩት መመሪያ ሊያወጣ ይገባል፡፡ ይኸውም የዋናው ተቆጣጣሪ መምሪያ ተጠሪነቱ ለባንኮቹ የሥራ አመራር ቦርድ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ከሆነ በቀላሉ የአንድ ግለሰብ ስሜት ብቻ የሚገዛቸውና የግለሰቡን ፍላጎት ብቻ አስፈፃሚ ከመሆን ያድናቸዋል፡፡

በሌላም በኩል ተጠሪነታቸው ለአንድ ግለሰብ መሆኑ ቀርቶ በቡድን ሆነው ባንኩን በከፍተኛ ኃላፊነት ለሚመሩት ለሥራ አመራር ቦርዱ ከሆነ የባንኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከኃላፊነቱና ከሥልጣኑ በላይ ለመንቀሳቀስ ቢፈልግ ለመገደብ ነፃነቱ ይኖራቸዋል፡፡ እንደዚሁም በድርጅቱ ውስጥ የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ስልጣን አለአግባብ ለመጠቀምና ለመበልፀግ የሚፈልጉትን የሥራ ኃላፊዎች ከወዲሁ እጃቸውን እንዲሰበስቡና በአግባቡ ኃላፊነታቸውንና ሥልጣናቸውን እንዲጠቀሙበት ለመግራት ያመቻቸዋል፡፡

ከዚህም በላይ በመምሪያው ተጠሪነቱ እንደገለፅኩት አሰራሩና አመራሩ አንድ ግለሰብ ብቻ መሆኑ ያበቃና የቡድን መልክ ይይዛል፡፡ ይህም አሰራር ቁጥጥሩን ሚዛናዊ እንዲሆንና ለውድቀትም ላለመጋለጥ እርስበርስ እንዲጠባበቁ ፈረንጆቹ /ቼክ ኤንድ ባላንስ/ የሚሉት ሁኔታ እንዲፈጠር እገዛ ያደርጋል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን በባንኮች ውስጥ በዋና ተቆጣጣሪነት የሚመደቡት ኃላፊዎች በመደበኛነት ያለፉበት የትምህርትና አግባብ ያላቸው ሥልጠናዎቻቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ያላቸው የሥራ ልምድና ታማኝነት በአጠቃላይ በሥነምግባር መርሆዎች ሲለኩ ሚዛን የሚደፉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸው መሆናቸውን መጠናትና መጤን ይኖርበታል፡፡

ልምዱ፣ አቅሙና ሙስናን ለመታገል ድፍረቱና ወኔው ሳይኖራቸው በቦታው የሚመደቡ ኃላፊዎች በቀላሉ ጆሯቸውን ለመጠምዘዝ የተመቹ ከመሆናቸውም በላይ እንኳን ሊቆጣጠሩና ለቁጥጥርም የሚያስቸግሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ምናልባት በዚህ በኩል ያለው አሰራር በዚህ መልኩ ከተስተካከለ ሙሉ በሙሉ ለሚፈጸሙት ስህተቶች መፍትሄ ይሆናል፤ ብለን በድፍረት ለመናገር ባንችልም እንኳ እስካሁን ላነሳናቸው ችግሮች ከሌሎች መፍትሄዎች ጋር ተቀናጅተው ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ፤ ብለን እናምናለን፡፡

ከዚህ በኋላ በመቋቋም ላይ ያሉ ባንኮች በአሰራራቸውና በአወቃቀራቸው ላይ የሌሎችን ባንኮች በጎ ተሞክሮ መውሰድ ብቻ ሳይሆን ስህተታቸውንም በማየት የሚፈጥሩት ባንክ ከዚያ የነፃ እንዲሆን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ለመማር ግድ ስህተት ውስጥ መዘፈቅ አይኖርባቸውም፡፡ ስህተት ባይኖር ጥሩ ነበር፡፡ ግን ሥራና እንቅስቃሴ ካለ በአጋጣሚም ቢሆን ስህተት ሊከሰት ይችላል፡፡ ግን አውቆ የሚሳሳቱትን ለመገደብ ከሌሎች ስህተት ትምህርት መውሰድ ይሻላል፡፡

ብልህ ራሱ እስኪወድቅ አይጠብቅም፡፡ በሌላው ስህተት ትምህርት ያገኛል፡፡ ትንግርት የሚሰኙትን ከሥነምግባር ውጭ ተከናወኑ የምንላቸውን የብድር አሰጣጥ፣ ዕቃ ግዥ፣ የሠራተኛ ቅጥር፣ ምደባ፣ ዝውውር ዕድገት፣ ስንብትና የመሳሰሉትን በመረጃ የተደገፉ የአንዳንድ ባንኮች ታሪኮችን አቅማችን እስከፈቀደ ድረስ እናስነብባችኋለን፡፡

 
< Prev   Next >