Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow ሁሉም ራሱን ይፈትሽ!
ሁሉም ራሱን ይፈትሽ! Print E-mail
Sunday, 29 June 2008
Imageዋናው ኦዲተር የ1998 እና የ1999 ዓ.ም ሪፖርት ሰሞኑን ለፓርላማ አቅርቧል፡፡ የቀረበው ሪፖርት የዋናው ኦዲተርን መስሪያ ቤት በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት ግልጽነትና ድፍረት ባለበት መንገድ ተግባሩን ያከናወን መሆኑን ያመለክታል፡፡ መንግሥት በዚሁ ሪፖርት ሊያምንና ሊኮራ እንጂ እውነቱ በመገለጡና በተሰጡት ወቀሳዎች ቅር ሊሰኝ አይገባም፡፡ እንደውም የተጠቆሙት ስህተቶች ለምን ተከሰቱ ብሎ ሊመረምርና ስህተትና ጉድለት ፈፅመዋል የተባሉት መስሪያ ቤቶች ችግር ለመፈተሽ ይረዳዋል፡፡

በመንግሥት መስሪያ ቤቶችና በአጠቃላይ በመንግሥት ታዩ የተባሉት ድክመቶች መንግሥት ከሚፈቅደው በላይ መበደሩ፣ ከአሰራር ውጭ ገንዘብ ወጪ የባጀት ዝውውር መደረጉ፣ ከሕግ ውጭ ገንዘብ መሰብሰቡ፣ ከአሰራር ውጭ ገንዘብ ወጪ መደረጉ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

እነዚህ ግድፈቶች በመንግሥት ደረጃ ለምን ተፈጠሩ? በመንግሥት ደረጃ ይቅርና በግለሰብ ሰራተኛ ደረጃ እንኳ፣ የሚፈቀድለት ብድር ከዚህ በላይ መሆን አይችልም፤ የሚል አሰራርና ሕግ፣ መንግሥት ራሱ እያወጣና እየተቆጣጠረ ራሱ የሚበደረው ብድር መጠን ግን ከተፈቀደለት በላይ እንዳያልፍ ለምን አልተቆጣጠረም?

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስራና ኃላፊነት በሕግና በዝርዝር የተገለፀ ነው፡፡ አንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሕግ ሳይፈቀድላቸው፣ ስልጣን ሳይኖራቸው እንዴት ገንዘብ ሊሰበስቡ ቻሉ?

ካለፈቃድስ እንዴት ባጀት ይዘዋወራል? ካለፈቃድስ እንዴት ወጪ ተደረገ?

እነዚህ ሁሉ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚታዩ ድክመቶች ሲሆኑ፤ መንግሥት የግል ዘርፉና ሲቪል ማህበረሰቡን አሰራራችሁ ይህ ይጉድለዋል ይህ አልተሟላም፤ ከማለቱ በፊት የራሱን አሰራርም ሊፈተሽና ውስጡን ሊገመግም እንደሚገባ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

መንግሥት የሌላውን ስህተትና ድክመት ማየቱ ያስመሰግነዋል እንጂ አያስወቅሰውም፡፡ የሌላውን ድክመት እያየ የራሱን ድክመትና ጉድለት ማየት ከተሳነው ግን ያስወቅሰዋል፤ ብቻ ሳይሆን ያስጠይቀዋልም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ውስጡን፣ መንግሥት ራሱን ይፈትሽ፡፡

በመንግስት በኩል እንደዚህ ዓይነት እንደዚህ ዓይነት፣ ስህተት አለ፤ ማለት የግል ዘርፉ እኔማ ጤነኛ ነኝ የሚያስብለው አይደለም፡፡ የግል ዘርፉም በግብር አከፋፈል፣ በፈቃድ አወጣጥ፣ በአሰራር፣ በአቀጣጠር፣ በገንዘብ አሰባሰብና በሌላ ሌላ በብዙ መንገዶች ሕግና አሰራር የሚጥስበት ሁኔታ ታይቷል፡፡

ይህ ስለሆነም መንግሥት እንደዚህ ነው፤ መንግሥት እንደዚያ ነው፤ እያለ የመንግሥትን ድክመትና ጉድለት ከመዘርዘር ይልቅ ራሱን ውስጡን ሊፈትሽና ሊያስተካከል ይገባዋል፡፡ የግል ዘርፉ የመንግሥት ድክመት፣ ጉድለት ብቻ አይቶ የራሱን ማየት ካልቻለ ያስወቅሰዋል፤ ያስቀጣዋልም፡፡ ምክንያቱም የራሱን ችግር የሚፈታበት ዓይንና ዓቅም እያጣ ከችግር ወደ ችግር ከጥፋት ወደ ጥፋት ይገባልና፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሲቪል ማህበረሰቡም እንደዚሁ ራሳቸውንና ውስጣቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ መንግሥት የራሱን ብቃትና አቅም አያረጋግጥም፡፡ የሌላውን ድክመት ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ ይህ አያስወቅስም፡፡ ያስመሰግናል እንጂ፡፡ የሌላ ማየት ካልቻሉ ግን ያስወቅሳልም፣ ያስጠይቃልም፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የመንግሥትንና የገዢውን ፓርቲ ድክመት እየመዘዙ በዝርዝር ቢያጋልጡ አያስወቅሳቸውም፡፡ እንደውም ያስመሰግናቸዋል፡፡ ኃላፊነታቸው የመንግሥት ድክመትን ለሕዝብ ማሳየትና እኔ እሻላለሁ ብሎ ሕዝብን አሳምኖ በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ስልጣን መያዝ ስለሆነ፣ አይጠየቁበትም፡፡ ካደረጉም በርቱ ተበራቱ ነው የሚባሉት፡፡

ነገር ግን፣ ነገር ግን፣ ነገር ግን፣ የመንግሥቱን ደክመት ብቻ እያዩ የራሳቸውን ድክመት ጉድለት የሚረሱት ከሆነ ይወቀሱበታል፣ ይጠየቁበታልም፡፡

እነሱ ራሳቸው የዴሞክራሲ ባህርይና አሰራር ሳይላበሱ መንግሥትንና ገዢ ፓርቲውን ዴሞክራሲያዊ አይደሉም ካሉ፣ እነሱ ራሳቸው ከሙስና ሳይፀዱ መንግሥትን በሙስና ከወነጀሉ፣ እነሱ ራሳቸው ሰብዓዊ መብት ሳያከብሩ መንግሥትን ሰብዓዊ መብትን በመጣስ ከወቀሱ፣ እነሱ ራሳቸው ከህግ በላይ ለመሆን እየሞከሩ፣ ግን መንግሥትን ሕግን በመጣስ ከወነጀሉ እነሱ ራሳቸው ለአገር ሳይቆሙ መንግሥትን የአገርን ሉአላዊነትና ደህንነት አያስጠብቅም፤ እያሉ ከወቀሱ ውጤቱ "ትዝብት ነው ትርፉ" ሳይሆን ይወቀሱበታል፣ ይጠየቁበታል፣ ይቀጡበታልም፡፡

ቅጣቱ ከመንግሥት ወይም ከፍርድ ቤት የሚመጣ ሳይሆን፣ መራጩ ሕዝብ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ሲያጠፋ እንደሚቀጣው ሁሉ ተቃዋሚውንም ሲያጠፋ ይቀጣል፡፡ የሕግ ቅጣትም የድምጽ ቅጣትም ይከተላል፡፡

ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ራሳቸውን ውስጣቸውን ይፈትሹ፡፡

ፕሬስም ራሱንና ውስጡን ይፈትሽ፡፡ በርግጥ ፕሬስ የሕዝብ ወገንተኛ ሆኖ ሕዝብን የሚጎዳ የሙስና፣ የመብት ረገጣ፣ የአፈና፣ የስርቆት፣ የዝርፊያ፣ የግፍ፣ የበደል ድርጊቶችን ያጋልጣል፣ ይጮሃል ይሟገታል፣ ያስተምራል፣ ያዝናናል፡፡ የሌላውን ደካማና ጠንካራ ጎን እየተከታተለ ለሕዝብ ያሳውቃል፡፡ የሌላው ድክመት በማጋለጥም ያስመሰግነዋል፡፡

ነገር ግን፣ ነገር ግን፣ ነገር ግን፣ ለራሱ አጭበርባሪ ፕሬስ ሆኖ ሌላ አጭበርባሪ አጋልጣለሁ ካለ፣ ራሱ ፀረ ሕዝብ ሆኖ ሌላውን በፀረ ሕዝብነት ከወነጀለ፣ ራሱ ሙሰኛ ሆኖ ሌላውን በሙስና ከወቀሰ፣ ራሱ ዘረኛና ጦረኛ ሆኖ ሌላውን በዘረኝነትና በጦረኝነት ከወነጀለ አያምርበትም፤ ሳይሆን ይጠየቅበታል፣ ይወቀስበታል፡፡

ስለዚህም ፕሬስም ውስጡን ራሱን ይፈትሽ፡፡

በአጠቃላይ ሁላችንም ውስጣችንን እንፈትሽ፣ እንይ፣ እንገምግም፣ ራሳችን አርአያ ሆነን ሌላውን ከድክመቱ እንዲላቀቅ እንቅስቃሴ እናሳይ፤ እንረባረብ፡፡

ጣታችን በሌላ ላይ ከመቀሰራችን በፊት ለምሆኑ እኔ ንፁህ ሆኜ ለአገር ለሕዝብ እሰራሁ ነው ወይ? ከሌላው የምጠብቀውን ራሴ እየፈፀምኩ ነኝ ወይ? ብለን ራሳችንን እየጠየቅን መልሳችን አዎንታዊ መሆኑን እናረጋግጥ፡፡ ስለዚህ በቅድሚያ ራሳችንን ውስጣችንን እንፈትሽ!!  
 
< Prev   Next >