| ከባለ ሃብትም ባለ ሃብት አለ! |
|
| Wednesday, 16 January 2008 | |
|
ባለሃብት ማለት በደረቁና በጥሬው ገንዘብ ያለው ማለት ነው፤ ተብሎ ከተወሰደ ብዙ ባለሃብቶች አሉን ለማለት እንችላለን፡፡ ገንዘብና ንብረት የመቁጠር ጉዳይ ነውና፡፡
ባለሃብት ሲባል ገንዘብና ንብረት ብቻ በመቁጠር የሚወሰን ሳይሆን የገንዘቡና የንብረቱ አመጣጥም መታየትና መመርመር አለበት፡፡ እውነተኛ ባለሃብት የሚባለው ገንዘብና ንብረቱን ለምን ዓላማ የሚያውል ነው? የሚባል ከሆነ ደግሞ በሚያሳዝን ደረጃ ያሉን ባለሃብቶች እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ብዙ ገንዘብና ንብረት መሰብሰብ ይቻላል፡፡ የመንግሥት ግብርና ቀረጥ ባለመክፈል የሚካበት ገንዘብና ንብረት አለ፣ አለአግባብ የባንክ ብድር በማግኘት የሚካበት ንብረትና ገንዘብ አለ፣ በማጭበርበር፣ በጉቦ፣ የሚካበት ሃብት አለ፣ ኮንትሮባንድ በመነገድ የሚከማች ገንዘብ አለ፣ አለአግባብ በሙስና ጨረታ በማሸነፍ የሚገኝ ገንዘብ አለ፣ ደካሞችንና ያልተማሩትን በማጭበርበር በሚገኝ ንብረት ባለሃብት መሆን አለ፡፡ የሲሚንቶ ተፈላጊነት፣ የብረት ተፈላጊነት እየናረ ሲሄድ ሁኔታውን በመጠቀም አለአግባብ አይን ያወጣ ዋጋ በመጨመር የሚካበት ሃብትም አለ፡፡ የበርበሬ ዋጋ ጉድ በሚያሰኝ ደረጃ በመጨመርና የአልጫ ሚሌኒየም ለማሳለፍ በማይፈልገው ሕብረተሰብ ላይ ጫናን ፈጥሮ ግፍ በመፈፀም የሚገኝ ሃብትና ንብረትም አለ፡፡ የፖለቲካ ዓላማንና ምርጫን ተገን በማድረግ በእርዳታ የተገኘውን ገንዘብ ለግል ጥቅምና "ኢንቨስትመንት" በማዋል የሚገኝ ገንዘብና ንብረትም አለ፣ ህሊናንና "ሥጋን" በመሸጥ የሚገኝ ንብረትና ሃብት አለ፣ ወንጀል ውስጥ በመግባት፣ በግድያና በዝርፊያ የሚገኝ ሃብትና ገንዘብም አለ፡፡ ከፍ ብለን በጠቃቀስናቸው መንገዶች የሚገኝ ሃብትና ንብረት በአንድ ወቅት የሚበንና የሚጠፋ ከመሆን አያልፍም፡፡ በፍርድ ቤት ሊወረስና ሊወሰድ፣ በተበደሉ ቤተሰቦች ሊጠቃ፣ በህዝብ ሊቀማና በመንግሥት ሊነጠቅ የሚችል ሃብትና ንብረት ነውና ባለሃብትነቱ "ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ" ነው፡፡ ባይነጠቅም የተገኘበት ዘዴና የሚጠፋበት መንገድ ሁሉ የአገር ሃብት ነው ተብሎ ሊኮራበትና ሊያስመካ የሚያስችል አይደለም፡፡ በእንዲህ ዓይነት መንገድ የሚገኝ ገንዘብና ንብረት የልማት አካል ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ "ባለሃብቶችም" አንዴ ቆም ብለው እንዲያስቡና ወደ ትክክለኛ ባለሃብትነት ለመቀየር ጠንካራ ውሳኔ እንዲወስዱ ያስፈልጋል፡፡ የያዙት ሃብት ለራስና ለቤተሰብ መዘዝ እንጅ ሃብት አይደለምና፡፡ መንግሥትም በእንደዚህ ዓይነቶቹ "ሃብት የለሽ ባለሃብቶች" ላይ ትኩረትና ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል፡፡ አደገኛ "ሃብት" ነውና፡፡ ሆኖም ግን ራሳቸው ኮርተው አገርን የሚያኮሩ ሃቀኛ ባለሃብቶች አሉ፡፡ ስለ ባለሃብች ስናወራ ስለእነኝህ ዓይነቶቹ ነው፡፡ ከቤተሰቦቻቸው ያገኙትን ትንሽ ገንዘብና ንብረት መነሻ በማድረግ፣ በሌላ ድርጅት ወይም መሥሪያ ቤት ተቀጥረው ሲሰሩ ያገኟት የነበረችውን ደሞዝ በማጠራቀም፣ የእቁብና የዘመድ አዝማድ ድጋፍ እንደመነሻ በመውሰድና ትንሽ የግል ስራን ወደ ትልቅ በማሸጋገር፣ በትክክለኛ መንገድ የገንዘብ ድጋፍ በማግኘትና በአግባቡ በመጠቀም፣ ሽርክና በመፍጠርና የጋራ ገንዘብን በጋራ ሃብት በማዋል ተንቀሳቅሰው ትልቅ ሃብት ያገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች አሉ፡፡ በእነዚህ እንኮራለን፡፡ የእነዚሁ ሃቀኛና ትክክለኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይም የሚያኮራ ነገር አላቸው፡፡ ያገኙትን ገንዘብ የሚያፈሱት በአገር ውስጥ ነው፡፡ ያገኙትን ወደ ውጭ አያሸሹም፡፡ እዚሁ ለአገርና ለወገን ጥቅም ነው የሚያውሉት፡፡ ለአገርና ለወገን ጥቅም መዋሉ ብቻም ሳይሆን የሚያውሉት የኢኮኖሚ ዘርፍም እጅግ አስፈላጊ፣ አትራፊና፣ ልማት ላይ አብይ ድርሻ የሚጫወት ነው፡፡ አዳዲስ እውቀትና አሰራርን የሚያስተዋውቅ ነው፡፡ ለመጪው ትውልድም መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ ሕዝብ እነዚህን ሊያበረታታ ይገባል፡፡ መንግሥትም ሊደግፋቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ሃቀኛ ባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች እንከን የለሽ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ እንኳን አስቸጋሪውን ኢንቨስትመንት በመሰለ ዘርፍ ይቅርና በሌላውም ቢሆን ችግር መታየቱ አይቀርም፡፡ ቁም ነገሩ የሚያጋጥማቸውን ችግር እየተቋቋሙና እያረሙ እየተከራከሩ መሄዱ ላይ ነው፡፡ እንዲህ እያደረጉ ጉዞ የሚቀጥሉና የሚያቀላጥፉ ኢንቨስተሮችም ይበልጥ ይመሰገናሉ፡፡ በኤክስፖርት ዘርፍ፣ በሪል ስቴት ዘርፍ፣ በእርሻ ዘርፍ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ፣ በትምህርትና ጤና ማስፋፋት ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪና ንግድ ዘርፍ ሃብት የለሽ ሃለሃብቶች እንዳሉ ሁሉ በእነዚህ ዘርፎችም አኩሪና ውጤማ የአገር የጀርባ አጥንት ሊሆኑ የሚችሉ ሃቀኛ ባለሃብቶች አሉ፡፡ ሃቀኝነትን የሚበረታታ ሃላፊነት፣ የሁሉም ዜጋና የመንግሥት ሃላፊነት ነው፡፡ በዋነኛነት ግን የራሳቸው የባለሀብቶቹ ሃላፊነት ነው፡፡ ታሪክ ሰርቶ ራስንና አገርን አኩርቶ መሄድ ትልቁ ክብር ነው፡፡ ሃብት ማግኘት ብቻ ሳይሆን እንዴት ተገኘ የትስ እየዋለ ነው? የሚለው ትልቅ መመዘኛ ማለፍም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው፤ ከባለሃብትም ባለሃብት አለ የሚባለው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |