| ምክር ቤቱ አዲስ የአሰራር ስልት ሥራ... |
|
|
| Sunday, 29 June 2008 | |
|
ምክር ቤቱ አዲስ የአሰራር ስልት ሥራ ላይ ለማዋል በመንቀሳቀስ ላይ ነው
በዳዊት ታዬ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለአባላት የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል አዲስ የአሰራር ስልት ሥራ ላይ ለማዋል በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የዚሁ እቅድ አካል የሆነውና ከላኪዎች ጋር የተደረገ ውይይት ሰኔ 20 ቀን 2000 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ እየሱስ ወርቅ ዛፉ እንደገለፁት እስካሁን ባለው የንግድ ምክር ቤቱ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ አባላት የሚፈልጉትን ያህል አገልግሎት አላገኙም፡፡ በሁሉም ዘርፎች ያሉ ችግሮች የተለያዩ ናቸው፡፡ አንዳንዴም ችግሮቹ ራሳቸው እርስ በርስ የሚጋጩ እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡ በተለይ በንግድና አገልግሎት ዘርፍ ላይ ያሉ ነጋዴዎች ችግር በአንድ ላይ ማስኬድ ባለመቻሉ ምክር ቤቱ የእያንዳንዱን ዘርፍ ችግር ለየብቻ በመመልከት የየዘርፉን ችግር መፍታት ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል፡፡ የንግዱ ዘርፍ ማኅበረሰብ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ሲፈልግ የሁሉንም ዘርፎች ጥያቄ አንድ ላይ ከማቅረብ ይልቅ በየዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለየብቻ ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ ለመፈለግ መሞከሩ አዋጭ እንደሆነም በማመን የምክር ቤቱ አባላትን በአስራ አንድ ዘርፎች ከፋፍሎ ችግሮቻቸውን ለመመልከትና የየራሳቸው ተወካዮች እንዲኖራቸው የማድረጉ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት የታቀፉት ከተለያዩ ዘርፎች በመሆኑ በአስራ አንድ ዘርፍ ተከፋፍሎ የሁሉም ዘርፍ ችግር ለየብቻ ለመመልከትና ሁሉም ዘርፎች በማኅበራቸው ተወካዮች በኩል የሚቀርቡ ጥያቄዎችና ችግሮችን ተቀብሎ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየትና መፍትሄ ለመፈለግ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት የየዘርፉን ተወካዮች የማስመረጥ ሥራና በአንዳንድ ችግሮች ዙሪያም ውይይት በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በዚሁ እቅድ መሠረት ከሁለት ቀናት በፊት ከላኪዎች ጋር በተደረገ ውይይት ችግሮች የተባሉት የተገለፁ ሲሆን አዲሱን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግም ላኪዎችን የሚወክሉ ተመርጠዋል፡፡ በወቅቱ ላኪዎች ካነሷቸው መካከል ከቅባት ላኪዎች የቀረበው ችግር አንዱ ነው፡፡ ላኪዎቹ እንደሚሉት ምርታቸውን ለመላክ ውል ከፈፀሙና እቃውን ከላኩ በኋላ ገዥ ኩባንያዎች ምርቱን አንቀበልም ስለሚሉ ምርቱ እንደሚበላሽና እነርሱም የሚከስሩበት አጋጣሚ እንደሚከሰት አመልክተዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የሚያካሂደው የዋጋ ቁጥጥርም ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን እኚሁ ላኪዎች የሚንልኳቸውን እቃዎች መሸጥ ያለባቸው በዚህ ዋጋ ነው እናንተ ባቀረባችሁት ዋጋ አይደለም በሚል መጉላላት እንደሚገጥማቸው አስረድተዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ትመናውየየወቅቱን አለምአቀፍ ገበያ ያገናዘበ ባለመሆኑ እኛ እንልክበታለን ያልነውን ዋጋ አንደር ኢንቮይስ እያደረጋችሁ ነው በሚል በሚደርስብን ተጽዕኖ ሥራችንን በአግባቡ ለመስራት አልቻልንም ብለዋል፡፡ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪዋን ለማሳደግና ላኪውም በአግባቡ እንዲሰራ ብሔራዊ ባንክ ወቅታዊና አለምአቀፋዊ የገበያ ዋጋ መረጃዎችን ሊኖሩት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ከቅባት እህል ላኪዎች የተሰነዘረ አስተያየት አንዳንድ የውጭ ገዥ ኩባንያ ለመግዛት የተስማሙትን ምርት ስንልክላቸው አንቀበልም ከማለታቸው በላይ እቃው ከተላከ በኋላ እናንተ ከሸጣችሁልን በታች ሌላ አግኝተናል የሚል ምክንያት የሚሰጡና ጥቂት የማይባሉ ላኪዎችን ኪሳራ ውስጥ የከተቱ ኩባንያዎች በመኖራቸው መንግሥት እንዲህ አይነት ኩባንያዎችን ሊቆጣጠረቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ላኪዎቹ ከሁሉም በላይ እየገረማቸው ያለው ጉዳይ ላኪዎችን ያከሰሩ ኩባንያዎች አሁንም ድረስ በነፃነት እየሰሩ መሆናቸውን ነው፡፡ ይህ ድርጊት የላኪው ብቻ ሳይሆን የአገር ጭምር ችግር በመሆኑ ነገ ተነገ ወዲያ ለሌሎችም አስመጪዎች ሊተርፍ ስለሚችል ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡ በዚሁ በቅባት እህል ላኪዎች በኩል እንደ ችግር የቀረበ ሙያ ጥራት ያለው ምርት አለመቅረብ ነው፡፡ አብዛኛው ላኪ ወደ ውጭ የሚልከውን ምርት የሚገዛው በቀጥታ ከገበሬው ሳይሆን ከነጋዴዎች ነው፡፡ ይህም በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ የሚሸጡልን ምርት ደረጃውን ካልጠበቁ ምርቶች ጋር ተደባልቀው አንዳንዴም ከባዕድ ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ ይህንን ለማበጠር በሚሞከርበት ጊዜ ለመለየት ጭምር ያስቸግራል፡፡ ይህ ደግሞ በዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ እንዲታጣ ከማድረጉም በላይ ላኪዎቹ ለተደጋጋሚ ኪሳራ ዳርጎናል ይላሉ፡፡ ሌላው የላኪዎች ትልቅ ችግር ብለው ያነሱት የፋይናንስ ጉዳይ ነው፡፡ ለላኪዎች የሚሰጠው የብድር አገልግሎት በጣም ደካማ ነው፡፡ ምርት ለመላክ በባንክ ቤቶች የሚጠየቀው ወለድ ከ10 በመቶ በላይ መሆኑ ብቻ ሳያንስ ብድር ለማግኘት ላኪዎች እስከ 70 በመቶ የሚሆን ገንዘብ ሊኖራቸው ይገባል የሚል አሰራር ባንኮች እየተከተሉ መምጣታቸው ላኪዎችን እየጎዳ ነው ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ በሌሎች አገሮች ኤክስፖርተሮች እንዲበረታቱ ልዩ የገንዘብ ድጋፍና የብድር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሩቅ ሳይኬድ የኬንያ ላኪዎች ሲበደሩ የወለድ መጠኑ እስከ 3 በመቶ ብቻ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለማሳደግ እንዲህ አይነቶቹን አሰራር ማዳበርና የብድር አሰጣጡን የበለጠ ውስብስብ ማድረግ እንደማይገባ ያመለክታሉ፡፡ የወጪ ንግድን በተመለከተ አስተያየት የሰጡ ሌላ ላኪ በበኩላቸው መንግስትን በተለይም ደግሞ በተለያዩ አገራት ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኞችን ወቅሰዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው እንደጠቆሙት መንግሥት በይፋ እንዳስታወቀው ኤምባሲዎች ዋነኛ ተልኳቸው የኢትዮጵያ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ገበያ ማፈላለግና ለአገሪቱ ኢንቨስትመንት እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሥራዎችን መስራት ቢሆንም የታዘብኩት ግን በተቃራኒው ነው ይላሉ፡፡ በኤምባሲዎቻችን የሚሰሩ ሥራዎች የራሳቸው ሲቪ ከፍ ለማድረግ እንጂ የሰሩት ሥራ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ትክክለኛ ገዢዎችን እያገኘን አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ግን ትልቅ ሥራ እየተሰራ ነው ብለው መረጃ ሲሰጡ ያሳዝነኛል በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህንን እና ይህንን መሰል አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከተሰነዘሩ በኋላ አቶ እየሱስ ወቅር ዛፉ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በእለቱ የቀረቡትንና በቀጣይ የሚቀርቡ ችግሮችን ላኪዎች በሚመርጡት ተወካዮች በኩል ተሰባስቦ ቻምበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀራረብ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡ በባንኮች የብድር አሰጣጥ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት የአገራችን ባንኮች አቅም ውስን ነው፡፡ ያላቸውም እሴት እንደ ልብ ብድር የመስጠት አቅማቸውን ያላዳበረ ነው፡፡ የብድር አሰጣጡ አቅምን ያገናዘበ ነው፡፡ አንዳንድ ብድሮች ብድር ለተሰጡባት አላማ አለማዋላቸው ለአሰራሩ መጥበቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ባንኮች የሚሰሩት የብድር አገልግሎት የሚሰጡት በብሔራዊ ባንክ ሞኒተሪ ፖሊሲና ሲስተም ሪጉሌሽን የሚሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ሌላው የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ሲባል ባንኮች የገንዘብ ዝውውሩን እንዲቀንሱ መደረጉም ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቁመው አሁን ያለውን የብድር አገልግሎትና ብድር ለመውሰድ የሚጠየቀውን የ70 በመቶ ጉዳይ አሁን ባለው አሰራር ወደ 25 በመቶ ማውረድ የሚቸግር ቢሆንም ጉዳዩን እንደ አንድ ችግር በመውሰድ ሊደረግ የሚገባውን መወያየት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ባንኮች ጥሩ ደንበኛቸውንና ጥሩ የብድር አመላለስ ሪከርድ ያለውን እንዲሁም የተበደረውን ብድር ለተበደረለት አላማ ያዋሉትን በራሳቸው አሰራር ወለድ ቀንሰው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አቶ እየሱስ ወርቅ ሌላው ያነሱት፣ የቅባት እህል ላኪዎች የሚሸጥላቸው ምርት ከባእድ ነገሮች ጋር ቀላቅለው የሚያቀርቡትን ማጋለጥ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |