Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow ለአእምሮእድገት ውስንነት የልዩ ፍላጎት ትምህርት
ለአእምሮእድገት ውስንነት የልዩ ፍላጎት ትምህርት Print E-mail
Sunday, 29 June 2008
Imageበምሕረት ሞገስ

ከአዳራሹ ወጣ ገባ በማለት ቤተሰቦቻቸውን በዓይናቸው ያማትራሉ፡፡ ወደ አዳራሹ የሚገባውን እንግዳ ደግሞ የሚያውቁትም ይሁን የማያውቁት ሰላምታ እያቀረቡ ወደ ወስጥ እንዲዘልቁ ይናገራሉ፡፡

ከወትሮው ለየት ያለ ባህሪ ይታይባቸዋል፡፡ አንድ ቦታ ብቻ ትኩር ብለው አያዩም፣ ጣታቸውን አፋቸው ውስጥ ከተው አይመጡም፣ ብቻቸውንም ሆነው ከራሳቸው ጋር ብቻ አይጫወቱም፡፡ በአብዛኛዎቹ ፊት ላይ ደስታ ይነበባል፡፡ ከደስታቸው የተነሳ እጃቸውን በማፋተገ ያጨበጭባሉ፣ በአዳራሹ ውስጥ ባለው ደረጃ ላይ ታች ይላሉ፡፡  

በልጆቹ የተሰሩ ወንበሮች፣ የፕላስቲክ ቦርሳ፣ የአበባ ማስቀመጫ፣ ስጋጃ እንዲሁም የጥልፍና የዲዛይን ሥራዎች ከአዳራሹ መግቢያ ተደርድረዋል፡፡

ስለአእምሮ እድገት ውስንነት በአገራችን ካለው ግንዛቤ ማነስ አንፃር የሰሩት ሥራ ቢገናዘብ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች እንዴት ሰሩት? ያውቃሉ? ይገባቸዋል ወይ? የሚለውንና የመሣሠሉትን ጥያቄዎች የሚያጭሩ ናቸው፡፡

በአዳራሹ ከተሰበሰቡት የልጆቹ ወላጆች አንዷ እንደገለፁልኝ፣ ልጃቸው እድገት ከሌሎቹ ልጆቻቸው የተለየ በመሆኑ ከ10 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ በቤት ውስጥ አስቀምጠውት ነበር፡፡ እንግዳ እቤት ሲመጣም ልጃቸው ከሚቀመጥበት ክፍል እንዲወጣ አይፈልጉም ነበር፡፡  ለዚህ ምክንያታቸው እሳቸው እንደሚሉት ከእርግማን የመጣ በሽታ ስለሆነ ሰው ፊት ማውጣቱ ያሳፍራቸው ስለነበር ነው፡፡ ዛሬ ግን ደስተኛ ናቸው፡፡ በአንድ ዘመዳቸው አማካይነት ከ5 ዓመታት በፊት ትምህርት ቤት የገባው ልጃቸው ዛሬ በመድረክ ላይ ሆኖ ሽልማቱን ሲቀበል ለማየት ችለዋል፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት በ1980 ዓ.ም ነበር በኮከበጽባህ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ህፃናት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ የተከፈተው፡፡
 
የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍሉ ሰኔ 15 ቀን 2000 ዓ.ም የክፍሉን መመስረት 20ኛ ዓመት አስመልክቶ በኮከበጽባህ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አዳራሽ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት አቶ ጌታቸው አለሙ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር እንደገለፁት፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍሉ ሲመሰረት የነበሩት 11 ተማሪዎችና 3 መምህራን ነበሩ፡፡

የተማሪዎቹን የጉዳት ዓይነትና ደረጃ በመለየት፤ ክፍተቱን በማስተማርና በማሰልጠን በመሙላት፣ ሕፃናቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ፣ አደናቃፊ መሰናክሎችን በመቀነስና በማስወገድ በሚያደርጉት ጥረትና ኅብረተሰቡም ከኋላ ቀር አመለካከት በመውጣት፤ ሕፃናቱ በትምህርት እንደሚለወጡ ግንዛቤ በመፍጠር በሚያደርጉት ትብብር በየጊዜው የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡

በ1988 ዓ.ም በልዩ ፍላጎት ትምህርት ከተመዘገቡት 24 ተማሪዎች ውስጥ 1 ሴትና 2 ወንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጥ አምጥተው ወደ መደበኛ ትምህርት ለመቀላቀል ችለዋል፡፡

በያዝነው አመት በልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል 34 ወንዶችና 26 ሴቶች እንዲሁም ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ባለው ተካትተው የሚማሩ 12 ወንድና 13 ሴቶች ያሉ ሲሆን፣ በ20 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜም 1 ወንድ ተማሪ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወስዶ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡

የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎች ከቀለም ትምህርቱ ባሻገር በልዩ ልዩ ሙያዎች ስልጠና የሚታገዙ ሲሆን ከእነዚህም የሥጋጃ፣ የጥልፍ፣ የስፌትና የቅርጻ ቅርጽ ሥራ ትምህርት ይጠቀሳሉ፡፡

በተማሪዎቹ የተሠሩ ዕቃዎች ተሸጠው የገቢ ማስገኛ ምንጭ በመሆን ክፍሉን የሚያግዙ ሲሆን ከእነዚህም ሌላ በልዩ ትምህርት ክፍል የተቋቋሙ ክበባት በየዓመቱ አዳዲስ ተማሪዎችን በመመልመል በሚኒ ሚዲያ ፕሮግራም በማሳተፍ ስለልዩ ፍላጎት ትምህርት ግንዛቤ ያስጨብጣሉ፡፡

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት 463 ወንዶችና 379 ሴቶች እስከዛሬ ባለው ሂደት በልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍሉ ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን ለተማሪዎቹ ከወላጅ በላይ ፍቅር በመስጠት፣ በመንከባከብና በማቅረብ ያሉትን ችግሮች ሁሉ በመቋቋም ምቹ ሁኔታን በመፍጠር፣ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ በማድረግ፣ ለዘላቂ ህይወታቸው የሚበጁ እውቀቶችን በማስጨበጥ፣ የሰው እጅ ሳይጠብቁ ራሳቸውን በራሳቸው የሚረዱበት ሁኔታ እየተፈጠረላቸው ነው፡፡

የ20 ዓመታቱ እንቅስቃሴ ግን በተመቻቸ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ክፍሉ ለብዙ ጊዜያት የራሱ በጀት ሳይኖረው በየዘመኑ ለመደበኛ ትምህርት ከሚፈቀደው በጀት እየተካፈለ የቆየና የውስጥ አስፈላጊ ቁሳቁስ እንደ ልዩ ፍላጎት ትምህርትነቱ ያልተሟላለት፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች (መምህራን) የማነቃቂያ ድጋፍ የሌለው፣ የሰለጠነ መምህር እጥረት ያጋጠመው በተለይም በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ ከግንዛቤ ማነስ በየቤቱ አስቀምጧቸው የነበሩትን ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤቱ ማምጣት በመጀመሩ የመማሪያ ክፍል እጥረትና የሙያ ትምህርት መስጫ ወርክሾፕ መጣበብ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው፡፡

አቶ ብርሃኑ መቆያ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል አስተባባሪ በበኩላቸው የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ህፃናት በማኅበረሰቡ ውስጥ የተሟላ ህይወት እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን ለማመቻቸት፣ በዕውቀትና በሙያ ተኮትኩተው እንዲያድጉ፣ ብቁ ሆነው በራስ በመተማመን ደረጃ ላይ እንዲደርሱ፣ ለአደጋው የተጋለጡ ህፃናት እንዳይገለሉ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የተዛባ አመለካከት ተለውጦ ህፃናቱ ተቀባይነት አግኝተው በፍቅር እንዲያድጉና በመደበኛ ትምህርትም እንዲታቀፉ ለማስቻል ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመተባበር እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል የተቋቋመው የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሕፃናት የሙያ ክህሎት የሚያጎናጽፍ ሥልጠናን ለመስጠትና እንዲሁም በህብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት የተነሳ ወደ ትምህርት ቤት ያልወጡትንና የተደበቁትን ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲያመጡ ለማድረግ ነው፡፡
 
< Prev   Next >