Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow ከፈተና ወደ ፈተና
ከፈተና ወደ ፈተና Print E-mail
Sunday, 29 June 2008
Imageበትዕግሥት ዘሪሁን

እናቷን በሞት ያጣችው ገና በ11 ዓመቷ ነው፡፡ እናቷ ከሞተች በኋላ በእግሯ መራመድ የማትችለውን የሁለት ዓመት እህቷን የእንጀራ አባቷን የመንከባከብ ኃላፊነት ወደቀባት፡፡ እሷ እንደምትለው እቤት ውስጥ የሚያስፈልገውን ስራ ሁሉ የምትሰራው ብቻዋን ነበር፡፡ ቤት ማፅዳት፣ ልብሳቸውን ማጠብ፣ ምግብ ማብሰልና አስፈላጊ የምግብ እህሎችን መግዛት ይጠበቅባታል፡፡

በካሳና በተጎሳቆለ ሰውነቷ የአሥር ወር ልጇን አዝላ ያገኘናት የ17 ዓመቷ ታዳጊ እንዳጫወተችን እናቷን ካጣች በኋላ ከእንጀራ አባቷ ጋር የቆየችው ረዥም ጊዜ አይደለም፡፡ እሷ እንደምትለው መጀመሪያ አካባቢ ለምግብ መግዣ የሚያስፈልገውን ገንዘብ እየሰጠ በሰላም ቤቱን እንድትመራ ቢያደርግም በዚያው ስሜት መቀጠል አልቻለም፡፡ "እስካሁን እናትሽን ሳኖር ቆይቻለሁ፣ አሁን ደግሞ አንቺን እየቀለብኩ የምኖርበት ምክንያት የለም" ይላታል፡፡ በተጨማሪም አንድ ቀን አስገድዶ ሊደፍራት እንደሞከረ ታስታውሳለች፡፡

"ሁል ጊዜ በጥዋት ነው ሥራ የሚሄደው፡፡ ያን እለትም ወደስራ ከሄደ በኋላ እህቴን ጎረቤት ቤት አደራ ብዬ እሱም ከመጣ እንዲሰጡት የቤቱን ቁልፍ አስቀምጬ ወደ ትምህርት ቤት ሄድኩ፡፡ ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ከፈተና ስመለስ አልጋ ላይ ተኝቶ አገኘሁት፡፡ ቁርስ እንድሰራለትና ሻይ እንዳፈላለት አዘዘኝ፡፡ የተባልኩትን አድርጌ ሳቀርብለት ጎትቶ አልጋ ላይ ወረወረኝ፡፡ ቢላዋ ጨብጦ ብትጮሂ በዚህ ነው የምዘከዝክሽ እያለ አስፈራራኝ፡፡ እኔ ግን በድፍረት ጮህኩ"

ታዳጊዋ እንደገለፀችው ይህ አጋጣሚ ከመፈጠሩ በፊት ጎረቤቷ ትመክራትና ታስጠነቅቃት ነበር፡፡ ፣ከዚህ ሰውዬ ተጠንቀቂ አንድ ነገር ሊያደርግም ቢሞክር ጩሂ፣ እያለች ትመክራት እንደነበር ትናገራለች፡፡ በዕለቱ ጩኸቷን ሰምታ ቀድማ የደረሰችላትም በፊትም ትመክራት የነበረችው ይህችው የጎረቤት ሴት ነበረች፡፡ ሴትዬዋ በሩን በርግጫ በርግዳ ስትገባ ታዳጊዋ ዘላ በመውጣት ጩኸቷን አሰማች፡፡ ጎረቤት ተሰብስቦ ለፖሊስ ስልክ ተደወለና ሰውየው በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡ ከቀናት በኋላ ግን ከእስር ተለቆ ትንሿን ልጁን ይዞ ወደ መቀሌ እንደሄደ ታዳጊዋ ገልፃልናለች፡፡

ተወልዳ ያደገችበት አውቶቡስ ተራ አካባቢ ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ረዳት በማጣቷ መኖር አልቻለችም፡፡ የእናቷ ጎረቤቶች ጎል ኢትጵያ የሚል ድርጅት ውስጥ አስገቧትና ትምህርቷን ቀጠለች፡፡ ድርጅቱ የትምህርት መጠለያና ምግብ ወጭዋን ሁሉ ሸፍኖላት ጥሩ ኑሮ ጀመረች፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት መስከረም ወር ላይ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሆና ስትጀምር ድርጅቱ ያሟላላት ሦስት ደብተር እና እስኪሪቢቶ ብቻ ነበር፡፡ በመሆኑም የሒሳብ ደብተር ለምን አላሟላሽም? የሚል ጥያቄ በዓመቱ አዲስ አስተማሪ ሆኖ በተቀጠረው መምህሯ ጥያቄ ቀረበላት፡፡ ምክንያቷን ነገረችው፡፡ በማግስቱ ደርዘን ደብተር፣ እስክሪቢቶና እርሳስ ገዝቶ አመጣላት፡፡ ታዳጊዋና አስተማሪዋ በዚሁ መቀራረብ ጀመሩ፡፡

የታዳጊዋና የመምህሯ ቅርርብ ወደ ፍቅር እንደተሸጋገረም አልሸሸገችም፡፡ ከመምህሯ ጋር የነበራት ግንኙነት ከሚረዳት ድርጅት እጅ እንድትወጣ ምክንያት ሆነ፡፡ የተፃፃፍኩት ደብዳቤ እንደእማኝ ቀርቦ የትምህርት ቤቷ ዳይሬክተር በተገኙበት በሰራችው ስህተት ድርጅቱን ለቃ እንድትወጣ ተፈረደባት፡፡ ከዚያ ወጥታ የት እንደምትሄድ ግን ለማንም ግልፅ አልነበረም፡፡ "የድርጅቱ ዋናዋ ኃላፊ በጣም ታዝንልኝ ነበር፡፡ ወጥተሽ ሜዳ ላይ ከምትወድቂ ብላ ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ የሚገኝ አንድ ፋብሪካ ውስጥ በወር ደሞዝ አስቀጠረችኝ"

ታዳጊዋ እንደምትለው ትምህርቷን አቋርጣ የእለት ህይወቷን ለማሸነፍ በተቀጠረችበት ፋብሪካ ውስጥ ከሁለት ወር በላይ አልሰራችም፡፡ እኔ ቤት ሆነሽ የቀን አስተምርሻለሁ እያለ የሚጎተጉታትን አስተማሪዋን ተስፋ አድርጋ ወደ ቤቱ ገባች፡፡ የሰማኒያ ወረቀት ሳይፈራረሙ በ15 ዓመቷ የአስተማሪዋ ቤት ውስጥ ሚስት ሆና መኖር ጀመረች፡፡

ወደ ቤቱ ከገባች በኋላ ግን የቀን አስተምርሻለሁ የሚል ቃሉን አጠፈ፡፡ እሷ እንደምትለው ሰበብ እየደረደረ ወደ ትምህርት ቤት እንዳትመለስ አደረጋት፡፡ በዚሁም ምክንያት ከስድስተኛ ክፍል በኋላ የመማር እድል አላገኘችም፡፡

ከመምህሯ ጋር ለዓመት ያህል አብረው ከኖሩ በኋላ በድንገት መታመም ጀመረች፡፡ "ያቅለሸልሸኛል፣ ያዞረኛል፣ ያስመልሰኛል፣ ምግብ አስጠላኝ፡፡ ጎረቤታችን ይሄ ነገር እርግዝና ሳይሆን አይቀርም አስመርምራት ስትለወ ሃኪም ቤት ወሰደኝና ሽንት ሰጠሁ፡፡ አርጉዝ መሆኔ ተነገረኝና ወደ ቤት ተመለስን፡፡ ከሃኪሟ ፊት ፣ምንም ችግር የለውም፣ ሲል ቆይቶ እቤት ስንሄድ ሊገድለኝ ደረሰ፡፡ ኑሮ ውድ ነው፣ ደሞዜ ትንሽ ነው፣ ለቤት ኪራይ እየከፈልኩ ነው የምኖረው ይሄንን ሁሉ እያየሽ እንዴት እንዲህ ታደርጊያለሽ ብሎ አምባረቀብኝ"

ተምሯል፣ ህፃናትን ለማስተማር ብቁ ነው ተብሎ የተቀጠረውና በእድሜ ከእጥፍ በላይ የሚበልጣት መምህሯና ባሏ ማርገዟን የሷ ሃጢያት አድርጎ አየው፡፡ እርግዝናን እንዴት መከላከል እንደምትችል ሳይነግራት፣ ሳያስተምራት እርግዝናው ከተከሰተ በኋላ ስህተት ሰራሽ እያለ ቁምስቅሏን አሳያት፡፡

ከቁጣ አልፎ ከቤቱ እንድትወጣም ጠየቃት፡፡ ከሱ ቤት ወጥታ መድረሻ እንደሌላት የምታውቀው ወጣት ግን እየተለማመጠችው መኖርን መረጠኝ፡፡ ዘዴዋ ግን አልተሳካም፡፡ የቀለብወጭ መስጠቱን አቆመ፡፡ ውጭ በልቶ ይመጣል፣ አያነጋግራትም፣ ሳንቲም የሚባል በዓይኗ አያሳያትም፡፡ እቤት ውስጥ የሚበላው ነገር ሙጥጥ ብሎ ካለቀ በኋላ እየተራበች ለሦስት ቀን ቆየች፡፡ አማራጭ ስታጣ ከቤት ወጥታ ካዛንቺስ አካባቢ ጎዳና ላይ መኖር ጀመረች፡፡

ጎዳና ላይ ስለ ኤች.አይ.ቪ በሚያስተምራቸው አንድ ግለሰብ አማካኝነት ከሁለት ወር በኋላ አንድ የሚያሳድጋት ድርጅት አግኝታ ገባች፡፡ የሦስት ወር እርጉዝ መሆኗን ግን ደብቃለች፡፡ ልብሷን መጠለያዋን፣ ምግቧንና አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ድርጅቱ እያሟላላት መኖር ጀመረች፡፡ ህይወት ቢመቻትም በየቀኑ የሚነፋውን ሆዷን ግን መደበቅ አልቻለችም፡፡ ድርጅቱ ነፍሰ ጡር ሴት አይረከብም ነበርና ከኃላፊዎቹ "ለምን ደበቅሽን?" በሚል ቁጣና ግልምጫ ደረሰባት፡፡ በመጨረሻም እዚያው ድርጅት ውስጥ እንዳለች ከወለደች በኋላ 15 ቀን ሲሞላት የሚረከባት ዘመድ እንድትፈልግ ካልሆነ ወደ ጎዳና እንድትመለስ ተነገራት፡፡

አሰላ የሚኖር የአባቷ አጎት ጋር ተደውሎ ሁኔታው ተነገራቸውና ወደ እሳቸው ተላከች፡፡ የአባቷ አጎት ያረጁና የገቢ ምንጭ የሌላቸው ነበሩና ለዘጠኝ ወራት አብራቸው ከቆየች በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሳ ራሷን ለማኖር እንድትሞክር መክረው ላኳት፡፡

ከ15 ቀን በፊት የ1ዐ ወር ልጇን አዝላ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰችው የ17 ዓመቷ ታዳጊ ባጋጣሚ ፓርኪንግ ከምትሰራ ወጣት በሰማችው መረጃ መሰረት ፆታዊ ጥቃት ተከላካይ ማህበር የሚባል ድርጅት አግኝታ ለጊዜው መጠለያና ምግቧን ችሏት እየኖረች ነው፡፡ ድርጅቱ ጥቃት ደርሶባቸው መጠጊያ የሌላቸው ሴቶችን እየተቀበለ ጊዜያዊ መጠለያ ይሰጣል፡፡ ታዳጊዋም የዚሁ ተጠቃሚ ሆናለች፡፡ ስለነገ ግን የምታውቀው ነገር የለም፡፡ "ድርጅቱ በመጠለያ ሊያቆየኝ የሰጠኝ ጊዜ አንድ ወር ነው፡፡ አሁን 15 ቀን ሆኖኛል፡፡ የቀረችኝን 15 ቀን ከጨረስኩ በኋላ ደግሞ የት እንደምወድቅ አላውቀውም" ትላለች፡፡

እንደ ታዳጊዋ ጥቃት ደርሶባቸው ለጊዜው መውደቂያ የሌላቸው 19 ሴቶች በተጠቀሰው ድርጅት መጠለያ ውስጥ ተመልክተናል፡፡ ከመካከላቸው ሰባቱ ነፍሰ ጡር ሲሆኑ አምስቱ ደግሞ ከቤት ይዘዋቸው የወጡ ልጆችን ታቅፈዋል፡፡

የታዳጊዋን ታሪክ እንደማሳያ አነሳን እንጂ በቦታው የተሰባሰቡ ሴቶች ሁሉ የተለያየ ጥቃት ሰለባዎች ናቸው፡፡ ሁሉንም ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ሌላው ነገር ደግሞ የሚጠጉበትና የሚረዳቸው አለመኖሩ ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች በመጠለያ ከሚደረግላቸው እንክብካቤ ባለፈ መጠለያውን ለቀው ሲወጡ ራሳቸወን የሚችሉበት ሁኔታስ ይመቻችላቸዋል ወይ? የሚልና ሌላም ጥያቄ በድርጅቱ የህግ ባለሙያ ለሆኑትን ወ/ሪት ማህሌት ኃይለማርያምን አነጋግረናቸው ነበር፡፡

በመጠለያ ውስጥ እስካሉ ድርስ የምግብ፣ ልብስና ንፅህና እንዲሁም የምክር አገልግሎትና የህግም አገልግሎት እንደሚያገኙ ባለሙያዋ ጠቅሰው እንደሴቶቹ የትምህርት ደረጃ ለወደፊት ኑሯቸው የሚጠቅሙ ስልጠናዎችንም እንደሚያገኙ ያስረዳሉ፡፡

ወ/ሪት ማህሌት እንደሚሉት በመጠለያው የሚቆዩበትን ጊዜ የሚወስነው የደረሰባቸው ጥቃትና ጉዳያቸው ነው፡፡ "መጠለያው ጊዜያዊ ነው፡፡ ጊዜያዊ ነው ተብሎ ግን ጉዳያቸውን ሳይጨርሱ አይወጡም፡፡ ለምሳሌ ተገዳ ተደፍራ አርግዛ የመጣች ሴት ከሆነች ወልዳ የምትሔድበት አጋጣሚ አለ፡፡ ተደፍረው ሳያረግዙ የሚመጡት ደግሞ ፍርድ ቤት ምስክርነት እስኪሰጡ፣ ከትዳሯ የተባረረች ሴትም በፍርድ ቤት ንብረቷን እስከምትካፈል ትቆያለች"

ወደ መጠለያ ሲገቡ መጠገያ የሌላቸው መሆኑ ይታወቃልና ከመጠለያ ሲወጡ ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታን ለማመቻቸት የሚደረግላቸውስ ነገር ይኖር ይሆን? እንደባለሙያዋ ገለፃ እንደትምህርት ደረጃቸው የፀጉር ሥራ፣ ኮምፒውተር፣ የእደ ጥበብ ሙያና የመሳሰሉት ስልጠናዎች ይሰጧቸዋል፡፡ ይሁንና ብዙዎቹ ጥቃት ደርሶባቸው ወደ መጠለያ የሚገቡ ሴቶች የቤት ሰራተኞችና ያልተማሩ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
< Prev   Next >