| ከፕሬስ ነፃነት ሽሽት |
|
|
| Wednesday, 02 July 2008 | |
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅርቡ ከኒውስዊክ መፅሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሚፀድቀው የፕሬስ ሕግ ኢትዮጵያን በፕሬስ ነፃነት መስፈርት በዓለም አሉ ከተባሉት በግንባር ቀደምትነት የሚያሰልፋት ይሆናል ብለው ቃል ገብተውልን ነበር፡፡ ትናንት የፀደቀው ግን ኢትዮጵያን በፕሬስ ነፃነት ግንባር ቀደም የሚያደርጋት ሳይሆን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባት ነው፡፡ ቃል የተገባልን ሌላ የፀደቀው ሌላ! ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከሶስት ዓመታት በፊት ራሳቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለፓርላማ የገቡት ቃል፣ ለሶስት ዓመታት ሳይፀድቅ የቆየው የፕሬስ ሕግ፣ ከውጭ አሉ የተባሉ ባለሙያዎች አምጥተን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የነፃነት ሕግ እንዲሆን ስለፈለግን ነው በቅርቡም እናደርገዋለን ብለው ነበር፡፡ ትናንት የፀደቀው ግን የባለሙያዎች አስተያየት አላካተተም፡፡ ቃል የተገባልን ሌላ የተሰጠን ሌላ! ኢሕአዴግ ራሱ ግንባር ቀደም ሆኖ ባዘጋጀው ሕገ መንግሥት አንቀፅ ሃያ ዘጠኝ የሰፈረው የፕሬስ ነፃነትን የሚያረጋግጠው ቃል እውነትም በዓለም አቀፍ ግንባር ቀደም ከተባሉት አገሮች ረገድ እንድንሆን የሚያደርግ ነው፡፡ ሆኖም ግን ትናንት የፀደቀው የፕሬስ ሕግ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን ቃል የሚሽር፣ የሚበላና የሚረግጥ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ሌላ፣ የፕሬስ ሕጉ ሌላ! የኢሕአዴግ መንግሥት ሊኮራበት የሚገባ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብትና የፕሬስ ነፃነት መርሆዎች ሁሉ ፈርሞ ተቀብሏል፡፡ ፈርሞ መቀበሉ ብቻ ሳይሆን በግልጽና በማያሻማ መንገድ የኢትዮጵያ ሕግ ሆነው ያገለግላሉ ብሎ በሕገ መንግሥቱ አስፍሯል፡፡ ማስፈር ብቻ ሳይሆን በአተረጓጎም እንዳይቀለበሱ በመጠንቀቅም የፈረመባቸው ዓለም አቀፉ ሕጎች በሙሉ የሚተረጎሙት ባለው በዓለም አቀፉ ትርጓሜ መሰረት ነው ብሎም በሕገ መንግሥቱ አስፍሯል፡፡ አሁን የፀደቀው የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት ሕግ ግን ዓለም አቀፍ ውሎችንና ትርጉሞቹን የጣሰና ያልተከተለ አፈንጋጭ ሕግ ነው፡፡ ቃል የተገባልን ሌላ የፀደቀው ሌላ! ኢሕአዴግ ከገባው ቃል ሸሸ" ፓርላማው ራሱ ካፀደቀውና ከገባው ቃል ሸሸ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው እምነትና መርሕ አርቃቂውም አፅዳቂውም ሸሸ! በእምነት ከፕሬስ ነፃነት መሸሽ ሳይሆን በአቀራረብም የፕሬስ ሕግንና የመረጃ ሕግን ደበላልቆ በማውጣት፣ የፕሬስ ሕጉን በፕሬስ ህግ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሕጎች በታትኖ በማውጣት እስካሁን ድረስ የነበረውን አካሄድም የካደ ነው፡፡ ሙያዊ አቀራረብን የሸሸ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የፕሬስ ሕግ ምን ይመስላል? ቢባል ከአንድ ነጋሪት ጋዜጣ መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡ የተወሰነው የፕሬስ ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ እንዲህ ይላል፡፡ ሌላው የፕሬስ ሕግ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ማጠናከሪያ ሕግ እንዲህ ይላል፤ ሌላው ሕግ በብሮድካስት ሕግ እንዲህ ይላል፣ ሌላው በኢንቨስትመንት ሕግ እንዲህ ይላል፡፡ በጉምሩክ ሕግ ደግሞ እንደዚህ የሚል አለ፡፡ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሕግ ደግሞ እንዲህ የሚል አለ፤ ተብሎ በመዋጮ የሚታይ እንጂ የትላንት ሕግ ብቻ በማየት ሕጉ ይህ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አቀራረብ እንዲቀረፅ መደረጉም በራሱ ከቅንነት የሸሸ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ከትክክለኛ የፕሬስ ነፃነት እምነት ሽሽት ለምን? ከትክክለኛ አቀራረብ ሽሽት ለምን? አካሄዱ አቀራረቡ አረቃቀቁ የለንደን ነው የጀርመን ነው የደቡብ አፍሪካ ነው የሚል የምክንያት ሽሽት ለምን? በዚህ ዙሪያ እየቀረቡ ያሉት ምላሾች ሁለት ናቸው፡፡ በአንድ በኩል እንዲያውም ከምንም ጊዜ በላይ እንዲጠናከር አደረግነው እንጅ አልሸሸንም ከሚል ጀምሮ እስከ የሸሸንበት ምክንያት እስካሁን ድረስ ያሉን ተሞክሮ ጋዜጦች ሕዝቡን እያነሳሱት፣ እያጋጩ፣ እየዋሹ፣ እየቀጠፉ ስለሆነ መቆጣጠር ስላስፈለገ ነው የሚል ነው፡፡ በሕገ መንግሥት የተሰጠው መሰረታዊ ሰብዓዊ መብትና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሬዲዮ ቴሌቪዥን ማቋቋም ይችላል፤ የሚለው ፓርላማ ያጸደቀው መብት፣ ተረግጦ ሕገመንግሥቱ እንደዚያ ቢልም እኛ ግን ቴሌቪዥን አንፈቅድም፣ ሬዲዮ እንጂ፣ ሬዲዮ ደግሞ አጭር ሞገድ ሳይሆን ኤፍ.ኤም. ብቻ ነው፣ ኤፍ ኤም ደግሞ ለሁሉም ሳይሆን ሁለት ብቻ ነው፡፡ ሁለት ስንል ደግሞ ዘጠና ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ብቻ ነው፤ እያሉ እየቆራረጡና መብት መሆኑ ቀርቶ በፓስተር ኢንስቲትዩት የሚቀመም መድሃኒት አስመስሎ በማንኪያ እየለኩ መስጠት ሽሽት አይደለም ከተባለ ሽሽት ምን ይሆን? ወደ ኋላ ተመልሶ በወንጀለኛ መቅጫ እውነት ራሱ መከላከያ አይሆንም፤ ከበስተጀርባው ሌላ መነሻ የሌለው መሆኑንም ተከሳሽ ማረጋገጥ አለበት፣ የሚል ሕግ እያወጡ መሸሽ ካልሆነ ሽሽት ምን ይሆን? በ1984 ዓ.ም የወጣ የፕሬስ ሕግ በሰላሳ ቀን ፈቃድ ካልተሰጠ እንደተሰጠ ይቆጠራል የሚለውን ቀይሮ አሁን አስፈሪና አሳፋሪ የፈቃድ ሕግ ማውጣትና የድሮው ሕግ "ጋዜጠኛ መረጃ የማግኘት መብት አለው፤ ባለሥልጣን መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት" የሚለውን ቀይሮ በህዝብ ግንኙነት በኩል ጠይቁ ማለት ሽሽት ካልሆነ ሽሽት ምን ይሆን? ጋዜጠኛው መብቱን በአግባቡ ስላልተጠቀመበት ነው ለሚባለው እኛም ጋዜጠኛው መብቱን በትክክል ተጠቅሞበታል የሚል እምነት የለንም፡፡ የሚያጋጭ፣ የሚያነሳሳ፣ ምግባረ ብልሹነት የተፀናወተው፣ ውሸታም፣ ቀጣፊ የሆነ፣ አገርም ሕዝብም ከማገልገል ይልቅ ግለሰቦችንና ሌሎች ሌሎችን የሚያገለግል ጋዜጠኛ አይተናል፤ እያየንም ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጋዜጦች እንደዚህ ይፅፋሉ፡፡ ያጠፉ ጋዜጦች ሕገ መንግሥት ጥሳችኋል ተብለው ይጠየቃሉ እንጅ መጥፎ ጋዜጣ ስላለ ሕገ መንግሥት አይጣስም፡፡ በአስቸኳይ ሩቅ ሳይኬድ ኢህአዴግ በፕሬስ ነፃነገት ዙሪያ አቋሙን ማስተካከል አለበት፡፡ አሁን የተያያዘው ግን ከፕሬስ ነፃነት ሽሽት ነው! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |