Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Sep 07th
Home arrow Sections arrow "እንደ እንጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ...
"እንደ እንጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ... Print E-mail
Wednesday, 02 July 2008
"እንደ እንጉዳይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊደርስ የሚችል የምግብ ዘር የለም"
ዶ/ር ዳዊት አባተ

እንጉዳይ በውስጡ ፕሮቲን፣ አሚኖ አሲዶች፣ ሚኒራሎች0ቫይታሚኖች፣ የያዘ ሲሆን እንዲሁም በምግብ አጣፋጭነቱና በመድሃኒትነቱ ይታወቃል፡፡ እንጉዳይን በጥናት በተደገፈ መልኩ ለማምረትና ለምግብነት ለማዋል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዮሎጂ ዲፓርትመንት አነሳሽነት ጥናት ማድረግ የተጀመረው ከ10 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥናቱ ውጤታማ ሆኖ ኦይስተር፣ ሽታኪ፣ በተን እና ናሜኩ የተባሉትን አራት ዓይነት ለምግብነት የሚውሉ የእንጉዳይ ዓይነቶች በኢትዮጵያ በመጠኑ ማምረት ተጀምሯል፡፡

ዶ/ር ዳዊት አባተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ ፋኩልቲ የሥነ ህይወት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና በእንጉዳይ (መሽሩም) ላይ ሲካሄድ የነበረው ጥናት ኃላፊ ናቸው፡፡  ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ከ12 ዓመታት በፊት በእንጉዳይ ዙሪያ ጥናት ለማድረግ መነሻችሁ ምን ነበር?

ዶ/ር ዳዊት፡-
የእንጉዳይ ጥናትን ከ12 ዓመታት በፊት ስንጀምረው ዓላማ አድርገን የተነሳነው ኢትዮጵያ ያላት የግብርና ውጤት (ውዳቂ) ላይ እንጉዳይ ስለሚያድግ ይህንን በመጠቀም እንጉዳይ ማምረትና ለምግብነት ማዋል ይቻላል የሚለውን ነበር፡፡ በመሆኑም ምን ዓይነት እንጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመረት ይችላል?፣ የማሳደጊያው ስፍራ ለየትኛው ዓይነት ይስማማል?፣ የትኛው የአየር ሁኔታ ለየትኛው እንጉዳይ ዓይነት ሊስማማ ይችላል ለሚሉትም መልስ ለማግኘት ነው ጥናቱን የጀመርነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህሉ የእንጉዳይ ዓይነቶች ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ነው ጥናታችሁ ያሳየው?

ዶ/ር ዳዊት፡
- በኢትዮጵያ በዱር የሚገኙ እንጉዳዮች በመቶ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አሁን ሊመረቱ የሚችሉ እንጉዳዮች በአጠቃላይ በዓለም ላይ 30 ዘር አላቸው፡፡ ከ30ዎቹ 4ቱን ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት ችለናል፡፡ በትንንሽ ደረጃ እየተመረቱም ገበያ ላይ መድረስ ችለዋል፡፡ በእነዚህ አራት ዘሮች ውጤት አግኝተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ያለው የአየር ሁኔታ አራቱን የእንጉዳይ ዘሮች ለማምረት አመቺ ሆኖ ነው ያገኛችሁት?

ዶ/ር ዳዊት፡
- የእንጉዳይ ተክል ሞቃት ቦታ አይፈልግም፡፡ ቀዝቀዝ ባለ አካባቢ ነው መመረት ያለበት፡፡ በኢትዮጵያ ደጋና ወይናደጋ አካባቢ እንጉዳይ ለማምረት ጥሩ ነው፡፡ አዲስ አበባም ለአራቱ እንጉዳዮች ተስማሚ ቦታ ናት፡፡ የአዲስ አበባ ሙቀት በተለይ በጥቅምት ወራት ይቀዘቅዛል፡፡ በዚህ ወቅት ትንሽ ማሞቅ ያስፈልግ ይሆናል እንጂ ምንም ዓይነት የሙቀት ሃይል ሳያስፈልግ ሊያድግ የሚችል ነው፡፡ እንደ የገብስና የጤፍ ጭድ፣ ሰጋቱራ የጥፍጥሬ ውዳቂ ተረፈ ምርት ለእነዚህ እንጉዳዮች ማሳደጊያነት ይጠቅማሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የእንጉዳይ ምርት በምን ደረጃ ላይ ነው? የእናንተስ አስተዋፅኦ?

ዶ/ር ዳዊት፡
- በኢትዮጵያ ውስጥ እንጉዳይ ማምረት ተችሏል፡፡ በእርግጥ በትንሽ ደረጃ ነው፡፡ የእንጉዳይ ማምረት ልምዱ በምርምር የተገኘ ነው፡፡ በእኛ በኩል ከምርምሩ ጋር በተያያዘ መፅሃፍ ፅፈናል፡፡ ስልጠናም ሰጥተናል፤ እየሰጠንም ነው፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫም ኮንፍረንስ አድርገን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አምራቾች ጠንካራ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ጠንከር ብሎ የገንዘብ ወጪ ያወጣ ባለሀብት እስካሁን አልመጣም፡፡ በትናንሽ ደረጃ የሚመረቱና ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ የሚያቀርቡ ጥቂት አምራቾች አዲስ አበባ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም ጠንካራ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ እነሱን አስተማማኝ አምራች ለማድረግ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም ሥልጠና መስጠት፣ የተመረጡ ዘሮች አቅርቦትን ማስተካከል እንዲሁም የእንጉዳይ አምራቾች ማህበር ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ የእንጉዳይ አምራቾች ማህበር ሲቋቋም ማጠናከርም ያስፈልጋል፡፡ ከምርምር የሚወጣ ግኝትን የማስተባበርንና ስልጠናን በማጠናከር የእንጉዳይ ማምረት አቅማችንን ማጐልበት ያስፈልገናል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ጅማሮ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንጉዳይ የመመገብ ባህላችን ጠንካራ አለመሆኑ ይሆን ዘርፍ እንዳይጠናከር ያደረገው?

ዶ/ር ዳዊት፡-
በኢትዮጵያ እንጉዳይን በምግብነት የመጠቀም ባህል በተወሰኑ አካባቢዎች አሉ፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች ባህሉ የለም፡፡ እንደውም እንጉዳይን እንደመጥፎ ነገር የሚያዩ አካባቢዎችም አሉ፡፡ በኢትዮጵያ እንጉዳይ የመመገብ ባህላችን ጠንካራ አይደለም፡፡ ሆኖም በቤንሻንጉል፣ በደቡብ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንጉዳይን ለምግብነት ይጠቀማሉ፡፡ መሃል አገር ያለው ደግሞ አጠቃቀሙ መጠነኛ ነው፡፡ እንጉዳይ የመብላት ባህላችን ብዙም ያልጠነከረ መሆኑ አንዱ ችግር ነው፡፡ በሌላ በኩል እንጉዳይ ውድ ነው፡፡ አምራቾቹም የሚያቀርቡት ለትላልቅ የገበያ ማዕከላት ነው፡፡ በትላልቅ የገበያ ማዕከላት በኪሎ ከ45 እስከ 60 ብር ይሸጣል፡፡ እናም ተጠቃሚዎቹና የሚገዙት ሰዎች ብዙዎቹ የውጭ ዜጐች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የእንጉዳይን ምግብነት በአገራችን ለማስለመድ የትምህርት ክፍላችሁ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ዳዊት፡-
እንጉዳይን የምግብ ባህላችን ለማድረግ ማስተዋወቅን የሚጠይቅ ነው፡፡ ስልጠና ባዘጋጀን ቁጥር ከእንጉዳይ ምግብ እየሰራን እናቀርባለን፡፡ ብዙዎች ከዚህ ቀደም እንጉዳይ ቀምሰው የማያውቁ ሰዎች ቀምሰውት ወደውታል፡፡ ከዚያ በኋላም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አንዳንድ ቦታ የተጠላበት ምክንያት መርዘኛ እንጉዳዮች ጫካ ውስጥ ስላሉ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሲለቅሙና ሲበሉ ተሳስተው መርዘኛውን ይለቅማሉ፡፡ መርዘኛውንና መርዘኛ ያልሆነውን ለመለየት ቀላል አይደለም፡፡ ስልጠና ያስፈልገዋል፡፡ የእንጉዳይ ጠቃሚነትና ምግብ አጣፋጭነቱ ላይ ግንዛቤ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲፈጠር እንጉዳይ የመመገብ ባህላችን እየጠነከረ ይሄዳል፡፡

ሪፖርተር፡- በጥናታችሁ መሠረት በመርዘኛውና መርዘኛ ባልሆነው እንጉዳይ መካከል በማየትም ሊሆን ይችላል መሠረታዊ ልዩነት ብላችሁ ያስቀመጣችሁት አለ?

ዶ/ር ዳዊት፡-
እንጉዳይን ለመለየት ትንሽ ያስቸግራል፡፡ በላቦራቶሪ በማይክሮስኮፕ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ማንኛውም ሰው መርዛማውን መርዛማ ካልሆነው መለየት የማይችለው፡፡

ሪፖርተር፡- መርዛማውን እንጉዳይ መርዛማ ካልሆነው በመለየቱና ግንዛቤ በማስጨበጡ የእናንተ ሚና ምንድን ይሆናል?

ዶ/ር ዳዊት፡-
በእኛ በኩል በኢትዮጵያ የሚገኙ እንጉዳዮችን እያጠናን በስዕል የተደገፈ መፅሃፍ በማዘጋጀት (ማኑዋል) መርዘኛና መርዘኛ ያልሆነውን ሕዝቡ በቀላሉ ሊለይበት የሚችለውን መንገድ ማሳየት እንዲሁም በየጊዜው እነዚህን መርዘኛ እንጉዳዮች አውቆ ሰው እንዳይጠቀመው በስልጠና እናሳውቃለን፡፡ የሚገኙበትንም ቦታ ጭምር ጠቅሰን በስልጠና ጭምር እናሳያለን ተጠቃሚው ራሱ እነዚህን እያወቀ ሲሰራ የመመረዙ እድል ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ በእኛ በኩል መሥራት ያለብን የኢትዮጵያን እንጉዳዮች የሚበሉና የማይበሉትን ለይቶ የሚያሳይ፤ በፎቶግራፍ የተደገፈ መፅሃፍ ያስፈልገናል፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት ይወጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአገራችን በመመረት ላይ ያሉት ከአራቱ የሚበሉ ዓይነት እንጉዳዮች ከመርዛማው ጋር ተቀላቅለው ቢመረቱስ?

ዶ/ር ዳዊት፡
- አሁን እየተመረቱ ካሉት ጋር መርዛማዎቹ በምንም ዓይነት ተቀላቅለው ሊመረቱ አይችሉም፡፡ አምራቾቹ የሚያመርቱዋቸው በሙሉ የሚበሉና የመርዘኛነት አደጋ ያለባቸው አይደሉም፡፡ መርዛማው የሚኖረው ጫካ ከሚበቅለው ተቀላቅሎ ነው፡፡ እዚህ የሚመረቱት መርዛማ ያልሆኑትና ዘራቸው የታወቀው ነው፡፡ ማንም አምራች የሚያመርተው ንፁህና የሚያሰጋ ነገር የሌለው ነው፡፡ በላቦራቶሪ የተመረተና መርዛማ ያለመሆኑ የተረጋገጠ ዘር ገዝተው ነው የሚያመርቱት፡፡

ሪፖርተር፡- የዘሩ አመራረት ላይ ቁጥጥር የሚያደርገው ማነው መርዛማው የመቀላቀል አጋጣሚን ለማስወገድ?

ዶ/ር ዳዊት፡-
የዘሩ አመራረት ቴክኖሎጂ አለው፡፡ በላቦራቶሪ ነው፡፡ እስካሁንም የእንጉዳይ አምራቾች ትልቁ ችግራቸው ዘር ማምረት ነው፡፡ ዘር ማምረቱ የላቦራቶሪ ፋሲሊቲ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ያንን ለማድረግ ወደፊት የምናስበው ነው፡፡ አሁንም የዘር አምራች ድርጅት እየተቋቋመ ነው፤ ይህንን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ለብቻውም ሊኖር ይገባል፡፡ በእኔ ስር የሚማር ተማሪም የዘር ማምረቻውን ጀምሯል፡፡ እንጉዳይ አምራቾች ዘሩን በጠርሙስ ነው የሚገዙት፡፡ ዘሩን መግዛት ከተቻለ እንጉዳይ ማምረት ለማንኛውም አምራች ከባድ አይደለም፡፡ ከባዱ ዘሩን ማምረት ሲሆን ትምርት፣ ልምድና ስልጠና ያስፈልገዋል፡፡ ወደፊት የሚፈለገው እያንዳንዱ እንጉዳይ አምራች የእንጉዳይ ዘርም የእንጉዳይ ምርትንም እንዲያመርት ሳይሆን ዘር እየገዛ እንዲያመርት ነው፡፡ የዘሩን አመራረት በተመለከተ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ ስልጠናም ተሰጥቷል፡፡ እኛም ትኩረት የምናደርገው ዘሩ ላይ ነው፡፡ በዘር አመራረቱም በሙከራ አራቱን ዓይነቶች በደንብ አውቀናል፡፡    

ሪፖርተር፡- በሳይንስ ፋኩልቲ በስነ ሕይወት ክፍል እራሱን የቻለ የእንጉዳይ አመራረት ኮርስ ይሰጣል?

ዶ/ር ዳዊት፡
- የተለየ ለብቻው ኮርስ ባንሰጥም ማይኮሎጂ የሚባል ኮርስ አለ፡፡ በዚህ ውስጥ የእንጉዳይ አመራረትን በተመለከተ ምዕራፍ አለው፡፡ በባዮሎጂ ዲፓርትመንት በማይክሮ ባዮሎጂ ክፍል ማስተርሳቸውን የሚሠሩ ተማሪዎች በሙሉ ሥለ እንጉዳይና የእንጉዳይ ዘር አመራረት ሰልጥነው ነው የሚወጡት፡፡

ሪፖርተር፡- እንጉዳይ ድርቅን የመቋቋም ሃይሉ እንዴት ነው?

ዶ/ር ዳዊት፡-
እንጉዳይ ድርቅ የመቋቋም ባህሪው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ እንጉዳይ በጣም እርጥበት ፈላጊ ነው፡፡ እርጥበቱ የሚያድግበት ቦታ ብቻ ሳይሆን የአየሩም ጭምር መሆን አለበት፡፡ እንጉዳይ ድርቅ ፈሪ ነው፡፡ ረዘም ያለ የዝናብ ጊዜ ያላቸው ቦታዎች ለእንጉዳይ ምርት ተስማሚ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አበባ በግሪን ሃውስ መመረት ይችላል?

ዶ/ር ዳዊት፡-
ቤቱ እንደግሪን ሃውስ፣ በዳስ ወይም በእንስራ ሊሆን ይችላል፡፡ በመስኖ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም እንጉዳይ መሬት ላይ ሳይሆን መደርደሪያ ላይ በሣጥን እየተሞላ ነው የሚመረተው፡፡የፀሃይ ብርሃን አይፈልግም፡፡ ጨለማም ሆነ ዋሻ ውስጥም ቢሆን ይበቅላል፡፡ ግሪን ሃውስ አሰራሩ እንደ አበባው ኢንዱስትሪ ሊሆን ቢችልም የአበቃቀልና የአዘራሩ ሁኔታ ግን ይለያያል፡፡

ሪፖርተር፡- እንጉዳይ በምን ያህል ጊዜ ይደርሳል?

ዶ/ር ዳዊት፡-
በተዘራ ከአንድ እስከ ሁለት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ይደርሳል፡፡ በክረምት ወቅትም እስከ ሶስት ጊዜ ሊደርስ ይችላል፡፡ እንጉዳይ በጋ ላይም የቤቱን እርጥበት ከፍ አድርጐ ዓመቱን ሙሉ በየሁለት ወሩ እየደረሰ ሊመረት ይችላል፡፡ ምንም ዓይነት እህል እንደ እንጉዳይ ባጭር ጊዜ ሊደርስ የሚችል የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የሚሰጠው ምርትስ?

ዶ/ር ዳዊት፡-
ሁኔታዎች ከተሟሉለት የሙቀቱና የእርጥበቱ መጠን እንዲሁም የሚያድግበት ሁኔታ ከተመቻቸለት የሚሰጠው ምርት አትራፊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በእንጉዳይ ምርምሩ የተሳተፉ ተቋማት አሉ?

ዶ/ር ዳዊት፡-
ጥናቱን የዛሬ 12 ዓመት ገደማ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ
ባዮሎጂ ዲፓርትመንት ገንዘቡን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሰጥቶን ነው የጀመርነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ሌሎቹ የመጡት፡፡ የሃረማያ ዩኒቨርሲቲም ጥናት ያካሂዳል፡፡ የግብርና ምርምርም መጠነኛ ምርምር ያካሂዳል፡፡ ውስንም ቢሆን የእንጉዳይ ምርምር እየተስፋፋ ነው፡፡ ግንዛቤውም በየተቋማቱ እየሰፋ ነው፡፡ ተቋማቱ ገንዘብ ቢያገኙ ምርምሩ እየሰፋ ይሄዳል፡፡

ሪፖርተር፡- በእናንተ በኩል ጥናት መደረጉ ብቻ በራሱ ህብረተሰቡ የእንጉዳይ ተጠቃሚ እንዲሆን አያስችልም፡፡ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር የሰራችሁት አለ?

ዶ/ር ዳዊት፡-
ኮንፍረንስ ከማካሄድ በስተቀር ከዚህ ቀደም ያደረግነው ነገር የለም፡፡ እንጉዳይ በዓለም በዓመት 45 ቢሊዮን ዶላር ነው ገበያው፡፡ የዓለም ገበያው ሰፊ ነው፡፡ እኛም በዚህ ገበያ ተጠቃሚ መሆን አለብን፡፡ ተጠቃሚ ለመሆን ለውጪ ገበያ መዘጋጀት አለብን፡፡ እዚህ ለመድረስ ደግሞ ጠንካራ አምራች ድርጅት መከፈት አለበት፡፡ የእንጉዳይ ገበያ በዓለም እያደገ ስለሆነ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት ኢትየጵያም ወደ ውጭ ልትልክ የምትችልበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፡፡ በኮንፍረንሱ ብዙ ድርጅቶች እንዲሳተፉ አድርገናል፡፡ ያነጋገሩንም ትልልቅ ድርጅቶች አሉ፡፡ ወደ እንጉዳይ ኢንቨስትመንት የሚገቡ ባለሃብቶች በቅርብ ጊዜ ይመጣሉ ብዬ በግሌ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የእንጉዳይ አመራረት በጥናት ተደግፎ መመረት መጀመሩ አዲስ ከመሆኑ አንፃር ባለሀብቱ በዘርፉ እንዲሳተፍ በእናንተ ደረጃ ምን እያደረጋችሁ ነው?

ዶ/ር ዳዊት፡-
ጥያቄው ከባለሀብቱ እንዲመጣ ነው የምንጠብቀው፡፡ ጥያቄው ከመጣ ስልጠናና ዘር መስጠት እንችላለን፤ እናማከራለንም፡፡ ከባለሃብቱ የሚመጣውን ጥያቄ ሁሉ እንመልሳለን፡፡ ያለንን እውቀትና ግኝታችንን ለማካፈል ዝግጁ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- እንጉዳይ ሊመረቱ በሚችሉባቸው አካባቢዎች ለገበሬው የእንጉዳይን ጠቀሜታ ለማስተዋወቅ ከመንግሥት ጋር ተነጋግራችኋል?

ዶ/ር ዳዊት፡-
ስራችንን ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ግብርናና ገጠር ልማት ሚንስቴር፣ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ያውቁታል፡፡ በግብርና ሚንስቴር በኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ አስገብቶ ገበሬው ተጠቃሚ የሚሆንበትን፤ ሥራ አጥ ልጆች በማደራጀት እንጉዳይ የሚያመርቱበትን መንገድ እንነድፋለን ተብሏል፡፡ በእኛ በዲፓርትመንት ደረጃ የኢትዮጵያን የዱር እንጉዳዮች የበለጠ ለማጥናት፣ የሕዝቡን እንጉዳይ የመብላት ባህሉን ለማወቅ፣ የእንጉዳይ ቴክኖሎጂን ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እያዘጋጀን ነው፡፡ በቅርቡ ለግብርና ሚኒስቴር የሚቀርብ ፕሮጀክትም እየሰራን ነው፡፡ ፍላጐቱ ሲመጣ የሚጠናከር ይሆናል፡፡ ከእኛው አገር እንጉዳዮች ወደ እርሻ ልንለውጣቸው የምንችለውን በመለየት ፕሮጀክቶች እየቀረፅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንጉዳይ ከተቆረጠ በኋላ ለረዥም ጊዜ ጠብቀን ማቆየት የምንችልበት ዘዴስ ታውቋል?

ዶ/ር ዳዊት፡-
ከሞላ ጐደል ታውቋል፡፡ አንዳንዱ እንጉዳይ ሲደርቅ የማይጣፍጥ አለ፡፡ አንዳንዱ እንደተቆረጠ ገበያ መቅረብ ወይም በቆርቆሮ መታሸግ አለበት፡፡ አንዳንዶቹን እንደ ቋንጣ ማድረቅና አሽጐ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ከገበያ የተረፈው ደርቆ ሊታሸግና ሊሸጥ ይችላል፡፡ ቀላሉ ዘዴ በፀሐይ ማድረቅ ነው፡፡ ገንዘብ ይፈጃል እንጂ በቆርቆሮ ማሸግ ይቻላል፡፡ በማቀዝቀዣ ውስጥ ለአንድ ሳምንት ከማቀዝቀዣ ውጭ ደግሞ ከ2 ቀን በላይ አይቆይም፡፡ በመሆኑም አምራቾች ለገበያው ቅርብ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ያሉት አምራቾችም በአዲስ አበባ ዙሪያ ናቸው፡፡ ከአራቱ ዓይነቶች ኦይስተርና ሽታኪ ሊደርቁ ይችላሉ፡፡ በተን እና ናሜኩ መታሸግ ነው ያለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የእንጉዳይ ምርት ቀጣይነትን ለማጠናከር ምርምሩ ይቀጥላል?

ዶ/ር ዳዊት፡-
በእኛ በኩል የእንጉዳይ ምርምር ይቀጥላል፡፡ አሁን ከሚመረቱት 30 ዓይነት እንጉዳዮች እኛ የቻልነው አራቱን ብቻ ነው፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ዘር እያመጣን ኢትዮጵያ በሚገኝ ጥሬ እቃ ላይ እንሞክራለን፡፡ እኛ ጋር አመራረቱ አዋጭ ሆኖ ከተገኘ እንዲቀጥል እናደርጋለን፡፡ በተቻለ መጠን ከ4ቱ በላይ የተለያዩ እንጉዳዮችን ማስፋፋት ነው የምንፈልገው፡፡ በቀላሉ ማምረት መቻልና በርካሽ ዋጋ ማቅረብ ከተቻለ ምርቱ ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንጉዳይ የተክል ምድቡ የት ነው?

ዶ/ር ዳዊት፡
- እንጉዳይ እንስሳም አይደለም ተክልም አይደለም፡፡ ፈንገስ ከሚባለው ይመደባል፡፡ በፆምም ሆነ በፍስክ ወቅት ይበላል፡፡ በምግብነት ይዘቱም በሁለቱ መካከል ያለ ነው፡፡ ሕዝቡ ከመርዘኛ እንጉዳዮች መጠንቀቅ አለበት፡፡ እንጉዳይ ይበላል ስለተባለ ብቻ ሕዝቡ አንስቶ እንዳይበላ እንፈራለን፡፡ በደንብ በባህሉ የዳበረ ማህበረሰብ ካልሆነ በስተቀር በማይታወቅ አካባቢ ሕዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡
 
< Prev   Next >