| ሰንደቅ ዓላማችን |
|
|
| Wednesday, 02 July 2008 | |
![]() በሔኖክ ያሬድ"በባንዲራ"" በባንዲራ"" በባንዲራችን"" በሕግ ቁም ብዬሃለሁ!!" ትለዋለች፤ እየተከተለች፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ፣ ወደ ቀጨኔ መድኃኔዓለም በሚወስደው መንገድ፣ ድልድዩ አጠገብ፣ ከአባ ሀብቴ ቤት አጠገብ ነው፡፡ ሴትየዋ ጠላ ሻጭ ናት፡፡ ሰውዬው እግረ መንገዱን ሲያልፍ ጠላ ሊጠጣ ይገባና ሳይከፍል ይወጣል፡፡ እሷ እንዳለችው ሁለት "ምኒልክ" ነው የጠጣው፡፡ ("ምኒልክ" የጠላ መጠጫ ዋንጫ ነው) እሱ ደግሞ "የለም አንድ ብቻ ነው" ይላል፡፡ የጎረቤት ሰው ጠርቷት ወጣ ብላ ተነጋግራ እስክትመጣ ድረስ ሰውዬው ከእንስራው ውስጥ ቀድቶ ሁለተኛውን "ምኒልክ" እሷ ሳታየው ጠጥቷል፡፡ እሷ ግን ሁለተኛ መጠጣቱን ደርሳበታለች፡፡ ሲወጣ የአንድ ምኒልክ ሒሳብ ከፍሎ ይወጣል፡፡ ጎረምሳ፣ ሰውነቱ ዘለግ ያለ ነበር፡፡ ሴትዮዋ ደግሞ ቀጭን፣ ኮሳሳ ድሀ ነች፡፡ ጥንካሬዋ ግን ባንዲራ ነበር፡፡ "በባንዲራ"" ወድቃ በተነሳችው""" ብላ በጮኸች ቁጥር ኩራትና ጥንካሬ ይሰማታል፡፡ በሌላ በኩል እየተከተለች "በባንዲራ"" ባለችው ቁጥር ሰውዬው እያነሰ፣ እየኮሰሰ ሄደ፡፡ መንገደኛው ሁሉ "ምንድነው ይህ ሰውዬ? በባንዲራ ሲባል አይሰማም እንዴ?" እያለ ሰውየውን ትኩር ብሎ ያየው ጀመር፡፡ ሰውዬው ግራ ገባው "ይህች ኮሳሳ ደሃ እንዲህ ታዋርደኝ?" ይላል በልቡ፡፡ የወንድነት ወኔው፣ የጎረምሳ ኩራቱ እያሸነፈው ለመቆም በጣም አመነታ፡፡ ዝም ብሎ ቢሄድ የሚያስከትለውን ነገር ባለማወቁ መሀል መንገድ ላይ ቀጥ ብሎ ቆሞ ከኪሱ ስሙኒ ፈልጐ ወረወረላትና መንገዱን ቀጠለ፡፡ ባንዲራዋ አሸነፈች፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ወይም ባንዲራ ሲነሳ፣ ሲወሳ ከተመዘገቡት ትዝታዎችና ገጠመኞች አንዱ ከላይ የተጠቀሰው በዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ መጽሐፍ የሰፈረው ነው፡፡ የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2000 ዓ.ም በሀገር ደረጃ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ዝክረ ሰንደቅ ዓላማን እንዘልቅበታለን፡፡ ሀ) የቃሉ መነሻ ደስታ ተክለወልድ ሰንደቅ ዓላማ በሰንደቅ ላይ የተሰቀለ የተንጠለጠለ ባለ አረንጓዴና ብጫ፣ ቀይ ቀለም፣ የመንግሥት ምልክት ባንዲራ በመካከሉ ጽሑፍና ያንበሳ ሥዕል ከዘውድ ጋራ ይታይበታል፤ አንበሳውም ሰንደቅ ዓላማ ይዟል፡፡ ሰንደቅ ዘንጉ መቋሚያው ከነእንክብሉ፤ ዓላማ ሐሩ፡፡ እርግጠኛው አጻጻፍ ግን (ዓላማ ሰንደቅ) የሰንደቅ ዓላማ ነው ይላሉ፡፡ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ በታሪክ ቅርንጫፍ ስለ ሰንደቅ ሲገልጹ በድባብና ጥላ ላይ በጫፉ የሚደረገው ትንሽ የመስቀል ምልክት ያለው እንደጉልላት የመሰለ ነገር ነው፡፡ በሳር የተከደነው ቤት በመፈጸሚያው ላይ ያለው ቁንጮውን በትግርኛ ሰንደቅ ይባላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ብዙ ልጆች ከወለዱ በኋላ በመጨረሻ ለሚወለደው ልጅ ሰንደቅ ብለው ስም ያወጡለታል፡፡ መጨረሻ ወይም መደምደሚያ ማለታቸው መሆኑ ነው፡፡ እንደ ከበደ ሚካኤል አገላለጽ ሰንደቅ ዓላማ የነጻነት ምልክት፣ የአንድ ሕዝብ ማተብ የኅብረት ማሰሪያ ጥብቅ ሐረግ ነው፡፡ "ተመልከት ዓላማህን፤ ተከተል አለቃህን፡፡" ነጋሪቱ እየተጐሰመ፣ ሠራዊቱ እየተመመ ሲሄድ ሰንደቅ ዓላማ ትእምርተ ኀይል፣ ትእምርተ መዊዕ ነው፡፡ ሁ) የሰንደቅ ዓላማ (ባንዴራ) አጀማመር በሦስቱ ቀለማት የተመሰለችው ሰንደቅ ዓላማችን ከጥንት ጀምሮ የነበረች ለመሆኑ የሚጠቀሱ የታሪክ ምስክሮች አሉ፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በኖረው ትውፊት ከ3519 ዓመት በፊት አፄ ሰንደቅ ዓላማ የሚባል ንጉሥ መንገሡና የአገር መለያ የሆነውን ዓላማ በርሱ ዘመን መመሥረቱን በመጽሐፈ ሱባኤ ተመልክቷል፡፡ "እኔም ዛሬ በሕያው አምላኬ ፈቃድ በአባቶቼ ዙፋን በረገጡዋት ምድር በአረፉበት መሬት በቀመሱትና በተጠመቁበት ውሃ ድንበር ሆኜ ይህን ለዘለዓለም የሚሆን በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን የፍቅር ምልክት ዓላማ በከፍታ ቦታ ላይ ሰቅዬ አውለበልብላችኋለሁ፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ሰማያዊ ቀለም መሆኑ፤ አረንጓዴ ምድራዊ፣ ብጫው የፍቅር አበባ፣ ሰማያዊው የሰማያውያን መንፈሳዊ አካል እንዳለን የመግለጽ ምልክት ነው፡፡" ዛሬ በአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ከሚገኘው ሌላ ከ1660 እስከ 1674 በነበረው ዘመን የማዕከላዊ መንግሥት መዲና ጎንደር በነበረበት ወቅት የነገሡት አዕላፍ ሰገድ ዮሐንስ በጎጃም ውስጥ ለምትገኘው ደብረ ወርቅ ማርያም ለመታሰቢያ በሰጡዋቸው ሁለት ሰንደቅ ዓላማዎች ቅርፃቸው፣ ይዘታቸው የቀለማቸው ዓይነትና አቀማመጥ ይኸው ዛሬ ያለው ሰንደቅ ዓላማ ዓይነት እንደሆነ የሚረጋገጥ ለመሆኑ በ1939 በወጣውና ፣ሰላማዊ ሰልፍና ውስጣዊ አሰራር፣ በሚለው ሰነድና በንጉሠ ዜና መዋዕል ላይ ተዘግቦ ይገኛል፡፡ የሰንደቅ ዓላማን መነሻ በተመለከተ ዘመንፈስ ቅዱስ እንደጻፉት የኢትዮጵያን መሬት በመጀመርያ የያዙና ያቀኑ ኩሳውያን ወይም አግዓዝያን የተባሉት አባቶቻችን ስለ ሃገሩ ለምለምነት ሲሉ አረንጓዴውን ቀለም ብቻ ዓላማቸው አድርገው ከክርስቶስ ልደት በፊት ቀዳማዊ ምኒልክ እስከ ነገሠበት ድረስ ይዘውት ሲኖሩ፣ ከምኒልክ በኋላ የኦሪት ሃይማኖት ከተቀበለ በኋላ ሊቃውንቱና መሳፍንቱ መክረው ከቅጠል በኋላ የፍሬ ተስፋ አበባ ይገባዋል ብለው በአረንጓዴው ላይ ብጫ ምልክት ቀጥለውበት እስከ አፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግሥት ድረስ በሁለቱ ቀለማት ቆይተዋል፡፡ አፄ ገብረመስቀል በ515 ዓ.ም ነግሠው የክርስትና ሃይማኖት በኢትዮጵያ ከተዘረጋ በኋላ የዓለም መድኃኒትና ፍሬ የተገኘው በክርስቶስ ደም ብቻ ነው ብለው ሦስተኛውን ቀለም ቀይ ምልክት ጨመሩበት ይባላል፡፡ በ1936 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የወጣው የኢትዮጵያ ገንዘብ ኖት፣ በ1992 ዓ.ም የቀለማት ቅደም ተከተሉ እስከተለወጠበት ድረስ የሰንደቅ ዓላማውን ታሪክና ምሳሌነት የያዘ ነበር፡፡ አንደኛነትን ለባለ አንድ ብር አረንጓዴ ኅብር የመሠረት ምሳሌ፣ ሁለተኛነትን ለባለ አምስት ብር ብጫ ኅብር የሕንፃ ምሳሌ፣ ሦስተኛነትን ለባለ አስር ብር ቀይ ኅብር የጠፈር ምሳሌ አቅፏል፡፡ በአክሱም ያለው ጥንታዊው ዓላማ አረንጓዴው በታች ቀዩ ግን በላይ ሆኖ ሦስቱም ቀለማት ሁሉ ለእያንዳንዱ ጫፍ የሾለ ማለት ሦስት ጦር የሚመስል ሆኖ የተሰፋ መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይ በ1897 ዓ.ም የቀለማቱ ድርድር አረንጓዴው ከላይ ቀዩ ከታች ሆኖ ከተሰደረበት ወዲህ ላለፉት 103 ዓመታት መደበኛ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ዓርማን በተመለከተ ዘመንፈስ ቅዱስ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፤ "በብጫው (መካከለኛ) ላይ በአንድ ወገኑ በወርቅ የተጠለፈ አንበሳ አለው፡፡ ከባለታሪኮች አፍ ረበአፈ ታሪክሪ እንደሰማሁትም በሌላኛው ወገኑ ደግሞ በወርቅ የተጠለፈ ፈረስ ነበረው ይባላል፡፡ ይህም የሚያመለክተው የጥንታውያኑ ነገሥታት ዋናው ኃይላቸው በፈረስ ብዛትና በፈረሰኛ ኃይል ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል አድርገው እንደ አንበሳ ይፈሩ እንደነበሩ የሚያስረዳ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ነገሥታት ማኅተማቸውን ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ (አሸናፊው የይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ) እያሉ ኖረዋል፡፡ የኅብረ ቀለማቱ አቀማመጥ በየጊዜው ቢለዋወጥም በአፄ ዮሐንስ አራተኛ ዘመን መደበኛ የነበረው ከላይ ቀይ ከሥር አረንጓዴ እንደነበረና በዶጋሊ ጦርነት በራስ አሉላ አዝማችነት በጣሊያን ላይ በተቀዳጁት ድል ሲውለበለብ የነበረው ሰንደቅ ዓላማ እርሱ መሆኑ ይነገራል፡፡ የአፄ ዮሐንስ ሰንደቅ ዓላማ በጎንደር ሲገኝ መስቀያው ሰማያዊ በዓላማውም ላይ "የይሁዳ አንበሳ" የሚለው የአንበሳ ሥዕል በቀኝ መዳፉ ሰንደቅ ዓላማውን ከነመስቀላዊ ምልክትነቱ እንደተሸከመ ተጠልፎበታል፡፡ በ1884 ዓ.ም ሶለይለት የተባለ መልእክተኛ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በተደረገለት ስጦታና ሽልማት በቀይ በነጭ በቢጫና በአረንጓዴ ኅብረ ቀለማት ላይ የተጠለፈ ኮከብ ጥብጣብ እንደቀረበለት ጠቅሷል፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ የቀጣዩ መባቻ አካባቢ በባቡር ኢትዮጵያ ገብቶ የነበረው ጆኒንግስ በጻፈው ማስታወሻ ላይ "ከዘጠነኛው ኪሎ ሜትር አቅራቢያ በሚገኝ ቋጥኛማ ኮረብታ ላይ ቀይ፣ ቢጫ እና አረንጓዴ ኅብረ ቀለም ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሰላምታውን አቀረበልን"". ብሎ ጥቅምት 29 ቀን 1903 ዓ.ም መጻፉን ማሞ ውድነህ በአንድ ጥናታቸው ገልጸውታል፡፡ የሰንደቅ ዓላማው ኅብረ ቀለማት ትእምርት በተመለከተ በታሪክና ምሳሌ እንደተጻፈው "ሰንደቅ ዓላማችን" ምሳሌያቸው አረንጓዴው ተስፋ ልምላሜና ሀብት፤ ብጫው ሃይማኖት አበባና ፍሬ፣ ቀዩ ፍቅር መሥዋዕትነትና ጀግንነት ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ታሪካዊ አመጣጥና ትርጓሜ በርካታ ጸሐፊዎች ቢጽፉም ሰፋ ያለ ትንተና የሰጡት የአፄ ምኒልክ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት ፓሻ ኃይለማርያም ሰራቢዮን ናቸው፡፡ በ1898 ዓ.ም "የኢትዮጵያ ትእምርተ መንግሥት" በሚል ርእስ "ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚናገር" በሚለው ምዕራፍ በገጽ 18 ላይ እንደሚከተለው ጽፈዋል፡፡ "ሰንደቅ ዓላማ ማለት የንጉሥና የሕዝብ ምልክት ነው፡፡ የዓለም ነገሥታትና ሕዝብ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ የወዴት አገር ንጉሥ ነው? ይህ የወዴት አገር ሕዝብ ነው እንዳይባል ልዩ ልዩ ሰንደቅ ዓላማ ያሲዛሉ፡፡ በበዓል ቀንም በየደጃቸው ይሰቅላሉ፡፡ ይህንም ያየ ሰው ሁሉ የእገሌ አገር ንጉሥ ነው፡፡ ይህ የእገሌ አገር ሕዝብ ነው ብሎ በሰንደቅ ዓላማው ያውቀዋል፡፡ ሰንደቅ ዓላማውም እጅግ ይከበራል፡፡ ሲሰቀልና ሲወርድም በዜማና በሰላምታ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማውን ያየ ሰው ሁሉ ቆቡን፣ ባርኔጣውን ያወርዳል፡፡ አለቆችም ሰይፍ ይመዛሉ፡፡ በሰልፍና በጦርነት በጸሎትና በፍሥሐ ቀንም ያለሰንደቅ ዓላማ አይሆንም፡፡ የክብር ሁሉ መሠረት ነውና፡፡ በጦርነት ጊዜም ንጉሡ ራሱ ሰንደቅ ዓላማውን በእጁ ይዞ ለጦር አበጋዙ አደራ ይሰጠዋል፡፡ እንዲህ ሲል በርታ አደራህን ሰንደቅ ዓላማችን በጠላት እጅ እንዳይገባ፡፡ እኛና ሕዝባችን እንዳንዋረድ፣ ክብራችን እንዳይጠፋ የጠላት መሳለቂያ እንዳንሆን አደራህን ይለዋል፡፡" በሰንደቅ ዓላማው ላይ እንደ አገሪቱ መንግሥታት ባሕርይ ዓርማዎች ሲጠለፉበት ኖሯል፡፡ በዘውዳዊው ሥርዓት የአንበሳ ምልክት፣ በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና በኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥታት የየራሳቸው ዓርማዎች ነበሯቸው፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዓርማ ባለ አምስት ኮከብ ሰማያዊ ቀለም ከዓላማው ጋር ተቀናጅቶ አካሉ ሆኗል፡፡ ለሰንደቅ ዓላማ አጀማመርና መሠረት የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በሥላሴ በመሰለችው ሦስቱ ኅብረቀለማት ላይ "ነዋ ወንጌለ መንግሥት" (እነሆ የመንግሥት ወንጌል) የሚል ሐረግና የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓርማ የተጠለፈበት ሰንደቅ ዓላማም አላት፡፡ ሂ) የሕዝብ መዝሙር ከሰንደቅ ዓላማ ክብር ጋር አብሮ ተያይዞ የሚገኘው የሕዝብ መዝሙር (ብሔራዊ መዝሙር) እና የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ መዝሙር ያገኘችው በ20ኛው ምእት ዓመት ሲሆን በሦስት ሥርዓቶች ሦስት የተለያዩ መዝሙሮችን አስተናግዳለች፡፡ የመጀመሪያው "ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ" በሚል መነሻ የሚዘልቀው በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ግጥም ደራሲነት፣ በነርሲስ ናልባንዲያን ዜማ ደራሲነት የተቀናበረው ነው፡፡ እስከ 1967 ዓ.ም መድረስ እንዲህ ተዘምሯል፡፡ "ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ ባምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ ተባብረዋል አርበኞችሽ አይነካም ከቶ ነፃነትሽ ብርቱ ናቸውና ተራሮችሽ አትነኪም በጠላቶችሽ ድል አድራጊው ንጉሣችን ይኑርልን ለክብራችን፡፡" ዘውዳዊው ሥርዓት ካከተመ በኋላ በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መንግሥት በ1968 ዓ.ም መስከረም መባቻ በአሰፋ ገብረማርያም ተሰማ ደራሲነት፣ በዳንኤል ዮሐንስ ዜማ ደራሲነት አዲስ መዝሙር ቀርቦ እስከ 1983 ዓ.ም. ቆይቷል፡፡ "ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ - ኢትዮጵያ ቅደሚ በኅብረሰባዊነት - አብቢ ለምልሚ ቃልኪዳን ገብተዋል - ጀግኖች ልጆችሽ ወንዞች ተራሮችሽ - ድንግል መሬትሽ ለኢትዮጵያ አንድነት - ለነፃነትሽ መስዋእት ሊሆኑ - ለክብር ለዝናሽ ተራመጅ ወደፊት - በጥበብ ጎዳና ታጠቂ ለሥራ - ላገር ብልጽግና የጀግኖች እናትነሽ - በልጆችሽ ኩሪ ጠላቶችሽ ይጥፉ - ለዘላለም ኑሪ" በ1984 ዓ.ም ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ አዲሱን ሥርዓት የሚያንፀባርቅ አዲስ የሕዝብ መዝሙር በደረጀ መላኩ ገጣሚነት፣ በሰሎሞን ሉሉ ዜማ ደራሲነት ወጣ፡፡ እስካሁን እየተሠራበት ይገኛል፡፡ "የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ጸንቶ ታየ ሕዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ ለሰላም ለፍትሕ ለሕዝቦች ነፃነት በእኩልነት በፍቅር ቆመናል ባንድነት መሠረተ ጽኑዕ ሰብዕናን ያልሻርን ሕዝቦች ነን ለሥራ በሥራ የኖርን ድንቅ የባህል መድረክ፣ የአኩሪ ቅርስ ባለቤት የተፈጥሮ ጸጋ የጀግና ሕዝብ እናት እንጠብቅሻለን አለብን አደራ ኢትዮጵያችን ኑሪ እኛም ባንቺ እንኩራ" ሃ) የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ሰንደቅ ዓላማው የአከባበር ሥርዓት አለው፡፡ በመንግስት ተቋማት በወታደራዊ ክፍሎችና በትምህርት ቤቶች የመስቀልና የማውረድ ሥርዓቱ ለየት ያለ ነው፡፡ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ሥርዓቱ ከሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ጋር የተጣመረ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣና ሲወርድ የክብር ሰላምታውን የደረሱት ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ሲሆኑ ዜማውን ያወጡት አቶ እሸቴ መኰንን ናቸው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣ (ሲሰቀል) "ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ በአርበኝነት ታጥቆ ጠላት ያስወገደ ንጉሡን አገሩን ክብሩን የወደደ ነጻነቱን ይዞ መልካም ተራመደ ሰንደቅ ዓላማችን ክብራችን ውዲቱ ያኮራሻል ንጉሠ ነገሥቱ፡፡" ሰንደቅ ዓላማ ሲወርድ ደግሞ የሚከተለው ይዘመር ነበር፡፡ "ተጣማጅ አርበኛ ባገር መውደድ ቀንበር ገዳይ ድል አድራጊ ደም አፍሳሽ ወታደር አንቺን እያሰበ ይጓዛል ሲፎክር ሰንደቅ ዓላማችን የነጻነት አገር ገናናው ክብራችን ሰንደቅ ዓላማችን ያኮራሻል አርበኝነታችን፡፡" የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ከዘመነ ደርግ ወዲህ ኅልው ሆኖ አልቀጠለም፡፡ የሁለተኛው ብሔራዊ መዝሙር ደራሲ አሰፋ ገብረማርያም ለሰንደቅ ዓላማው ማውጪያና ማውረጃ ግጥም ቢደርሱም ሶሻሊስት አገሮች የባንዲራ መዝሙር የላቸውም በሚል ፈሊጥ ሥርዓት ሳይበጅለት ቀርቷል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በየትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የሰንደቅ ዓላማ መዝሙሮችን ብቻ ሳይሆን "ውዳሴ ዓላማ" የሆኑ ዝማሬዎችን ያቀርቡ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ድልድዩን መቀጠል እንደሚገባ ይታመንበታል፡፡ ያኔ እንዲህ እያሉ ይዘምሩ ነበር፡፡ "ይህች ሰንደቅ ዓላማ ያገራችን ቤዛ ተነሥታ ብትቆም እሱን ተመርኩዛ ሕዝቡንም ደስ አለው አገኘ ሰላም፣ ከእዚህ የበለጠ ምን አለ ዓለም፡፡" ዓላማ ማለት ዘወትር ትክ አድርገው በፍቅር ስሜት ሊመለከቱት የሚገባ የነጻነት ዋስና ሕይወት ወይም የአንድ ኅብረታዊ መንግሥትና ሕዝብ መለዮው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ከዳዊት መጽሐፍ እንዲህ ተገልጿል፡፡ በዘመነ ደርግ ፈረንሣይ ውስጥ ስደት የነበረች ኢትዮጵያዊት "ኢትዮጵያ ኤምባሲ መግባት አልችልም እዚህ አገር ስደተኛ ነኝ፣ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ፊት ለፊቴ ነች፡፡ በሳምንት አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ኤምባሲ በራፍ ላይ ቆሜ ትልቁን የኢትዮጵያ ባንዲራ ለጥቂት ደቂቃዎች አይቼ አልቅሼ ጸሎቴንና ምኞቴን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አድርሼ እመለሳለሁ፡፡ ባንዲራችንን ሳይ ጥንካሬ፣ ተስፋና እምነት አገኛለሁ፡፡ ከሀገር ብታስወጡኝም እናንተ የማታውቁት ይህንን እምነቴን፣ ጥንካሬዬን ተስፋዬን ፍቅሬን አለመውሰዳችሁን ነው" ብላለች፡፡ በ1960ዎቹ መጨረሻ ለደራሲው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |