| የኢትዮጵያ የመንግሥታት ስርዓት ምሁራንን አከራከ |
|
|
| Wednesday, 16 January 2008 | |
|
ፕ/ር ኤፍሬም ውጭ የተማሩ ኢትዮጵያንን አምርረው ወቀሱ ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን፣ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ፣ ፕ/ር እንድርያስ እሸቴና እንዲሁም ፕ/ር አሉላ ሪቻርድ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ስርዓት፣ ባህልና የወደፊት ዕድል አስመልክተው ከባድ ክርክር አደረጉ፡፡ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ የውጭ ምሁር ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ላይ ባላቸው ግንዛቤ ላይ ወቅሰዋል፡፡ ትናንትና በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ ማዕከል "ኮንፈረንስ ኦን ፎስተሪንግ ሸርድ ኮር ናሽናል ቫልዩስ፣ ኤክስፓንዲንግ ኮመን ፖለቲካል ስፔስ ኢን ዘኒው ኢትዮጵያን ሚሌኒየም" በሚል አጀንዳ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ የቀረቡ የጥናት ጽሁፎች ተወያይ ምሁራንን አወዛግበዋል፡፡ የመጀመሪያ የጥናት ጽሁፍ አቅራቢ ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን ሲሆኑ "ዘ ፕሮሚስ ኦፍ ኢትዮጵያ፤ ፐብሊክ አክሽን፣ ሲቪል ፎርጊቨንስ፣ ክሬቲቭ ፓወር" በሚል ርዕስ ነው፡፡ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ በበኩላቸው "ዘ ቻሌንጅ ኦፍ ዘ ኒው ሚሌኒየም፤ ሪነሰንስ ኦር ሪፕሬዛል" በሚል ርዕስ ለተሳታፊዎች የጥናት ጽሁፋቸውን አቅርበዋል፡፡ በእነዚህ የጥናት ጽሁፎች ላይ ሁለት ተወያይ ምሁራን የትችት ሃሳብ ሰጥተውበታል፡፡ የመጀመሪያው ተወያይ ምሁር ፕ/ር አሉላ ፓንክረስት ሲሆን በሁለቱም የጥናት ጽሁፎች ላይ የማጠናከሪያ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ሌላ ተወያይ ምሁር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕ/ር እንድርያስ እሸቴ ሲሆኑ በሁለቱም የጥናት ጽሁፎች የቀረቡ አንዳንድ ሃሳቦች ላይ ትችት ሰጥተዋል፡፡ ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን ኢትዮጵያ በመዋሃድ ሂደት ላይ እያለች በ1960ዎቹ በተፈጠሩ የግራ ዘመም አቀንቃኝ ፖለቲከኞች የተጀመረው ተቃውሞ የኢህአዴግ የብሄር ፌደራሊዝም እያፈረሰው እንደሆነ በመግለጽ፣ እስካሁን ከ15 እስከ 20 በመቶ ኢትዮጵያውያን መዋሃዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሃሳብ በፕ/ር እንድርያስ እሸቴ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን በመጀመሪያ በመቶኛ ተዋህደዋል የተባለ የህዝብ ቁጥር ጥያቄ ውስጥ አስገብተውታል፡፡ በማከልም ኢትዮጵያውያነት የእያንዳንዱ ብሄረሰብ ማንነት በማጥፋት መፈጠር እንደሌለበትና በመከባበርና በመፈቃቀድ የእያንዳንዱ ማንነትን በጠበቀ መልኩ እንዲገነባ በማሳሰብ ፕ/ር ሌቬን ያስቀመጡት ሂደት ነቅፈዋል፡፡ በተመሳሳይ ፕ/ር እንድርያስ እሸቴ ይቅር መባባልና የህዝብን ሃሳብ ማክበር የሚለው ሃሳብ ከፕ/ር ሌቪን የሚስማሙ ቢሆንም ይህ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን አሜሪካ በኢራቅ ያደረገችው ወረራና በጓንታናሞ ያለው ኢሰብዓዊ አያያዝ ለምን አታሻሽልም? በማለት የአገራቸው የአሜሪካ መንግስት ዴሞክራሲያዊነት ተጠራጥረዋል፡፡ ፕ/ር እንድርያስ እሸቴ በፕ/ር ባህሩ ዘውዴ የጥናት ጽሁፍም ተችተዋል፡፡ በተለይ የመሬት ባለቤትነት፣ በፕሬስ ነፃነትና በብሄርተኝነት ጉዳይ ላይ ያቀረቡት ሀሳብ ተቃውመዋል፡፡ የመሬት ፍፁም ባለቤትነት ለገበሬ መስጠቱ የሚያስከትለው አደጋ የኬንያና የታንዛኒያ ተሞክሮዎች አካፍለዋል፡፡ እነዚህን ሃሳቦች የተቃወሙ ፕ/ር እንድርያስ በመቻቻል ፖለቲካ፣ በራስ መተማመን፣ በራስ መግለጽ የመሳሰሉ ማንነቶች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ በምሁራኑ መካከል ክርክሩ ለረዥም ጊዜ የቆየ ሲሆን በመጨረሻም ሳይስማሙ ቀርተዋል፡፡ ከውይይት ተሳታፊዎችም ጥያቄና አስተያየት ቀርቧል፡፡ የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በፕ/ር ሌቬን ላይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በይቅር መባባል ውስጥ ከልብ "ጥፋትን ማመን" ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግስትም በመርህና በተግባር እኩል መሆኑን በመጠየቅ ራስ በራስ የመተዳደር አንድ የዴሞክራሲ መገለጫ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አምባሳደር ሙሉጌታ ኢተፋ በበኩላቸው ፕ/ር ዶናልድ የስብጥር ማንነት (ኮሌክቲቭ አይደንቲቲ) ለመፍጠር የብሄር ማንነትን (ኢትኒክ አይደንቲቲ) ለማጥፋት ማሰብ አምርረው ተቃውመዋል፡፡ የአንቀጽ 39 በህገ መንግስቱ መኖሩ አለመኖሩ ለመበታተን ምክንያት አይሆንም ብለዋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ልዩነትን ተቀብለን ተከባብረን መኖሩ ነው ብለዋል፡፡ ..በኢትዮጵያ ትንሳኤ.. ላይ ንግግር ያደረጉ ፕ/ር ኤፍሬም ኢሳቅ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ላይ የጨለምተኝነት ተስፋ የሚያስቡ የኢትዮጵያ የውጭ ምሁራን ላይ ወቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ልዩ የሆነ የራስዋ የዴሞክራሲ ባህልና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ መኖሩን በማስገንዘብ ይህንን ሳያውቁ ኢትዮጵያን ገና የዴሞክራሲ ጀማሪ አድርገው የሚጽፉና የሚያስቡ ወገኖች ወደ ገጠር የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሄደው ትክክለኛ እውነታውን እንዲያውቁ አሳስበዋል፡፡ የኦሮሞው የጋዳ ስርዓት፣ የትግራዩ የ..ባይቶ.. ስርዓት የመሳሰሉ ዴሞክራሲያዊ አገር በቀል አሰራሮች ጠቅሰዋል፡፡ "ኢትዮጵያ በቁስ አካል ድሃ ብትሆንም በደምና አጥንት የተገነባ ባህልና ታሪክ አላት" ያሉት ፕ/ር ኤፍሬም፣ በኢትዮጵያ የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸው በተለይ (በምዕራብ) በውጭ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ምሁርን የሚጽፉትና የሚናገሩትን ወቅሰዋል፡፡ ምሁሩ የኢትዮጵያ የወደፊት መሪዎች እንሆናለን የሚሉት ወጣቶች፣ ለኢትዮጵያው ለውጥ የሚመኙ ምሁራንና ፖለቲከኞች እጅ ለእጅ ተያይዘው አገሪቱን ካለችበት እንዲያነሱ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ "ኢትዮጵያ የእውነት፣ የፍትህ፣ የሰብዓዊነትና የርህሩህነት አገር ናት፡፡ ዓለምም ይህንን ይወቅ" በማለት ተሳታፊዎቹን የሚያስፈነድቅ ንግግር አድርገዋል፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |