Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow የኢትዮጵያ የመሬት ይዞታና...
የኢትዮጵያ የመሬት ይዞታና... Print E-mail
Sunday, 06 July 2008
የኢትዮጵያ የመሬት ይዞታና የልማት ኋላ ቀርነት
ከፊታውራሪ አመዴ ለማ

የአንድ ሀገር መንግሥት መንግሥት ነው ሊባል የሚችለው አራት ነገሮችን አሟልቶ ሲገኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ በአንድ ሀገር ላይ የሰፈረ ሕዝብ መኖር አለበት፡፡ ያለ ሕዝብ አገር ወይም መንግሥት ብቻውን መኖር አይችልም፡፡ ሁለተኛው የዚያ መንግሥት ወይም ሀገር በድንበር የተከለለ መሬት ነው፡፡ ያ መሬት ደግሞ ለእያንዳንዱ ዜጋ ከፈጣሪ የታደለው ጢንጦ ሃብቱ ነው፡፡ ጢንጦ ማለት የአንድ ግለሰብ የራሱ የሆነ ድርሻ ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው ሕዝቡ መንግሥት ነህ ብሎ ያስቀመጠው የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር ነው፡፡ ይህ የመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር የሕዝቡን ሰላም፣ ደህንነት፣ መብትና ፍላጎት እንዲጠብቅ የተቀመጠና የአስተዳደር ተግባራትን የሚያከናውን አካል ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ ምን ጊዜም ሊደፈር የማይገባው አንድ ሀገር ሉአላዊነት መከበር ነው፡፡
እንግዲህ መሬት ለሰው ልጅ ከፈጣሪው የተሰጠችው ጢንጦ ሃብቱ ናት፡፡ ይህችን የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ጢንጦ ማንም ተነስቶ እንደፈለገው ሊያደርጋትና ሊያዝባት አይችልም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በጢንጦው ላይ የግል ባለሃብትነት መብት ሊኖረው ይገባል፡፡

ኢትዮጵያውያን አያት ቅድመ አያቶቻችን ህይወታቸውን ሰውተው፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ በጢንጦ ያገኙዋትን ሀገር ዳር ድንበሯን ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ እያስተላለፉልን እዚህ ደርሰናል፡፡ አያት ቅድመ አያቶቻችን ይሄንን ሁሉ መሥዋዕትነት የከፈሉት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ሲሉ ነው፡፡

እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ የነበረው የመሬት ሥሪት ጥቂቶቹን ጠቅሞ፣ ብዙሃኑን ጎድቶ፣ የቆየ የመሬት ሥሪት ነበር፡፡ የገባር መሬት፣ የርስት መሬት፣ የሰሞን መሬት፣ የወቅፍ መሬት፣ አየተባለ የተለያዩ ስሞች ተሰጥተውት በአራሹ ገበሬና በመሬት ባለሃብቱ መካከል የበዝባዥና የተበዝባዥን ሥርዓት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ በዘመኑ ወታደሩም ቢሆን የሚተዳደረው በመሬት ነበር እንጂ በደመወዝ አልነበረም፡፡ ይህ አይነቱን የተዛባ ሥርዓት ለመገርሰስ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተጀመረው የመሬት ላራሹ መፈክር በሌሎችም ትምህርት ቤቶች እየተስፋፋ ሄደና መፈክሩ የአብዛኛው ምሁር ጥያቄ እየሆነ መጣ፡፡

የመሬት ላራሹን ጥያቄ ተከትሎ የውሎ ድርቅና ረሃብ ተከሰተ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ከስልጣን ሲወርዱ ደርግም የኢትዮጵያውያንን በተለይም የምሁሩን ትግል አፍኖ በሶሺያሊዝም ስም ከስልጣን ወንበር ላይ ፊጢጥ አለ፡፡ መሬት ላራሹ ሲባል የቆየውን የምሁራንንና የሰፊውን ሕዝብ መፈክር በተግባር ላይ አውላለሁ፣ የሶሻሊዝምን ፍልስፍና በተግባር እተረጉማለሁ አለና እያንዳንዱ ገበሬ እስከ አሥር ሄክታር ድረስ የሚደርስ መሬት እንዲያገኝ ይደረጋል የሚል ተግባራዊ ያልሆነ አዋጅ በማወጅ የመሬት ባላባቱን አስወገደ፡፡ የገበሬ ማህበራትንም አቋቋመ፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ በሚገባ ታስቦበት፣ ሕዝብ አስተያየቱን ሰጥቶበት በተለይም ምሁራን መክረውበት የታወጀ አዋጅ ባለመሆኑ ሁሉም ነገር ዝብርቅርቁ ወጣና ከአዋጁ ማግስት የእህል ምርት መጠን በየአመቱ እያሽቀለቆለና የርሃቡም መጠን እየቀጠለ መሄድ ጀመረ፡፡

የደርግ ሥርዓት ወድቆ የኢሕአዴግ መንግሥት ሲተካ ሁኔታው በዚሁ ቀጠለ እንጂ የመሬት ይዞታ ፖሊሲን አስመልክቶ የተሻለ ለውጥ አልመጣም፡፡ ኢሕአዴግ አሁንም በግል የመሬት ይዞታ ላይ ያለው አመለካከት መሬት በመንግሥት ቁጥጥር ይሆናል፡፡ መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም የሚለው ፖሊሲው ገበሬው በሚያርሰው መሬት ላይ የራሱ የሆነ የባለቤትነት ስሜቱን ከሞላ ጎደል እያሟሸሸው ሄደ፡፡

ዛሬ መሬት አዳም እንደተፈጠረ እንደ መጀመሪያዋ ጊዜ አይደለችም፡፡ መሬትን የሰው ልጅ በሥልጣኔና በዕውቀት አሻሽሎ ንብረት አድርጎ ይዟት ይኖራል፡፡ ለልማቱም አውሏታል፡፡ ስለሆነም ዋናው የሰው ልጅ ሃብቱ መሬት ነው፡፡

የመሬት ሥሪት እንደ ጥንቱ ለባላባቱ ይመለስ የሚል አስተሳሰብ ፈጽሞ የለኝም፡፡ የባላባቱንም ሥርዓት በየጊዜው ስቃወመው ቆይቻለሁ፡፡ ከአሁን ወዲያ ይህ ሥርዓት እንደገና ሊያንሰራራም አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊሸጠው፣ ሊለውጠው፣ ተበድሮ ወይም የዕደ ጥበባት ምርት ሊያስፋፋበት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ደግሞ የጎጆ ኢንዱስትሪ ሊያቋቋምበት የሚችልና የራሱ የሆነ የባለቤትነት ስሜት የሚፈጥርለት የመሬት ይዞታ ሊኖረው ይገባል የሚል አመለካከት አለኝ፡፡

አንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ ውይይት ላይ "መሬትን እኮ ሰው ፈጥሮ አልሠራትም፡፡ በፍትሀዊ መንገድ ለሁሉም እንድትዳረስ መሬት በሊዝ መሸጥ አለባት" የሚል ሃሳብ ተነሳ፡፡

"እግዚአብሄር የፈጠረው መሬትን ብቻ ነው እንዴ? ሰውንስ ማን ፈጠረው? ሌሎቹንም እንስሳትስ ማን ፈጠራቸው? በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን ሁሉ የሰው ልጅ በእውቀቱ አሻሽሎና ንብረት አድርጎ ይዟቸው ይኖራል፡፡ መሬት እንደ ሌላው ነገር ሁሉ የሰው ልጅ ንብረት ነች፡፡ እያንዳንዱን ዜጋ መሬት የለህም የሚል መንግሥት ሊኖር አይገባም፡፡ ለምሳሌ አድዋ፣ ማይጨውና በሌሎቹም የጦር ግንባሮች ለምን ተዘመተ? ይሄ ሁሉ እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገሩ በድንበር ተከልላ የተሰጠችውን ጢንጦ ሃብቱን ለመከላከል ሲል ነው፡፡ መሬት የለህም ከተባለ ግን ይህቺ አገር ምን ታደርግልኛለች ሊል አይደለም? ስለዚህ እያንዳንዱ ዜጋ ጢንጦውን ማግኘት ይገባዋል" የሚል ሃሳብ አቀረብኩ፡፡

ዛሬ የምግብ እህል እጥረት ችግር ለምን ተፈጠረ? ለምንስ የእህል ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጣ? ለምንስ የርሃብ ችግር ተሰከተ? የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ከሞላ ጎደል የግል የመሬት ይዞታ ባለመኖሩና ገበሬውም የራሱ የሆነ የባለቤትነት ስሜቱን እያጣ ስለሄደ ነው፡፡ ለተከታታይ የልማት እንቅስቃሴ የመሬት ባለንብረትነት ወሳኝ ነው፡፡ መሬትን ማልማትና ረሃብን መከላከል የምንችለው የባለቤትነት ስሜት ሲኖረን ነው፡፡ ደን ያለ አግባብ ተመነጠረ እንላለን፡፡ ደን ባለቤት ከሌለው ማን ይጠብቀዋል?

አንድ ቀላል ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ከተማችን እያንዳንዱ ግቢ ውስጥ ዛፍ አለ፡፡ አበባ አለ፡፡ ሌሎችም የአትክልት ዓይነቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እያንዳንዳችን ግቢያችንን እናለማለን፡፡ ደክመን ያለማነውን ደግሞ ማንም ከግቢያችን ውስጥ ቆርጦ መውሰድ አይችልም፡፡ ለምን ቢባል ባለቤት አለውና፡፡ በሌላ አንፃር ደግሞ የሲ.ኤም.ሲን ግቢ ብንመለከተው መሬቱ ድንጋይ ብቻ ነው፡፡ ለምን ቢባል እያንዳንዱ ተከራይ ለመሬቱ የባለቤትነት ይዞታ ስለሌለው ስለ ግቢው ልማት ብዙም አይጨነቅም፡፡ ስለዚህ ባለቤት የሌለው መሬት ለልማትም እንቅፋት ነው፡፡

በሀገራችን የምግብ እህል እጥረትን ለማስወገድና ልማትን በሰፊው ለማካሄድ የመሬት ይዞታ አስተዳደርን መንግሥት ማሻሻል አለበት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እያንዳንዱ ዜጋ የግል መሬት ሊይዝና የራሱ የሆነ የባለቤትነት ስሜት ሊኖረው ይገባል፡፡ በሁተለኛ ደረጃ ደግሞ ሰፋፊና ማካናይዝድ እርሻዎች በግለሰቦችም ሆነ በመንግሥት ደረጃ መስፋፋት አለባቸው፡ ዘመናዊ እርሻ ለአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት ነው፡፡ በየጊዜው የሚያሽቆለቁለውን የእርሻ ምርት ለማስወገድና ሕዝቡን ከረሃብ ለማዳን ዘመናዊ እርሻ መስፋፋት አለበት፡፡ ረሃብን ለመከላከል ሰፋፊና ዘመናዊ የእርሻ አጠቃቀም እንጂ የተበጣጠሰ እርሻ ውጤት ሊያስገኝ አይችልም፡፡

ሰፊና ዘመናዊ እርሻ ይስፋፋ ሲባል ደግሞ ጦጣና ዝንጀሮ የሚፈነጩበትን ከጥቅም ላይ ያልዋለ መሬት መንግሥት ለኢንቨስተሮች መፍቀድ አለበት እንጂ፣ በኢንቨስትመንት ስም ገበሬው ለዘመናት ደክሞና ለፍቶ ያለማውን መሬት ይነጠቅ ማለት አይደለም፡፡ የኢንቨስትመንት ዋና ዓላማ የመንግሥትን ካዝና ማዳበርና ገበሬውን ማፈናቀል ሳይሆን ገበሬው ለዘመናት ከለፋበትና ከደከመበት መሬት ተጠቃሚ እንዲሆንና ኑሮውን እንዲያሻሽል ማድረግ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ የእህል ምርት በሰፊው ለገበያ ሊቀርብና ሕዝብም ከርሃብ መዳን አለበት፡፡

የመንግሥት ዋና ዓላማ ደግሞ ዘመናዊ የእርሻ ዘዴ በተጠናከረ መልኩ እንዲካሄድ የእርሻ ምርምር ተቋሞች ኢንዲስፋፋ ደኖች እንዲጠበቁ የማሰልጠኛ ተቋሞች እንዲከፈቱ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በእርሻ ልማቶች እንዲሳተፉ በማገዝና በማበረታታት ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚሁ ጋር አብሮ ለእርሻ ልማት የሚውሉ ብድሮችን በመፍቀድ ዘመናዊ የመስኖና የማዳበሪያ አጠቃቀም እንዲስፋፋና እንዲለመድ ድጋፍ መስጠቱ የመንግሥት ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡

ለምሳሌ ያህል የአሜሪካ ገበሬ ከጠቅላላ ሕዝቡ 5 በመቶ ነው፡፡ የሀገራችን የኢትዮጰያ ገበሬ ደግሞ 80 ከመቶ ነው፡፡ የአሜሪካ ገበሬዎች ዘመናዊና ሰፋፊ እርሻዎች ስላሉዋቸው ከራሳቸው አልፈው ሌላውን ሕዝብ የመመገብ አቅም አላቸው፡፡ በሀገራችን በኢትዮጵያ ግን 80 በመቶ የሆነው ገበሬ በተበጣጠሰ የመሬት ሥሪትና በኋላ ቀር የአመራረት ዘዴ በሚያመርተው ምርት ረሃብን መከላከል አልቻልንም፡፡ ስለዚህ ረሃብን መከላከል የምንችለውና በእርሻ ምርት ሀገራችንን ማልማት የምንችለው የእኔ የሚለው የግል ባለሃብትነት ስሜት ሲኖርና ሰፋፊ መካናይዝድ እርሻዎች ሲስፋፉ ብቻ ነው፡፡
 
< Prev   Next >