| በየመስኩ የእውር ድንብር ጉዞ |
|
| Wednesday, 16 January 2008 | |
|
ያልተለመደው አገር ወግና ባህሉ አላደረገውም ምናልባትም የተነወረ ነው እንጂ የአንድ አገር የእድገትና የልማት መደበኛ ሥራም ሆነ ዘመቻ እንቅፋት አድርገን የማናየው አንድ የኪሳራ አይነት አለ፡፡ ይህም በአገራችን የኢንሹራንስ ፖሊሲ የማይገዛለት የትኛው አይነት መልካም የኮርፖሬትም ሆነ የግለኛ ሰው የሪስክ ማኔጅመንት ጥበብ የማይከላከለው ወይም ወደ ሌላ ሦስተኛ ተጠያቂ ሰው የማያስተላልፈው ጉዳትና ኪሳራ ነው፡፡ ወደ ኋላ ላይ ቀስ እያልኩና በተቻለ መጠን እያብራራሁት እያፍታታሁት የማሳየውን የዚህን ክፉ የጉዳትና የኪሳራ አይነት ይበልጥ የከፋና መጥፎ ገጽታ የሚያጎናፅፈው ከጉዳቱና ከጥፋቱ ይልቅ ኪሳራው የሚያጎድለው መጠንና ልክ በአገራችንና ድህነትን ለመዋጋት በተሰለፍንበት የአገር አቀፍ ዘመቻ ባህላችን ውስጥ መለኪያ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ በባህርይው መለኪያ /መስፈሪያ የሌለው ወይም የማይኖረው ስለሆነ አይደለም፡፡ እኛ ጉዳቱ ይሰማናል፣ ጥቃቱ እንደ እግር እሳት ይበላናል እንጂ ልክና መጠን አለው አንልም፡፡ እንዳንልም በአዋጁም ባይሆን በተጨባጭ በኑሮ ተሞክሮና በሥራ እንዲያምን ሆነናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳንዶቻችን ሲደላን፣ ከውጭ ወይም በአገራችንም የውጭ አገር ሰው ሲል ሰምተን ውኃ፣ ማብራት ሄድ ጥፍት ስትል ስልክ ሲቋረጥ ኮንትራት የያዝነው የከተማም ሆነ የአገር አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት መኪና በተለያየ ምክንያት የመኪናውን መንገድ የእግር ሲያደርገው ሃሳባችንን ብሶታችንን የምንገልፀው ግፋ ቢል ሦስተኛውን ዓለም ወይም አፍሪካን መፍጠር ጣጣ ነው ብለን ነው፡፡ መድህናችንም በዓይናችን አልቅሰን በእጃችን አብሰን ለለፈጣሪ መስጠት ብቻ ነው፡፡ የሚከሰን ጉዳቱንና ኪሳራውን የሚሸከምልን ቀርቶ የጉዳቱንና የኪሳራውን ልክ ይህ ነው ብሎ የሚያሳየው ቀን የምንገምትበት መስፈሪያ የለንም፡፡ የዚህ ችግር ሰለባ ብቸኛውና ተራው ምስኪን ሰው ብቻ አይደለም፡፡ መንግስትም፣ በተለይም ጉዳቱንና ኪሳራውን ከመተመንና ከመለካት አንፃር ያው እንደ ተራው ሰው እሱም ምስኪን መባሉ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁለት ምሳሌዎችን ባጭሩ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንደኛው የቅርብ ጊዜ የመንግስት ተሞክሮ ምርጫ 97ትን ተከትሎ በአገሪቷ በአጠቃላይ የተፈጠረውን፣ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አጥንቶና አጣርቶ አቀረበ በተባለው በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሪፖርት ውስጥ የታየው አሰራርና ስልት የማያመላክተው የአገር አቋም የጉዳትና የኪሳራ እይታችንና ግንዛቤያችን ነው፡፡ መንግስት ከላይ የተጠቀሰው አይነት በአገር ውስጥ ብቻ የታጠረ የሚመስል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዓለማቀፋዊ ሃይላት ስፋት ባላቸው ልዩ ልዩ ክፉ ገጠመኞችም ሲፈተን ሲሞክር በታሪክም በአይናችንም አይተናል፡፡ በንጉሠነገስቱ መንግስት ዘመን በተለይም ከ1933 ዓ.ም ድልና ነፃነት በኋላ ጠላት/ኢጣሊያኖች ይዘውት ስለነበረው ርስት ስለሚመለስበት አለዚያም የርስት ዋጋ ስለሚከፈልበት ሁኔታ (1935 ዓ.ም) እንዲሁም ኢጣሊያኖች በማናቸውም ሰው ንብረት ላይ ባደረጉት ጉዳት ካሳ ይገባኛል በማለት የሚቀርብ ጥያቄ፣ የሚስተናገድበት አሰራር (በ1936 ዓ.ም) በመዘርጋት የተለያዩ አዋጆች ወጥተው እንደነበር ታሪካችን ያስታውሰናል፡፡ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት የጦርነት ወንጀል ኮሚሽን በወቅቱ የፍርድ ሚኒስቴር አማካኝነት ያቀረበችውን የወንጀል ምርመራ ዝርዝር ይዘት ለማየትና ለመረዳት እድሉ ያጋጠመው ሰው እንዲሁም የኢትዮጵያን ዘመናዊ አስተዳደር ለማደራጀት ተቋሞችንም ለመዘርጋት በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው የነበሩት እንግሊዞች ስለመሆናቸው ከጦርነት ወንጀሉ አኳያ ምርመራውን ለማካሄድ የምርመራውን ውጤትና አደረጃጀት ቀርፆና ይዘቱን ትርጉም ያለው ለማድረግ የእንግሊዞች ድጋፍ ምን ያህል ወሳኝ አለዚያም የማይናቅ መሆኑን፣ ለማገናዘብ ሰው የንጉሰ ነገስቱ መንግስት ሌላውን ጉዳይ በሚመለከት ረገድ ቢያንስ ቢያንስ የጉዳቱን ልክና ዝርዝር ይዘቱንና ስፋቱን በሚመለከት ከማሰባሰብና ከመመዝገብ አኳያ ይሳነዋል ብሎ የሚጠራጠርበት ምንም አይነት ምክንያት ሊኖረው ባልቻለ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሳይሳካ የቀረ በዘፈቀደ የተመራ እንዳሻው የታለፈ ጉዳይ ሆኖ የቀረው በዘመናዊት ኢትዮጵያ ውስጥ የከሸፈው የመጀመሪያው ግዙፍ ሙከራ ግን ይህኛው ነው፡፡ በወታደራዊው መንግስት ዘመን በሲያድባሬ ዘመን የተደረገብንን ወረራ ተከትሎ ደርግ የሶማሊያ ወረራ ጦርነት አጥኚ ልዩ ኮሚሽን የሚባል በ1970 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 145/70 አቃቁሞ እንደነበርም የሚታወቅ ነው፡፡ ከነመቋቋሙ ጭምር በወቅቱም ቢሆን ብዙ የማይታወቀው ይህ ኮሚሽን ተልዕኮውን ብቻ ሳይሆን ራሱ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ የሶማሊያም ወረራ ያስከተለው በመብት፣ በነፃነት፣ በሃብትና በንብረት የተከፈለ ዋጋ ሳይታወቅ ቀርቷል፡፡ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኤርትራን በኢትዮጵያ ላይ ወረራን ከዚያም በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት ከተቋቋሙት ሁለት ዳኝነት ሰሚ አካላት መካከል አንዱ ከድንበር ኮሚሽኑ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚታወቀው የካሳ ኮሚሽን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምን ያህል የተሳካ የካሳ የአለኝታ ጥያቄ አሰባስባና አጠናቅራ እንደቀረበች የምናየው ኮሚሽኑ በዚህ ረገድ የመጨረሻውን ውሳኔ ሲሰጥ ነው፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች በከፍተኛና በመንግስት ደረጃ ምን ያህል የአሰራር ሥርዓትና ተቋማዊ ስልትና ዘዴ አለን የሚለውን ጥያቄ ስንመልስ ያጋጠሙት አብነቶች እንጂ ሁሉንማ ብቸኞቹ የችግሩ መገለጫዎች አይደሉም፡፡ የኬንያ የ2007/08 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ተከትሎ የተከሰተውን ሁከት ብዙዎች የአገራችን ዜጎች ፈልገውም ሆነ ሳይፈልጉ የሚከታተሉት ጉዳይ የጎረቤት አገር ችግር በመሆኑ፤ የጎረቤት ችግር ወደደም ተጠላም የሚመለከተንና ሊመለከተን የሚችል መሆኑ ስለማይቀር ብቻ አይደለም ይልቁንም በዚህ ረገድም ኬንያን በያዛት ጉንፋን ቀጥተኛ ምክንያት በእጅጉ ሲያስነጥሱ የምናያቸው ለኬንያ ተፈናቃዮች ከሚደርሰው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድርጅት እርዳታ ባልተናነሰ ድርሻ የሚከፍሉት፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉት ሌሎች ጎረቤት አገሮች ናቸው፡፡ የኡጋንዳና የሌሎች የኬንያ አጎራባች አገሮች እጣ ለምን ለኢትዮጵያ አልተዳረሰም ብለው የሚቀኑበት ጉዳይ አይደለም እንጂ ጉዳዩ ግን ራሱን የቻለ መልዕክት ያለው ነው፡፡ ምልክትነቱም የደግ አይደለም፡፡ የኬንያ ሁከት ከዚህ አልፎ ተርፎ የገዛ ራሳችንን መመልከቻ መስተዋት ሆኖ ያገለገለበትም ብዙ መገለጫዎች አሉ፡፡ ኬንያውያን ምን ያህል እንደሞቱ ከሞላጎደል አጣርተው ያወቁት አጣሪ ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ አይደለም፡፡ አጣሪ ኮሚሽን እንዲቋቋም የምርጫው ውጤት እንደገና እንዲቆጠር የጠየቀው እንደ ኢትዮጵያ ዓለማቀፋዊ ማህበረሰብ ወይም በዚያ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ወይም የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ/ፓርቲዎች (ብቻ) አይደሉም፡፡ ከሁሉምና ከማንም በፊት ይህንን ጥያቄ ያስተጋቡት የኬንያ ጠቅላይ ፀቃቤ ህግ እና በመንግስቱ በጀት የሚተዳደረው መንግስታዊ ተቋምም የሆነው የኬንያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ናቸው፡፡ በተለይ ኮሚሽኑ አፍ አውጥቶ አደባባይ ወጥቶ ከአምስት መቶ በላይ ለሆኑት ኬንያውያን መሞት ቀጥተኛ ምክንያትና ተጠያቂው መጣራት ያለበት ቢሆንም መጣራት ያለበት መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአገሪቷ የምርጫ ኮሚሽን ግን የሩቅ ምክንያቶችና ከቅርብም ሰበብ ሆኖ ከመጠየቅ እንደማይድን አቋም ይዞ ይህንን በነፃነት ገልጿል፡፡ ምርጫ ኖረም አልኖረ፣ ምርጫውን ተከትሎ የተከሰተ ችግር ይኑር አይኑር ከዚህ አኳያ ከአገራችን ክፉ ችግሮች መካከል አንዱ የሰላምም ሆነ የክፉ ጊዜ የአደጋ ጊዜ ሞትና ጉዳት ቆጠራ ስርዓትና የተቋቋመ አሰራር የሌለን መሆኑ ነው፡፡ ይህ በሌላው አገርና ቦታ ኬንያንም ጨምሮ የሁሉምና በየትኛውም አገር መጀመሪያና መነሻ የስልጣኔ የደረጃ መለኪያ ነው፡፡ እኛ አገር ለምሳሌ ሆስፒታሎች መነሻ ማጣቀሻ በሚሆኑበት እንደ አዲስ አበባ ከተማ ባሉት ቦታዎች እንኳን ሳይቀር ሆስፒታል አለመሄድ አለመወሰድ ሊኖር ይችላል፡፡ ሆስፒታሎችንና ሐኪሞቻቸው ፍርሃት እያረበበባቸው የነፃነት እጦት ችግር እየተጠናወታቸው ከዚያም አልፎ ህክምናም ሆነ ምርመራ ጠይቆ እጃቸው የገባውን በህይወት ያለው ሰው ሆነ አስከሬን እንደ ታካሚ/በሽታኛ ሳይሆን እንደ ጠላት ወይም እንደ ወገን ፈርጀው ስለሚያዩት ሁሉንም እውነት የሞቱን ምክንያት ጭምር ልናገኝ አንችልም፡፡ በሰላምና የልማት ሥራ በመደበኛና በዘመቻም በሚካሄድበት ወቅት ሲያጎድለን የምናየው በተመሳሳይ ሁኔታ ይህንኑ የኪሳራና የጉዳት መጠን የሚለካ ለክቶም የሚካስ /አለዚያም የማይካስ ስለመሆኑ መወሰን የሚገባው ስርዓትና ተቋም የሌለን መሆኑ ነው፡፡ የሁሉም የአገራችን ህመም ችግር ይኸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንድ ሌላ ወቅታዊ ምሳሌ አንስተን እንመልከትና የችግሩን ስፋት እንቃኝ፡፡ የአዲስ አበባ የግንባታ ስራ አገራችን በተያያዘችው ከድህነት የመላቀቅ ችግር በምሳሌነት እየተጠቀሰ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን የሚያስተባብሉ የመኖራቸው ጉዳይ የሚታይበት አቅጣጫ ራሱ ጤነኛ ነው ባይባልም የአዲስ አበባን የመንገድና የህንፃ ግንባታ ስራ አዎንታዊ ገጽታ ለሚቀበሉም ቢሆን መታየቱ ያልቀረ የአገር ችግር አለ፡፡ ከችግሩ ይልቅ ችግሩ እውቅና ማጣቱ ይህን እውቅና ከማጣቱ ጋር ተያይዞም የጉዳቱ ልክ አለመታወቁ ሌላው የችግሩ ችግር ነው፡፡ አገራችን ውስጥ አሁን ተፈፃሚነት ባለው ህግ መሰረት በተለይም የመሬት አስተዳደርን በተመለከተ የሕዝም ጥቅም ማለት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ህዝቦች በመሬት ላይ ያላችውን ተጠያቂነት ለማረጋገጥና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በቀጣይነት ለማጎልበት አግባብ ያለው አካል በከተማ መዋቅራዊ ፕላን ወይም በልማት እቅድ መሰረት የህዝብ ጥቅም ብሎ የሚወስነው ነው አግባብ ያለው አካል ማለት ደግሞ የከተማ ቦታን ለማስለቀቅ በሊዝ ለመፍቀድና ለማስተዳደር ስልጣን የተሰጠው የክልል ወይም የከተማ መስተዳደር አካል ነው፡፡ ይህ የህዝብ ጥቅም ትርጓሜ በራሱ በይዘቱ ብቻ ሳይሆን ከአሰራርም የህዝብ ጥቅም ብሎ ከሚወስነው አግባብ ያለው አካል ማንነት አኳያ ዋነኛና መሰረታዊ ችግር አለበት፡፡ ይህንን ከሁለቱም አንፃር ከንጉሰ ነገስቱ መንግስት ዘመን ተፈፃሚነት ከነበረው ህግ ጋር አወዳድሮ መመልከትና መረዳት ይቻላል፡፡ አንድ ደሳሳ ጎጆ ፈርሶ የተሻለ ህንፃ የሚሰራ ግለሰብ ይወስደው ዘንድ መሬት የማስለቀቅ ቤቱንም ግምት ሰጥቶ ማፍረስ የህዝብ ጥቅም ነው ማለት የዚህ ማብቂያ የተለየ ነው? የሚል ጥያቄ ከማንነት አኳያ ራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሸራተን በተሰራበት ቦታ ላይ የነበረውን የመንግስትም ሆነ የግል ንብረት ማፍረስ በህዝብ ጥቅም ትርጉም ውስጥ ይሸፈናል ማለትን የሸራተን ህንፃ ውበትና ድምቀት ካፀደቀው ከሸራተን ብዙ ሺህ ጊዜ የሚበልጥ የልማትና የግንባታ ሥራ ከመጣ ሸራተንን ማፍረስ የህዝብ ጥቅም ነው የማይባልበት ምን አይነት ምክንያት ይኖራል፡፡ ይህ መከራከሪያ ዋነኛውንና መሰረታዊውን ጉዳይ የማያነሳና የማይመልስ ቢሆንም ጥቅም ለውጡና አብዮቱ መጣላቸው የሚባሉትን ልማታዊ ባለሃብቶች ራሳቸውን አያስደነግጥም ማለት ዘበትና ራስን ማታለል ነው፡፡ ትልቁን ልማታዊ ባለሃብት ለመጥቀም የትንሹን ይዘትና ንብረት ማስለቀቅ የልማት መንገድ ነው ማለት የትልቁ ሌላ ትልቅ ሲመጣስ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ለህዝብ ጥቅምና አገልግሎት የሚጠቀሙ ሀብቶችን ስለማስለቀቅ የነበረው የተቋቋመ አሰራር በንጉሰ ነገስቱ ዘመን የህገመንግስታዊ ድንጋጌ ደረጃ የያዘ ነበር፡፡ በወቅቱ ሥራ ላይ የነበረው በቅርቡ የወጡ የመሬት ይዞታ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ስለሚለቀቅበት ሁኔታ የሚደነግጉት (194 እና የ97) ሐጎች በግልጽ ሳይነገር እስኪሽሩት ድረስ ሥራ ላይ እስካሁንም የቆየው በፍትሃብሄር ህግ ይደነገግ የነበረው ግን ከዚህ በተለየና ያለቀም ነበር፡፡ መጀመሪያ የመሬት ይዞታም ሆነ የግል ንብረት የሚወስደው ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሲሆንና የሚኒስሮች ምክር ቤት ተስማምቶበት በነጋሪት ጋዜጣ ለሚያወጣው ትዕዛዝ ሲወሰን ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በህግ የተወሰነ የተቆረጠ ትክክለኛ ግምት አስቀድሞ የመክፈል ጉዳይም ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የህዝብ ጥቅም ብሎ የሚወስነው የመንግስት አካል አሁን አግባብ ያለው አካል የተባለው ሳይሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት መሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ትዕዛዝ በነጋሪት ጋዜጣ ሊወጣ የሚገባው የመሆኑ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የህዝብ ጥቅም ራሱ ልዩ ትርጉም ነበረው ይህም በፍትሃብሄር ህጉ እንደተወሰነው ጎዳናዎችን መንገዶችን የውሃ ቦዮችን የምድር ባቡሮችን በተለይም ለህዝብ አገልግሎት እንደ ምሽግ ያሉት ናቸው፡፡ ችግሩ ግን በዚህ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የነበረው ህግ በወቅቱ ሰርቷል የአሁኑም በወቅቱ የማይሰራበት ምክንያት የለም የሚለውን መከራከሪያ በተለያዩ ምክንያቶች መቀበል ይቻል ይሆናል፡፡ ተቀበልነውም እንበል የአገር ተቋማት መለካት የማይችሉት ብቻ ሳይሆን ስለመኖሩም የማያውቁት ኪራይና ጉዳት መኖሩን በየቤቱ የምንቆጥረው ይህንን ሌላ ገጽታ ስናይ ነው፡፡ ለመንገድ ሥራ የሚፈርሱትንና የሚለቀቁትን ስናይም በህዝብ ጥቅም ትርጉም መጣላትና መከራከር አያስፈልገንም፡፡ የሚፈርሱትና የሚለቀቁት በአብዛኛው የመንግስት ንብረቶች መሆናቸውም የችግሩን መጠን የሚቀንሰው ሊመስል ይችላል፡፡ ከቀበሌ ቤቶች አኳያ ግን ይህ እውነት አይደለም፡፡ የቀበሌ ያልሆኑ የግል ቤቶችም ይህንኑ መሰል ችግር ያሳያሉ፡፡ የግሎቹ አገሪቱ ውስጥ ባለው የቤት ኪራይ እጦትና እጥረት ምክንያት በተለይም ለንግድ አገልግሎት የተከራዩት አስቀድሞ የሚከፈልባቸው ናቸው፡፡ አስቀድሞ የሚከፈለው የኪራይ መጠን ደግሞ የአገሪቱ አርቲፊሻል የአከራይ ተከራይነት ግንኙነት ያወጣውን ህግ ተከትሎ ለ6 ወር ለዓመት የሚከፈል ነው፡፡ አገራችን ደግሞ ሰው እንዳይበልጥ እንዳይጠቃ መከላከል ይቻል ዘንድ መረጃ በነፃ የሚንሸራሸርባት አይደለችም፡፡ ይህ ወይም ያኛው መንገድ በዚህን ያህል ስፋት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እንደሚሰራ በዚህም ምክንያቶች ይህና ያኛው ንብረት እንደሚፈርስ ዘርዝሮና ለቅሞ የሚያስታወቅ አሰራር ባህል የለም፡፡ ይልቁንም ይህና ሌላው ሁሉ የመንግስት ምስጢር ጥበቃ ምስጢር ነው፡፡ በዚህ መካከል ተከራይ ነጋዴው ተከራይ ልማታዊ ባለሃብቱ ከዘወትሩ መፈናቀል በላይ ሌላ ተጨማሪ ገንዘቡን ያጣል ይባላል፡፡ ፍርድ ቤት ይኬዳል እንዳይባል ይህም ተቋም ከመክሰስ ይልቅ ተከሰው በቀረበቡበት የሚያኮራና የሚያኩራራ ነው፡፡ የቀበሌ ቤቶች አከራዮች ደግሞ በሚገርም ሁኔታ በርካታና ሰንሰለታቸው የበዛ ነው፡፡ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር አሰራር እጅግ በጣም እንግዳ በሆነበት ሁኔታ የቀበሌ ቤቶች አከራዮች የተከራይ አከራይ የተከራይ ተከራይ ተከራይ አከራዮች ናቸው፡፡ የተወረሱት ሰዎች እዚያው አፍንጫቸው ስር አይናቸው እያየ ተከራይተው የሚያከራዩ አከራዮች በዚህ የንግድና የልማት ሥራ የተሰማሩ አንቱ የሚባሉ ናቸው የሚባለውን አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ክስ የሰማሁት አሁን በቅርቡ ነው፡፡ ይህንን የሚመለከታቸው ሊያስረዱን ይገባል፡፡ የሚገርመው ቀበሌው የገዛ ራሱን የኪራይ ቤት ቤቱ የሚፈርስ በመሆኑ የኪራይ ውሉ ከዚህ ቀን ጀምሮ ተቋርጧል፡፡ ንብረት አውጥተው ይውጡ ብሎ ትዕዛዙን ይፋ ካደረገ በኋላ ቤቱን የሚያፈርሱት ተከራዮቹ ሳይሆን ከቀበሌ የተከራዮች አከራዮች /የተከራይ ተከራዮች ናቸው፡፡ ያፈርሳሉ ብቻ ሳይሆን ቤትም ይሰራሉ፡፡ ከመንገዱ መሰራት ይተርፋል የሚባለውን የቤቱን ክፍል አፍርሶ ወይስ ራሱ ሰርተው ያከራያሉ፡፡ ሰርተው የሚያከራዩት ቤት የሚገዛው በነባሩ የቤት ኪራይ ውልና በታወቀ ጣጣው መሰረት በመሆኑ እንደገና ሌላ አዲስ ውል ሌላ ቅድሚያ ክፍያ ሌላ ወጭ አለ፡፡ ከቁም ሳጥን የማይበልጥ ፋንክሽናሊ ቤት ተብሎ መጠራት የማይችል ግንባታም ከፈራሹ ውስጥ ኪሳራ እናያለን፡፡ ይህ ቤት ነገ ሲፈርስ ኪሳራው ጉዳቱ መምጣቱ አይቀርም፡፡ እንደ የአየር ሁኔታው ግን በትክክል የሚተነበይ በቀጥታ የሚደርስ አሰራና መረጃ የለንም፡፡ እውን የሚያደርገው ይኸው ተቋም ስርዓት ያለው በእውር ድንበር የምንመራበት ጉዞ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |