| የቡድን አስተሳሰብ በተማሪው እይታ |
|
|
| Wednesday, 09 July 2008 | |
|
በምህረት አስቻለው
ወቅቱ ለተከታታይ ዓመታት በመንግሥትም ሆነ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች የሚመረቁበት ነው፡፡ ተማሪዎቹ ከትምህርት ጐን ለጐን የተለያዩ ማሕበራዊ እሴቶችን ተጋርተው ከተቋማቱ ይወጣሉ፡፡ ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገውና በያዝነው ዓመት ሰኔ 14 ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀው ወጣት የሦስት ዓመት ቆይታውን በጥቂቱ ገልፆልናል፡፡ ተወልዶ ያደገው ጐንደር ከተማ ነው፡፡ ዲግሪውን ያገኘው በሳይኮሎጂ ሲሆን በግቢው ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የተማሪዎች ክበባት ይሳተፋል፡፡ “በሦስት ዓመት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር አብሮና ተቀራርቦ መኖር ምን እንደሚመስል አውቄአለሁ፡፡ በዚህም በርካታ ነገሮችን አግኝቻለሁ፡፡ በተቃራኒው ፅንፈኛ ጐሰኝነትን የተላበሰ አመለካከት የተሞላበት እንቅስቃሴንም አይቻለሁ፡፡ የቡድን አስተሳሰቡ በመኝታ ሕንፃ ምደባ፣ በክበባት አመራርነት ምርጫና በግሬድ አሰጣጥ ላይ የሚንፀባረቅበት ሁኔታ አለ፡፡ ከዚህ ለመረዳት የሚቻለው በድርጊቱ መምህራንም የሚሳተፉበት ሁኔታ መኖሩን ነው” በማለት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚታየው የቡድን አስተሳሰብ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ከሚታየው (በተወሰነ መልኩ) የተለየ እንደሆነ ገልጿል፡፡ እንደ ወጣቱ ገለፃ፣ እሱ ትምህርቱን በተከታተለበት ሂውማኒቲስ ኤንድ ሶሻል ሳይንስ ዲፓርትመንት ያለው ጽንፈኛ የብሄርተኝነት (የቡድን አስተሳሰብ) ከፍተኛ ነው፡፡ ተማሪዎች ምን ሰሩ የሚለውን ያህል ከየት መጡ የሚለውም በከፍተኛ ሁኔታ ሚዛን የሚደፋ ጉዳይ ነው፡፡ የቡድን አስተሳሰብ በአጠቃላይ በግቢው የተስፋፋ ነው ብሎ ማጠቃለል ባይቻልም ያልተለመደ ግን አይደለም፡፡ እንዲያው ተማሪውም አስተማሪውም በይፋ ባይሆንም በጋራ የተስማማበት የዩኒቨርሲቲ ባህል ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ የተመለከታቸውን በተለይም በግሬድ አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ በማስመልከት ለግቢው የስነ ምግባር ቢሮና ለሌሎችም መሥሪያ ቤቶች አቅርቦ ነበር፡፡ ሴሚስተር መጀመሪያ ላይ መምህራን ሲመደቡ እያንዳንዱ ተማሪ የመምህሩን ብሔር ወይም የትውልድ ቦታ በመነሳት የመምህሩን የግሬዲንግ ሲስተም የሚገምትበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገረው ወጣት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ተማሪ ተመርቆ ሲወጣ ከፍተኛ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖረው አቋም ምን ዓይነት ሊሆን ይችላል በማለት ይጠይቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ በርካታ ተማሪዎች ቢገነዘቡትም በሚያዩት ያልተገባ ድርጊት ዘወትር ቅሬታ ለማቅረብ ቢሞክሩ ከባድ ችግር ሊገጥመን ይችላል በሚል ፍራቻ ራሳቸውን እንደሚገድቡ አመልክቷል፡፡ “ለተግባር በተመደብንበት ወቅት ሌሎች ሁለት ተማሪዎችም አብረውኝ ነበሩ፡፡ በቅርብ መዛኛችን (ሱፐር ቫይዘር) የተሰጠን ነጥብ ተመሳሳይ ሲሆን ግሬድ በሚሰጠው መምህር የተሰጠን ግሬድ ግን የተለያየ ነው፡፡ ጉዳዩን አንስተን ተወያየን፤ ነገር ግን በግቢው በተደጋጋሚ የሚከሰት በመሆኑ አዲስ ባይሆንብኝም ሁኔታውን ለማጣራት የተወሰኑ ሙከራዎችን አድርጌ ነበር” በማለት ከተመሳሳይ አካባቢ የመጡ ተማሪዎች ተመሳሳይ ግሬድ የሚያገኙበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን አልደበቀም፡፡ እሱ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት ከቡድን አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ ከሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የተለየ ነገር ሰምቶ እንደማያውቅ በማስታወስ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በቆየባቸው ሦስት ዓመታት ግን በቡድን አስተሳሰብ (ጐሰኝነት) ምክንያት የሚፈጠሩት ሁኔታዎች እየተስፋፉ (የግቢው መለያ ባህል) እስከመሆን መድረሳቸውን አስረድቷል፡፡ በዚህ ባህል በተለያየ ጊዜ የተወሰኑ ተማሪዎች ሲጠቀሙ ሌሎቹ ደግሞ ይጐዳሉ፡፡ ይህ በተማሪዎቹ መካከል መጥፎ ስሜት እንዲፈጠር ከማድረጉ በላይ ተማሪዎች በቡድን አስተሳሰብ ምክንያት የሚፈፀሙ ኢፍትሀዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በአንድ ላይ እንዳይነሱ አድርጓል ብሎ ያምናል፡፡ እንደ ወጣቱ አባባል መማር ልዩነትን የሚያሰፉ ነገሮችን ማጉላት ሳይሆን አንድነትን የሚያጐለብቱ የጋራ ነገሮች ላይ በማተኮር በጋራ የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት ባህልን ማምጣት ብሎም ለአገርና ለወገን ጠቃሚ ተግባር መፈፀም ነው፡፡ “ነገ ለአገርና ለወገን የበኩላቸውን ያበረክታሉ ተብለው የሚጠበቁ የአገሪቱ ወጣቶች በሚወጡበት እንዲሁም በትምህርት የጐለበቱና ልምድ ያካበቱ መምህራኖች ባሉበት ተቋም ውስጥ ፅንፈኛ አስተሳሰብ መኖሩ ያሳዝነኛል፡፡ የሚጠበቅም አይመስለኝም” ብሏል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |