Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Sep 07th
Home arrow Sections arrow የሙዚየሞቻችን ጉዞ
የሙዚየሞቻችን ጉዞ Print E-mail
Wednesday, 09 July 2008
Image
ዶክተር ካሳዬ በጋሻው
በሔኖክ ያሬድ

ሙዚየም ወይም ቤተ መዘክር የአንድ ሀገር ባህላዊና ታሪካዊ እንዲሁም ጥንተ መሰረት የሚገለጽበትና የሚታይበት ማዕከል ነው፡፡ በዓለማችንም ሆነ በአገራችን በርካታ ሙዚየሞች ይገኛሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የሙዚየም ማኅበራት አማካይነት በየሀገራቱ የሚከበር የሙዚየም ቀን ከመኖሩ ባሻገር በዓመቱ ውስጥ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚታሰበው ዕለት ለዓመቱ የሚያገለግል መሪ ሐሳብ አለው፡፡ የዘንድሮ 2000 ዓ.ም (2008) መሪ ሐሳቡ “ሙዚየሞች ለማኅበራዊ ለውጥና ዕድገት አጋዥ ኃይሎች” የሚለው ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ ይታሰባል፡፡ በዚህ መሪ ሐሳብ መሰረት በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሆኑ ሙዚየሞቻችን ስላሉበት ደረጃና ሂደት የሚሉት አላቸው፡፡

የመጀመሪያው ተናጋሪ የታሪክና አርኪዮሎዢ ምሁር ዶክተር ካሳዬ በጋሻው ናቸው፡፡

“ሙዚየሞች ለማኅበራዊ ለውጥና ዕድገት አጋዥ ኃይሎች” የሚለው መሪ ቃል አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ የዓለም ሙዚየም ቀን በየዓመቱ ሲከበር የዘንድሮው መወያያ ሐሳብ ለየት ያለ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ካሳዬ በጋሻው ሙዚየም ሲሠራባቸው ከቆየው አንዳንድ ሥራዎቹ ወጣም ያለ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚታወቀው ሥራው መሰብሰብ፣ መሰነድ፣ መጠበቅ ጥናትና ምርምር በየዕለቱ የማከናወን ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሙዚየም ምን ሆኖ መገኘት ይገባዋል፣ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል የሚለው ተተኳሪ  ነጥብ ነው፡፡ ለለውጥ የሚያዘጋጅ የሚያነቃቃ ነው፡፡ መሪው ቃል በ70 አገሮች 20”000 ሙዚየሞች የሚወያዩበት ሐሳብ ነው፡፡

መጀመሪያ ትኩረት የሚሰጥበት ርዕሱ ላይ አንዱ የአስተዳደር ጽንሰ ሐሳብ በመሆኑ ሙዚየም ብቻውን ውሳኔ ሰጪውን ክፍል ብቻ ሳይሆን በውስጡ ያሉትን ባለሙያዎች አቅፎ የሚገኝ ነው፡፡

ለማኅበራዊ ለውጥ በምናስብበት ጊዜ ሕንፃውን፣ ቅርሶችን ብቻ ሳይሆን የሚያንቀሳቅሰው ክፍል ጭምር ነው፡፡ በሁለተኛነት የሚያሳየው ሙዚየሙ ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት አቅም አለው ወይ? ራሱስ ሳይለወጥ ሌላውን መለወጥ ይችላል ወይ? ለለውጥስ ተዘጋጅተዋል ወይ? ይኸንን የሚሸከም ኅብረተሰብ አለ ወይ? መንግሥትስ ይኸን ሐሳብ ይገነዘባል ወይ? እነዚህን መገንዘብ እንደሚስፈልግ ምሁሩ አጽንዖት ይሰጡበታል፡፡

ሙዚየሞች ምን ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ የሙዚየም ብያኔ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ይዳስሳል ወይ? ነባሩ ብያኔ ግማሽ ምዕት ዓመት አሳልፏል፡፡ አሁን የምንለውን መሸከም ይችላል ወይ? የሚሉት ዶክተር ካሳዬ ሙዚየሞች የመገናኛ ቦታ፣ ሐሳብ መለዋወጫ ችግርን የመቅረፊያ መድረኮች ናቸው፡፡ ባላቸው ስብስብ በመገናኘትና ታሪክና ባህልን ብቻ በማሰባሰብ ሳይወሰኑ ሌሎች ዘርፎችን እንደ ማዕድን፣ ኢነርጂን ማካተትና ገንዘብን የማስገባት ለቱሪዝም ዕድገት የሚበጁ መሆናቸውን ማወቅ ይገባል ይላሉ፡፡

ሙዚየም የአገሪቷን ችግር በኤች.አይ.ቪ፣ በሥነ አካባቢ በፖለቲካ ቀውሶች ዙሪያ የሚነጋገሩበት መድረክ መሆን እንደሚገባው የሌሎችን አገሮችን ተሞክሮ በምሳሌነት በማቅረብ ያብራራሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን መጀመሪያ ከባርያ ንግድ፣ ቀጥሎ ከቅኝ ገዢዎች፣ ከአፓርታይድ ነፃ ለመውጣት በተዘጋጁበት ጊዜ ሕገ መንግሥት ስላስፈለጋቸው ያን ለመጻፍ ብዙ ውይይቶችን አካሄደዋል፡፡

የቤት ሥራ ከተሰጣቸው ተቋማት አንዱ ሙዚየም ሲሆን ሙዚየሙ ያደረገውም ታዋቂ አርቲስቶችን በመሰብሰብ ምሁራን በብዕራቸው፣ ሰዓሊዎች በብሩሻቸው እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡ ሁለተኛው ምሳሌ ኡጋንዳ ከሎርድ ሬዚስታንት አርሚ ጋር የነበራትን የርስ በርስ ግጭት ለመፍታት ሙዚየሞች ሚና እንዲጫወቱ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት የኡጋንዳ ብሔራዊ ሙዚየም “ሰላም በኡጋንዳ” በሚል ርእስ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የፈጠራ ሥራ እንዲያቀርቡ ሲያደርግ የ4ኛ ክፍል ተማሪ ሙሴቬኒንና የሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ መሪ ሲጨባበጡ የሚያሳይ ሥዕል በመሥራቱ የሁሉንም መንፈስ የገዛ ነበር፡፡

ሙዚየም ኅብረተሰብን የማገናኘት በማኅበረሰቡ ውስጥም አንድነትና ግንኙነት ማድረግ ትልቁ ተግባሩ በመሆኑ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚኖረው ተቋም ተገቢ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ በአዲስ አቀራረብ፣ በአዲስ ርእይና ሐሳብ መታጠቅ እንደሚገባውና ለዚህም ባለሙያዎች መነሳሳት እንደሚገባቸው ዶክተር ካሳዬ አሳስበዋል፡፡

ሙዚየሙ ለማኅበራዊ ለውጥ በሚጠቅም መልኩ ስብስቡ ውክልና ያቀፈ መሆን እንደሚገባው ለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አገሪቱን የመሠረቱ ብሔረሰቦች የሚገኙበት እነሱን በምልዐት የሚወክል ሊሆን ይገባዋል፡፡

ስብስቡ ለአገሪቱ የልማትና ማኅበራዊ ለውጥ ሙዚየሙ አዘጋጅቶታል ወይ? ይህንን ሊያዘጋጅ የሚችል ባለሙያስ አለ ወይ ብለው ምሁሩ ይጠይቃሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሙዚየም ላይ ቅኝት ያደረጉት አንጋፋው አርኪዮሎጂስት ዶክተር ብርሃኔ አስፋው ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው አባባል ሙዚየም እንደ ትምህርት ቤት የሚታይ የመረጃ ማዕከል ነው፡፡ ዋና ሥራው ቅርሶችንና ታሪካዊ እሴቶችን ጠብቆ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ዜጋን የሚቀርጽ፣ ባህልን የሚያስተምር፣ ታሪክን የሚያስረዳ ተቋም ነው፡፡ ከሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋሞች የተለየ የሚያደርገው ሙዚየም ጊዜን የጠበቀ መረጃ ማቀበል መቻሉ ነው፡፡

ብሔራዊ ሙዚየም ኢትዮጵያን ከተፈጥሮ ታሪክ ከባህል፣ ከታሪክ፣ ከኤትኖግራፊ (የሕዝብ ባህል) አንፃር ቁስ አካላዊና ቁሳዊ ያልሆኑ እሴቶችን በማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ከተመራማሪዎች ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር ብርሃኔ፣ ለ30 ዓመታት በተመራማሪነት በቆዩበት ከ12 በላይ የሰው ዘር ግኝቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገኙም ስለ እነርሱ የሚመለከት መረጃ ያለው እስካሁን ድረስ አንድም የትምህርት መጽሐፍ አለመዘጋጀቱ የሚያሳስብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሌሎች አገሮች የትምህርት ተቋማት ስለኢትዮጵያ ግኝቶች በቂ መረጃ ሲኖር እዚህ የታሪኩ ባለቤት የሆነው ሕዝብ በትምህርት ተቋሞቹ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የተካተተ አይደለም የሚሉት አርኪዮሎጂስቱ ያለው ተሞክሮ ምንም ስፋት በሌለው ስለ ሉሲ በትክክል የዝርያ ስሟን እንኳ በትክክል ሊገልጽ በማይችል በተቀነጨበ ሁኔታ ተካትቶ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ሙዚየም ለቱሪዝሙ መልክ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሊያደርግ ቢችልም በአገሪቱ እስካሁን ቱሪዝም የላቀ ትኩረት ያላገኘ ትልቅ ኢንዱስትሪ መሆኑን ያስታወሱት ምሁሩ ካለፉት ስድስት ሚሊዮን ዓመታት አንስቶ እስካሁን ዘመን ድረስ መረጃ ሊያቀርብ የሚችል ሙዚየም ለቱሪዝም ተጠቃሚ እንዲሆን እንደ ወርቅ ቆፍሮ የማውጣት ተግባር መታየት እንደሚገባው አስምረውበታል፡፡

በሦስተኛው ዓለም ቀውስ እያለ ስለ ቅርስ እናወራለን፤ አመራር ሰጪውም ስለ ዳቦ ያነሳል ይህንን ጉዳይ እንዴት እናስታርቀዋለን ብለው ጥያቄ ያነሱት ዶክተር ካሳዬ ለረሀቡም ሆነ ለችግሩ ቅርሱ መፍትሔ ሊሰጥ ይችላል ይላሉ፡፡ ትልቁ ጥያቄ ቱሪዝምን ተግባራዊ አለማድረጉ ነው፡፡

መንግሥት ግብርና ተኮር እንደሚለው ሌላ አማራጭ ቱሪዝም ተኮር ማለት ለዘለቄታ ልማት ፕሮግራም አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ቅርሶች ለታሪክና ባህል መረጃ ብቻ ሳይሆን ለልማት ትልቅ አስተዋጽዖ መሰረት ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ከነዳጅ ዘይት በበለጠ ትልቁ ኢንዱስትሪ ቱሪዝም ነው፡፡

የተፈጥሮና የባህል ቅርሶች ያላት አገር በቱሪዝም ላይ መንግሥት ካሰበበት ብዙ መጓዝ ይቻላል፡፡ ከግብፅም ከኬንያም የተሻለ የቱሪስት መስህብ ቢኖረንም ገቢ የሚያስመጣ ስትራቴጂ እና ተግባር አልተሠራም፡፡

ዶክተር ብርሃኔ እንዳሉት፣ የኛን ግንዛቤ ሊያሳድግ፣ ስለታሪካችን ለማስተማር የሚችለው፣ ከተመራማሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው ብሔራዊ ሙዚየም ስለሆነ አስተዋጽዖ በባህል ማቆያነት ኅብረተሰብን ከመገንባት ባሻገር ለምጣኔ ሀብት ትሩፋት ያለው ተቋም ስለሆነ መንግሥትም ኅብረተሰቡም ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ነው፡፡

ብሔራዊ ሙዚየም እስካሁን የሄደበት ረዥም ጉዞ አጥጋቢ ባይሆንም አገሪቱ ባካሄደችው ወጣ ገባ ታሪክ ሳይፈርስ፣ ሳይዘረፍ፣ ቅርስ ሳይባክንበት የቆየ ተቋም ስለሆነ ሊከበር እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ 
 
< Prev   Next >