| ክቡር ሚኒስትር |
|
|
| Thursday, 10 July 2008 | |
|
እንሂድ እስቲ አንዴ አይተንለት እንምጣ፡፡
- እንዴት? - ፉቲንግ የለ! ምሰሶ የለ! - አብራችሁ ሻይ ቡና ስትጠጡ ስትገባበዙ አይቼ አላውቅም፡፡ አንተ አባቴ ነህ፡፡ ግን ሚኒስትር ጋብዘህ ታውቃለህ? እኔ ሁሌ ይገርመኛል፡፡ - ምንድነው የሚገርምሽ? - በጫካ ያ ሁሉ ጊዜ አብራችሁ ኖራችሁ፣ ታግላችሁ እዚህ ግን እንዴት እንደማትቀራረቡ ይገርመኛል፡፡ - አብረን እኮ ነው የምንውለው፡፡ - ስብሰባ ነዋ መነሻው፣ ምንጩ፡፡ በእውነቱ በመሰረቱ ስትሉ እንጂ ስለኑሯችሁና ስለቤተሰባችሁ አታወሩም፡፡ ካወራችሁ ደግሞ ትግል ያቆማችሁና ግለኛ የሆናችሁ ይመስላችኋል፡፡ - በይ በይ አሁን አትለፍልፊ ተነሽ መኪና ውስጥ ግቢ፡፡ - እኔ ለምንድነው የምሄደው? - አስተያየት ትሰጪያለሽ፡፡ ትምህርትሽ ደግሞ እሱ አይደለም? - እሺ በል እንሂድ፡፡ (ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር ሌላኛው ክቡር ሚኒስትር የሚሠሩበት የመኖሪያ ቤት ሳይት ደረሱ) - በጣም አመሰግናለሁ፡፡ አይመቻችሁም ይሆናል ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡ አንቺ ደህና ነሽ? ትልቅ ሴት ሆነሻል፡፡ እኔኮ ማርጀቴን የማውቀው እናንተን ሳይ ነው፡፡ - እኔ ደግሞ ማርጀታችሁን የማውቀው የአስተዳደግ ልዩነታችንን ሳስተውል ነው፡፡ - በይ በይ በቃሽ፡፡ ተናጋሪ ነሽ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ የግንባታው ሁኔታ ይህን ይመስላል፡፡ እንዴት ታዩታላችሁ? - እሷ ባለሙያ ስለሆነች አስተያየት ትስጥህ፡፡ ለመሆኑ አርክቴክቱ ኮንትራክተሩ ማን ነው? - አንዱ ነበር፡፡ እንዲህ ካልሆነ እንዲህ ካልተደረገ እያለ ሲጨቀጭቀኝ አባረርኩት፡፡ አሁን ከአንድ ወዳጄ ጋር ሆኜ ራሴ እየሰራሁት ነው፡፡ - ክቡር ሚኒስትር ሰውየው ምን ስላለ ነው ያባረሩት? - ይኸውልሽ አንዴ ..ሶይል ቴስት.. ይላል፡፡ አንዴ ሜትር ተኩል ወደታች ካልተቆፈረ ይላል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ..ፉቲንግ.. ይላል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ሙያዬ አይፈቅድልኝም እያለ አልንቀሳቀስ አለኝ፡፡ በዚህ ዲዛይን መሠረት መገንባት አለበት ብሎኛል፡፡ ይኸው ዲዛይኑ፡፡ - (ዲዛይኑን እያየች) እና በዚህ ዲዛይን መሰረት መሰራት አለበት ማለቱኮ በጣም ትክክል ነው፡፡ አሁን እርሶ መሠረቱ ምን ያህል ነው ያደረጉት፡፡ - ግማሽ ሜትር በቂ ነው ብዬ ግማሽ ሜትር አደረግኩት፡፡ - ሜትር ተኩል መደረግ አለበት በዲዛይኑ መሰረት፡፡ - ምን ያስፈልጋል? ግማሽ ሜትር ያደረግኩት ሰው አማክሬ ነው፡፡ - ምን ዓይነት ሰው ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ያ ወዳጃችን ታውቁት የለም? በጣም ታማኝ ነው፡፡ በካዛንችስ የራሱን ቤት አሰርቷል፡፡ እሱም መሰረቱን ግማሽ ሜትር ነው ያደረገው፡፡ - ክቡር ሚኒስትር በተለያየ አካባቢኮ የተለያየ አፈር ነው ያለው፡፡ - የእሱም እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ የሁለታችንም አንድ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ - ዲዛይኑ ላይ ምሰሶዎች አሉ፡፡ ቤቱ ግን ምሰሶዎች የሉትም፡፡ - የእኔ ልጅ በአሁኑ የብረትና የሲሚንቶ ዋጋ ያለምሰሶም ዋጋው አልተቻለም፡፡ - በዋጋ ምክንያት ምሰሶውን ከተዉት ይደረመሳል፡፡ ምን ዓይነት ወዳጅ ነው እንዲህ ያማክረዎት? - እጅግ በጣም ታማኝ ነው፡፡ ከምርጫው በኋላ በነበረው ግርግር ከእኛ አልተለየም፡፡ ከአቋሙም ዝንፍ አላለም፡፡ የክፉ ቀን ወዳጅ ነው፡፡ - በፖለቲካው ስለታመነ በምህንድስናውም ታማኝ ሆነ፡፡ - የእኔን አቅምና ችግር ያውቀዋል፡፡ ባጀቴን ይገነዘበዋል፡፡ በባጀቴ ልክ ያማክረኛል፡፡ - ፍሳሽ በየት በኩል ነው የሚሄደው? ቱቦዎቹ የት ነው የሚቀበሩት? ስፕቴክ ታንክሩ የት አለ? - እሱ ቀስ ብሎ ይሰራል፡፡ መጀመሪያ ግንቡ፡፡ ልጅህ ይህን ሁሉ ስትለፈልፍ አንተ ምነው ዝም አልክ? - እሷን አትስማት፡፡ እኔ በባለሙያ አሰራለሁ፤ ብዬ ያወጣሁት ገንዘብ እስካሁን ይቆጨኛል፡፡ በል በርታ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንመጣለን፡፡ የዘንደሮ ልጆች አወቅን አወቅን ነው የሚሉት፡፡ የሷን ነገር አትስማ፡፡ በትግሉ ጊዜ ካለመሃንዲስ ስንት መንገድ እንደሰራን መቸ ያውቁትና፡፡ ቻው ጌታዬ፡፡ - ቻው አመሰግናለሁ፡፡ (ከሳይቱ ሲመለሱ ክቡር ሚኒስትርና ልጃቸው ለደቂቃ ተኮራርፈው ዝም ተባባሉ፡፡ ቆይተው ንግግር ጀመሩ) - አንቺ ይህን ምላስሽን አትቆጣጠሪም፡፡ - መቸስ ምንጊዜም ይሁን የትም ይሁን በሽታችሁ አንድ ነው፡፡ - የማን በሽታ? - የእናንተ የኢሕአዴጎች በሽታ.. - ምን በሽታ? - ያለማዳመጥ በሽታ፡፡ - እንዴት ያለማዳመጥ በሽታ? ማንም ቀውስ መጥቶ ፉቲንግ ስሩ፣ ምሰሶ ገንቡ፣ ባለ ቁጥር መገንባት አለብን? - ለሰውዬው ብላችሁኮ አይደለም የምትገነቡት፡፡ ለራሳችሁ ቤት ጥንካሬና ዘላቂነት ብላችሁ ነው፡፡ - ይኸው ካለሰውየው ምክር ቤት እየተሰራኮ ነው፡፡ - ነገ ይደረመሳል፡፡ - ለምንድነው የሚደረመሰው? - ቤቱን የሚሸከም መሰረት የለውም፡፡ ጣሪያውን የሚሸከም ምሰሶ የለውም፡፡ - ሁለት ሰዎች ተመካክረው እየሰሩማ እንዲህ ልታንቋሽሺያቸው አትችይም፡፡ - ይኸውልህ ክቡር አባት ሚኒስትር፣ የፖለቲካ ታማኝነት የኢንጅነሪንግ እውቀት ሊሆን አይችልም፡፡ የታለየዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ታማኝ ፖለቲከኛ እየዘለለ ፓይለትና ዶክተር መሆን አይችልም፡፡ ራሱን የቻለ ለየት ያለ ሙያ ነው፡፡ ማንም ፓይለትና ዶክተርም እየዘለለ ፖለቲከኛ መሆን አይችልም፡፡ እሱም ለየት ያለ ሙያ ነው፡፡ - ያንቺ አስተሳሰብ ታማኝ ፖለቲከኛን የሚያሳጣ ነው፡፡ - ከይቅርታ ጋር ያንተ አስተሳሰብም ታማኝ ባለሙያ የሚያሳጣ ነው፡፡ - የመኖሪያ ቤት ፉቲንግና ምሰሶ አንሰራም ስለተባለ፡፡ - አይደለም፡፡ በጠቅላላ አመለካከታችሁ እንኳን ለግንብ ለራሱም ለኢሕአዴግም ፉቲንግና ምሰሶ የሚያሳጣው ነው፡፡ - እንዴት ብሎ? - ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው የሚያደርግ ምክር ከመስጠት ይልቅ መሰረቱንና ምሰሶውን ንዶ የሚደረምሰውን ምክር እያዳመጠ ስለሚውል፡፡ - እንዴት ተገለጠልሽ እባክሽ? - ይኸውልህ የእኔ ትዝብት በዚህ በክቡር ሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት ግንባታ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ኢምንት ነገር ነው፡፡ ጠቅላላ በአካሄዳችሁ ግን ምክር አትሰሙም፡፡ ሃቀኛ ሂስና ትችት አትወዱም፡፡ ተለውጣችኋል፡፡ አደገኛ ለውጥ ነው፡፡ - ምን ስላደረግን? - ይኸውልህ አባባ በቀደም ሙሉ ቀን የሳምንቱን ጋዜጣና መጽሄት ሰብስቤ ሳነብ ነበር፡፡ በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ ይሰነዘሩ የነበሩት አስተያየቶች በጣም ጠቃሚዎች ናቸው፡፡ በፀደቀው ሕግ ላይ የቀረቡት ወቀሳዎች ትክክለኛ ናቸው፡፡ የሴቶች መብት ተሟጋች ነን የሚሉ ሴቶች ያሉበት ፓርላማ ሴት አስገድዶ መድፈር በፍርድ ቤት የሞራል ካሳ አንድ ሺህ ብር ብቻ እንዲሆን አፀድቀው፣ ፕሬስ የባለሥልጣን ስም አጠፋ ከተባለ ግን የሞራል ካሳ አንድ መቶ ሺህ ብር ይቀጣል ብለው ሲያፀድቁ በእጅጉ የሚዘገንን ነው፡፡ ይህን ወቀሳ ያልተቀበላችሁ ምን ልትቀበሉ ነው፡፡ ይህ ሕግ ያረቀቀ ወዳጃችን ነው ስለምትሉ ግን ይህን የተቸ ጠላት ነው ትላላችሁ፡፡ - ታማኝ ደጋፊዎቻችንማ በየመንገዱ እያንገበገብን አንቃወምም፡፡ አቅፈን ይዘናቸው እንጓዛለን፡፡ - አስተዋጽኦ በሚያደርጉት ሁሉ ያደርጉ፡፡ የሁሉም ነገር ባለሙያ ናቸው ብላችሁ ግን አትውሰዱ፡፡ - አልገባኝም፡፡ - ይኸውልህ ዳዲ፣ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡ እዚህ ጎረቤታችን ያሉት አቶ ዮሐንስ ኢሕአዴግ ሲገባ ወህኒ ቤት የነበሩት ሶስት ልጆቻቸውን ለቆላቸዋል፡፡ አለአግባብ የተወረሰው ቤታቸውንም መልሶላቸዋል፡፡ ስደት የነበሩ ልጆቻቸውም ተመልሰዋል፡፡ አሁን ሞቅ ያለ ቤተሰብ ሆኗል፡፡ መላው ቤተሰብ ዕድሜ ለኢሕአዴግ እያለ ይኖራል፡፡ መቶ በመቶ የኢሕአዴግ ታማኝ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ - እንዴታ.. እንዴትስ አይሆኑም? - ታማኝ ደጋፊዎች ናቸው ማለት ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ ከሚገዛ ኤይርባስ ይገዛ ካሉ መንግሥት ይቀበላቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ታማኝ መሆን ሌላ ነው የአቪየሽንና የአየር መንገድ ባለሙያ መሆን ሌላ ነው፡፡ - በይ በይ አሁን ቤት ደርሰናል ምሳ ልብላና አንድ ስብሰባ አለኝ ልሂድ፡፡ - በዚህ በዝናብ የት ትሄዳለህ? ቤት ዋል እንጂ፡፡ (ምሳ እየበሉ ነው፡፡ ሃይለኛ ዝናብ ጣለ፡፡ በየአካባቢውም ሃይለኛ ጎርፍ ይፈስ ጀመር፡፡ ምሳ እንደጨረሱ ክቡር ሚኒስትሩ ሞባይል ላይ ስልክ ተደወለ፡፡ - ሃሎ፣ አንተ ማን ነህ? - የክቡር ሚኒስትር ወዳጅ ነኝ፡፡ - ማን ክቡር ሚኒስትር? - ጧት እኔ አልነበርኩም እንጂ እርስዎ ከልጅዎ ጋር መጥተው ያዩት የመኖሪያ ቤት እያስገነቡ ያሉት ሚኒስትር ጓደኛ ነኝ፡፡ - ይቅርታ፡፡ አዎን ጧት እዚያ ነበርን፡፡ አንተ ብዙ እንደምትረዳው አጫውቶኛል፡፡ - በአቅሜ ሁሉ እሞክራለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ግን እሳቸው ጎበዝ ስለሆኑ ብዙ ምክርም አያስፈልጋቸውም፡፡ አሁን ግን ችግር ገጠማቸው፡፡ - ምን ችግር? - በፊት የነበረው ኮንትራክተር ጤነኛ አልነበረም፡፡ ጥሩ ስላልነበር አሁን... - አሁን ምን? - አሁን እንዳለ ግንባታው ተደረመሰ፡፡ - መቼ? - አሁን አሁን ሃይለኛ ዝናብ እየዘነበ ነው፡፡ ጎርፉም ነው፡፡ - እና ምን ሆነ ነው የምትለኝ? በግልፅ ተናገር እንጂ፡፡ - ጎርፉ ይዞት ሄደ፡፡ - ምኑን? - ቤቱን.. - እየተገነባ ያለውን ቤት? - አዎን የመሰረቱ ድንጋይ ጎርፍ ስለወሰደው ምሰሶም ስለሌለው ተደረመሰ፡፡ - አሁን እሳቸው የት አሉ? - እሳቸው አይተውት ተናደው እየበረሩ ሄደዋል፡፡ እርስዎ እሳቸው ጋ ደውለው እንዲያጽናኑዋቸው ነው የደወልኩት፡፡ የመኪና አደጋ እንዳይደርስባቸውም ፈርቻለሁ፡፡ - እሺ ቻው፡፡ (ስልኩ ተዘጋ፡፡ ልጃቸው በስልክ መጯጯሁን ትሰማ ስለነበር ደንግጣ ወደ አባቷ መጣች) - አባዬ ምን ሆነህ ነው? - አይ ደህና ነኝ አንዱኮ ስልክ ደውሎ ነው፡፡ - ማን? - አሁን የነበርንበት ቦታ ባለቤት ጓደኛ፡፡ - እየተገነባ ያለው ቤት? - አዎን፡፡ - ምን አጋጠመ? ሚኒስትሩ ምን ሆኑ? ዝናብና ጎርፉ ደስ አላለኝም፡፡ ምን ሆኑ? - እሱ ምንም አልሆነም፡፡ - ታዲያ ምን አጋጠማቸው? - ያየሽው ቤት ተደረመሰ፡፡ - ምን? - ጎርፉ ወሰደው፡፡ ደስ አለሽ? - እንዴት ደስ ይለኛል? - ቅድም ስለው የነበረው ደረሰ ብለሽ ነዋ.. - እኔኮ ያልኩት እንዲፈርስ እፈልጋለሁ አይደለም፡፡ አሰራሩ ለአደጋ የተጋለጠ ነው፤ በባለሙያ አልተሰራም ነው ያልኩት፡፡ ታማኝነት ሌላ ሙያ ሌላ ነው ያልኩት፡፡ - ያልሽውማ ብዙ ነው፡፡ - አዎን ብያለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት አካሄድ እንኳን ለሕንጻ ግንባታ ለፖለቲካ ግንባታ፣ ለመንግሥት ግንባታ፣ ለአገር ግንባታ አይበጅም ነው ያልኩት፡፡ አሁንም ደጋግሜ እለዋለሁ፡፡ አንድ ዓይነት ችግር አንድ አይነት ብሶት እየታዘብኩ ነው፡፡ የሚጎድል ነገር አለ፡፡ - ምን ጎደለ? |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |