| በጎውን እናበረታታ እናጠናክር! |
|
|
| Sunday, 13 July 2008 | |
ጎጂውን እናውግዝ እናስወግድ!አካፋን አካፋ ማለትን መልመድ አለብን፡፡ የተፀናወተንን የማውገዝ ወይም በአጠቃላይ የማወደስና ማምለክ አባዜ ትተን አመለካከታችንና አገማገማችን “ስራህ ያውጣህ” የሚል መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው ጠንካራ ጎንን ማጠናከርና ደካማ ጎንን ማስወገድ የምንችለው፡፡ በአጠቃላይ መንግሥትን ወይም ገዢው ፓርቲን ስንመለከት በአጠቃላይ እንዳለ የምናመልክበት ወይም እንዳለ የምናወግዝበት አካሄድ መኖር የለበትም፡፡ የብሔር ብሄረሰቦች እኩልነት ማረጋገጡ፣ የበርካታ መንገዶችና የመብራትና የቴሌፎን አገልግሎት ማስፋፋቱ፣ በገጠርም በከተማም ትምህርት እንዲስፋፋ ማድረጉ፣ ባለፈው ያልነበረው ዴሞክራሲያዊ ሂደቶች ጅማሬዎች ማሳየቱ፣ የመሳሰሉት በርታ የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን ፖሊሲዎች ቢያሻሽል በርካታ ኢንቨስትመንት ሊገኝ በፖሊሲ ምክንያት ግን የተፈለገው የውጭ ኢንቨስትመንት ሊታይ አለመቻሉ፣ በአፍሪካ ደረጃ እንኳ ረዥም ርቀት ሊሄድ ይችል የነበረውን የፕሬስ ነፃነት፣ የመደራጀት ሂደት፣ የተቋማት ግንባታ፣ በምግብ ራስን የመቻል ዕድል፣ የተሻለ የአንድነት መንፈስ መፍጠር የመሳሰሉት እንደተፈለገው እንዳይሄድ በማድረጉ ይወቀስበታል፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሆነው አገርንና ሕዝብን ለማገልገል ቆርጠው የተነሱ መሾማቸው መንግሥትን ያስመሰግነዋል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ለአገር የማይጠቅሙ፣ ስግብግብና ሙሰኞች፣ ዓቅመ ሞራለ ቢስ ሹመኞች ይዞ መጓዝ፣ ይህን ለማሻሻል የሚረዳው በቂ መረጃ እያለው ለማስተካከል አለመሞከሩ በእጅጉ ይወቀስበታል፡፡ እንዲያስወግድም ይጮህበታል፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ቢሮክራሲ ሕዝቡን ለማገልገል ሲንቀሳቀሱ ይታያል፡፡ ኢምግሬሽንና የዜግነት መስሪያ ቤት በአሁኑ ጊዜ አሰራሩን ቀልጣፋና ቀላል ማድረጉ በገሃድ ይታያል፡፡ የውልና ማስረጃ መስሪያ ቤት ስራውን በቀላልና በተቀላጠፈ መንገድ ሲያካሂድ ይታያል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የአሰራር ቅልጥፍና እየታየ ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ ያልታየው በክልል ደረጃ መታየቱ ያስመሰግነዋል፡፡ እንዲያውም የምስራቅ ሸዋ ዞን በአገርም በክልልም ግንባር ቀደም ሆኖ መረጃ ለማግኘትና ለመስጠት የኔትዎርኪንግ እንቅስቃሴ መጀመሩ እንዲመሰገን ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ሌላው መሥሪያ ቤት የጉቦ፣ የዝቀተት፣ የመብት መጨፍለቅና መቀነስ ወኪል ሆኖ ሲንቀሳቀስ ሲታይ፣ እናወግዛለን ብቻ ሳይሆን መንግሥት እንዲያወግዝ መስሪያ ቤቱንም ሰውንም እንዲቀይርልን አቤት አቤት እያልን እንማፀናለን፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም እንዳሉ አናወግዝም፡፡ ሕግ አክብረው ሰላማዊ የትግል ስልት መርጠው ዓላማቸውንና ፍላጎታቸውን ግልፅ አድርገው ተከታይ አሰባስበው የሚታገሉ አሉ፡፡ በርቱ ተበራቱ እንላለን፡፡ ከዚህ በተፃራሪ ደግሞ ሕገወጥ ሆነው ዓመፅ አስነስተው እነሱ ራሳቸው ባህር ማዶ ሆነው ሌላው ሞቶላቸውና ቆስሎላቸው የስልጣን ቦታ ክፍት ሆኖ ኑ ብሎ እንዲጠራቸው የሚጠባበቁ አሉ፡፡ በፖለቲካ ፓርቲ ስም የአክስዮን ማሰባሰብና የአትራፊነት ቢዝነስ የሚያካሂዱ ስግብግቦችና አጭበርባሪዎች አሉ፡፡ ተጠያቂነት እንዳይነሳባቸው በትጥቅ ትግል ስም ሸፍነው የሚደበቁና የሚሸሸጉ አሉ፡፡ እነዚህ ዓይነት ደግሞ መወገዝና አካሄዳቸው መወገድ አለበት፡፡ ጅምላ ሙገሳ ወይም ጅምላ ውግዘት የለም፡፡ ባለሃብት ሆነውም ከውጭ አገር ተመልሰው አገር ለማልማት የሚፈልጉ አሉ፡፡ አገር ውስጥ ሆነውም ያገኙትን ሁሉ ለአገር ልማት ለማዋል ሌት ተቀን ቀና ደፋ የሚሉ አሉ፡፡ ሁሉም ነገር በሕጋዊ መንገድና በአግባቡ የሚሰሩ የልማት አጋር ባለሃብቶች አሉ፡፡ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ሌቦች ቀጣፊዎችና ነቀዞች አሉ፡፡ የአገር ሃብት የሚዘርፉ፣ የሚዋሹና የሚያጭበረብሩ እንዳሉ የዘመኑ ዜና ይፋ አድርጎታል፡፡ እንደዚህ ዓይነት እንዳይቀጥሉ እንዳይበረክቱና እንዳይኖሩ ሀይለኛና “አይምሬ” ትግል ያስፈልገዋል፡፡ ከትምህርት ተቋማት፣ ከጤና ተቋማት፣ ከገንዘብ ተቋማት፣ ብንመለከት የሚመሰገኑ አሉ፣ የሚወገዙ አሉ፡፡ ለአገር አስበው ጥሩ ዜጋ ለማፍራት የሚንቀሳቀሱ የትምህርት ተቋማት አሉ፤ ይመሰገናሉ፡፡ “የትም ፍጪው ገንዘቡን አምጪው” ብለው ገንዘብ ከፈሉ እንጂ ስለሰርተፊኬትና ድግሪ ማግኘት አትጨነቁ ብለው የሚቀልዱም አሉ፡፡ ጤና የሚያስቀድሙ የጤና ተቋማት አሉ፡፡ ገንዘብ ማስቀደም ብቻ ሳይሆን ገንዘብ እስከፈለ ድረስ የውጤት ወረቀት ለመፃፍ ዝግጁ ነን፤ ብለው ራሳቸውን ለሽያጭ ያዘጋጁ አሉ፡፡ ኧረ ስንቱ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሲታይም እንደዚሁ ለአገር ቆመው ገንዘብን አገልግለው የሚያልፉ አገርና ሕዝብ አኩሪ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከሃዲና አገር ሻጭ ሆነው ከጠላት ጋር ተመሳጥረው አገርን የሚወጉና የሚያጠቁም አሉ፡፡ የሚመሰገኑ አሉ፤ የሚወገዙ አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት አርአያ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ በራሱ ባለሥልጣኖቹ ውስጥ የሕዝብ አገልጋይ የሆነ የሚመሰገኑና በሕዝብና በአገር የሚቀልዱ ሊወገዙና ከሃላፊዎቻቸው ሊወገዱ የሚገባቸውን ገምግሞና ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ አገርና ሕዝብ የሚያገለግሉ ሊጠበቁ እንጂ ሊወገዙና ሊጠቁ አይገባም፡፡ መጠላት ብቻ ሳይሆን በመምሪያዎቹ ምክንያት የጥሩዎቹ በጎ መንፈስ እንቅስቃሴም ፍሬ አልባ በመጥፎዎቹ ምክንያትም የራሱ የገዢው ፓርቲ ሆነ በጎ ፍላጎትም ፍሬ አልባ ይሆናልና፡፡ ይህ ቆራጥ ውሳኔ ይፈልጋል፡፡ ምርጫውም ቀላል አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ተነካን ብለው የሚያኮርፉ፣ ሰም የሚያጠፉና የሚተናኮሉ ሰዎች ይፈጠረሉ፡፡ በሌላ በኩል የተሻለ አገልጋዮች መጡልን ብሎ የሚደሰት ይህ ለካስ መንግሥት ለካ ያዳምጠናል፡፡ ችግራችንን ያውቃል፣ ይፈታል፤ የሕዝቡ ወገንተኛ ነው፤ ብሎ መንግሥትን የሚደግፍ ሕዝብ ይኖራል፡፡ ምርጫው “ግለሰቦች ወይስ ሕዝብ” የሚል ነው፡፡፡ ለነገሩ ምርጫው ምርጫ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ከሕዝብ በላይ ማንም የለምና፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |