| ኢትዮጵያ በግብፅ የሚገኙ የኤርትራ... |
|
|
| Sunday, 13 July 2008 | |
|
ኢትዮጵያ በግብፅ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን ለመቀበል ጠየቀች
በጋዜጣው ሪፖርተር የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ዲሞክራሲያዊ ጥምረትንና የኤርትራዊያን ዓለም አቀፍ ወንድማማችነትን በግብፅ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን ስለመቀበልና ስለማጓጓዝ ስላለው ፈቃደኝነት ጉዳይ ማነጋገሩን አዌቴ ዶት ኮም ድረ ገፅ ዘገበ፡፡ እንደ አቶ ሰመረ ሀብተማርያም የኤርትራውያን ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ዳይሬክተር ገለፃ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ የግብፅን መንግሥት ማነጋገሩም ተገልጿል፡፡ አቶ ሰመረ ከኤርትራ ዲሞክራሲያዊ ጥምረት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ለድረ ገፁ ሲናገሩ “ይህ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለማምራት አነስተኛ እርምጃ ነው፡፡ . . . .እናም በሁሉም ኤርትራዊያን ትብብር ለኤርትራዊያን ሰቆቃ የተሻለ ሁሉን አቀፍ መፍትሔ ለመስጠት ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡ ግብፅ ኤርትራዊያንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ አፍሪካዊያንን ብትታገስም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥብቅ መቆጣጠርና በሺዎች የሚቆጠሩትንም ማሰር ጀምራለች፡፡ በሰኔ ወር ብቻ ግብፅ ከሰብአዊ መብት ድርጅቶች ተቃውሞ ቢገጥማትም 1,000 ያህል ኤርትራዊያንን ወደ ኤርትራ ተገደው እንዲጓዙና በደረሱም ጊዜ ለእስርና ግርፋት እንዲዳረጉ አጋልጣቸዋለች፡፡ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ተይዘው ወደ ኤርትራ የሚመለሱበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ናቸው፡፡ የግብፅ ጐረቤት ሊቢያም በበኩሏ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያንን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በዝግጅት ላይ ነች፡፡ የኤርትራ ዲሞክራሰያዊ ጥምረት ባሰራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ የሊቢያ መንግሥት ኤርትራዊያን ስደተኞችን በግዴታ ወደ ሃገራቸው እንዳይመልስ ያሳሰበ ሲሆን ምክንያቱን ሲያትት “ወደ ሃገራቸው በግዴታ ከተመለሱት ስደተኞች መካከል ጥቂቶቹ በጓደኞቻቸው ፊት በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ የተገደሉ መሆናቸውን አረጋግጠናል፡፡ ይህም የተደረገው ተመልካቾቹን ለማስፈራራትና ለማምለጥ እንዳይሞክሩ ለማድረግ ነው” ብሏል፡፡ እስራኤል ወደ 2000 የሚጠጉ አፍሪካዊያን ስደተኞች ያሏት ሲሆን ግማሹ በኤርትራ ድንበር በኩል የመጡ ኤርትራዊያን ናቸው፡፡ በርካታ ስደተኞች የእስራኤልን ድንበር ሲሻገሩ በግብፃዊያን ፖሊሶች ተገድለዋል፡፡ ድንበሩን ሲያቋርጡ የተያዙ ኤርትራዊያን ወይ ወደ ኤርትራ ተገደው ተጓጉዘዋል አልያም በግብፅ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እስራኤል አፍሪካዊያን ስደተኞችን ለሚወስድ አፍሪካዊ ሀገር ጥሪ ያቀረበች ሲሆን ስደተኞችን ለመቀበል ፈቃደኛ ለሆኑ አገሮች የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት እንደምትፈልግ ተዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያ አስቀድሞ በተንቀሳቃሽ ካምፖች ውስጥ በሰሜናዊ የኤርትራ ድንበር አካባቢ ባለና ሽመልባ በተባለ ሥፍራ የሚኖሩ 20,000 የሚጠጉ ኤርትራዊያን ስደተኞችን አስተናግዳለች፡፡ ማቆሚያ የሌለው ወታደራዊ ምልመላ፣ ተስፋ አስቆራጭ መፃኢ እድል፣ ምህረት አልባ ፖሊስ ሲደመሩ የኤርትራ መንግሥት የመሠረተው ሥርዓት ኤርትራን በዓለም ላይ ስደተኞች ወደ ውጭ በመላክ ተቀዳሚዋ ሀገር የሚያደርግበትን ተጨባጭ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |