| የአሥራ አንድ ዓመታቱ አሥረኞች |
|
|
| Sunday, 13 July 2008 | |
![]() ተስፋዬ ፀጋዬ ![]() ወይዘሮ ሀና ደሜ የዚያድ በሬ መንግሥት ወታደሮች በ1969 በኢትዮጵያ ላይ ወረራ አካሂደው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚያ ጦርነት ተማርከው በሶማሊያ የተለያዩ እሥር ቤቶች ከ11 ዓመታት በላይ ታስረው የነበሩ የቀድሞ ጦር አባላትና ሲቪሎች በአገር አቀፍ ደረጃ በማኅበር ለመደራጀት ችለዋል፡፡ አባላቱና ሲቪሎቹ “ሆርን ኦፍ አፍሪካ ኮንፍሊት ኤንድ ኮልድ ዋር ቪክተም አሶሴሽን” በሚል የተደራጁት ጉለሌ በሚገኘው የፖሊስ መኰንኖች ክበብ ስብሰባ አድርገው በጉዳዩ ላይ ውይይትና የሃሳብ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ፀጋዬ እንዳመለከቱት፣ በሶማሊያ እሥር ቤቶች የነበሩ ከሦስት ሺህ በላይ የቀድሞ ጦር አባላትና ሲቪሎች በመላ ሀገሪቱ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በማኅበሩ ለመታቀፍ እስካሁን የተመዘገቡት 15ዐዐ ያህሉ ናቸው፡፡ ምንም መተዳደሪያና ገቢ ለሌላቸው የማኅበሩ አባላት አቅም በፈቀደ መጠን በሕክምናና መልሶ በማቋቋም ላይ ያተኮረ እገዛ ለማድረግ መታቀዱን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡ በቶጎውጫሌ የእሥረኛ ሻለቃ ሦስተኛ ሻምበል አንደኛ ተነጣይ የመቶ ፈጥኖ ደራሽና የሰላማዊ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ምክትል ኮማንደር ጌታቸው ዘውዴ በሰጡት አስተያየት በወቅቱ በግንባር ተሰልፎ የነበረው ጦር ግማሹ ያህል ወደሌላ ግንባር በመዛወሩ ተመናመነ፣ ይህንንም አገጣሚ በመጠቀም የዚያድ ባሬ ሠራዊት በሁሉም አቅጣጫ ወረራ ማካሄድ ቀጠለ፡፡ ለወገን ጦር ስንቅም ሆነ ሌላ ሎጀስቲክ በጊዜው ሊቀርብለት ስላልቻለ ራሱን ሲከላከል ቆይቶ ምሽትን ተገን አድርጎ ከምሽጉ እየወጣ ራሱን ለማዳን ወደ ጅጅጋ መሸሽ ጀመረ፡፡ በመንገድ ላይ እንዳለም በሶማሊያ ወታደሮች ተለቃቅሞ ተይዞ ለእሥር ተዳረገ፡፡ እንደምንም አምልጦ ወደ ሐረር የባውም ጦር በመልሶ ማጥቃት ጊዜ በግንባር ተሰልፎ ግዳጁን በመፈፀም ላይ እንዳለ አብዛኛው ተሰዋ፡፡ “ሶማሊያ በማገኙት በተለያዩ እሥር ቤቶች ከአሥራ አንድ ዓመት በላይ ቆይታ በኋላ በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበር አማካይነት በ1981 ተለቀቅን ወደ አገራችን ተመለስን” ያሉት ምክትል ኮማንደር ጌታቸው ወደ አገር ቤት እንደገቡም በእሥር ላይ የቆዩበት ዘመን በአገልግሎት እንደሚያዝላቸው፣ የኮርስ ጓደኞቻቸው የደረሱበት ደረጃ እንዲደርሱና ባለሌላ ማዕረጎችም በያዙት ማዕረግ ላይ አንድ ማዕረግ ዕድገት እንዲያገኙ እንደሚደረግ ቃል መገባቱን፣ ይህም በጦሩ ክፍል ወዲያውኑ ተግባራዊ ሲሆን በፖሊሱ ክፍል ግን መዘግየቱን አስረድተዋል፡፡ በአንድ የሶማሊያ እሥር ቤት ብቻ 170 መደበኛ ጦር በግፍ እንደተገደሉና ከሞት የተረፈው እሥረኛ ደግሞ በ1975 አምስት ቀን የረሃብ አድማ መምታቱን በሦስተኛው ክፍለ ጦር የ18ኛ ሻለቃ የሕክምና ክፍል ሠራተኛ የነበሩት የአሥር አለቃ ዓለማየሁ እሬሶቦና አስረድተዋል፡፡ በ1980 መጨረሻ ላይ እሥር ቤት ውስጥ የሚገኘውን ሠራዊት ብዛት ከነማዕረጋቸው ጭምር በአማርኛና በእንግሊዝኛ ጽፎ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለኘሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በምስጢርና በልዩ ዘዴ እንዲደርስ ተደረገ፡፡ ወይዘሮ ሀና ደሜ በበኩሏ እንዳመለከተችው የስድስት ዓመት ሕፃን እንዳለች የሦስት ዓመት ሕፃን ከሆነችው እህቷና የሁለት ወር አራስ ከሆነው ወንድሟ ጋር በወራሪው ጦር ተይዛ ሀርጊሰ በሚገኘው እሥር ቤት ገባች፡፡ ከአሥር ቀን በኋላም አራሱ፣ ቀጥሎ ደግሞ እህቷ ሞቱ፡፡ ከዚህም ቀደም ሲል እናቷ ከወራሪው ጦር በተተኮሰው የከባድ መሳሪያ ጥይት ተመተው ወዲያውኑ እንደሞቱ፣ ከእሷ በአንድ ዓመት የምታንሰው ሌላው እህቷ በጠላት ጦር እንደተወሰደችና የፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ አባል የነበሩት አባቷ ደግሞ በውጊያው ላይ እንደተሰዉ አስረድታለች፡፡ ሀና በሶማሊያ የተለያዩ እሥር ቤቶች ለ11 ዓመት ያህል በቆየችበት ወቅት በእርሻ፣ በሰብል ጥበቃ፣ በልብስ አጠባ፣ በፅዳትና በልዩ ልዩ የጉልበት ሥራ ላይ ያሰማሯት እንደነበር ገልፃለች፡፡ መሀመድ አህመድ የተባለው ሌላው አስተያየት ሰጪ "በ1969 የሁለት ዓመት ሕፃን ነበርኩ፡፡ እናቴ በጀርባዋ አዝላኝ ሽሽት ላይ እንዳለን ግራ እጄ በጥይት ተመታ፡፡ እናቴም የሞትኩ መስሏት ጫካ ውስጥ ጥላኝ ሸሸች፡፡ ወዲያው የሶማሊያ ወታደሮች መጥተው አነሱኝ፡፡ የተንጠላጠለውንም እጄን በሕክምና ቆረጠልኝ፡፡ ሞቃዲሾ በሚገኘው ሴንትራል እሥር ቤት ለ11 ዓመታት ያህል ታሰርኩ" ብሏል፡፡ ከእስር ተፈቶ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለስ ወለጋ ነቀምት በሚገኘው የመካነ ኢየሱስ ሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ገብቶ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ተምሯል፡፡ የደርግ ሥርዓት ሲፈርስ ማዕከሉ ሊንከባከበው ባለመቻሉ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣና በአሁኑ ወቅትም ፒያሳ በሚገኘው የሕዝብ ንጽህና መጠበቂያ ውስጥ በጥበቃ ሥራ ሕይወቱን እየመራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |