| “ማዕከሉ የሚገባውን አላደረገልንም” |
|
|
| Sunday, 13 July 2008 | |
አቶ ቸርነት እሸቱ፣ አቶ ካሳዬ ተከስተ፣ አቶ ተረፈ ኃይሌ፣ አቶ አህመድ ሁሴን “ማዕከሉ የሚገባውን አላደረገልንም” አንዳንድ የስቃይ ሰለባዎች “እገዛ እያደረግን ነው” የስቃይ ሰለባዎች መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል አመራር አባላት በታደሰ ገብረማርያም የስቃይ ሰለባዎች መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከል የሕክምናና የመልሶ ማቋቋም አገልግሎት በአግባቡ እንደማያከናውንና ከተሰጠውም ፈቃድ ውጭ እንደሚንቀሳቀስና ይህ አይነቱም አካሄድ ለከፋ ችግርና ጉዳት እንደዳረጋቸው የስቃይ ሰለባ ከሆኑ የማዕከሉ ተጠቃሚዎች መካከል አንዳንዶቹ አስታወቁ፡፡ የማዕከሉ አመራር አባላት ደግሞ በደርግ ሥርዓት በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ የተለያየ ጉዳት ለደረሰባቸው 130 የስቃይ ሰለባዎች የመልሶ ማቋቋም፣ የሕክምናና ምክክር አገልግሎት በመስጠት የበኩሉን እገዛ ማድረጉን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ስቃይ እንዳይፈፀም ለማድረግ በሚያስችላቸው ተግባር ላይ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና ለዚህም እውን መሆን የአድቮኬሲና የካውንስሊንግ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ የስቃይ ሰለባዎቹ እንዳብራሩት፣ ማዕከሉ የተቋቋመውና የሥራ ፈቃድም ያገኘው በደርግ ሥርዓት በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ ስቃይ ለተፈጸመባቸው ወገኖች የሕክምናና የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለማከናውን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከተባበሩት መንግሥታት፣ ከአንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከዕርዳታ ሰጪ አገራት በርካታ የገንዘብ ዕርዳታ አግኝቷል፡፡ እነሱ ግን አገልግሎቱን በአግባቡ እንዳላገኙ፣ በዚህም ሳቢያ ለከፋ ችግርና እንግልት እንደተዳረጉ አስረድተዋል፡፡ አቶ ተረፈ ኃይሌ የተባሉት የስቃይ ሰለባ እንደገለጹት ማዕከሉ ወርቁ ሠፈርና ሽሮ ሜዳ በተባሉት ሁለት ጣቢያዎች ለ20 የስቃይ ሰለባዎች አገልግሎት የሚውሉ በድምሩ ስድስት የእህል ወፍጮዎችን አስተክሎ እንዲቋቋሙበት አድርጓል፡፡ ከ100ሺህ ብር በሚበልጥ ወጪ የተገዙት እነዚሁ ወፍጮዎች ያገለገሉና አሮጌ በመሆናቸው የተነሳ ሦስት ቀን ሰርተው ከአንድ ወር በላይ በብልሽት ሳቢያ ይቆማሉ፡፡ ይህ አይነቱም ሁኔታ የስቃይ ሰለባዎች ወደ ቦዘኔነት እንዲለወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ለወፍጮው መግዣ የዋለው ገንዘብ ከአንዲት የውጭ አገር በጎ አድራጊ በዕርዳታ የተገኘ ነው፡፡ በጎ አድራጊዋ ከሰጠች ከአንድ ዓመት በኋላ ተመልሳ መጥታ ተቋቋሚዎችንና የወፍጮዎችን ሁኔታ ስትመለከት በጣም ነው ያዘነችው፡፡ ፣እኔ ተለውጠው፣ ሕይወታቸው ጥሩ ሆኖና ተሻሽለው አገኛቸዋለሁ ብዬ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከቀድሞ በባሰ ሁኔታ ሆነው በማየቴ በጣም አዝናለሁ፣ በማለት ቅሬታዋን እንደገለጸች አስተያየት ሰጪው አስረድተዋል፡፡ የስቃይ ሰለባ የሆኑ 22 ወጣቶች በማውንት ፉዱ ቴክኒክ ኮሌጅ የሜካኒክነት ሙያ ሥልጠና ተከታትለዋል፡፡ ይሁን እንጂ እኩል ሰዓትና አንድ ዓይነት የሙያ ስልጠና የተከታተሉ ሌሎች ተማሪዎች በየወሩ 125 ብር ሲከፍሉ የስቃይ ሰለባዎቹ ግን በየወሩ 500 ብር ይከፍሉ ነበር፡፡ ማዕከሉ ከደንብና መመሪያ ውጭ የመክፈሉን ሁኔታም አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ አቶ ካሳዬ ተከስተ የተባሉት ሌላው የስቃይ ሰለባ በበኩላቸው ከዴንማርክ፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከጀርመንና ከአሜሪካ የመጣው ዕርዳታ ለእኛ ምንም አልፈየደልንም፣ አፋችንን አስከፍተው የወለቀውን ጥርሳችንን፣ ልዩ ልዩ የአካል ክፍሎቻችንና እግሮቻችን ፎቶግራፍ አንስተው በኤግዚቢሽን መልክ ያሳያሉ፡፡ የሕይወት ታሪካችንንም መለመኛ እያደረጉት ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አቶ አህመድ ሁሴን በበኩላቸው እንዳብራሩት በተፈፀመባቸው ስቃይ ሳቢያ እግራቸው ክፉኛ አብጧል፡፡ ከዚህ በፊት ማዕከሉ መድሃኒት በመስጠት ይተባበራቸው ነበር፡፡ ሆኖም ዕርዳታው ካቋረጠ ሶስት ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ምንም አይነት ሕክምና ባለማግኘታቸውም ስቃዩ እየበረታባቸው መጥቷል፡፡ ባለቤታቸውም በጡታቸው ላይ በተፈፀመባቸው ስቃይ የተነሳ ታመው ጥቁር አንበሣ ሆስፒታል ተኝተው በመታከም ላይ እንዳሉ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ለሕክምና ያወጡትን ማስረጃ ሰብስበው ለማዕከሉ በማቅረብ እርዳታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጥያቄያቸው ግን ተቀባይነት እንዳላገኘ ገልፀዋል፡፡ አቶ ቸርነት እሸቱ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪ ሶስት ወንድሞቻቸው በቀይ ሽብር እንደተገደሉባቸውና እናትና አባታቸውም በተከታታይ እንደሞቱ፣ እሳቸውና ባለቤታቸው ብቻ እንደቀሩ ተናግረዋል፡፡ ባለቤታቸው በመታመማቸው ወደ ማዕከሉ ለሕክምና እንደወስድዋቸው፣ ምርምራም ሲደረግላቸው ጽንስ እንዳላቸውና በዛ ላይ ደግሞ የታይፈስና ታይፎይድ በሽታ እንዳደረባቸው መረጋገጡንና ለበሽታው ፈውስ የሚሆን ክኒን እንደታዘዘላቸው ተናግረዋል፡፡ ክኒኑን መውሰድ በጀመሩ በሦስተኛው ቀን ሕመሙ እየፀናባቸው መጣ፡፡ በተለያዩ ሶስት ሆስፒታል እየተዘዋወሩ ሕክምና ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ ጽንሱ ስለተበላሸ እንዲጠረጉ ተደረገ፡፡ ይህም ሁሉ ሆኖ ምንም ዓይነት ፈውስ ባለማግኘታቸው በአሁኑ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተኝተው በመታከም ላይ ናቸው፡፡ “ምንም ገቢ የሌለኝ ደሀ በመሆኔ ለሕክምና እስካሁን ድረስ ያወጣሁት ታስቦ ማዕከሉ ዕርዳታ ያድርግለኝ ብዬ ባመለክት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ኢንጂነር ታደለ ብጡል የማዕከሉ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ እና የጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ “ማዕከሉ በሁለቱም ጣቢያዎች ያስተከላቸው ወፍጮዎች አዳዲሶች ናቸው፡፡ የተገዙትም ሦስት ፕሮፎርማዎች ቀርበው የተሻለውን በመምረጥ ነው፡፡ የወፍጮ ቤቱንም የስድስት ወር ኪራይና የኤሌክትሪክ ወጪ በቅድሚ ተከፍሎላቸዋል፡፡ ወፍጮዎቹ ምናልባት ሥራ ካቆሙ ለመጠባበቂያ በ22ሺህ ብር ጤፍ፣ ስንዴ ወዘተ፣ ተገዝቶላቸዋል፡፡ የየራሳቸውን ኮሚቴ አቋቁመው መርጠው ወፍጮዎቹንና እህሉን ተረክበዋል፡፡ የርክክቡም ሥነ ሥርዓት የተከናወነው የየቀበሌዎቹ አመራሮች በተገኙበት ነው” ብለዋል፡፡ በዚህ መልኩ ርክክቡን ካከናወኑ በኋላ ግማሾቹ ለሌላ ግለሰብ አከራዩት፣ ከፊሉ ደግሞ የቤት ኪራይና የተጠቀሙበትን የኤሌክትሪክ ፍጆታ መክፈል አቃታቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የኤሌክትሪክ መስመር ተቆረጠባቸው፡፡ ቤቱን ያከራዩት ሰዎች የተቆረጠውን የኤሌክትሪክ መስመር አስቀጥለው አከራዮቹ እየተገለገሉበት እንደሚገኙ ኢንጅነር ታደሰ ተናግረዋል፡፡ የስቃይ ሰለባ ለሆኑ 22 ወጣቶች በማውንት ፉድ ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የሜካኒክነት ሙያ ሥልጠና የተከታተሉት በየወሩ 125 ብር እየተከፈለ ነው፡፡ ከተመረቁም በኋላ ለመቋቋሚያ በነፍስ ወከፍ 749 ብር በድምሩ ከ16ሺህ ብር በላይ ተሰጥቶቸዋል፡፡ ገንዘቡን ከተከፋፈሉ በኋላም ጠፍተዋል፡፡ ሥራ ፈልጎ የማግኘት የእነሱ ፈንታ እንጂ የማዕከሉ ግዴታ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡ አቅም በፈቀደ መጠንም የዕይታ ችግር ላለባቸው ልዩ ልዩ አይነት መነጽሮች ተገዝቶ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የመራመድ/ የመንቀሳቀስ እክል ላጋጠማቸው ሰው ሰራሽ እግር ገብቶላቸዋል፡ ጥርሳቸው የወላለቀባቸው አርቴፊሻል ጥርስ ተገጥሞላቸዋል፡፡ ጫማ ለሚያስፈልጋቸው ይህም ተሟልቶላቸዋል፡፡ ከምክክር አገልግሎት ባሻገር መደበኛ ሕክምና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ አገልግሎት የተሰጠው በማዕከሉ ገንዘብ ስለሆነ ለማስረጃ ያህል ፎቶግራፍ መነሳት ግድ ይሆናል፡፡ ይህንንም ፎቶግራፍ ሰኔ 9 ቀን 2000 በተካሄደው ዓለም አቀፍ የስቃይ ሰለባ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዕለት በኤግዚቢሽን መልክ ቀርቦ እንዲታይ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውጭ በሌላ ቦታ የታየበት ጊዜ የለም፡፡ ክሊኒኩም የተቋቋመው እንደማንኛውም መደበኛ ክሊኒክ ቁስል ለማከምና መርፌ ለመውጋት ሳይሆን መሰረታዊ የስነ ልቦና የምክክር አገልግሎት ለመስጠት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ “ማዕከሉ ለስቃይ ሰለባዎቹ ይህንን አገልግሎት ሊሰጥ የቻለው ለመጀመሪያ ጊዜ በዕርዳታ ባገኘው 60ሺህ ብር ነው፡፡ የተቋቋመውም በደርግ ሥርዓት የተሰቃዩትን ወገኖች ብቻ ለማቋቋም አይደለም፡፡ የተሰጠውም ፈቃድ ለዚህ አይደለም፡፡ ገና ሲጀምር ለመነሻ ያህል በደርግ የስቃይ ሰለባዎች ላይ ሆነ እንጂ ማንም ስቃይ የደረሰበትን ሁሉ አቅም በፈቀደ መጠን ለመርዳት የተቋቋመ ማዕከል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ “በዚህም የተነሳ የ1997 ምርጫን ተከትሎ በተነሳው ግርግር አይኑ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን አንድ ወጣት ደቡብ አፍሪካ በመላክ የቀዶ ሕክምና እንዲያገኝ አድርገናል.. ያሉት ኢንጂነር ታደለ ለሊቢያ ተፈናቃዮች የማቋቋሚያ፣ ለኤርትራ ተፈናቃዮች ደግሞ የሕክምና፣ የመድሃኒት አቅርቦትና የምክክር አገልግሎት በመስጠት የተሻለውን ያህል እንደተንቀሳቀሰ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዕርዳታ ሰጪዎች ለዚህ አይነት ተግባር የሚያደርጉትን እገዛ አቁመዋል፡፡ የትኩረት አቅጣጫው በግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር ላይ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ይህ አይነቱ ስቃይ በድጋሚ በአገር ውስጥ እንዳይከሰት የሚያስገነዝብ የንቃተ ሕሊና ማጎልመሻ ትምህርት ማዕከሉ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ በአዲስ አበባ፣ በአዳማና በባህርዳር ከተሞች ለሚገኙ የሕግ አካላትና ጠበቆች የግንዛቤ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ ወደፊትም በሌሎች ስድስት ከተሞች ተመሳሳይ ትምህርት ለመስጠት ታቅዷል፡፡ የማዕከሉ እንቅስቃሴ እንዲገመገም ከፍትህ ሚኒስቴር በተላለፈው መመሪያ መሰረት ሰባት አባላት ያሉበት አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሰፋ ያለ ግምገማ አካሄዷል፡፡ በግምገማውም መሰረት ማዕከሉ ሕጋዊና አግባብነት ያለው ተግባር እያከናወነ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህም ውጤት ለሚኒስትሩ በሪፖርት መልክ ቀርቦላቸዋል፡፡ ሚኒስትሩም የአቤቱታ አቅራቢዎች ጥያቄዎችንም ተጨባጭ እውነታ የሌለው ስለሆነ ማዕከሉ የተለመደውን ሥራ መቀጠል ይችላል የሚል መልስ መስጠታቸውን ከኢንጅነር ታደሰ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዶክተር ያሬድ ጥላሁን የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ማዕከሉ ለስቃይ ሰለባዎች አገልግሎት የሰጠበትን ገንዘብ በዕርዳታ ያገኘው “ዩናይትድ ኔሽን ቮለንተሪ ፈንድ ፎር ቪክትምስ ኦፍ ቶርቸር ከተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቅርንጫፍ ነው” ብለዋል፡፡ እንደ ቅርንጫፉ መሥሪያ ቤቱ አተረጓጎም የስቃይ ሰለባ (ቪክትምስ ኦፍ ቶርቸር) ማለት ጉዳቱ የደረሰበት ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡንም ጭምር እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ማዕከሉ እስካሁን ድረስ ለበርካታ የስቃይ ሰለባዎች የመልሶ ማቋቋሚና የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን፣ ይህም ሁኔታ ሊቀጥል የሚችለው ዕርዳታ ሰጪዎች እስካመኑበት ድረስ መሆኑን፣ እስካሁን ያደረገው እንቅስቃሴ ውጤት አለማምጣቱን ይህም ሊሆን የቻለው የዕርዳታው ተጠቃሚዎች የጥገኝነት አመለካከት እያሳዩ በመምጣታቸው የተነሳ መሆኑንና በዚህም ምክንያት የትኩረት አቅጣጫውን ወደ ካውንስሊንግ ማተኮር ግድ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |