| ፣የዓመቱ ምርጥ የፈጠራ ሴት፣ |
|
|
| Sunday, 13 July 2008 | |
![]() ሃና ፀጋዬ "መንገድ ላይም ይሁን በማንኛውም ቦታ የሰዎችን አለባበስ በትኩረት እመለከታለሁ፡፡ እዚህ ጋር እንዲህ፣ ቀለሙ የዚህ ዓይነት ቢሆን ብዬ አስባለሁ፡፡ የማውቀው ሰው ከሆነ ደግሞ አስተያየት እሰጣለሁ፡፡ ማንኛውም ሰው በሄደበት ሁሉ ከሙያው ጋር የሚገናኙ ነገሮችን ማስተዋሉ አይቀርም፡፡ የምገዛቸው ልብሶችንም ቢሆን በምፈልገው መንገድ አስተካክላቸዋለሁ" ትላለች ፣የዓመቱ ምርጥ የፈጠራ ሴት፣ ተብላ ሽልማት ማግኘት የቻለችው የልብስ ዲዛይነር፡፡
የሃያ ሰባት ዓመቷ ሃና ፀጋዬ የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ከዓለም አቀፍ አእምሮአዊ ንብረት ድርጅት፣ ከኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎችና ከፈጠራ ሥራ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ሚያዚያ ሀያ በብሔራዊ ቴአትር ባካሄደው ዝግጅት ላይ ዲዛይነሯ ፣የዓመቱ ምርጥ የፈጠራ ሴት፣ በመባል የወርቅ ሜዳሊያና የአሥር ሺህ ብር ተሸላሚ ለመሆን ችላለች፡፡ በሙሉ ለሽልማት ያበቃት ምን እንደሆነ ሀናን ጠየቅናት፡፡ "ዝግጅቱ እንደሚካሄድ አውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ለሽልማት እበቃለሁ የሚል ሀሳብ ፈፅሞ አልነበረኝም፡፡ ቆዳን ከአገር ባህል ጥበብ ልብስ ጋር በመደባለቅ የተለያዩ ልብሶችን ሠርቼ ነበር፡፡ በዚህም ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጥበቃ የባለቤትነት ማረጋገጫ አግኝቼ ነበር፡፡ ለሽልማት ያበቃኝም ይኸው የፈጠራ ሥራዬ ነው" ተሸላሚ መሆኗ በሥራዋ ያገኘችው አስደሳች ውጤት ከመሆኑ ባሻገር በልብስ ዲዛይኒንግ ሽልማት ካገኙት መካከል ብቸኛዋ ሴት መሆኗ የተለየ ስሜት እንዳልፈጠረባት ትናገራለች፡፡ ለዚህ ምክንያት ነው የምትለው ደግሞ መሥራት እንዳለባት ያመነችበትን ነገር ከዳር ለማድረስ እንደምትጥርና በሴትነቷ ያሰበችውን ከማድረግ የሚያግዳት ሁኔታ ይኖራል ብላ የማትሰጋ መሆኗን ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ የልብስ ዲዛይን ለመማር በወሰነችበት ወቅት ቤተሰቦቿ ዝንባሌዋን ቀደም ብለው በመረዳታቸው ምንም ዓይነት ጫና እንዳላሳደሩባት የምትናገረው ሀና የልብስ ዲዛይን ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ሥራ ስትገባ ዲዛይን ያደረገችውን ልብስ መስራት በጣም ከባድ ሆኖ እንዳገኘችው አልደበቀችም፡፡ ያነጋገርናት ዲዛይን ያደረገቻቸውን ልብሶች በምትሸጥበት ሱቅ ሲሆን ተሰቅለው የተመለከትናቸው ልብሶች በአጠቃላይ የሴቶች ናቸው፡፡ ፋሽን ያለው የሴቶች ልብስ ላይ በመሆኑ፣ እሷም ዘወትር የምትሰራው የሴቶችን ልብስ ብቻ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የምትሰራቸው ልብሶች ቀላልና በማንኛውም ወቅት፣ ከማንኛውም ልብስ ጋር ሊለበሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በበርካታ ሥራዎቿ የጥበብ ልብስን ቆዳን ጨምሮ ከሌሎች ጨርቆች ጋር መደባለቅ ታዘወትራለች፡፡ እንደዛጐል፣ የዶሮ ላባ፣ የተለያዩ ስፌቶችን (ሰፌድና) ባሕላዊ ጨርቃ ጨርቆችን በልብስ ፋሽን ዝግጅቶች ወቅት ትጠቅማለች፡፡ "ከሸማኔዎች ጋር መሥራት በሥራዬ የገጠመኝ ፈታኝ ነገር ነው፡፡ የነገርኳቸውን የጥበብ ዓይነት ወደ ጐን ትተው የመሠላቸውን ይሠራሉ፡፡ በቀጠሮ አለማድረስ፣ የተፈለገውን መጠን አለመጠበቅና ቀለም መቀየር እለት ከእለት የሚገጥመኝ ችግር ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች የተሰማኝን ስሜት በንዴትና በጩኸት ከመናገር ወደኋላ አልልም" በማለት በተጠቀሱት ምክንያቶች የተቀበለችውን ቀብድ የምትመልስበትና ከደንበኞች ጋር አለመግባባት የሚፈጠርበት አጋጣሚ ጥቂት አለመሆኑን ትገልፃለች፡፡ ሀና እንደምትለው፣ የልብስ ዲዛይነር ማለት ዲዛይን አድርጐ፣ ጨርቅ ቆርጦ የሚሰፋ ባለሙያ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ዲዛይን የሚያደርግ ብቻም የልብስ ዲዛይነር የሚባልበት ሁኔታ አይጠፋም፡፡ ለዲዛይነሮች ልብስ ዲዛይን ማድረግ እንዳለ ሆኖ የጨርቅና የቀለም አመራረጥ ማወቅም መሠረታዊ ነው፡፡ አንድን ሰው የልብስ ዲዛይነር ለማለት ይህ ነው ተብሎ የተቀመጠ ነገር ባይኖርም ለሙያው አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮችን የሚያውቅና በሙያው የሰለጠነ መሆን አለበት፡፡ ዲዛይን የምታደርጋቸውን ልብሶች ወደ ምትሸጥበት ሱቅ የሚሔዱ አብዛኞቹ ደንበኛዎች ሥራዋን በሚያውቁ ሰዎች ጥቆማ እንደሆነና ራሷ ከምትሰራቸው የልብስ ዓይነቶች ውጭ በራሳቸው ፍላጐት ለማሠራት ደንበኞች የሚሰጡትን ትእዛዝ በአግባቡ በመቀበል እንደምትሰራ አመልክታለች፡፡ የደንበኞችን ትእዛዝ በመቀበል የእሷንም ሙያዊ አስተያየት በማከል መሥራቷ የደንበኞችን ፍላጐት ከማሟላት ባሻገር ለሷም የሚጨምርላት ነገር መኖሩን ገልፃለች፡፡ ለሥራዎቿ ደማቅ ቀለም ያላቸውን ጨርቆች ትመርጣለች፡፡ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካገኘችበት ፈጠራዋ ውጪ ያሉ ሥራዎቿ ሁሉ ብዙ ስለደከመችባቸው ትልቅ ቦታ እንደምትሰጣቸው ትናገራለች፡፡ የልብስ ዲዛይኒንግ ሙያ በአገራችን አለማደጉ ከሚንፀባረቅባቸው ነገሮች መካከል የተለያዩ ዲዛይነሮች የፈጠራ ሥራ በሌሎች የልብስ ዲዛይነሮች ተመሳሳይ ተደርጐ መሠራቱ እንደሆነ አስረድታለች፡፡ የራሷ ሥራዎች በተመሳሳይ መሠራታቸውን፣ ሱቋ ድረስ በመምጣት ለማሳያ የተሰቀሉ ሥራዎቿ ፎቶ ግራፍ ተነስተው በተመሳሳይ ተሰርተው ተመልክታለች፡፡ ከባለሙያው ውጭ ካሉ ነገሮች ይበልጥ ምንም እንኳ የተቀመጠ ደንብ ወይም የአሰራር ልምድ ባይኖርም በባለሙያው ራሱ የሌላውን የሙያ አጋሩን የፈጠራ ስራ አለማክበር ሙያው እድገት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድር አስረድታለች፡፡ የሀያ ሠባት ዓመቷ ዲዛይነር ሀና ከስድስት ዓመታት በፊት ወደ ልብስ ዲዛይኒንግ ሙያ መግባቷን ትናገራለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታና የተለያዩ የልብስ ዲዛይኖች ቢታዩም ሙያው እድገት አሳይቷል ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ አለመኖሩን አመልክታለች፡፡ ሕብረተሰቡ ለፋሽንም ሆነ ለልብስ ዲዛይን ያለው አመለካከት ወደ ሙያው በገባችበት ወቅት ከነበረው ብዙም የሚለይ አለመሆኑን በቁጭት ገልፃልናለች፡፡ የሙያው አለመታወቅ፣ የዲዛይነሮችን የፈጠራ ሥራ ተቀብሎ ለመልበስ አለመፈለግ ባለሙያውን ከማያበረታቱ ነገሮች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው እንደ ዲዛይነሯ ገለፃ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |