Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 28th
Home arrow Sections arrow እስራኤል በኢራን ላይ እርምጃ...
እስራኤል በኢራን ላይ እርምጃ... Print E-mail
Sunday, 13 July 2008

እስራኤል በኢራን ላይ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷን ገለፀለች
በጋዜጣው ሪፖርተር

እስራኤል ጥቃት ይደርስብኛል የሚል ስጋት ካደረባት በኢራን ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተዘጋጀች መሆኗን መከላከያ ሚኒስትሩ ገለፁ፡፡

 

የኢራንን የሚሳኤል ሙከራ አስመልክተው በቴልአቪቭ መግለጫ የሰጡት መከላከያ ሚኒስትሩ ኢሁድ ባራክ "እስራኤል የደህንነት ሁኔታዋ ስጋት ላይ የወደቀ ከመሰላት ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰድ እንደማትገታ ባለፉት ጊዜያት አረጋግጣለች" በማለት በአሜሪካና በእስራኤል ላይ ውጥረት ለፈጠረው የኢራን የሚሳኤል ሙከራ አገራቸው አፀፋውን ልትመልስ እንደምትችል አመልክተዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ወደ ሌላ አማራጭ ከመሄድ በፊት የዲኘሎማሲ መፍትሄ መከተል እንደሚያስፈልግ ባራክ ሳይገልፁ አላለፉም፡፡

"በአሁኑ ሰዓት ትኩረቱ ሁሉ በኢራን ላይ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀብ እንዲጣልባትና ጠንካራ ዲኘሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እንዲደረግባት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ አካሄድም እስከ መጨረሻው ድረስ መቀጠል አለበት" ብለዋል፡፡

ኢራን ከአራት ቀን በፊት የሚሳኤል ሙከራ ያደረገች ሲሆን ከተሞከሩት ሚሳኤሎች አንዱ እስራኤል የመድረስ አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡

የኢራን መገናኛ ብዙሀን እንዳስታወቀው በመጀመሪያው ቀን የተከናወነው የሚሳኤል ሙከራ (ሻሀብ-3 ሚሳኤል) ሁለት ሺ ኪሎ ሜትር ዘልቆ ጥቃት ማድረስ ይችላል፡፡ ሚሳኤሉም ከምድር ወደ ባህር ከምድር ወደ ምድር እና ከባህር ወደ አየር እንደሚወነጨፍ ተገልጿል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንደሊዛ ራይስ ጉዳዩን በማስመልከት ሲናገሩ "ዩናይትድ ስቴትስ በክልሉ ያላትን የፀጥታ ኃይል አጠናክራለች፡፡ ኢራንም አሜሪካ ስላላት አቅም ፣መደናገር፣ አይገባትም" ብለዋል፡፡

እስራኤል በበኩሏ በኢራን ላይ ስለላ ማካሄድ ይችላል ያለችውን ዘመናዊ የጦር አውሮኘላን በሰማይ ላይ እያበረረች በማሳየት ለኢራን የሚሳኤል ሙከራ አፀፋ መልሳለች፡፡

መንግሥት የሚቆጣጠረው የእስራኤል ኤይሮስፔስ ኢንዱስትሪ የኤይታም አውሮኘላን የተጠናቀቀው ባለፈው ዓመት መሆኑን ገልፆ አወሮኘላኑ እጅግ በተራቀቀ መልኩ የስለላ ሥራ እንዲያከናውን ተደርጐ መስራቱን ገልጿል፡፡

ከኢራን ጋር ብቻ ሳይሆን ከሶሪያና ፍልስጤም ጋር ያለው ሁኔታ ውስብስብ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ባራክ "ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት እንሞክራለን ካልሆነ ግን አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት ጠላቶቻችን ድባቅ መምታት አለብን" ብለዋል፡፡

ባራክ እንደሚሉት እስርኤል በኢራን ላይ እርምጃ በምትወስድበት ጊዜ የኢራን ደጋፊ የሆኑ አገራት ሊፈፅሙ የሚቻሉትን ምላሽ ትኩረት ውስጥ ታስገባለች፡፡

"የጠላቶቻችንን ምላሽ ትኩረት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡ ሀማስ፣ ሂዝቦላህ፣ ሶሪያውያኖችና ኢራውያኖች ሁላቸውም ከአጠገባችን ሆነው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ለግጭት ያለው ሁኔታም የሰፋ ነው"

ይህ በእንዲህ እያለ የኢራንን የሚሳኤል መከራ የሚያሳየው ምስል በዲጂታል መሳሪያ የተቀነባበረ መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ኘሬስ ገልጿል፡፡

በኢራን ሪቮሊዩሽነሪ ጋርድ ድረ ገጽ የተቀመጠውና ቢቢሲን ጨምሮ በብዙ የሚዲያ ድርጅቶች የሚታየው ፎቶ ግራፍ አራት ሚሳኤሎች ከበረሀ ተነስተው ሲወነጨፉ ያሳያል፡፡ ነገር ግን ተመሳሳይ ምስል የያዘው አሶሽየትድ ኘሬስ ኢራን የሞከረችው አንድ ሚሳኤል በላውንቸሩ ላይ እያለ በእሳት ሲቃጠል ያሳያል፡፡

የቢቢሲው ድረ ገጽ የስዕል ኤዲተር ፊል ኩምስ አስተያየቱን ሲሰጥ "ከአጃንስ ፍራንስ ኘሬስ የተገኘውን ምስል ከመረመርነው የተወሰነው የሚሳኤል ሙከራ ምስል የተቀነባበረ መሆኑ በግልጽ ይታያል" ብሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እስራኤልና ኢራን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎቻቸውን በመሞከርና በማሳየት ወታደራዊ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ግን ወታደራዊ እንቅስቃሴያቸው በሙሉ የሚከናወነው ራሳቸውን ለመከላከል በማሰብ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

የእስራኤል አየር ኃይል ሰሞኑን በሜዲትራንያን ባህር ላይ ከፍተኛ የጦር ልምምድ አድርጓል፡፡ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት የእስራኤል የጦር እነቅስቃሴ በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈፀም ከማቀድ ጋር የተገናኘ ይመስላል፡፡ ኢራን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ በመገንባት ላይ መሆኗን እስራኤል ታምናለች፡፡ ኢራን ግን የኒዩክሌር ኘሮግራሟ ለኃይል ማመንጫ አገልግሎት ብቻ እንደሚውል ትናገራለች፡፡ የምዕራብ አገራት በበኩላቸው ኢራን ለኒዩክሌር ግንባታ የሚውለውን ዩራኒየም መጠቀም እንድታቆም ለማግባባት ሲሞክሩ ቆይተዋል፡፡ ኢራን ግን በተመድ እና በአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ቢጣልባትም ወይ ፍንክች ብላለች፡፡

በሌላ በኩል ኢራን በዚህ ሳምንት ያካሄደችው የሚሳኤል ሙከራ ዩናይትድ ስቴትስ በአወሮፓ ልትገነባው ያሰበችው የሚሳኤል መከላከያ አላስፈላጊ መሆኑን እንደሚያመላክት የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቨሮቨ ገልፀዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንደሚሉት ኢራን የሞከረችው ሚሳኤል 2ዐዐዐ ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ የሚጓዝ በመሆኑ አውሮፓ ውስጥ ፀረ ሚሳኤል መገንባት አያስፈልግም፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ እራሷንና አጋሮቿን የሚሳኤል ጥቃት ሊፈፅሙ ከሚችሉ ፣ሰይጣናዊ አገሮች፣ ለመከላከል በፓላንድና ቼክ ሪፐብሊክ የሚሳኤል መከላከያ መገንባት እንደምትፈልግ ትገልፃለች፡፡

ከሚሳኤል ሙከራው በኋላ ከተለያዩ አገሮች ውግዘት የደረሰባት ኢራን ለመወያየት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች፡፡

የአገሪቱ ዜና ወኪል እንደገለፀው ኢራናዊው ተደራዳሪ ሰኢድ ጃሊሊ ከአንድ ሳምንት በኋላ ከአውሮፓው ህብረት መልዕክተኛ ሀቪየር ሶላና ጋር በጂኔቫ ለመገናኘት አቅደዋል፡፡ የሀቪየር ሶላና ቢሮ ግን በጉዳዩ ላይ ማረጋገጫ አልሰጠም፡፡
 
< Prev   Next >