| ዓድዋ ላይ ምልክት ለማስቀመጥ |
|
|
| Wednesday, 16 January 2008 | |
|
ኮምፓክት ሪከርድስ በተባለው ድርጅቱ አማካኝነት ከሌላ ድርጅት ጋር በመሆን ለሥራ ወደ ትግራይ በሄደበት አጋጣሚ የዓድዋ ኗሪዎች የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበትን ሥፍራ ሲያሳዩት ቦታው ዓድዋ መሆኑን የሚያመላክት ጽሁፍ የማስቀመጥ ሃሳብ እንደመጣለት ይናገራል ወጣት ሰለሞን ግርማ፡፡ ..ቀደም ሲል ስለ አድዋ በትምህርት ቤትና በተለያዩ ሚዲያዎች የሰማሁት ትልቅ ነገር ነበር፡፡ በቦታው ተገኝቼ ሥፍራውን የአካባቢው ኗሪዎች ሲያሳዩኝ የአድዋ ተራሮች ራሳቸው በጦርነቱ ሚና ነበራቸው የሚል እንዲሁም በዚያ ጦርነት ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉ ጀግኖችን የማግኘት ስሜት ተሰማኝ፡፡ በተቃራኒው ቦታው ላይ ፎቶግራፍ ለመነሳት ሳስብ አድዋ መሆኑን የሚገልጽ ምንም አይነት ነገር አለመኖሩ ደግሞ ቅሬታ ፈጠረብኝ.. ይላል ሁኔታውን ሲያስታውስ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ለሦስት ወራት ያህል በጉዳዩ ላይ ሲያስብበት ከቆየ በኋላ ለትግራይ ባህልና ቱሪዝም ኮሚሽን አድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ በይበልጥም የአድዋ ጦርነት የተካሄደበት ገሠሠው ተራራ ላይ አድዋ የሚል ጽሁፍ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የማስቀመጥ ሃሳብ እንዳለው የሚገልጽ ደብዳቤ ፃፈ፡፡ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮም ሀሳቡን እንደሚደግፈውና አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ የሚገልጽ መልስ እንደሰጠው ገልጿል፡፡ ከዚህ በኋላ ዓድዋ ላይ ምልክት የማስቀመጥ (የዓድዋ ላንድ ማርክ) ፕሮጀክትን ቀርፆ ለክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኮሚሽን በማስገባት ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ እንደ ወጣት ሰለሞን ገለፃ፣ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር የተደረገው ስምምነት የአድዋ ላንድ ማርክ ፕሮጀክት ሃሳብ ባለቤት እሱ መሆኑንና ከአድዋ ሰንሰለታማ ተራራዎች ገሠሠው ተብሎ በሚጠራው ተራራ ላይ አድዋ /ኤ.ዲ.ደብሊዉ.ኤ/ የሚል ጽሁፍ እንዲቀመጥ መታሰቡንና ለዚህ ፕሮጀክት መሳካትም እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ከሰንሰለታማ የአድዋ ተራራዎች የአድዋ ጦርነት የተካሄደበት ሥፍራን የሚወክለው የትኛው ነው? የሚለው ላይ የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ኮሚሽን ባካሄደው ጥናት መሠረት ገሠሠው ተራራ ላይ አድዋ የሚል እያንዳንዱ ፊደል መቶ ካሬ የሆነ ጽሁፍ የማስቀመጥ ሃሳብ ላይ የተለያዩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁራንን አነጋግሯል፡፡ ጽሁፉ ምን አይነት ይዘት ሊኖረው እንደሚችል፣ የመሬቱን የመሸከም አቅም እንዲሁም የአካባቢውን የንፋስ ሁኔታና ጽሁፎቹ በምን ዓይነት ጥሬ ዕቃ ሊሰሩ እንደሚችሉ በሚመለከት ጥናት ለማካሄድ ሁለት መቶ ሺህ ብር የሚገመት ገንዘብ ይጠይቅ ነበር፡፡ ቢሆንም ኮንስትራክሽን ዲዛይን አክስዮን ማኅበር የተባለ መንግሥታዊ ድርጅት የአድዋ ላንድ ማርክ ፕሮጀክት አገራዊና ትልቅ ጉዳይ መሆኑን በማመን ከትራንስፖርትና ከውሎ አበል ውጭ የስትራክቸር ጥናቱን በነፃ እንዳደረገ ሰለሞን አመልክቷል፡፡ በፕሮጀክቱ ተፈፃሚነት ላይ ከትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ኮሚሽን ጋር ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ስለ ሁኔታው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር መሀሙድ ድሪርን እንዳነጋገራቸውና ከጎኑ እንደሚቆሙ ቃል በመግባት ቀና ምላሽ እንደሰጡት ገልጿል፡፡ ..ዓድዋ አገራዊ ጉዳይ በመሆኑ ፕሬዚዳንቱ ይህን ፕሮጀክት ሊያውቁት ይገባል በሚል ወደ ፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት አመራን፡፡ የሚደግፉት ሃሳብ እንደሆነ ገለፁልን፡፡ እኛም የፕሮጀክቱ የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ ጥያቄ አቀረብንላቸው ተስማሙ.. ብሏል፡፡ የፕሮጀክቱ ስምምነት የተፈረመው ግንቦት ሁለት ቀን 1999 ዓ.ም ሲሆን የፕሮጀክቱን ሃሳብ ባለቤትና ፕሮሞተር መሆኑን የሚያሳይ ሰርተፍኬት ደግሞ ግንቦት 14 ቀን 1999 ዓ.ም ላይ ተሰጥቶታል፡፡ እያንዳንዱ ፊደል መቶ ካሬ ሆኖ በአልሙኒየምና የኤሌክትሪክ ምሰሶ ለመስራት በሚጠቅም ብረት /አንግል አይረን/ የሚሰራ ሲሆን አጠቃላይ ሥራውን ለመጨረስ ሶስት ወር እንደሚወስድ ተገምቷል፡፡ የአድዋ ላንድ ማርክ ፕሮጀክት አራት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው ስምምነቶችና ጥናት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ሁለተኛው የፕሮጀክቱን ሃሳብ ለህዝብ የማስተዋወቅ፣ ሦስተኛው ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ያስፈልጋል ተብሎ የተገመተውን ገንዘብ (ሃያ ሚሊዮን ብር) የማሰባስብና ሥራውን በቀጥታ የማስጀመር ሂደቶች ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱን በተለያዩ ሚዲያዎች እንዲሁም በሚያዘጋጁት ድረ ገጽ ለማስተዋወቅ ማቀዳቸውን ሲገልጽልን ገንዘቡንስ በምን መልኩ ለማሰባሰብ አስባችኋል? ስንል ጥያቄ አቀረብንለት ..ዓድዋ አገራዊ ጉዳይ በመሆኑ በተወሰነ መልኩ ከሕዝብ እንጠይቃለን፡፡ ዓድዋ የአገር መከላከያ ታሪክ በመሆኑም የመከላከያ ተቋማትም የተወሰነ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡ ባለሃብቶችም እንደ ፍላጎታቸው እያንዳንዱን ፊደል ወይም አጠቃላይ ጽሁፉን ስፖንሰር በማድረግ ስማቸውን ከዘመን ወደ ዘመን ማሻገር የሚችሉበት ሥራ ነው.. በማለት መልሶልናል፡፡ ዓድዋ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ለአፍሪካውያንም የነፃነት ተምሳሌት በመሆኑ የአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም የአፍሪካ አገራት ለዚህ ፕሮጀክት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ላይ ይገኛል፡፡ ለትግራይ ባህልና ቱሪዝም ኮሚሽን ያስገባው ፕሮጀክት ፕሮፖዛል በተለያዩ የሥራ ጫናዎች ምላሽ ሳያገኝ ስድስት ወር ያህል መቆየቱን የሚናገረው ሰለሞን ስለ ጉዳዩ ካነጋገራቸው በኋላ ሃሳቡ ጥሩ መሆኑንና እንደሚደግፉት ከገለፁለት በኋላ ድጋፋቸወን በተግባር ከማሳየት ያፈገፈጉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን አልደበቀም፡፡ በምሕረት አስቻለው |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |