Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 29th
Home arrow Sections arrow የአማራ ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች...
የአማራ ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች... Print E-mail
Wednesday, 16 July 2008
የአማራ ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ለማይሰሩ መምህራን ደመወዝ ይከፍላሉ

የኮሌጆቹ ዕጣ ፈንታ በአመቱ መጨረሻ ይለያል


በኃይሌ ሙሉ

በአማራ ክልል የግብርና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ስራ ፈት ለሆኑ መምህራን ከአንድ ዓመት በላይ ደመወዝ ሲከፍሉ ቆይተዋል፡፡ ለአጭር ጊዜ የተቋቋሙት ኮሌጆች የወደፊት እጣ ፋንታ በዘንድሮው አመት መጨረሻ ላይ ይታወቃል፡፡

የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ የሰው ኃይል ሥራ አመራር ሂደት አቶ ወርቅ አየሁ ጥላሁን ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በሚገኙ አምስት የግብርናና የቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ውስጥ የሚያስተምሩ አብዛኞቹ መምህራን ስራ ፈት ናቸው፡፡ መምህራን በዘንድሮው አመት ብቻ ውስጥ 4 ሚሊዮን 797ሺ 177 ብር ደመወዝ ተከፍሏል፡፡ ይህ ችግርም በሌሎች ክልሎች ጭምር የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በየኮሌጆቹ የሚገኙትን ስራ ፈት መምህራን ከመበተን ይልቅ የኮሌጆቹ እጣ ፈንታ ሲታወቅ የመጨረሻ ውሳኔ መወሰን ይሻላል በሚል እሳቤ ከአንድ ዓመት በላይ የተቀመጡ መምህራን ደመወዝ ሲከፈላቸው መቆየቱን የሚናገሩት አቶ ወርቅ አየሁ የኮሌጆቹን እጣ ፈንታ በሚመለከት በፌዴራል ቢሮ በኩል ጥናት መደረጉን፣ በጥናቱም መሰረት በቅርቡ የመጨረሻ ውሳኔ ይተላለፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

"የሰለጠነ የሰው ኃይል ስራ ሳይሰራ ደመወዝ እየተከፈለ ነው፡፡ በዚህ ሁላችንም ይሰማናል" ያሉት አቶ ወርቅ አየሁ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ያጋጠመው ችግር ለግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የተገለጸለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀላፊው ገለጻ የአማራ ክልል ግብርና ገጠር ልማት ቢሮ ለሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በላከው የጽሁፍ መረጃ የእያንዳንዱን ኮሌጅ ጥናት ለማሻሻል የሚረዳ የጥናት ሰነድ አቅርቧል፡፡ በኮሌጆቹ ሲሰጥ የነበረው የዲፕሎማ ፕሮግራም ወደ ዲግሪ ሊያድግ የሚቻልበትን ሀሳብም አቅርቧል፡፡ ከፌዴራል ቢሮ መልስ ከተሰጠው የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የራሱን ውሳኔ እንደሚወስድ የተወሰኑ ኮሌጆች አሁን የሚሰሩትን ስራ ይዘው ይቀጥላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ወርቅ አየሁ ገልፀዋል፡፡

ከአቶ ወርቅ አየሁ እንደሚሉት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ላቀረበው የጥናት ሰነድ የፌዴራል ቢሮው እስከ ሐምሌ 5/2000 ዓ.ም ምላሽ እንዲሰጡ የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ምንም መልስ አልደረሰውም፡፡

ጉዳዩን በማስመልከት ያነጋገርናቸው የፌዴራሉ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጋሻው ገዳ በበኩላቸው በአማራ ክልል የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መምህራን ስራ ፈት ሆነው መቀመጣቸውን በግል እንደተመለከቱ ገልፀው ይሁን እንጅ ኮሌጆቹን የማስተዳደር ሀላፊነት ለክልሎች የተሰጠ በመሆኑ የፌዴራል ቢሮው በአሰራርና በውሳኔ ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ ክልሎቹ ችግር አጋጥሟቸው ትብብር እንዲደረግላቸው ከጠየቁ ግን ቢሮው ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡

አቶ ወርቅ አየሁ በበኩላቸው ጉዳዩ እንደ አገር ጉዳይ ታይቶ መወሰን እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ ክልሎቹ በአብዛኛው የሚተዳደሩት ከፌዴራል በሚሰጥ የድጎማ በጀት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ወርቅ አየሁ "የአማራ ክልል ብቻ ተነጥሎ የራሱን ውሳኔ ቢወስን የሀብት አጠቃቀም ላይ ክፍተት ያጋጥማል" ብለዋል፡፡ ለዚህም ለሁሉም የሚጠቅም የጋራ ውሳኔ መወሰን አለበት ብለው ያምናሉ፡፡

በአማራ ክልል በሚገኙ አምስት የግብርና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከ150 የማያንሱ መምህራን ተቀጥረው ደመወዝ የሚከፈላቸው ሲሆን ኮሌጆቹ ከተቋቋሙበት ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ 9200 ተማሪዎች ተመርቀዋል፡፡

ሥራ ለማይሰሩ በግብርና የቴክኒክ ማሰልጠኛ ኮሌጆች መምህራን ደመወዝ የመክፈል ችግር በሌሎችም ክልሎች የሚታይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ 
 
< Prev   Next >