| የኪዊን በርገር ባለቤትና ሰራተኞች... |
|
|
| Wednesday, 16 July 2008 | |
የኪዊን በርገር ባለቤትና ሰራተኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉበተሾመ ንቁ ቦሌ ኦሎምፒያ አካባቢ በሚገኘው ኪዊን በርገር ከ40 በላይ ሰዎች በርገር በልተው መታመማቸውን ተከትሎ የኪዊን በርገር ባለቤትን ጨምሮ ሰባት የድርጅቱ ሰራተኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ኢንስፔክተር አካሉ ቢሰውር የድርጅቱ ባለቤት ወ/ሮ ሊዲያ አባተንና ስድስት የድርጅቱ ሰራተኞች የተመረዘ ምግብ ጋር በተያያዘ ወንጀል በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡ ኢንስፔክተር አካሉ ከድርጅቱ በርገር ተመግበው መታመማቸውን በመግለፅ አስራ ሁለት ሰዎች ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤ ክስ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መነሻነት የክፍለ ከተማው ፖሊስ የድርጅቱን ባለቤትና ሰራተኞችን ካለፈው አርብ ጀምሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኢንስፔክተር አካሉ ገልፀዋል፡፡ ኢንስፔክተር አካሉ የክፍለ ከተማው ፖሊስ ጉዳዩን በተመለከተ ያለፈው ሰኞ ለቦሌ ክፍለ ከተማ 6ኛ ምድብ ችሎት ጉዳዩን ማቅረቡንና ለ20/11/2000 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ውስጥ ተጨማሪ መረጃ እንደሚያሰባስቡና ኪዊን በርገር ተመግበው የታመሙ ቅሬታ አቅራቢዎችን ለማነጋገር ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ የምርመራ ክፍል ሀላፊው በ22 ማዞሪያ፣ በቦሌ ኦሎምፒያ አካባቢ እንዲሁም በናዝሬት የድርጅቱ ቅርንጫፍ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ እስካሁን ከቦሌ ከሚገኘው የድርጅቱ ክፍል በርገር የተመገቡ መታመማቸውን ለማወቅ እንደቻሉ ገልፀዋል፡፡ ከሶስቱ የድርጅቱ ክፍሎች ናዝሬት ከሚገኘው በስተቀር በሁለቱ ላይ ፍተሻ ማካሄዳቸውንና አስፈላጊ ናሙናዎች ለኢትዮጵያ የስነ ምግብና ጤና ምርምር ኢንስቲትዩት (ፓስተር) ለምርመራ መላካቸውን የምርመራውን ውጤት እየጠበቁ መሆኑን ኢንስፔክተር አካሉ ገልፀዋል፡፡ የፓስተር የምርመራ ውጤትን ጨምሮ የታማሚዎችን ማስረጃ በማሰባሰብ ለአቃቤ ሕግ እንደሚቀርብና ክስ እንደሚመሰረት ኢንስፔክተር አካሉ አስረድተዋል፡፡ የምርመራ ሀላፊው እስከ አሁን ድረስ ከታመሙ ሰዎች በስተቀር የሞት አደጋ አለመድረሱን ገልጸዋል፡፡ የኪዊን በርገር ስራ ማቆሙንና መዘጋቱንም አይይዘው አስታውቀዋል፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነችውና ከኪዊን በርገር በመብላቷ መታመሟን የገለፀችው ወ/ት ዲና መኩሪያ፤ "ታምሜ ኦሎምፒያ ቤተዛታ ሆስፒታል ተኝቼ የኪዊን በርገር ባለቤት ወ/ሮ ሊዲያ ተጠርተው መጥተው ይቅርታ ጠይቀውኛል" ስትል ገልጻለች፡፡ ወ/ት ዲና "ወ/ሮ ሊዲያ ይቅርታ የጠየቁኝ የሆነ የሰሩት ስህተት እንዳለ ቢያውቁ ነው" ስትል ጥርጣሬዋን አስረድታለች፡፡ ወ/ት ዲና ከጓደኞችዋ ጋር 1/11/2000 ዓ.ም ኪዊን በርገር በመመገቧ በፅኑ መታመሟን አስረድታለች፡፡ በዚህም "በገዛ ገንዘባችን መታመም የለብንም፣ ፍትህ ማግኘት አለብን" ስትል ፖሊስ እንዲያጣራና አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወሰድ አሳስባለች፡፡ በተያያዘ ዜና በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ሦስቱ የድርጅቱ ሰራተኞች በተመሳሳይ መልኩ ታመው በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ሆነው ህክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ ከክፍለ ከተማው ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡ የኪዊን በርገር ሰራተኛ የሆነችውና በአሁኑ ሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የምትገኘው ወ/ሮ አለም ፀሐይ አምባው ለባለቤቷ በወሰደችለት በርገር ባለቤቷም ለከፍተኛ ሕመም መዳረጉንና ሆስፒታል መተኛቱን አረጋግጠናል፡፡ በርገሩን በመብላታቸው መታመማቸውን የሚናገሩ ታማሚዎች በቤተዛታ፣ በቅዱስ ገብርኤል፣ በብሩክ፣ በአፍሪካ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ በሀያት፣ በኢትዮ ጥራት፣ በሰናይና ናሽናል ሆስፒታል ህክምና የተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |