| ኢንቨስተሮችን ለመሳብ እንረባረብ! |
|
|
| Wednesday, 16 July 2008 | |
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጭ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መኖሩን አስተውለናል፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ቃል እየገቡ ናቸው፡፡ በዚህ ወር በቢልዮን የሚቆጠር ብር ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉ ባለሃብቶች ከሳውዲና ከዱባይ መጥተዋል፡፡ በተለይ የኢመሬቱ ቢልየነር እጅግ አስፈላጊ የሆኑት የምድር ባቡር፣ የነዳጅ ቧንቧ በመዘርጋት ሥራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ሊበረታታና ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ መንግሥት ማበረታታት አለበት፡፡ በኮርያ፣ በጃፓን፣ በማሌዥያ፣ በሲንጋፖር ወዘተ. እየታየ ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት መንግስትና የግል ዘርፉ በጋራ ያደረጉት የውጭ ኢንቨስትመንት የመሳብ እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ ይህን ሁሉ ለማድረግ ጎን ለጎን ማድረግ ያሉብን በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚሆን አስፈላጊ መረጃ አዘጋጅተናል? አንብበውና አዳምጠው ሊወስኑ የሚያስችላቸውን የመረጃ ዳታ ቤዝ አለን? ወይስ የፈለገው ግለሰብ በቃል ነው የሚነግራቸው፡፡ የተለያዩ ሰዎች በቃል የሚያቀርቡላቸው መረጃስ አንድ ዓይነት ነው? አበረታች መረጃዎች አሉ? የአገልግሎት መስጫ ቢሮዎች መረጃ አላቸው? ምኒስቴሮች በእጃቸው መረጃ አለ? ምን ያህል መሬት ለእርሻ የተዘጋጀ አለ? የት አካባቢ? ከመንገድ ምን ያህል ይርቃል? ከወደብና ከአውሮፕላን ማረፊያስ? ውሃ አለ? የኤሌክትሪክ ሃይል አለ? የባንክ ፖሊሲው ምን ይላል? የታክስ ፖሊሲስ? የሊዝ ዋጋስ? ከውጭ ለሚመጣ ኢንቬስተር መረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራትና መዘጋጀት ያለበት ነው፡፡ "አይዞህ ጎበዝ" በሚል ቃል ብቻ ኢንቨስትመንት የለም፡፡ አስፈላጊና አበረታች ሕጎችና መመሪያዎችስ አሉን? ይህም ሌላ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ እንመርምራቸው፡፡ መሻሻል፣ መቀየር ያለባቸው ይሻሻሉ ይቀየሩ፡፡ ቢሮክራሲያዊ አሰራራችንስ ምን ይመስላል? ያን ያህል ሃብት ኖሮት የሚመጣ ሰው፣ የጊዜ እጥረት እንዳለበትም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች እኛ ጋ ኢንቨስት አድርግ ብለው የሚማፀንዋቸው ተወዳዳሪዎች እንዳሉም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ያለንበት ወቅት የውድድር ነው፡፡ አንዱ ምንጣፍ አንጥፎ ሲቀበል ሌላው በቢሮክራሲ ተተብትቦ ሲያዳክም ሁለቱም ተወዳዳሪዎች ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ቀልጣፋው ያሸንፋል፡፡ ከዚህ አንፃር ቢሮክራሲያችንን ፈጣንና ብቁ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ሠራተኞቻችን፣ ሹሞቻችንስ? ብቁና ንቁ ናቸው? በውጭ ኢንቨስትመንት ያምናሉ? የመስማት ፍላጎታቸው ጠንካራ ነው? ሥራን የማቀላጠፍ አቅም አላቸው? ይህን ሁሉ መፈተሽና ማስተካከልም ያስፈልጋል፡፡ "ሙያ በልብ ነው" እያልን የምንኮራበት ጊዜ አልፏል፡፡ ተናግረን፣ ተሯሩጠን የምናሸንፍበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ይህ ሁሉ ከተደረገ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅማችን ያድጋል፡፡ መካከለኛው ምሥራቅ በቅርበት፣ በባህል ተመሳሳይነት ለኢትዮጵያ የተመቸ ቦታ ነው፡፡ ሁኔታዎች ከተመቻቹ ገንዘብ አለ፣ ፍላጎትም አለ፡፡ ባለሃብቶቹም ለሚጠቅመንና ለምንፈልገው የኢንቨስትመንት ሴክተር መሳካት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ከዱባይ ከመጡት ባለሀብት ጋር በምድር ባቡርና በነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ያተኮረ መግባባት ላይ መደረሱ መልካም ነው፡፡ ሁለቱም እጅግ አስፈላጊ ዘርፎች ናቸው፡፡ በሌላውም ዘርፍ እንደዚሁ ኢንቨስተሮችን እያበረታታን ራሳችንም መበረታታት አለብን፡፡ በአንድ በኩል ጥሩ ነገር ሲታይ በሌላ በኩል ደግሞ አደናቃፊ ነገር አይጠፋምና ከወዲሁ እንደዚህ ዓይነት የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ምንድን ናቸው? እነማን ናቸው? ብሎ ለይቶ አውቆ መፍትሄ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህን በአስቸኳይ" መደረግ አለበት፡፡ ከዚህ ሌላ ክትትልና ቁጥጥርም ያስፈልጋል፡፡ ከውጭ የመጡት እንዴት እየተጓዙ እንደሆነ፣ ያሉት ምን እያደረጉ መሆናቸውንና በእቅዱ እየተጓዙ መሆናቸውን መከታተል፣ ችግር ካለባቸው መርዳትና ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ከልብ ኢንቨስት የሚያደርጉትን ሊበረታቱ የሚገባቸውን ያህል የማያደርጉ ካሉም ሊነገራቸውና ሊስተካከሉ ይገባል፡፡ ካልተስተካከሉ ደግሞ "ቀልዱን ተው" ማለት የግድ ነው፡፡ የውጭ ኢንቬስተር ለመሳብ እንረባረብ ስንል የሚያለማ፣ ቴክኖሎጂ የሚያመጣ፣ የሰው ሃይል እውቀትና ልምድ የሚያዳብር፣ ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የሚሰራ እንጂ እዚህም እዚያም አጥሮ የሚያስቀመጥና ሌላ ሃብታም እንዳይፈጠር የሚከላከል፣ ጥገኝነትን የሚያጠናክር እንዳይሆን ማረጋገጥና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የኢንቨስትመንት ሥራ የተግባር እንጂ የቃል አይደለም፡፡ መንግሥትም ኢንቨስተሩም ቃላቸውን ያክብሩ፡፡ ድርቅና ረሃብ ለጊዜው በእርዳታና በብድር ይቃለል ይሆናል፡፡ ዘላቂ መፍትሄው ግን ኢኮኖሚን ማሳደግ ነው፡፡ ለኢኮኖሚ እድገት ዋስትና ደግሞ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ለኢንቨስትመንት ዋስትናም አስተማማኝ ፖሊሲ፣ ፍትሃዊ አሰራር፣ አወቃቀርና የሰው ሃይል ነው፡፡ ስለዚህም የውጭ ኢንቬስተሮችን ለመሳብ እንረባረብ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |