| የረሀብ ፖለቲካ |
|
|
| Wednesday, 16 July 2008 | |
በሰለሞን ጎሹየዓለም የነዳጅ ዋጋ ባልተጠበቀ ዋጋና ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ የአብዛኛው ህብረተሰብ የእለት ምግብን የሚሸፍኑት ጤፍና ጥራጥሬዎች ከእጥፍ በላይ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በዚህ ዓመት ብቻ አስተናግደዋል፡፡ ስለዚህ ሃገራችን ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ስለመኖሩ ጥያቄ የሚያነሳ የለም፡፡ የነዳጁ ጭማሪ በተቀረውም ዓለም ቢሆን የምግብ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ የምግብ እጥረቱ ባስከተለው የጉዳት መጠን ላይ ስምምነት የለም፡፡ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትሩ በተጎጂዎች መጠን ላይ በ2 ሚሊዮን የሚለያዩ አሀዞችን በማስቀመጥ አለመስማማታቸውን በግልፅ ቢያሳዩም (እርግጥ ነው በኋላ ላይ ምክትሉ የዋናው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ (ቁጥር) ደግፈዋል) ሁለቱም ግን ለተጎጂዎች ቁጥር መጋነን ተጠያቂ አድርገው ጣታቸውን የቀሰሩት የእርዳታ ድርጅቶች ላይ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ኘሮግራም የኢትዮጵያ ተጎጂዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ለመመገብ አቅም እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ዩኒሴፍ በበኩሉ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ለአደገኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ እድሜአቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በኢትዮጵያ እንደሚገኙ መግለፁን ሮይተርስ ባሳለፍነው ሳምንት ዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያ የእርዳታ ድርጅቶች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የድርቁ ተጠቂዎቹን ቁጥር በሀሰት እንዳጋነኑ ብትወቅስም 4.6 ሚሊዮን ህዝብ ስለመራቡና ወደ 75"000 ህፃናት እርዳታ እንደሚፈልጉ ግን አልካደችም፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ ምክንያት የምታደርገው ባለፈው መጋቢትና ሚያዚያ ወር መዝነብ የነበረበት ዝናብ ያለመዝነቡን እውነታ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ትብብር (OCHA) ኢትዮጵያ የ325 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልጋት ቢገልፅም መንግሥታችን ግን የድርቁ አልያም የርሃቡ ጉዳይ ከቁጥጥር ውጭ እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ ነው፡፡ በ1965 እና 1966 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረው ረሃብና ድርቅ ለአጼው መንግሥት ውድቀት ከፍተኛውን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ከ1976 እስከ 1981 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረው ረሃብና ድርቅ ደግሞ ደርግን አዳክሞ ሲዋጉት የነበሩትን ኃይሎች በማጠናከር ውድቀቱን ያፋጠኑበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ እነዚያ መጠነ ሰፊ ድርቅና ረሃቦች ለአደባባይ ከበቁ የእኔን ደካማነት ያሳያሉ ያሉት ሁለቱ መንግሥታት ጉዳዩን ለመደበቅ መጣራቸውም የረሃብና የድርቁን ያህል ይፋ ነበር፡፡ ኢህአዴግስ የእነሱን ፈለግ እየተከተለ ይሆን? በዘመነ ኢሕአዴግ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት የተሰኙ ቃላት በጣም የተለመዱ ናቸው፡፡ በእርግጥም ሦስቱ ፅንሰ ሃሳቦች እርስ በርስ የተዛመዱ እና ለአንዳቸው መሟላት ሌላው እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚያ ላይ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የባህል፣ የሃይማኖትና የብሄር ልዩነት ያላቸውን ቦታ ካየን ከድህነት ለመላቀቅ እንዲሁም በሰላም እና በዲሞክራሲ ለመኖር ያለብን ፈተና የተወሳሰበ ይሆናል፡፡ ኢሕአዴግም ሆኑ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን የመሩት መንግሥታት ስልጣንን ወደ ማዕከል ካሰባሰቡ በኋላ በስልጣናቸው ላይ ፈተና የሚሰነዘርባቸው ከዳር ወይም ድንበር አካባቢ ካሉ ቦታዎች ነው፡፡ የአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት በርካታ አመፆችን፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፣ የሽምቅ ውጊያ፣ የከፋ የግብር አመፅ አስተናግዶ ሁሉንም በተለያዩ ፖለቲካዊ መንገዶች ቢያመልጥም ረሃብና ድርቁን ለመደበቅ ሲሞክር ግን ብሔሮች አንድ ሆነው ግብዓተ መሬቱን እውን አድርገዋል፡፡ በርዕዩተ ዓለም፣ በብሔርተኝነት ስሜትና በሀይማኖት ልዩነት ቢኖራቸውም የአጼውን መንግሥት በመጣል የኢኮኖሚ ቀውሱን ከህዝቡ ላይ ለማንሳት ግን እጆቻቸውን አስተባብረዋል፡፡ ይህን የብሔርተኝነት ስሜት ደርግ የፖለቲካ ስልጣኑን ለማመቻቸት ቢጠቀምበትም የሶሻሊስት ሥርዓትን ለመጫን በመቻሉ በርዕዮተ ዓለምና በብሔር ፖለቲካው የታከኩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለማስተናገድ ብዙ ጊዜ አላጠፋም፡፡ ከተቃዋሚ ኃይሎች ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከጎረቤት ሐገር ሶማሊያ ጋር ለበርካታ ዓመታት ጦርነት ውስጥ በገባበት ወቅት በረሃብና በድርቅ እየተጠቁ የነበሩ ህዝቦቹን በተለይም ቆሜለታለሁ የሚለውን ወዛደር ከችግሩ አላላቀቀውም፡፡ የሶሻሊዝምን ሥርዓት ለመተግበር በርካታ ውስብስብ የአሰራር ሂደቶችን ማለፍ ቢጠይቅም ኢትዮጵያም ሆነ የደርግ መንግሥት ለሥርዓቱ አመቺ አልነበሩም፡፡ የደርግ አካሄድ ያልተመቻቸው ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እርዳታቸውን መቀነስ ከመጀመራቸውም በላይ የደርግ ጠላቶች እየበረከቱ እና ህብረት እየፈጠሩ ሲመጡ በመሐል 1977 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ "ታላቁ ረሃብ" ተብሎ የሚታወቅ መጠነ ሰፊ እልቂት ተከሰተ፡፡ ክርስቲን ኡርባች እ.ኤ.አ በ2006 በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ ጆርናል ላይ "Famine as a human rights violation: The case of Ethiopia and the Great Famine of the 1980s" በሚል ርዕስ ባወጣችው ፅሁፍ የደርግ መንግሥት ረሃቡ እንደሚከሰት ቀድሞ ያውቅ እንደነበረ፣ ረሃቡን አቅዶና አውቆ ያባባሰው ስለመሆኑና ይህም ስልጣኑን ለማራዘም እንደነበረ ተከራክራለች፡፡ በ1966 ዓ.ም. የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ተቋቁሞ የምግብ ተጠቂዎችን ለመርዳትና እርዳታዎችን ለማከፋፈል እንዲሁም ስለረሃብ ሁኔታው ነፃ ሆኖ ሪፖርት እንዲያቀርብ የሚጠበቅበት ቢሆንም ደርግ ኮሚሽኑ የሚሰበሰውን እርዳታ ለሲቪል ዜጎችና ለጠላት ተዋጊ ወታደሮች ጭምር ሳይሆን ለደርግ ወታደሮች ብቻ እንዲሰጥ እንደተደረገ ክርስቲን ከላይ በጠቀስነው ፅሁፏ ጠቁማለች፡፡ ክርስቲን እንደምታምነው ደርግ ታላቁን ረሃብ አመጣውም፣ መጣበትም በስተመጨረሻ ህዝቡ ከጠላቶቹ ጋር አብሮ ከነፈጠራቸው የተራቆተ ተፈጥሯዊ አካባቢ እንዲሁም ደካማ የመንግሥት መሠረተ ልማት መወገዱ አልቀረም፡፡ ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን በጊዜያዊ የሽግግር መንግሥቱ አማካኝነት በኋላም በመጀመሪያው የ1987 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ በስርዓቱ ሲመጣ ሀገሪቱ በብዙ መልኩ የተራቆተች በመሆኗ ብዙ ስራ እንደሚጠብቀው ግልፅ ነበር፡፡ በርካታዎቹ ችግሮች በአጼው መንግሥትና በደርግ ተፈጥረው እየተንከባለሉ የመጡ በመሆናቸው ኢሕአዴግ መጠነ ሰፊውን ችግር ለመቅረፍ በሚቀርፀው ስትራቴጂ ከተለያየ ባህል ለመጡ እሴቶች ዋጋ መስጠት፣ የምክክር መድረክ መፍጠር፣ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ስለረሃብ መከላከል ማስተማርና የሰብዓዊ እርዳታ የሚገኝበትን፣ የሚከፋፈልበትንና ቁጥጥር የሚደረግበትን ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተውት ነበር፡፡ ከደርግና ከኃይለስላሴ መንግሥታት ትምህርት የወሰደ የሚመስለው ኢሕአዴግ፣ በ1985 ዓ.ም. የግብርና ልማት መራሽ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ (Agricultural Development-Led Industrialization (ADLI)) በመቅረፅ የእድገትና የልማት ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ ይህም በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከተከሰተው አበረታች የኢኮኖሚ እድገት አኳያ ስኬታማ ለውጥ እንደሚመጣ ብዙዎች ተስፋ እንዲያደርጉ አስገድዷቸው ነበር፡፡ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ክፍል መረጃ ከሆነ ወደ 81 ሚሊዮን ከሚጠጋው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ገበሬና በገጠር የሚኖር ነው፡፡ ይህ ከሆነ አድሊ በአግባቡ ከተተረጎመ አዋጭ ፖሊሲ ይሆን ነበር፡፡ ፖሊሲው 15 ዓመታት አሳልፎ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ እንዳልሆነ አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ አሚን አብደላን የመሳሰሉ ምሁራን ፖሊሲው ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት አዋጭ እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ አማን አብዳላ በ1996 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ባሳተመው መፅሀፍ ላይ (Agricultural Development-Led Industrialization (ADLI) Compatibility Analysis" በተሰኘው ርዕስ ስር የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በገንዘብ የመደጎም ደካማነት፣ ወደ ውጭ የመላክ አቅም አለመኖር፣ የበለፀገ የሰው ኃይል እጥረት ከመኖሩ፣ ከግሎባላይዜሽን ፈተናዎች፣ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ሃገሪቱ ለማምረት ካላት የአቅም ውስንነት በተጨማሪ አንድን ፖሊሲ በጥራትና በአስተማማኝ ሁኔታ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የፖለቲካ፣ የመሰረተ ልማት፣ የተቋማዊ አደረጃጀትና ሌሎች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምክንያቶች ተሟልተው በሃገሪቱ ስለማይገኙ አድሊ ውጤታማ ሊሆን እንዳልቻለ አብራርተዋል፡፡ መንግሥት የሰላም፣ የዲሞክራሲና የልማት ፖሊሲው ውጤታማ እንደሆነ በሚወተውትበት በዚህ ዓመት እንደ እርዳታ ድርጅቶቹ ጥቆማ 6.7 ሚሊዮን ህዝብ እንደ መንግሥት ይፋዊ ሪፖርት ደግሞ 4.6 ሚሊዮን ህዝብ መራቡን ተቀብሎ ሁሉም ነገር "በቁጥጥር ሥር ነው" እያለ ነው፡፡ የኢዴአፓ መድኅን ሊቀመንበር ልደቱ አያሌውን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን "ከኢሕአዴግ ቁጥጥር ውጭ የሚሆነው ምንድን ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በዚሁ ዓመት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽኑን አፍርሶ በግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ሥር እንዲሆን የተደረገበትን የመንግሥት ውሳኔ ይኮንናሉ፡፡ "የሚጠበቅበትን ሥራ አልሰራም" የሚለውን ሰበብም አይዋጥላቸውም፡፡ "አንድ መንግሥት ሥራውን በአግባቡ አልሰራም ብለን ሃገሪቱ መንግሥት አያስፈልጋትም አላልንም፡፡ ይልቁንም ሥራውን በአግባቡ የሚሰራ መንግሥት እንዲፈጠር እንታገላለን እንጂ" ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ኢሕአዴግ በሀገር በቀል እውቀቶች፣ በባህላዊ ልምዶችና አካባቢያዊ ተቋማት የመጠቀም አዝማሚያው ደካማ በመሆኑ አሁን ያለውን ድርቅና ረሃብ በተለይም በኦሮሚያ፣ በሶማሌ እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥታት እጅግ ተባብሶ ያለውን ድርቅና ረሃብ ለመቀነስ እንዳልተቻለ ይተቻሉ፡፡ የደርግ እና የኃይለስላሴ መንግሥታት ለሀገር በቀል እውቀቶች፣ ባህላዊ ልምዶች እና አካባቢያዊ ተቋማት እውቅና የሚሰጥ ሥርዓት ባይኖራቸውም የኢሕአዴግ ድክመት የአፈፃፀም መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ህዝብን አሳታፊ የልማት ግቦችን በወረቀት ደረጃ ቢቀበልም ድህነትን ከሥር መሠረቱ ለመዋጋት ህዝቡን ተዋናይና የትግሉ አጋር አለማድረጉን ይወቅሳሉ፡፡ እንደማሳያም ለበርካታ ዓመታት የመንግሥት የልማት አጋር የነበሩትን ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶችንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመስራት የሚያስቸግር አዲስ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቱንና ለረሃብና ለድርቁ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ እነሱኑ ለመውቀስና ለመተቸት ፍላጎት ማሳየቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም የደርግና የኃይለስላሴ መንግሥታት የውድቀት መጀመሪያ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ደርግና ኃይለስላሴ ረሃብና ድርቁን ለማድበስበስ ሲሞክሩ የተቃዋሚው ኃይል ተጠቃሚ እንደነበር ከላይ ተገልጿል፡፡ ኢሕአዴግም ላሳየው ድክመት ተቃዋሚ ኃይሎች ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተዋልን? ለበርካታ ዓመታት ሲፈራሩ የነበሩት የተቃዋሚ ኃይሎች በቅርቡ የጀመሩት የምክክር መድረክ ወደ ጥምረትም ያመራል መባሉ እንደ አንድ የምላሹ መጀመሪያ እርምጃ ሊታይ ይቻላልን? የኢሕአዴግ ቱባ ባለሥልጣናት በቁጥር ላይ የፈጠሩት ልዩነት የአመለካከት ልዩነት በፓርቲው ውስጥ ስለመፈጠሩ ምልክት ሊሆን ይችላልን? የቀድሞው የፓርቲው አባላት በኤርትራ ጦርነት፣ በሶማሊያ ጦርነት፣ በሱዳን ድንበር ጉዳይ ላይ መጠነ ሰፊ ወቀሳ መሰንዘራቸውስ በፓርቲው ጥብቅነት ላይ ጥርጣሬ አይጥልምን? ዞሮ ዞሮ ግን ረሃቡንና ድርቁን ለመዋጋት ተቃዋሚዎች የኢሕአዴግ አጋር የመሆናቸው አስፈላጊነት ጎልቶ ይታያል፡፡ የሕዝባቸውን የሞት አደጋ በአስተማማኝ ሁኔታ ከገቱ በኋላ እንደየብሔራቸው መሆን ይችላሉ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |