Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Monday
Sep 08th
Home arrow Sections arrow ከእኛ በላይ ስለኛ ማንም ሊናገር አይችልም!
ከእኛ በላይ ስለኛ ማንም ሊናገር አይችልም! Print E-mail
Wednesday, 16 July 2008
እንደሚታወቀው ሁሉ አምባገነኑ የደርግ መንግስት በመጣል ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲና ለብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር የተካሄደው የትጥቅ ትግል ለድል የበቃል በመላው ህዝባችን ተሳትፎና በጠራ መስመር የሚመራ አላማ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው አገር ያወቀው ሃቅ ነው፡፡ የታገልንለት ህዝባዊ መሰረት ያለው አላማም የታጋዩን የመላው ኅብረተሰብ የአላማ ጽናትና አይበገሬነት በተግባር ያስመሰከረ፣ ለአረመኔው የደርግ ስርዓትና ጋሻጃግሬዎቹ እንደ እግር እሳት እያንገበገበ ህዝባዊ ቀንዲልን ያወገገ ታሪካዊ ፍጻሜ እንደሆነም ሁሉም የሚመሰክርለት ጉዳይ መሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየሚዲያው የሔዋኗ ራዕይ የቀድሞ ታጋይ ሴቶች ማህበር በሚል በግል ተነሳሽነት ማህበር መመስረታቸውን የሚገልፁት ወ/ሮ ምጽላል ኃ/ስላሴ አሁን ያለንበትን የሰላም፣ የዴሞክራሲ እና የልማት መድረክ ያጎናፀፉንን ሰማዕታትና ታጋዮች ታሪክ በፈጠራ ከሽነው ሃቁን በማዛባት በህዝብ ልጆች መስዋዕትነት መሳለቃቸው እጅጉን አስገርሞናል፡፡ የሌለና ያልነበረ ታሪክ ፈጥረው አጀብም አሰኝተውናል፡፡ በሪፖርተር ጋዜጣ ግንቦት 24 ቀን 2000 ዓ.ም የእሁድ እለት እትም ታትሞ ከወጣው ጽሁፍ እንደተረዳነው በየዋህነት ይሁን አለማወቅ ወይዘሮዋ ታገልኩለት ለሚሉት አላማ የነበራቸው ግንዛቤ ከግል ጥቅም የመነጨ ያስመስልባቸዋል፡፡ በመሰረቱ ታጋዩ ያን አስቸጋሪ ውጣ ውረድ ተቋቁሞ እንደ ሻማ እየቀለጠ ክቡር ህይወቱን የሰዋውና አካሉን የከፈለው የህዝብን ጥቅምና ሰላም ለማስከበር እንጂ ከግላዊ ጥቅም የመነጨ እንዳልሆነ ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ አወቅሽ አወቅሽ ሲሉዋት. . . እንዲሉ በግል የመሰረቱት ማህበር በአደረጃጀት ደረጃ ቀድሞውንም ቢሆን ቆሜላችኋለው  በሚሉዋቸው አባላት ተሳትፎ ያልተመሰረተና የሁሉም ተሳትፎ በሌለበት በታጋይ ሴቶች ስም በተለይ በሴት ታጋይ አካል ጉዳተኞች ስም መነገዳቸው ሳያንሳቸው አካላችን ከፍለን ደርግን ያህል ስርዓት በመገርሰስ ያገኘናቸውን ድሎች በማንቋሸሽ ግንቦት 20 የጽልመት ቀን ሊሆንባቸው የሚችለው ለወ/ሮ ምጽላል እና መሰሎቻቸው ብቻ ነው፡፡

"የትግራይ ህዝብ አካላችሁ ከፍላችሁ ክፉ ስርዓት አመጣችሁብን ይለናል. . ". ብለው መናገራቸውም ከጽሁፉ ተረድተናል፡፡ ለመሆኑ በትግሉ ታሪክ ሁሉም ህዝባችን እንደታገለ ዘንግተውት ይሆን? ዳሩ ግን በእኛ አረዳድ ህዝቡን ከትግል በመነጠልና በአሁኑ ሰዓት የተመዘገቡትን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ስራዎች በማንቋሸሽ ለህዝባዊ ትግላችንና ለተከፈለው መስዋዕትነት ያላቸውን ዝቅተኛ አመለካከት በግልጽ ያሳዩበት አገላለጽ ነው፡፡ በዚሁ አባባላቸውም እጅጉን አፍረንባቸዋል፡፡ በማያውቁት ጉዳይ ዘው በማለትም ስለ የጦር ጉዳተኞች በር በድህረ እርስ በርስ ግጭት በአፍሪካ ካሉት የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ውስጥ በአለም አቀፍ ተቋማትና መድረኮች ሳይቀር ጥንካሬው ስለተመሰከረለት ማህበራችንና የጦር ጉዳተኛ አባሎቻችን ያስተላለፉት መልዕክት ከአሳፋሪነቱ አልፎ በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ውንጀላ መሆኑ ሳይገባቸው ቀርቶ አይመስለንም፡፡
 
ለመሆኑ ሕወሓትም ሆነ ኢህአዴግ በትጥቅ ትግሉ ወቅትም ሆነ በኋላ በጦር ጉዳተኛ አርበኞች እንክብካቤና ማቋቋም ዙሪያ የነበራቸው አመለካከትና የተከተሉት አቅጣጫ ምን ይመስል ነበር? በምን ሁኔታስ ላይ ነው ያለው? ብሎ መፈተሹ ሃቁን ለመረዳት ይረዳልና እንደሚከተለው በአጭሩ አስቀምጠዋል፡፡

በትጥቅ ትግሉ ወቅት አካል ጉዳተኞቹ በሜዳ ሆስፒታሎች ህክምና ካገኙ በኋላ የአካል ጉዳታቸውና አቅማቸው በሚፈቅደው መሰረት በተለያዩ ህዝባዊ አደረጃጀቶች እንዲሳተፉ በማድረግ የይቻላልን መርህ በተግባር አሳይቶና አስተምሮ አልፏል፡፡ ከደርግ ውድቀት ማግስትም የቀድሞ የጦር አባላትንና የጦር ጉዳተኞች ሰላማዊ ኑሮ ለመምራት እንዲያስችላቸው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀል ስለነበረባቸው ይህንን በማጤን መንግስት የቀድሞ የጦር አባላትና የጦር ጉዳተኞች ተሃድሶ ኮሚሽን በሚል ባቋቋመው ኮሚሽን አማካኝነት ብዙ ሚሊዮን ብር በመመደብና ስለጠና እንዲሰጥ፣ ለማቋቋሚያ የሚሆን የመነሻ ገንዘብ እንዲያገኙ በማድረግ ሌሎች ድጋፎች በማከል የበኩሉን ኃላፊነት ተወጥቷል፡፡

ከባድ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የኢህአዴግ ታጋይ አካል ጉዳተኛ አርበኞች ኮሚሽኑ በዓዲግራት የተሃድሶ ማዕከል አቋቁሞ የነበረ ቢሆንም በማዕከሉ ያለፉት ታጋዮች ካገኙዋቸው የአካዳሚ ትምህርትና የሙያ ስልጠና ባሻገር በማዕከል አሰባስቦ ማኖሩ የራሱ አሉታዊ ገጽታ ስለነበረው ጉዳተኞቹ በራሳቸው ጥያቄና እምነት እንዲሁም ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አቋም በመውሰድ በህዝቡ መሀል በመቀላቀል እንዲቋቋሙ በማድረግ ኅብረተሰብ ማዕከል ያደረገ የማቀላቀልና የማቋቋም ስራ እጅጉን በተቀናጀና በተሳካ መልኩ ሊሰራ በቅቷል፡፡ ሆኖም ግን የማቋቋሙና የማቀላቀሉ ስራ በማጠናቀቁ ምክንያት ኮሚሽኑ ሲፈርስ እንዲሁም በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋዎች በላሸቀችው አገርና ማኅበረሰብ ጉዳዩ ከመንግስት ኃላፊነት ብቻ ነው ብሎ መውሰድ አንድም የዋህነት በሌላ በኩል ደግሞ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው ብለንም እናምናለን፡፡

በራሳችን ጊዜ ተደራጅተን የህዝቡንና የሁሉም አካል ተሳትፎና ኃላፊነት በሚያረጋግጥ መልኩ ማህበር መስርተን እጅግ አኩሪ ስራ በመስራት ላይ ያለን ድርጅትም ነን፡፡ የጦር ጉዳተኞቹም በቡድንና በግል የስራ መስክ በመሰማራት በቀሪው አካላችን ከተጧሪነት ተላቀን የፀረ ድህነቱን ትግል አካል በመሆን የራስን መቻል መርህ በተግባር እናረጋግጣለን ከሚል የፀና መንፈስ በልማቱ አጋርነታቸው በተግባር እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡ በነገራችን ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በዚሁ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የጦር ጉዳተኞቹ ሁኔታ በቅርበት ስለሚከታተሉትና ከላይ የጠቀስናቸው ሐቆች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ እኛ የጉዳዩ ባለቤት የሆንን የጦር ጉዳተኞች እምነትና አመለካከትም ጭምር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ተደራጅተን በተለያዩ የልማት ስራዎች እያስመዘገብን ያለነው አኩሪ ስራ በልማቱ መስክ ዳግም ታሪክ ለመስራት በቁርጠኝነት በመነሳት እየሰራንበት እንገኛለን፡፡ የህዝባችን፣ የመንግስትና የሌሎች የልማት አጋሮች ድጋፍ በተመለከተ ከምንግዜው በይበልጥ ለስኬታችን መሰረት በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም እንተማመናለን፡፡

የወይዘሮዋ ሌላው አሳፋሪ አስተያየት ከሻዕቢያ ጋር ማነፃፀራቸው ነው፡፡ ምናልባት የሻዕቢያ የጦር ጉዳተኛ አርበኞች ሁኔታ በተገላቢጦሽ ተርጉመው ማቅረባቸው ለምን እንደሆነ ባይገባንም በባህሪውም ይሁን በአመለካከት ደረጃ መሰረታዊ ልዩነቶች ያለው ነው፡፡ የሻዕቢያ የጦር ጉዳተኞች ላቀረቡት ጥያቄ በጥይት እንደተጨፈጨፉ ሳያውቁ ቀርተው አይመስለንም፡፡ አሁንም ጉዳዩን የፖለቲካ አላማ መጠቀሚያ ሊያውሉት መሞከራቸው ከሆነ እጅጉን አሳዛኝ አገላለጽ ነው፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ሁሉም በተለያዩ ኃላፊነቶች ተመድቦ የበኩሉን አስተዋጽኦ የደረገ ሲሆን በዚህ መልኩ የተሳተፉትን ወገኖች የትግል እንቅስቃሴ ለማሳነስ መሞከራቸውና ክብርት የሆነችውን የታጋይዋ ሴት ክብር በሚያዋርድ አገላለጽ የሰጡት አስተያየት ከምን ላይ እንዳሉ የሚገልጽ ይመስለናል፡፡

ማኅበራችን ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ጉዳተኞች በመረጡዋቸው የማቋቋም ስራ ከተሰማሩና የዓዲግራት የጦር ጉዳተኞች ማዕከል ከፈረሰ በኋላ በቀጣይነት የሚፈልጓቸው ድጋፎች ለማስተባበርም ሆነ ከአካል ጉዳታቸው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሕገመንግስቱንና ሌሎች ህጎች ያጎናፀፈንን መብቶች በትክክል ከማስከበር አኳያ የጋራ ራዕይ በመሰነቅ በጉዳተኛ አባላት የተመሰረተ ማህበር ነው፡፡ ማህበሩ በፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦና አንድ መንግስታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ማሟላት ያለበትን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት ህግንና ስርዓትን ተከትሎ እየሰራ ያለ የልማት ድርጅት ነው፡፡ በሁሉም የትግራይ ወረዳዎችና ዞኖች እስከ ቀበሌ/ጣቢያ የወረደ አደረጃጀት እንዲሁም በአዲስ አበባ የማስተባበሪያ ቢሮና ከትግራይ ውጪ ያሉትን የጦር ጉዳተኞች የሚያስተባብር አደረጃጀትና አሰራር አለው፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ መሰረት የስራ አመራሩን የሚመርጠውና የሚሽረው ጠቅላላ ጉባኤው ሲሆን ከሁሉም አካባቢ በተወከሉ አባላት የሚሰየም ነው፡፡

በማኅበሩ ካሉት 25"000 በላይ አባላት ውስጥ ሴት የጦር ጉዳተኞች 10 በመቶ የሚሆኑት ሲሆኑ ላለፉት ሶስትና አራት አመታት ከህላሑ (ዓለም አቀፍ የስራ ድርጅት) እንዲሁም ከክልሉ የፀረ ኤድስ ሴክሬተሪያት ጋር በመተባበር በሴት የጦር ጉዳተኞች ብቻ ያተኮሩ የስልጠና፣ የብድርና ሌሎች የአቅም ግንባታ ስራዎች በመስራት ለጦር ጉዳተኞቹ ህይወት መለወጥና መሻሻል አብነታዊ ስራዎች ሰርቷል፡፡

በአጠቃላይ ግን ማህበሩ የተቀናጀ ማህበረሰብ አቀፍ የተሃድሶ ፕሮግራም /Comprehensive Community Based Rehabilitation/  በመንደፍና በመተግበር ላይ ሲሆን በአገራችን እጅጉን ትልቅና የተደራጀ የሚባል የሰው ሰራሽ አካል ማምረቻና የፊዝዮቴራፒ ህክምና ተቋም በተጠናከረ ሁኔታ በማደራጀት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በኢኮኖሚው፣ በስነ ልቦናና ማህበራዊ ተሃድሶ ፕሮግራም እንዲሁም በመብት ማስከበር ዙሪያም የአጭርና የመካከለኛ እቅዶች በመንደፍ የሁሉም አካልና ድጋፍ ሰጪ ማህበረሰብ ተሳትፎ ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እየሰራ ይገኛል፡፡ በአስራ ሁለት ዓመታት ጉዞው ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ በየጊዜው በማቅረብ ላይ ቢሆንም ሃቁን ማድበስበሱና "በጦር ጉዳተኞች ስም የሚመጣውን ብር የት እንደሚውል አይታወቅም" መባሉ አውቆ ለተኛ. . . እንዲሉ ይሆናል፡፡ አባላቱ በወከሏቸው ወኪሎች በጋራ ያቅዳሉ፣ ይፈጽማሉ፣ ያስፈጽማሉ፡፡ የማህበሩ ሒሳብ በውጭ ኦዲተሮች ኦዲት እየተደረገ ለሚመለከተው የመንግስት አካል የሚቀርብ ሲሆን እስከ ታህሳስ 2007 እ.ኤ.አ ድረስ ኦዲት ተደርጓል፡፡ ስለ ማህበሩ የሃብት ምንጭና አጠቃቀም፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ የሚሰራ ነው፡፡ የግንዛቤው ችግር እዚህ ላይም ይንፀባረቃልና፡፡

በመሰረቱ የማቋቋም ስራ በአንድ ጀምበር ተጀምሮ የሚያልቅ ሳይሆን የተለያዩ እንቅስቃሴዎችና ግብአቶች በማጣመር በቀጣይነት ሊሰራ የሚገባ መሆኑ አለማወቃቸው ሌላው ችግራቸው ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ለልጆቹና ለከፈሉት መስዋዕትነት የሚሰጠውን ክብር አንኳሰው የሰጡት አስተያየት የሚያስገምታቸው ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ መረጃ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

በአጠቃላይ በማንኛውም ወቅት በማንኛውም ቦታ ማንም ቢሆን ስለኛ ከእኛ በላይ መናገር እንደማይችል ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በእውነትና ስለ እውነት ለመስራት ከታሰበ በመደራጀትና የጋራ ራዕይ በመስነቅ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲጫወት በማድረግ የሚመጣ ሁለገብና ዘላቂ ልማት እንጂ በጥገኛ አስተሳሰብ /አመለካከት/ ላይ የተመሰረተ የማቋቋም ስራ ፍሬ የለውም ብለን እናምናለን፡፡ ተደራጅተን ጠንካራ ማህበር እንደመሰረትነው ሁሉ የጀመርናቸውን አላማዋች እና ግቦች ከህዝባችን፣ ከመንግስትና ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር እጅና ጓንት ሆነን በመስራት ዳር ከማድረስ የሚያግደን ነገር እንደሌለ አስረግጠን እንናገራለን፡፡ እንደ አንድ የኅብረተሰብ አካልም አጠቃላይ ችግሮቻችን የሚፈቱት መሰረታዊ የሆኑ የማህበረሰባችን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲፈቱ እንደሆነ በማመን ሁሉም ወገን ራስን የመቻል መርህ በተከተለ መልኩ ለልማቱ መፋጠን የጀመረውን ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሉን እገዛ መጫወት እንዳበት ጥሪያችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡
 
< Prev   Next >