| የወጣቶቹ ፍሬ |
|
|
| Wednesday, 16 July 2008 | |
|
ሦስት የኮምፕዩተር ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡ ሦስቱም ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በኮምፕዩተር ሣይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1999 ዓ.ም አግኝተዋል፡፡ የ23 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወጣቶች (ምስጢርን እንዴት መላክ እንደሚቻል) (ስቴጋኖ ግራፊ) በመመራመር ውጤት ላይ ደርሰዋል፡፡ ሣሙኤል ከፈለኝ በግሉ የተለያዩ ምርምሮችን በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ በለጠ ኃይሉና ዳንኤል ታረቀ ደግሞ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከሥራ ሰዓት ውጪ ያለውን ጊዜያቸውን ሦስቱም አንድ ላይ በመሆን ምስጢርን እንዴት መላክ እንደሚቻል ቴክኖሎጂ በመመራመር ላይ ያውሉታል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአማርኛ ምስጢር መጠበቂያ እንዲሁም ወርድ ላይ ጽሁፍን እየፃፉ በኋላ ፊልሞችን ለማየት የሚያስችል ሶፍት ዌር እንዲሁም ከኮምፒዩተር ጋር ተገናኝቶ በኤፍ.ኤም ሬዲዮ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ማሠራጨት የሚችል ትራንስሚተር እንደሠራ ወጣት ሣሙኤል ተናግሯል፡፡ አሁን ደግሞ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በስቴጋኖ ግራፊ ቴክኖሎጂ (በምስጢር መጠበቂያ ዘርፍ) ከፍተኛ የሚባለውን በምርምር ደረጃ ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ በመሥራት ይፋ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ ቴክኖሎጂውን ለመሥራት እንቅስቃሴ የጀመሩት ከሁለት ዓመት በፊት ትምህርት ቤት እያሉ ነው፡፡ በወቅቱ ይቻላል ብሎ ለማሰብ በራሱ ከባድ እንደነበር ነው ሣሙኤል የሚጠቅሰው፡፡ ምክንያቱም በፎቶግራፍ፣ በዘፈን ወይም በፊልም ውስጥ ሌላ ፎቶግራፍ፣ ሌላ ዘፈን፣ ሌላ ፊልም ወይም ምስጢር መላክ ይቻላል የሚለውን ለመቀበል አዳጋች ስለነበር ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ይህንን አሠራር ይፈቅዳል ወይ የሚለውም አሳማኝ አልነበረም፡፡ በየወቅቱ የተፈጠሩትን መሰናክሎችን በመቋቋም ቴክኖሎጂውን እውን አድርገውታል ወጣቶቹ፡፡ መጀመሪያ በእንግሊዝኛ ሠሩት፣ ቀጥሎ የአማርኛ ቋንቋን ድጋፍ እንዲያደርግ አደረጉት፡፡ ሃሳቡንም ያመነጩት በጋራ ነው፡፡ በምስጢር መጠበቅ ሂደት ውስጥ የመጨረሻው ሊሰበር የማይችል ነገር መሥራት አንችልም ወይ ከሚል ውይይት የተገኘ ነው፡፡ ..ኢንክሪፕሽን የማቲማቲክስ ፎርሙላዎችን ነው የሚጠቀመው፡፡ ፎርሙላዎቹ የማሽኖቹን ፓወር በመጠቀም ብዙ ጊዜ ይወስዳሉ እንጂ ይሰበራሉ፡፡ እነዚህን እንዳይሰበሩ ይህን ቴክኖሎጂ መፍጠር እንዳስፈለገ ወጣቱ አስረድቷል፡፡ ብዙ የፎቶ (የምስል) መልዕክቶችን በኢሜል ሲላኩ ሰውየው ምስሉ ውስጥ ሌላ መልዕክት ሊደበቅ እንደሚችል መጠርጠር እንዳለበት ወጣት ሣሙኤል ይገልፃል፡፡ የጠረጠረው ሰው የእነርሱ ሶፍት ዌር ያስፈልገዋል፡፡ ቀጥሎ የተጠቀሙበትን ኢንክሪፕሽን አልጎሪዝምን አግኝቶ በእርሱ መስበር እንዳለበት ነው፡፡ እነዚህን ሂደቶች ማለፍ ስለሚያስፈልግ የተሻለ ምስጢር ለመጠበቅ ነው ቴክኖሎጂውን የፈጠሩት፡፡ ኅብረተሰቡ ይህንን ቴክኖሎጂ የሚፈልግበት ጊዜ ላይ ተደርሷል ይላሉ ወጣቶቹ፡፡ የመንግሥት አካላት ቴክኖሎጂው ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሕዝብን ደህንነት የሚጠብቁ መሥሪያ ቤቶች ምስጢራቸውን በከፍተኛ ደረጃ መጠበቅ ስላለባቸው ቴክኖሎጂው እንደሚያስፈልጋቸው ሣሙኤል አመልክቷል፡፡ ስቴጋኖ ግራፊ የግሪክ ቃል ሲሆን ስቴጋኖ ማለት ድብቅ፣ ግራፊ ደግሞ መፃፍ ማለት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ሂድን ራይቲንግ ማለት ሲሆን በአማርኛ ድብቅ (የምሥጢር) ጽሁፍ ይሆናል፡፡ ቴክኖሎጂው በምርመራ ላይ ስለሆነ የስቴጋኖ ግራፊ የሚሸጥ ሶፍት ዌር እንደሌለ ወጣት ዳንኤል አመልክቷል፡፡ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ የሚሆንባቸው ሆስፒታሎች (የሕሙማን ምስጢር ለመጠበቅ..፣ መከላከያ፣ ባንክ፣ ደህንነትና ሌሎችም መሥሪያ ቤቶች ተጠቅሰዋል፡፡ የአንድን ሕመምተኛን ፎቶግራፍ በማስቀመጥ ምስጢሩ ዶክተሩ ብቻ እንዲያውቀው ማድረግ ይቻላል፡፡ ሌላ ሰው ሊያገኘው አይችልም፡፡ ሌላው ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው ባንክ የገንዘብ ዝውውር ቢኖር ኮድ ተጠቅመው ምስጢር ወደ ሁለተኛው ቅርንጫፍ መላክ ያስችላል፡፡ ለስለላ፣ ከፍተኛ ምስጢር ለሚይዙ መሥሪያ ቤቶች ቴክኖሎጂው አስፈላጊ እገዛን ይሰጣል፡፡ በተጨማሪ ዳንኤል ያነሳው ዚፕ ቴክኖሎጂን ነው፡፡ ድብቁን ምስጢር በኢንተርኔት አሳንሶ መላክ ያስችላል፡፡ ከስሩ ኢንክሪፕሽንም ይኖረዋል፡፡ ድንገት ተመልካቹ ቢጠረጥር (ምስሉ፣ ሙዚቃው .. ደብዳቤ መልዕክት ቢኖረው ሙዚቃው ይጫወታል፡፡ ጠርጣሪው ከጠረጠረ ሶፍትዌር ያስፈልገዋል፡፡ ሶፍትዌሩን በአጋጣሚ እንኳ ቢያገኝ ቁልፍ ያስፈልገዋል፡፡ ኢንክሪፕሽኑን ለመዝለል ብዙ ደረጃዎች አሉ፡፡ የቴክኖሎጂው የፈጠራ ባለቤት መሆናቸው ማን እንዳረጋገጠላቸው ጠይቀናቸው ነበር፡፡ በሶፍት ዌር ቴክኖሎጂ የኢትዮጵያ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ እውቅና እንደማይሰጥ ነው ወጣቶቹ ያስረዱን፡፡ ዩኒቨርሲቲያቸው ግን ቴክኖሎጂው የእነርሱ ውጤት መሆኑን ማረጋገጫ ሊሰጥ እንደሚችል ወጣት በለጠ ኃይሉ ነግሮናል፡፡ የእነሱ ምስልና እነርሱ መሥራታቸውን ማረጋገጫ ዘዴዎች ስላሉት ሶፍት ዌሩም እንደማረጋገጫ ያገለግላል፡፡ ወጣቶቹ፣ ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ደብዳቤ ቢያስገቡም ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም በዚህ ሥራ መጠቀም የሚችሉ መሥሪያ ቤቶች መጠቀም እንዲችሉ ጠይቀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |