Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Wednesday
Aug 20th
Home arrow Sections arrow ጉርሻ (ቲኘ) እንደ ዋና የገቢ ምንጭ
ጉርሻ (ቲኘ) እንደ ዋና የገቢ ምንጭ Print E-mail
Wednesday, 16 July 2008
Imageበብርሃኑ ፈቃደ

በርካታ ጥናቶች ተደርገውበታል፡፡ ባደጉት፣ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደህና በሚባሉት የበለፀጉ አገሮች ዘንድ ለብዙ ሙያተኞችና ምሁራን ዋና የመነጋገሪያ ርዕስ እስከ መሆን ደርሷል፡፡

ከአንዳንድ ጥናቶች በመነሳት ለመገንዘብ እንደቻልነው በአሜሪካ በሚገኙ ግዛቶች በአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ከሚሰሩ ሰዎች አብዛኛዎቹ 30 በመቶና ከዚያም በላይ የሚሆነው ገበያቸው በዋናነት የሚገኘው ከቲኘ (ከጉርሻ) መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ሳይንሱን መሠረት በማድረግ ሰዎች ጉርሻ የሚሰጡበት ምክንያት በተለይ ከኢኮኖሚክስ የሙያ ዘርፍ አንፃር ይህ ነው ብለው ለመናገር የሚችሉበት ተጨባጭ ነጥብ የለም፡፡ በቲኘ ዙሪያ የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ ግን በዋናነት ተጠቃሚዎችና ደንበኞች ከማኅበራዊ ግዴታ በመነሳት አሊያም ከፍትሐዊነት እሳቤ በሚመነጭ ስሜት ቲኘ እንደሚሰጡ ያስረዳሉ፡፡

አንዳንድ  ጥናቶችና አስተያየቶች ደግሞ በተቃርኖ ይመለከቱታል፡፡ አንድ አሜሪካዊ ምሁር የካፌና የሬስቶራንስ ባለቤቶች ወይም ሌሎች አገልግሎቶች ሰጪ ድርጅቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ አንድ የደመወዝ አካል በመቁጠር ደንበኞቻቸው ቲኘ እንዲሰጡ በይፋ እስከመጠየቅ መድረሳቸውን ይገልፃሉ፡፡ "ለመሆኑ ለተሰጠኝ አገልግሎት ተገቢውን ክፍያ ከመክፈል ባለፈ ቲኘ እንድሰጥ ግድ የምባለው ምን ሲደረግ ነው?" በማለት ይጠይቃሉ፡፡

ስታር-ትሪቡን የተሰኘ አንድ የአሜሪካ ጋዜጣ እ.ኤ.አ በግንቦት 2008 ባሰራጨው የድረ ገፅ ዘገባ ቀላል የማይባሉ ታክሲ ሾፌሮች፣ አስተናጋጆች፣ ፀጉር አስተካካዮችና በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች በዋናነት የገቢያቸው ምንጭ ቲኘ እንደሆነ ያትታል፡፡ ነገር ግን ይላል ጋዜጣው ነገር ግን አሁን ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት በፈጠሩት ውጥረት የእነዚህ ሰዎች የገቢ መጠን ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ ሄዷል፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ አንዳንድ የቦስተን ግዛት ራተኞችን አነጋራል፡፡

ሜሊ ሜትዝ የተባለች የቡና ቤት አስተናጋጅ እንዳለችው ከቲኘ ታገኝ የነበረው ሣምንታዊ ገቢ 25 በመቶ ቀንሷል፡፡ "ደንበኞቻችን አልፎ አልፎ ነው የሚመጡት፤ ቢመጡም ብዙ አይቆዩም፡፡ በፊት አምስት ብር ቲኘ የሚሰጡት አሁን ሁለት ብር ብቻ በመስጠት ላይ ናቸው" ብላለች፡፡ ዳዊት ብርሃኔ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ መተዳደሪያው የታክሲ ሹፍርና ነው፡፡ ከቲኘ የሚያገኘው የገቢውን 2ዐ በመቶ ሲሆን የነዳጅ ወጪውን በሚገባ ይሸፍንለት እንደነበር በአሁኑ ወቅት ግን ወደ 5 እና 1ዐ በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን አንዳንዴም ከነጭራሹ ቲኘ እንደማያገኝ ይገልፃል፡፡

ሌላኛዋ ጁዌል ከንዴፍ የተባለች አስተናጋጅ 75 በመቶ ገቢዋን ከቲኘ የምታገኝ መሆኑን ተናግራለች ከአንድ ትዕዛዝ በአማካይ 2ዐ በመቶ የሚሆን ጉርሻ ይሰጣት ነበር፤ አሁን ግን ቀርቷል፡፡ "ብዙ ሰዎችን ማስተናገድ ካልቻልክ ብዙ ቲኘ ልታገኝ አትችልም" ብላለች፡፡

በእኛ አገር ምን እንደሚመሰል እንይ፡፡ የስታር ትሪቡንን ፅሑፍ በዋቢነት ተጠቅመን በመዲናችን አንዳንድ ቦታዎች በመዘዋወር የካፌ አስተናጋጆችን አነጋግረናል፡፡ ቦሌ፣ ኦሎምፒያ፣ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ጊዮርጊስ በመሳሰሉት ሥፍራዎች በሚገኙ አገልግሎት መስጫዎች ውስጥ ተፍተፍ ሲሉ ያገኘናቸውን ለጠየቅናቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

ሠርካለም ድንቁ ትባላለች፡፡ ካቴድራል አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፌና ሬስቶራንት ውስጥ ተቀጥራ ነው የምትሠራው፡፡ በቀን ለስምንት ሰዓት ያህል ሰርታ ከድርጅቱ የሚከፈላት የወር ደመወዝ 15ዐ ብር መሆኑን ገልፃለች፡፡ አሁን አለው የኑሮ ውድነት አንፃር እንዳልሆነ፣ ከመቀመጥ ይሻላል ብላ እንደሆነና በቲኘ በምትገኘው ገቢ ችግሩ ይሸፈናል የሚል እምነት አላት፡፡

በአማካይ ስለሚኘው የቲኘ መጠንም ስታስረዳ "አልተገኘም ከተባለ በቀን ከ10-13 ብር፣ በደንብ ስንሰራ ደግሞ እስከ 2ዐ ብር የምናገኝበት ወቅት አለ" ብላለች፡፡ እያንዳንዱ ሰው ከ5ዐ ሳንቲም እስከ አምስት ብር በአማካይ የሚሰጥበት ወቅት መኖሩንም ታስረዳለች፡፡

ሌላዋ ጊዮርጊስ አካባቢ በዚሁ በመስተንግዶ ሥራ ላይ ሦስት ዓመታትን እንዳሳለፈች የምትገልፀው ሜላት ገብሬ ናት፡፡ ከድርጅቱ በወር 1ዐዐ ብር የሚከፈላት ሲሆን በምታገኘው የቲኘ ገቢ ወጪዎቿን ትሸፍናት፡፡ ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በአሁን ወቅት የምታገኘው የቲኘ መጠን ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር እንደቀነሰ የምትናገረው ሜላት፣ ለሙዚቃ ትምህርቷ የሚሆን ክፍያ ከቤተሰቦቿ ለመጠየቅ ትገደዳለች፡፡

አራት ኪሎ አካባቢ ያገኘነው ወጣት በወር ብር 2ዐዐ ይከፈለዋል፡፡ ቀኑን ሙሉ በዚሁ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይውላል፡፡ ቤት ተከራይቶ የሚኖር በመሆኑም የግድ ቲኘ ካላገኘ ኑሮውን መደጐም ከባድ እንደሚሆንበት ይገልፃል፡፡

በተዘዋወርንባቸው ሥፍራዎች አሥር ወጣቶችን አነጋግረናል፡፡ ሁለም ማለት ይቻላል በአማካይ የወር ደመወዛቸው ዝቅ ሲል 1ዐዐ ብር ከፍ ካለም 15ዐ ብር ነው፡፡ በዋናነት ዓይነተኛ የገቢ ምንጫቸው ከደንበኞቻቸው የሚያገኙት የቲኘ መጠን ነው፡፡

ከቀድሞው ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ መቀነስ ቢታይበትም ተስተናግዶ መጠነኛ ቲኘ ጣል ሳያደርግ የሚሄድ እምብዛም እንደሆነ በአንድ ድምፅ የሚስማሙት እነዚህ ሰራተኞች ወደፊት የኑሮ ውድነቱ ማቆሚያ ከሌለው የቲኘ ገቢ አስጊ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

ከአሰሪዎቻቸው የተለየ ክፍያ አልፎ አልፎም ቢሆን ያገኙ እንደሆነ ተጠይቀው ምንም እንደማያገኙ እነዚሁ ሰራተኞች ይብሱኑ ከዚያችው ገቢያቸው ላይ በዓል ሲመጣ ለሚሰሩበት ቤት ውበት የባህል ልብሶችን ገዝተው እንዲለብሱ በሚጐድሉ እቃዎችና የሚጎድልባቸው ሒሳብ ከወር ደመወዛቸው ላይ የሚቆረጥባቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከላይ ያነሳነው የአሜሪካውያን መፍትሔ እንመልከት፡፡ እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ መንግሥት በዋናነት በአነስተኛ የሥራ ውጤት በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ የተሰማሩትን በማገዝና የገቢ መጠናቸውን ከፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ዝቅተኛው የደመወዝ መጠን ከነበረበት የ"5.15 በሰዓት እያደገ መጥቶ በመጪው ዓመት ወደ "7.25 በሰዓት እንደሚያሻቅብና ይህም በመንግሥት እየተደረገ የሚገኝ ማሻሻያ መሆኑን የአሜሪካው የኢኮኖሚክስ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ትንታኔ ያስረዳል፡

ለእነዚህ ሠራተኞች የጤና ሽፋን ዋስትና፣ የማኅበራዊ ዋስትናና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን እንደሚሰጥ የምናገኛቸው መረጃዎች ያብራራሉ፡፡

በተለይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሠራተኞች ለገቢያቸው መሻሻል ይበጃል ያሉትን መፍትሔ ከመፈለግ አልቦዘኑም፡፡ የእረፍት ጊዜያቸውን ወደ ሥራ በመቀየር፣ በሳምንት የሚሰሩባቸውን የሥራ ሰዓቶች ከፍ እንዲሉ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ በመግቢያችን ላይ ያነሳናት ሜሊዛ ሜትዝ በቲኘ ማሽቆልቆል ሳቢያ በሳምንት ትሰራ ከነበረው 4ዐ ሰዓት ወደ 5ዐ በማሳደግ ገቢዋን ለመደጐም መቻልዋን ገልፃለች፡፡

በአንዳንድ ቦታዎች ለመታዘብ እንደሞከርነው የንግድ ቤት ባለቤቶች ሰራተኞችን ለመቅጠር ከሚደራደሩበት አንዱ መስፈርት በቤታቸው ውስጥ ከሚስተናገደው ሰው የሚገኘው የቲኘ መጠን ከፍ ያለ መሆን ነው፡፡ በቀን 8 ሰዓት ወይም ሙሉ ቀን ቢሰሩ 1ዐዐ እና 15ዐ ብር መክፈል በቂ ነው ይላሉ፡፡ ግማሽ ያህሉ ያነጋገርናቸው ሠራተኞች ይኸው ደመወዛቸው ወቅቱን ተጠብቆ የማይሰጣቸው መሆኑን ነው፡፡ እንዳንዶቹም "ዛሬ ወጪ ስላወጣሁ፣ እቃ ስለገዛሁ፣ ሌላ ጊዜ ይሰጣችኋል" የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸውም ይናገራሉ፡፡

የኮንትራትና የጊዜያዊ ቅጥር ሠራተኞችን መንግሥት ምንም ሊያደርጋቸው አይችልም የሚለውን በመቀየር እንደ አሜሪካ ባይሆን እንኳ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ይቻላል፡፡ አብዛኛዎቹ ቀጣሪ ድርጅቶች ለመንግሥት ግብር እና ታክስ ይከፍላሉ፡፡ ከእነዚህ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚሰበሰበው ገቢ ተሰልቶ በተገቢው መንገድ በጥናት ላይ በመመርኮዝ የመነሻ ደመወዝ በዚህ መጠን ይከፈል ማለት ይቻላል፡፡
 
< Prev   Next >