Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Sep 07th
Home arrow Sections arrow ክቡር ሚኒስትር
ክቡር ሚኒስትር Print E-mail
Wednesday, 16 July 2008

(ሚኒስትር መሥሪያ ቤት በኃላፊነት እንዲያሳካ የተሰጠውን ፕሮጀክት የሚገመግም ከአገር ውስጥና ከውጭ የተውጣጣ የኤክስፐርቶች ቡድን ክቡር ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት ድረስ መጥቷል፡፡ እሳቸውም ከባለሙያዎቻቸው ጋር ናቸው፤ ስብሰባው ተጀምሯል)

 

- ክቡር ሚኒስትር፣ ይህ ግምገማ የሚካሄደው በሁለት ዙር ነው፡፡ የአሁኑ ዙር በዋነኛነት የመረጃ ማሰባሰቢያ ስብሰባ ነው፡፡ ሁለተኛው ለወደፊቱ የምናደርገው ስብሰባ የመጨረሻ ግምገማ አስተያየታችን የምንሰጥበት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክቱ ሲነደፍ የነበረ ውል ነው፤ ታውቁታላችሁ፡፡
- አዎን እናውቀዋለን፡፡ ለዚህም ተዘጋጅተናል፡፡
- አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡ በናንተ በኩል ፕሮጀክቱ እንዴት ተካሄደ? ውጤታማ ነው? አስተያየታችሁን ለማወቅ እንፈልጋለን፡፡ ከእናንተ በኩል ሃሳቡን ማቅረብ ይቻላል፡፡
- (የሚኒስትሩ ረዳት) በእውነቱ እሳቸው እዚህ ባይኖሩና ፊታቸው ባልናገር እመርጣለሁ፡፡ ተናገር ከተባልኩ ልናገርና በእውነቱ በክቡር ሚኒስትራችን ብቁና ንቁ አመራር፣ ከተጠበቀው በላይ በተሳካ ሁኔታ የታገዘ ፕሮጀክት ሆኗል፡፡
- (የሚኒስትሩ የፕላኒንግ ኃላፊ) ይህ መሥሪያ ቤትና ይህ ፕሮጀክት የታደሉ ናቸው፡፡ ቀንና ሌሊት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሰሩና የሚመሩ ሚኒስትር አሉን፡፡ ዕድሜ ለክቡር ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ የተሳካ ፕሮጀክት ነው ብዬ በሙሉ ልብ እናገራለሁ፡፡
- ክቡር ሰብሳቢ አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ ፕሮጀክቱ ተሳካ ብላችኋል፡፡ በታቀደለት በጀት እየሄደ ነው?
- (የፋይናንስ ኃላፊው) እሱ ነው ዋናው አስደናቂው ነገር፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አንዲት ፍሬ አሸዋ እንዳትባክን ይቆጣጠራሉ፡፡ በእሳቸው ጥብቅ ቁጥጥርና አመራር ከባጀት በታች በሆነ ገንዘብ ነው ፕሮጀክቱ እየተጠናቀቀ ያለው፡፡ ዕድሜ ለሳቸው ለክቡር ሚኒስትሩ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ምነው ዝም አሉ፤ እርስዎም ቢናገሩ ጥሩ ነው፡፡
- አመሰግናለሁ፡፡ ቁራ መጀመሪያ ሲፈጠር ነጭ እርግብ ነበር አሉ፡፡ እግዚአብሔር መልዕክት እንዲያደርስ ወደ አንድ ቦታ ላከው፡፡ መልዕክቱን ሳያደርስ ቀረ፡፡ ጌታችንም ቅር አለውና ረገመው፡፡ ከአሁን በኋላ ጥቁር ቁራ ሁን ብየሃለሁ አለው ይባላል፡፡ እኔም የተሰጠኝን ኃላፊነት ባልፈፅም እግዚአብሔርም እንደሚረግመኝ ሕዝብና መንግሥትም እንደሚወቅሱኝ አውቃለሁ፡፡ ብሰራ ምን ይገርማል? የተሾምኩት እንዳገለግል አይደለም?
- ሰብሳቢ እንደገና ሌላ ጥያቄ ላንሳ፡፡ ፕሮጀክቱ የሃያ ሚሊዮን ዶላር ሆኖ በዋነኛነት የዚህ መሥሪያ ቤት ኃላፊነት ቢሆንም ሌሎች መሥሪያ ቤቶች በአፈፃፀሙ እንዲሳተፉ የሚያደርግ ነው፡፡ የእነሱ ተሳትፎ እንዴት ነበር ክቡር ሚኒስትር? ለዚህ መልስ ከእርስዎ ብጀምር፡፡
- የእናት ሆድ ዝንጉርጉር ነው ይባላል፡፡ አንዱ ቀንና ሌሊት ይሰራል፣ ሌላው ተለምኖም ተወትውቶም ንቅንቅ አይልም፡፡
- (የሚኒስትሩ ረዳት) በዚህ ጉዳይ ላይ ክቡር ሚኒስትሩ ለመናገር እንደሚቸገሩ አውቃለሁ፡፡ ቢናገሩ ጉራ ይመስላል፡፡ የሌሎች መሥሪያ ቤቶች ተሳትፎ ደካማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ክቡር ሚኒስትር አንድ ቀን ሰብስበው እነሱ መሥራት ስለማይፈልጉ የእነሱም ኃላፊነት ደርበን እንስራ ብለውን ደርበን ሰርተን ነው ፕሮጀክቱን ለስኬት ያበቃ ነው፡፡
- እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ሌላ ጥያቄ ለክቡር ሚኒስትሩ እንዳነሳ ይፈቀድልኝ፡፡ እርስዎ ክቡር ሚኒስትሩ ለምን እምቢ ላሉት መሥሪያ ቤቶች ችግሩን አላነሱም? ተወያይታችሁ ለምን አልፈታችሁትም?
- ሁሉም ወታደር ወታደር ስለተባለ በጦር ሜዳ እኩል ጀግንነት ያሳያል ማለት አይደለም፡፡ ለምን ጀግና አልሆንክም ብሎ መውቀስም መገምገምም አይቻልም፡፡
- ለምን ፈሪ ሆንክ፣ ለምን የጦር ሜዳ ግዳጅህን አልተወጣህም? ብሎ መገምገም ግን ይቻላል፡፡ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ተብሎ የለ፡፡
- ታዲያ ይህ ችግር በካቢኔው ስብሰባ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያሳውቁ አይሻልም? ይህ ገንዘብ በብድር የመጣ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሌሎች ሚኒስትሮች ማወቅ አለባቸው፡፡ ተሳሳትኩ ክቡር ሚኒስትር?
- የሶማሊያ ሃሳብ፣ የኤርትራ ሃሳብ፣ የነዳጅ ችግር ሃሳብ፣ የምግብ እጥረት ሃሳብ ወዘተ. እያለባቸው ደግሞ እኔ መሸፈን የምችለውን ችግር እያነሳሁ ላስቸግራቸው?
- ለመሆኑ ሁሉም ነገር ኦዲት ይደረጋል?
- (የፋይናንስ ኃላፊው) አዎን ኦዲተሮች እስኪገርማቸው ድረስ እንደውም አንዱ ኦዲተር በእጅጉ ከመደነቁ የተነሳ መሥሪያ ቤታችንን "የመላዕክት ሚኒስቴር" ብሎታል፡፡
- አሁን መቼ ተጠናቆ መቼ ይመረቃል ብላችሁ ታስባላችሁ?
- (የፕላኒንግ ኃላፊው) በእኛ በኩል ባለፈው ወርም በተመረቀ ነበር፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ሌላ እንግዳ ጥሩ እንጂ እኔ አልመርቅም፣ አልቆርጥም አሉን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ሥራ አላቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ውጭ አገር ናቸው፡፡
- ችግራችሁ የቆራጭ ችግር ነው ማለት ነው?
- እንዲያው ግርማ ሞገስ ባለው ሁኔታ ለማስመረቅ ነው፡፡

(ቀኑን ሙሉ በተለያዩ ጉዳዮች ውይይት ተካሄደ፡፡ የመጨረሻው ግምገማና አስተያየት ከአንድ ወር በኋላ እንደሚሆን ተስማምተው ስብሰባው ተበተነ)

- ክቡር ሚኒስትር ነገሩን ሁሉ አዩት አይደል?
- አልገባኝም፡፡
- ሰዎቹኮ እጅግ ደስ ብሏቸው ተደንቀው ነው የሄዱት፡፡
- ይገባቸዋል ብለህ ነው?
- እንዴ ፊታቸው ፈክቶ ፈገግታ በፈገግታ ሆነው ነውኮ የወጡት፡፡ በተለይ".
- በተለይ ምን?
- ክቡር ሚኒስትር፣ በተለይ ኢትዮጵያውያኑ በደስታ ነው ፍልቅልቅ ሲሉ የነበሩት፡፡ የፈረንጆቹ ፊት አያስታውቅም እንጂ፡፡
- አንድ ምቀኛና ቀናተኛ ሹክ ቢላቸው ሃሳባቸውን ይቀይሩ ይሆናል፡፡ የእኛን ስኬት የማይፈልጉ በርካታ ሰዎችና መሥሪያ ቤቶች እንዳሉ አትርሳ፡፡

(ከወር በኋላ ለመጨረሻ ግምገማ ስብሰባ ተደረገ፡፡ እንዳለፈው ክቡር ሚኒስትሩም አሉ፡፡ ሰብሳቢው የመግቢያ ንግግሩን ጨረሰ፡፡ መድረኩ ተከፈተ)

- እና ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ግልፅ ውይይት ማካሄድ አለብን፡፡ ፕሮጀክቱ እናንተ እንደነገራችሁን ሆኖ አላገኘነውም፡፡
- (የፕላኒንግ ኃላፊው) እንዴት?
- ምንም የተጠናቀቀ ነገር የለም፡፡ ገንዘብ አወጣጡ ላይ ብዙ ችግር አለ፡፡ የገንዘብ አወጣጡ ግልፅ አይደለም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የፋይናንስ ኃላፊው ሊያስረዱ ይችላሉ፡፡
- (የፋይናንስ ኃላፊው) አሁን የተባለውን ያለፈው ስብሰባችን እንዳለቀ ክቡር ሚኒስትሩ ያሉኝን አስታወሰኝ፡፡ "የእኛን ስኬት የማይፈልጉ በርካታ ሰዎችና መሥሪያ ቤቶች እንዳሉ አትርሳ" ብለውኝ ነበር፡፡
- ጊዜ ስለሌለን ወደ ቁም ነገሩ ብንገባ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
- ለማለት የፈለግኩት ሌሎች ሰዎች አሳስተዋችሁ እንዳይሆን ተጠንቀቁ፤ ለማለት ነው፡፡
- አታስቡ፣ አልተሳሳትንም፡፡ ለምሳሌ በተጨባጭ ከተገዛው ንብረት ግማሹ ደረሰኝ የለውም፡፡
- ወደ ሥራ ስንጣደፍ ያልሰበሰብነው አለ፡፡ ሲያልቅ ሊሰበሰብ ይችላል፤ አሁን ጊዜ አናጥፋ ብለን የሄድንበት አለ፡፡
- ተገዛ ከተባለውም ወደ ፕሮጀክቱ ያልገባ በርካታ ንብረት አለ፡፡ እንዲያውም ወደ ራሳቸው ቤት ግንባታ ያግዙት ነበር የሚል መረጃ ነው የደረሰን፡፡
- በሁለት ዓመት የፕሮጀክት ሥራ ወቅት ሁለቴ ብቻ ነው ለአስቸኳይ ሥራ ሁለት መኪና ወደ መኖሪያ ቤት ሥራ የሄደው፡፡
- ሁለቴ ቢሆንስ ለምን ይሄዳል?
- ክቡር ሚኒስትሩ ቤት እየሰሩ በድንገት ሲሚንቶ ሲያልቅባቸው ይተካል ተብሎ የተወሰደው ሁለቴ ብቻ ነው፡፡ ከሁለት ሺህ ጭነት ሁለቴ ብቻ፡፡
- ሰብሳቢ ነኝና ጥያቄውን ወደ ክቡር ሚኒስትሩ ላዙረው፡፡ ሁለት መኪና ወደ ቤትዎ ማሰሪያ መላክዎ ትክክል ነው?
- ኧረ ይህ ሰውዬ ውሸታም ነው፣ አትመኑት፡፡ እኔ ምንም መኪና ወደ ቤቴ አላስላኩም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ረሱት መሰለኝ፡፡ አንዴ ባለቤትዎን፣ አንዴ ልጅዎን ልከው ሁለት መኪና አስጭነው ያውም በቴክስት "ታንክዩው" ያሉኝን ይኸው እስካሁን ድረስ አላጠፋሁትም፡፡
- በቃ በቃ አሁን ቴክስት ወስደን መመርመር አንችልም፡፡ ወደ ሌላ ጉዳይ ስንሸጋገር ደግሞ በተጨባጭ የነበረው ፕላን ተቀይሯል፡፡
- (የፕላኒንግ ኃላፊ) ምን የተቀየረ አለ?
- ፕላኑ አዲስ ግንባታ ለማካሄድ አዲስ ተጨማሪ መስራት እንጂ፣ የነበረውን እያፈረሱና እሱን እያጓጓዙ አይደለም፡፡
- አልገባኝም፡፡
- ከአሁን በፊት የተሰሩትን እያፈረሳችሁ የእነሱ ብረት፣ ድንጋይና ቆርቆሮ እያጋዛችሁ ነውኮ አዲስ ሰራን የምትሉት፡፡ ክቡር ሚኒስትር ግልፅ ነኝ?
- ግልፅ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ግን "ልግመኛ እረኛ ለምሳ የታሰረለትን ለእራት ያደርገዋል" ይባላል፡፡ ቀደም ብሎ  የተሰራላቸውን ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ ወደሚጠቀሙበት ብናዞረው ያስመግነናል እንጂ አያስወቀሰንም፡፡
- አንተ የፕላኒንግ ኃላፊ ሆነህ ይህ ነገር ሲሆን ለክቡር ሚኒስትሩ ከፕላኑ ውጭ ነው አትላቸውም ነበር፡፡ ባለሙያ አይደለህም?
- ብያቸው ነበር፡፡
- እናስ?
- አልሰማ አሉኛ"
- እኔ እንደሚኒስትር እዚህ ከተሾምኩ ጀምሮ አንተ አንድ ሃሳብ አቅርበህ እኔ አይሆንም ያልኩህ ቀን አለ?
- ይኸው አሁን ያልኩት ቀን
- እየተደማመጥን፡፡ እኔ እንደ ሰብሳቢ በማነሳው አጀንዳ ላይ እንወያይ፡፡ አልቋል ያላችሁትም አላለቀም፡፡
- ምን ቀረው?
- ክቡር ሚኒስትር፣ ዋናው የመሥሪያ ቦታኮ ገና አልተጀመረም፡፡ በመቀስ የሚቆረጥበት ቦታ ብቻ ነው ያለቀው፡፡
- ስራውን እየሰሩ ጎን ለጎን ግንባታውንም ማካሄድ ይቻላል ብለን ነው፡፡
- ታዲያ አልቋል ብላችሁ ለምን ሪፖርት ታደርጋላችሁ?
- የእኔ ረዳት በስህተት ነው አልቋል የሚል ቃል የተጠቀመው፡፡
- (የሚኒስትሩ ረዳት) እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ እኔ ምዕራፍ አንድ ተጠናቋል ስል እርስዎ ምዕራፍ አንድ ምዕራፍ ሁለት እያልክ አታንዛዛ፣ ምዕራፍ የሚለውን ዝርዝር ትተህ አልቋል የሚለውን ብቻ ተጠቀም አላሉኝም?
- ይቅርታ፣ አሁንም እንደ ሰብሳቢ መድረኩን ልምራውና አሁን ማን ምን አለ ብለን የምናጣራበት መድረክ አይደለም፡፡ እሱ ለብቻችሁ ተነጋገሩበት፡፡ ጨርሰናል አመሰግናለሁ፡፡

(ግምገማው አለቀ፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ክቡር ሚኒስትሩ ፀሐፊያቸውን ጠሩና ቆጣ ብለው ንግግር ጀመሩ)

- ደብዳቤውን ምን አረግሽው?
- ሶስቱም ደብዳቤዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
- አምጪልኝ፡፡

(አምጥታ ክቡር ሚኒስትሩ ፈረሙ)

- አሁኑኑ ጠርተሽ ስጪያቸው፡፡ የፋይናንስ ኃላፊ ተብዬ፣ የፕላኒግ ኃላፊ ተብዬ፣ የሚኒስትሩ ረዳት ነኝ ባዩም አይናቸውን እንዳላይ፡፡ ቶሎ ጠርተሽ ስጪያቸውና ከዚህ ግቢ እንዲወጡ ሁለተኛ እዚህ ግቢ እንዳይገቡ፡፡
- እሺ" ክቡር ሚኒስትር
- አሁን አሁን ደውለሽ ጠርተሸ ስጪያቸው፡፡ በቃ እኔ ቢሮ እንዳታስገቢያቸው፡፡
- እሺ፡፡

(ፀሐፊዋ ወጥታ፤ ደወለች፡፡ ደጋግማ ደወለች፡፡ ተመልሳ ክቡር ሚኒስትር ቢሮ ገባች)

- ሰጠሻቸው?
- ጠራኋቸው ኑና ውሰዱ አልኳቸው፡፡
- እህ"
- አንመጣም አንወስድም አሉ፡፡
- አ"ን"ወ"ስ"ድ"ም?
- አዎን አንመጣም አንወስድም አሉ፡፡
- አለቃቸው መሆኔን ረሱ፡፡ የአለቃ የሚኒስትር ትዕዛዝ ነው ኑና ውሰዱ አትያቸውም?
- አልኳቸው ሳቁብኝ፡፡
- ምን ብለው?
- አለቃችንም ሚኒስትራችንም አይደሉም፡፡ ከአሁን በኋላ አይደሉም አሉ፡፡
- ጠገቡ፡፡ አመፀኛ ሆኑ አትይኝም?
- እንደውም ክቡር ሚኒስትር ለእኛ ደብዳቤ ከመፃፍ ለራሳቸው የመጣውን ደብዳቤ ቢያነቡት ይሻላል አሉ፡፡
- ለእኔ የመጣ ደብዳቤ አለ እንዴ?
- አዎ"  
 
< Prev   Next >