| ክቡር ሚኒስትር |
|
|
| Wednesday, 16 January 2008 | |
|
የስራ ሰዓት ደርሷል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ግን ከቤት አልወጡም፡፡ ሾፌራቸው ግራ ገባውና ገብቶ ጠየቃቸው - አሞዎታል እንዴ ክቡር ሚኒስትር? ዶክተሩን ይዤው ልምጣ? - አይ አላመመኝም፡፡ ቢሮዬን ዛሬ ማደስ ስለሚጀምሩ ቤት ሁኜ ልስራ ብዬ ነው፡፡ - ከሦስት ቀን በኋላ ውጭ ይሄዱ የለ፡፡ ያኔ ለምን አያድሱትም? - የለም የለም፡፡ እኔ ራሴ እያየሁ እየተቆጣጠርኩ ካልታደሰ ያበላሹታል፡፡ ያልሆነ ቀለም ይቀባሉ፣ ያልሆነ ሶፋና መጋረጃ ይገዛሉ፡፡ እኔ እያለሁ ነው የሚሻለው፡፡ ለምንስ አሁን አይተናቸው አንመጣም፡፡ መጣሁ አንዴ ልልበስ ጠብቀኝ፡፡ ለባበሱና ሄዱ - ስማ፡፡ - አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ቀለሙን ወድጄዋለሁ፡፡ ይህ ሶፋ ግን እኔ ቢሮ ይገባል ብለህ አታስብ፡፡ - እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ይህኮ ምርጥ የውጭ አገር ሶፋ ነው፡፡ ሰባ ሺ ብር እኮ ነው የገዛነው፡፡ - ችግሩ ሰባ፣ ሰማንያ መሆኑ አይደለም፡፡ ድብር ያለ ቀለም እንደማልወድ ለፀሐፊዋ ነግሬያት ነበር፡፡ - እንደዛ ዓይነት ገዝተንኮ ፀሐፊዋ የሚያብለጨልጭ ነገር ያስጠላል፤ ብላ እንድንመልሰው አድርጋን ነው፡፡ - የሚታደሰው የእሷ ቢሮ ነው የእኔ? - ይቅርታ፣ ክቡር ሚኒስትር፡፡ መመለስ ይቻላል፡፡ - እኮ በአስቸኳይ ይመለስ፡፡ ፀሐፊዋን ጠርተዋት ገባች - ስሚ እኔንስ ናቂኝ ግድ የለም፡፡ ነገር ግን የሚኒስትር ቢሮ ስለሆነ ለቢሮው ክብር ብለሽ ደህና ሶፋ ብትመርጪ ምን አለበት? - እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ ይኸ ምርጥ ሶፋ ነው፡፡ - በይ መልሽ፡፡ - አይመልሱልንማ ውሉ ላይ አይመለስም ይላል፡፡ - ካልመለሱ ሌላ ይገዛ.. - ጠቅላላ አገልግሎቶቹ አይፈቅዱማ፡፡ - ደግሞ የመሥሪያ ቤቱ የበላይ ሃላፊ ጠቅላላ አገልግሎቶች ሆኑ? - ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ እሺ ሌላ ይገዛል፡፡ እዛው ስለሆነ የገዛነው ሻተሩን እስቲ ይዩት፡፡ - ይህም አይመለስም በሉኛ፡፡ - ምነው፤ አልወደዱትም ክቡር ሚኒስትር? - ሻተር አልወድም፡፡ የጨርቅ መጋረጃ ሆኖ በልኩ የተሰፋ ይሁን፡፡ - እንደውም የእርሶ አማካሪ ሻተር ይሻላል ብሎኝ ነው እንጂ፣ እኔ ቡናማ መጋረጃ ቆንጆ መርጬ ነበር፡፡ - ደባሪ ቀለም አልወድም፡፡ ፈካ ያለ ብሩህ ቀለም አትመርጡም? - ነጭ ይሁን፡፡ - ነጭ ወይም ብጫ ቆንጆ ነው፡፡ - በቃ ሻተሩንም እንደሶፋው እንመልሰዋለን ጠቅላላ አገልግሎቶቹ ግን እምቢ ስለሚሉ ትዕዛዝ ይስጡልኝ፡፡ - እምቢ ሲሉ ያለውን ንገሪኝ፡፡ ለአገር ክብር ተብሎ እንጂ ለእኔ ግል ክብር ተብሎ አይደለም የሚገዛው፡፡ - እነሱማ አምና ታድሶና ዕቃ ተገዝቶ ለምን ዘንድሮ እንደገና ይገዛል ብለው ተናደዋል፡፡ - አምና ደሞዝ ተጨምሮልሃል ዘንድሮ አይጨመርልህም፤ ቢባል ግን ይራገማል፡፡ - እሱማ አይቀርም፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ እነሱ የሚሉት ያለፉት ሚኒስትር በነበረው እቃና ሶፋ የተሻለ ሥራ ሰርተው የለም ወይ ነው፡፡ - የነበሩት ሚኒስትር ሰነፍ ናቸው አላልኩም፡፡ ቢሮው ደረጃውን የጠበቀ ይሁን ነው ያልኩት፡፡ እንግዶች ሲመጡ ምን ያህል እንደሚታዘቡ ማወቅ አለባችሁ፡፡ - እንግዶቹማ የድሮው ሚኒስትር ቢሮ በጣም ይወዱት ነበር፡፡ - ለምን ነበር የሚወዱት? - ቀለል ያለ አንጃ ግራንጃ የሌለበት ቢሮ ነው ይላሉ፡፡ እውነትም ጫካ የነበሩ ናቸው ይሉ ነበር እንግዶቹ፡፡ - ጫካ የነበሩ ሲሉ ዘመናዊ ያልሆኑ ማለታቸው እኮ ነው፡፡ - አይደለም፤ ክቡር ሚኒስትር...፡፡ ስለ ግል ክብርና ዝና ደንታ የሌላቸው ሲምፕል ማለታቸው ነው፡፡ - ፈረንጅ ሲምፕል ካለ ንቆሻል ማለት ነው፡፡ ቋንቋቸውን በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ - እሺ ክቡር ሚኒስትር፣ ሶፋውንም ሻተሩንም አሁን እንመልሰዋለን፡፡ ከመለሱ መለሱት፡፡ ካልመለሱ አዲስ ይገዛል፡፡ - በአስቸኳይ በዚህ ሁለት ቀን ጨርሱና ከዛ ኮምፒዩተርና ፕሪንተር ይገባል፡፡ እሱም እኔ እያለሁና እየተቆጣጠርኩት መሆን አለበት፡፡ ዞር ስል ነገር ይበላሻል፡፡ - እንዴ ለሶፋና ለዕቃ እንኳ አንታመንም እንዴ ክቡር ሚኒስትር? - ይኸው አምኘሽ ነበር፤ ግን ያልሆነ ሶፋና ሻተር ገዛሽ፡፡ - ሰራተኛውኮ ፕሮጀክቶች እየተበላሹ ናቸው፤ ሚኒስትሩ ሶፋና ቀለም ይቆጣጠራሉ እያለ ይሳለቃል፡፡ - ምን የተበላሸ ፕሮጀክት አለ? ሁሉም ውጤታማ ነው፡፡ - ከሁለት ዓመት በፊት መጠናቀቅ የነበረባቸው ፕሮጀክቶች እስካሁን አልተጀመሩም፤ እያሉ ያወራሉ፡፡ - ፕሮጀክቶቹ ከተጀመሩ በኋላ ከሚቆሙ መጀመሪያ አቅም እንገንባ ብለን ነዋ.. - ሰራተኛውኮ ስለአቅም ግንባታ እየቀለደ ነው፡፡ - ምን ብሎ ነው የሚቀልደው ደግሞ? - ሶፋውና ሻተሩ ሲራገፍ አይተው እውነትም አቅም ግንባታ ብለው አሾፉ፡፡ - ኮምፒዩተሮች ሲገቡ ነገሩ ቀልድ እንዳልሆነ ይገባቸዋል፡፡ - ኮምፒዩተሮቹኮ እርስዎ ቢሮ ነው የሚገቡት እንጂ ሰራተኛው አይደርስባቸው፡፡ - ታዲያ ቢሮዬን ቴሌ ሴንተር ልታደርጊው ፈለግሽ እንዴ? - ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ እንደዛ ማለቴ አልነበረም፡፡ - ማለትሽ ነው እንጂ፡፡ እንደውም ከዛሬ ጀምሮ እዛው የምታምኛቸው ጠቅላላ አገልግቶቹ ጋር ተመድበሻል፡፡ ሌላ ቀልጣፋ ፀሀፊ አመጣለሁ፡፡ ከሶስት ቀን በኋላ አዲስ ሶፋና መጋረጃ ገብቶ ተጠናቀቀ፡፡ ፀሐፊ ተቀይራለች፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እያሉ ኮምፒዩተር የሚገጣጥሙት መጡ - እንኳን ደህና መጣችሁ እናንተ የኮምፒዩተር ኤክስፐርቶች ናችሁ? - የምን ኤክስፐርቶች? እኛ ኮምፒዩተር ለመገጣጠም ነው የመጣነው፡፡ - እኮ የኮምፒዩተር ባለሙያዎቹ ናችሁ ወይ ማለቴ ነው፡፡ እሺ ግድየለም ገጣጥሙት ብቻ፡፡ - በአንድ ሰዓት ውስጥ እንጨርሳለን፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ ከዛ እናሳየዎታለን፡፡ - ጎሽ፡፡ ይህ ታሪካዊ ቀን ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እዚህ ሚኒስትሩ ቢሮ ኮምፒዩተር የገባበት ቀን ተብሎ ይታወሳል፡፡ - ያለፉት ሚኒስትር ኮምፒዩተር እንደሚያስፈልጋቸው ብንነግራቸው መጀመሪያ ለብዙ ስራ የምትጠቀምበት ፀሐፊዋ ስለሆነች እዛ አስገቡና የኔ ይቆይ አሉን፡፡ - አዎን የኮምፒዩተር ጥቅም ሰው አሁን አሁን ነው የገባው፡፡ - እሳቸውምኮ ቅድሚያ ለፀሀፊዋ ይግባ አሉ እንጅ ትንሽ ላፕ ቶፕ ነበረቻቸው፡፡ ይዘዋት ይመጣሉ ይዘዋት ይሄዳሉ፡፡ - እ.እ የመሥሪያ ቤት ንብረትማ ወደቤት መሄድ የለበትም፡፡ - ሲመጡ እኮ ይዘዋት ይመጡ ነበር፡፡ - እኮ የመሥሪያ ቤት ንብረት አይሄድም አይመጣም፡፡ - አንድ ሚልዮን ብር የሚያወጣ መኪና ቤት እየሄደ እየመጣ አምስት ሺ ብር የሚያወጣ ላፕቶፕ ቤት ቢሄድና ቢመጣ ምን አለበት ክቡር ሚኒስትር? - አሰራራችን ግልፅና ንፁህ መሆን አለበት ማለቴ ነው፡፡ መኪና ቤት ባይሄድም ባይመጣ መኪናም ባልተባለ ነበር፡፡ - ላፕቶፕ ካልሄደና ካልመጣም ዴሴክ ቶፕ ይባል ነበር፡፡ - ለነገሩ ወደ ቤት እንኳ አልወሰደውም፡፡ ነገር ግን ከአዲስ አበባ ስወጣ ይዤው የምወጣ ላፕቶፕ እኮ ያስፈልገኛል፡፡ - ለጠቅላላ አገልግሎቶቹ ይዘዝዋቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡ ፀሐፊያቸውን ጠሩ አዲስዋ ፀሐፊ ገባች - ይኸውልሽ ለጠቅላላ አገልግሎቶቹ ከዚህ ኮምፒዩተር በተጨማሪ አንድ ላፕቶፕ እንዲገዛ ንገሪያቸው፡፡ - ወይ ክቡር ሚኒስትር እዛ ቦሌ መንገድ ሚሊንየም ቴክ የሚባል የኮምፒውተር ሱቅ አለ ከዛ ነው መገዛት ያለበት፡፡ - ስሊም እና ኩል የሆኑ ላፕቶፖች እዛ አሉ፡፡ አሪፍ አሪፍ አይፓድ ደግሞ አላቸው፡፡ እሱማ ይገዛ ክቡር ሚኒስትር በጣም ኢንጆይ ያደርጉታል፡፡ - በቃ እሱም እንዲገዛ አዘዋል በይ፡ - ግሬት ክቡር ሚኒስትር፡፡ በጣም ሞደርን ነዎት፡፡ ኮምፒዩተር ተገጣጥሞ አልቋል፡፡ ባለሙያዎቹ ስለአጠቃቀሙ ክቡር ሚኒስትሩን እያሳዩ ናቸው - እንግዲህ ክቡር ሚኒስትር አስፈላጊ ፕሮግራም ሁሉ ተጭኗል፡፡ መጀመሪያ ሲከፍቱት ይህ ነው የሚመጣው ፐርሰናል ፋይል ይላል፡፡ - ምንድነው ፐርሰናል ፋይል ደግሞ? - እርሶ የሚሰሩበት ፋይል ማለት ነው፡፡ ፐርሰናል ሲል ባለኮምፒዩተሩ ፋይል የሚሰራበት ፋይል ማለት ነው፡፡ ያው ፐርሰናል ማለት የግል ማለት አይደለም? - ታዲያ እኔ የአገር ጉዳይ እንጂ ምን የግል ጉዳይ አለኝ፡፡ የአገር ፋይል እንጂ የግል ፐርሰናል ፋይል የት አለኝ፡፡ - ጉዳዩ የአገር ጉዳይ ሆኖ እርሶ የሚከፍቱት የሚዘጉት ማለት ነው፡፡ - እሺ፡፡ - አስፈላጊ ከሆነ የፈለጉትን በዚህ ፕሪንተር ፕሪንት ማድረግ ይችላሉ፡፡ በርግጥ ነጭና ጥቁር ብቻ ነው የሚያትመው፡፡ - ለምን ከለር አያትምም? - ከለር ምን ያስፈልግዎታል? - አሁን ይህ ሁሉ ብላክ ኤንድ ዋይት ብቻ የሚያትም ነው ያመጣችሁት? - አዎን፡፡ - የአንድ ነገር ቀለም ነገር ማየት ስለፈለግሽ? - ክቡር ሚኒስትር ስክሪን ላይ ከነቀለሙ ያዩታል ፕሪንት ሲደረግ ግን ነጭና ጥቁር ይሆናል፡፡ - ሳየው ግን በቀለም ነው? - ስክሪን ላይማ በቀለም ነው፡፡ - እንደዛ ከሆነ እሽ፡፡ - በቃ ጨርሰናል፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - አመሰግናለሁ ቻው፡፡ አዲስ ቀለም፣ አዲስ ሶፋ፣ አዲስ ወንበርና ጠረጴዛ፣ አዲስ መጋረጃ፣ አዲስ ኮምፒዩተር አዲስ ቴሌቪዥንና ቴፕ፣ አዲስ ምንጣፍ ገብቶ ተጠናቋል፡፡ ጠቅላላ እቅድ ተሳካ፡፡ አዲስ ፀሐፊ ገባች - ክቡር ሚኒስትር እነዚህ የፋይናንስ ሰዎች ደባሪዎች ናቸው፡፡ - ምነው? - አንዴ ገብተን የምናስፈርማቸው አለ፤ ይላሉ፡፡ - ግቡ በያቸው፡፡ ገቡና ለፊርማ የተዘጋጀ ሰነዱ ለክቡር ሚኒስትር ሰጡ - ምንድነው ይህ ስድስት መቶ ሺ ብር የሚለው? - ክቡር ሚኒስትር ለምንጣፍ፣ ቴሌቪዥን፣ መጋረጃ፣ ሳተላይት ዲሽ፣ ወንበር ጠረጴዛ፣ ሶፋ፣ መጋረጃ ጠቅላላ የወጣ ወጪ ነው፡፡ - እና? - እናማ በእርስዎ ትዕዛዝ የወጣ ወጪ መሆኑን እንዲፈርሙልን ነው ያመጣነው፡፡ - የግድ እኔ መፈረም አለብኝ? - አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ ከፕሮጀክቶች ባጀት የተወሰደ ገንዘብ ስለሆነ በኋላ ማን ነው የፈቀደ ቢባል ለእኛ ጣጣ ነው፡፡ - ከፕሮጀክቱ ነው የተወሰደው? - አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ በፁሑፍ ያዘዙን እንደዛ ብለው ነው፡፡ - ለምን ከፕሮጀክቱ ተወሰደ? - ከሌላማ ከየት እናምጣ? - ለወንበር፣ ለጠሬጴዛ የሚል ባጀት የለም እንዴ? - አለ፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡ - ስንት? - አስራ ሶስት ሺ፡፡ - አሁን የተገዛውስ? - ስድስት መቶ ሺ.... |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |