Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow በአሁኑ የምርት ወቅት ብዙ የዋጋ...
በአሁኑ የምርት ወቅት ብዙ የዋጋ... Print E-mail
Wednesday, 16 January 2008

በአሁኑ የምርት ወቅት ብዙ የዋጋ መቀነስ ላይኖር ይችላል
ዶ/ር በዛብህ ኢማና
በግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር

ዶ/ር በዛብህ ኢማና የግብርና ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአለማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸው ከጀርመን አገር አግኝተዋል፡፡ በአለማያ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በኃላፊነት ለብዙ አመታት የሰሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በገጠር ልማት ..ኤስ.ኣይ.ዲ ኮንሰልት.. የሚል ድርጅት አቋቁመው የምርምርና የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡  የግብርና ምርታማነትና የምርትን በሚመለከት አነጋግረናቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዘንድሮ ምርት እንደሚጨምር ተገምቷል በዋጋ ላይ የሚኖረው ለውጥ ምን ይመስላል?

ዶ/ር በዛብህ፡- የዘንድሮ ምርት ጥሩ እንደሆነ የሚያሳይ ግምት አለ፡፡ ይህ ዋጋን በተወሰነ መልኩ መቀነስ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ምን ያህል ይሞላል የሚለው ሲታይ የፍላጎት ግፊት ስለቀጠለ ብዙም የዋጋ መቀነስ ላይኖር ይችላል፡፡

ባለፉት ጊዜያትም ምርት ጨመረ ብንልም በምግብ እህል ራሳቸውን የቻሉ አካባቢዎች ጥቂት ናቸው፡፡ የውጪ ምግብ የመጠበቅ ፍላጎት አለ፡፡ የግብርና ምርት ሲጨምር የምርት ዋጋ ይቀንሳል፡፡ ይህ አሁን የሚታይ አይሆንም፡፡ ዋጋውን ለማስተካከል ምርት በሚጨምርበት ሁኔታ ላይ ድጎማ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ዋጋው በሚቀንስበት ሂደት ተቀባይነት ያለው ጣልቃ ገብነት ከመንግሥት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዋጋ መጨመሩ የተከሰተው ገበሬው ምርት ስላጠራቀመ እንደሆነ ይነገራል፤ እውነት ነው?

ዶ/ር በዛብህ፡- ይህንን አላምንበትም፡፡ ገበሬው ምርት ሊያከማች የሚችለው ለሳምንታትና ወይም ለወር ነው፡፡ ከዚያ በላይ ገንዘቡን ይፈልገዋል፤ ወደ ገበያ ያወጣል፡፡ ለረዥም ጊዜ ማስቀመጥን የኢኮኖሚ መርሆዎቹ አይጋብዙም፡፡ ባለፉት ወራት አቅም ኖሮት ቢያስቀምጥ እንኳ የዚህ ዓመት ምርት ከመምጣቱ በፊት ሊሸጠው ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ አልታየም፡፡

ሪፖርተር፡- በምግብ እህል ራስን የመቻል ሂደቱ ምን ይመስላል?

ዶ/ር በዛብህ፡- ለውጥ አለ፡፡ ምርታማነት ጨምሯል፡፡ ነገር ግን በጣም ምርታማ በሚባሉ አካባቢዎች፡፡ የአቅርቦት ክፍተት አለ፡፡ በምግብ እህል ራሳቸውን የሚችሉትን ለማወቅ በተመረጡ ሦስት አካባቢዎች ያለውን ሂደት ማየት እንችላለን፡፡ በጣም ጥሩ ምርት አለባቸው ከሚባሉት አካባቢዎች ከባሌ ጎሮ፣ ጥሩ ምርት ካለበት ከቦረና አሬሮ እና አነስተኛ ምርት ካለባቸው በሰሜን ወሎ ደሃና፣ በምግብ እህል ምን ያህል ራሳቸውን ችለዋል የሚለውን ብናይ፡፡ 1998 ዓ.ም በጎሮ ለ12 ወራት በምግብ እህል ራሳቸውን የሚችሉት 60 በመቶ፣ በአሬሮ 16 በመቶ በደሃና 9 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ፡፡ ይህን ቁጥር 1999 ስናየው በጎሮ 72 በመቶ፣ በአሬሮ 7 በመቶ፣ በደሃና 6 በመቶ ነው የቀረው ለመሙላት ገበያ ያስፈልጋል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ምርት ከውጪ ይፈለጋል፡፡ የገበያ ምርት የሚያመርቱ ገበሬዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን የገበያ ክፍተት አለ፡፡
ዛሬ ያመረቱትን ለአንዳንድ ወጪዎች ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ በዘር ወቅት ከገበያ የሚሰበስቡት ሁኔታ አለ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ገበሬዎች የገበያ እህሎችን እንዲያመርቱ እየተበረታቱ ነው ይህ በምግብ እህል ላይ ጫና አይፈጥርም?

ዶ/ር በዛብህ፡- በገጠር የገበያ ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ አበረታች ውጤት አለው፡፡ ጠንካራ ገበሬዎች ብዙ እንዲያመርቱ የሚፈቅድ ከሆነ አንፃራዊ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ምርት ያመርታሉ፡፡ የገቢ አቅማቸውን ያሳድጋል፡፡ በዚህ ግን እንደ አየር ንብረቱ አዋጪ የሆኑትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ይህንን እንደ አቅጣጫ መያዙም መልካም ነው፡፡ ሆኖም ይህን አምርቱ ጥሩ ገበያ አለ ማለት ይከብዳል፡፡ በአገራችን ያለው ችግር አንድ ነገር ሲጀመር ሁሉም ቦታ ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ የመሬት አይነት፣ የአየር ንብረት የተፈጥሮ ሃብት መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡

ለስንዴ አንፃራዊ ጠቀሜታ ባለበት አካባቢ በጥቂት ስብጥር በተቻለ መጠን ምርቱን መጨመር ያስፈልጋል፡፡ ስንዴ በጣም ገበያ ላይ ሲኖር አቅርቦት ይሻሻላል፡፡ ትኩረት አድርገው ለሚያመርቱት ደግሞ ጥሩ ገበያ ይፈጥራል፡፡ ቦታ በሚፈቅደው ላይ እናምርት ስንል ግን ስብጥርን መቀነስ የለብንም፡፡ በሽታ፣ የዝናብ ልዩነት ይኖራል፡፡ ገበሬው ኢንሹራንስ ስለሌለው ስብጥሩ ኢንሹራንሱ ነው፡፡ ግብርና  የአባወራዎች ፓኬጅ ሶስት የተለያዩ ምርቶችን እንዲያመርት አንዱን ምርት የአካባቢው አንፃራዊ ተጠቃሚነት ታይቶ በዋናነት ምርቶችን እንዲያመርቱ አንዱን በዋናነትና አንፃራዊ ተጠቃሚነት እንዲሆን ይጠይቃል፡፡ ይህ በትክክል ተግባራዊ እየሆነ አይደለም፡፡ የመሬት ምርታማነት ለመጨመር ማፈራረቅ አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምርታማነትን ለማሳደግ ምን ያስፈልጋል?

ዶ/ር በዛብህ፡- በአገራችን ትልቁ የምርት ግብአት ርጥበት ነው ግብርናችን ዝናብን መሰረት ያደረገ ስለሆነ ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ በውሃ ልማት ላይ ትልቅ ኢንቨስትመንት  ያስፈልጋል፡፡ ለመስኖ ኢንቨስት ማድረግ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን ውጤታማ ያደርገዋል፡፡ የግብርናና ቴክኖሎጂ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ የሚጠቀሙትን ድርሻ ስናይ በጣም ዝቅተኛ ነው፤ መሻሻል አለበት፡፡ ውጤታማ የሆኑት ገበሬዎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የተረዱ ናቸው፡፡ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የመሬት አስተዳደር መሻሻል አለበት፡፡ መስኖ ሲባል ውሃ ብቻ አይደለም፤ አጠቃቀሙን በጥልቀት ማየት አለብን፡፡ 

የምርት አስተዳደራችንም ሆነ በመሬት አያያዝ በአለም በአነስተኛ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ የምናርሰው በድሮ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ መሻሻል የለም፡፡ አሁን ትኩረቱ የሞተውን ማገገም ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬም የሚበላሽ መሬት አለ፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እንዳይጠቀሙ የሚያግዳቸው ምንድነው?

ዶ/ር በዛብህ፡- በዘር አቅርቦት ብንወስድ ግብርናና ምርምር ቴክኖሎጂ ያወጣል፡፡ ከዚያ በኋላ አይታይም፡፡ የአቅም ጉዳይ ቢኖርም በምርምር የተገኘውን ለማስፋፋት ችግር አለ፡፡ የማዳበሪያ ድጎማ ስለቀረ ዋጋው ከባድ ነው፡፡ ማዳበሪያን በድጎማ መልክ መስጠት በነፃ እርዳታ ከመስጠት ይበልጣል፡፡ በማዳበሪያ የዋጋ ችግር አለ፡፡ አብዛኛው ሕብረተሰብ ደሃ ነው፡፡ አዲስ ቴክኖሎጂን ተጠቅሜ አመርታለሁ ብሎ አደጋው መጋፈጥ ይከብዳቸዋል፡፡
በአጠቃቀሙ ዙሪያ ያለን እውቀት ውሱን ነው፡፡ 50 ኪ.ግ ማዳበሪያ ገዝቶ ለብዙ መሬት ማዳረስ ይፈልጋል፡፡ ለውጦች አሉ ነገር ግን ብዙ መሰራት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማህበራት ማዳበሪያን በማቅረብ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

ዶ/ር በዛብህ፡- ማህበራት ገበሬውን ወክለው ተወዳዳሪ ሆነው መስራት አለባቸው፡፡ ራሳቸው ገበሬ ስለሆኑ ለገበሬው በተሻለ መልኩ ያቀርባሉ፡፡ ብዙዎቹ አገልግሎት ሰጪና ንግድ ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰሩ ናቸው፡፡ መኖራቸው ነጋዴው ዋጋን እንደፈለገው እንዲያደርግ ያደርጋሉ፡፡ በቦንጋ አንድ የቡና ማህበር ዋጋ መድቧል ነጋዴዎች በላይ ጠየቀ፡፡ ይህ ማህበሩ የፈጠረው ሂደት ነው ነጋዴ በራሱ ገበያውን እንዳይቆጣጠር/ሞኖፖሊ እንዳያደርግ ያደርጋል፡፡ ሆኖም አቅማቸው አናሳ በመሆኑ ተጠናክረው ገበያ ውስጥ እንዲገቡ እገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ድጎማ እንዳይሰሩ ያደርጋል ይባላል፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምን ይመስላል?

ዶ/ር በዛብህ፡- ሳይለፋበት የሚገባበት ስለሆነ አይበረታታም፡፡ ነገር ግን ድጎማውን በተለያየ መልክ እንዲሄድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የብድር የአከፋፈል ሂደቱን ማስተካከል፣ በገጠር ያሉት አነስተኛ የብድር ተቋማት የሚያስከፍሉት ገበያ ላይ ካለው በበለጠ ወለድን ከአቅም ጋር ዝቅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ማዳበሪያ እንዳይጠቀሙ የካፒታል እጥረት አለ፤ ይህን ማቃለል ያስፈልጋል፡፡ እንደ እርዳታ ከመስጠት የገበያ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል፡፡

ማዳበሪያ ወስዶ ሌላ ነገር ሸጦ ከመለሰ ተመራጭ አይደለም፡፡ በማዳበሪያ ተጠቅሞ ውጤት ማምጣት አለበት፡፡ ማዳበሪያ ዝም ብሎ ለገበያ መልቀቅ አይበረታታም፡፡ መንግሥት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ድጎማ እየሰጠ ነው፡፡ ለገበሬው መስጠቱ ምርታማነትን ይጨምራል፡፡ በግብዓት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሚገኘው በብድር ነው፡፡ እንደገባ አምጡ ሲባል በአነስተኛ ዋጋ ያመጣሉ፡፡ ሌሎች መንግሥት ሊሰራቸው የሚገባቸው ስራዎች አሉ፡፡ ዘመናዊ ማሽኖችን ሆነ ግብዓቶችን ለመጠቀም ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የገበያ፣ የግብዓት፣ የእውቀት የካፒታል ያለባቸውን ችግር ማወቅ መረዳት ድጎማ ነው፡፡ ይህ እንዲሰሩ ያበረታቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የገጠር መሰረተ ልማት ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?

ዶ/ር በዛብህ፡- የገጠር መንገድ አሁን ያለው ሂደት ሁሉም ቦታ ሳይሆን ደህና ነው፡፡ ገበያ በቅርበት የሌለበት ቦታ አለ፡፡ ነጋዴ አይመጣም፡፡ ጥሩ ፍራፍሬ ምርት ባለበት አካባቢ ገበያ፣ መንገድ ከሌለ ሲያመጡ ምርቱ ተበላሽቶ ይደርሳል፡፡ የከብት ገበያም በርቀት ከሆነ አቅም ያለው ብቻ በተሻለ ዋጋ ይሸጣል፡፡ በተለይ በክረምት ብዙ መንገዶች አገልግሎቶች አይሰጡም፡፡ መንግሥት ሊያጠናክረው ይገባል፡፡ የአካባቢ አስተዳደሮች ገበያው በሚጠናከርበት ሂደት ላይ መስራት አለባቸው፡፡ ገበያ ካለ ትራንስፖርት ቢሮ መኪና መመደብ ይኖርበታል፡፡ ብዙ ቦታ ላይ የምርት ደረጃን ያለማወቅ፣ በሚዛን የመታለል ሁኔታ አለ፡፡ ጥራትን የሚወስነው ነጋዴ ነው፡፡ የሕግ ከለላ ያስፈልጋል፡፡ ነጋዴዎች ደረጃ አውጥተው ከፋፍለው ገዝተው እዛው ይቀላቅሉታል፡፡ ደረጃውን ገበሬው ሊያወጣ አይችልም፡፡ የደረጃዎች መዳቢ ባለሥልጣን ነው፡፡ መንግሥት ዋጋን ባይወስንም ብዙ ነገር ማስተካከል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ግብርናና ለኢንዱስትሪው ካፒታል እንዲፈጥር ይጠበቃል እንዴት እየሄደ ነው?

ዶ/ር በዛብህ፡- አንዱ ሴክተር ሌላውን ይፈጥራል የሚለው ይከብዳል፡፡ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚልኩት የግብርና ምርት ነው፡፡ ተጠናክረው ኢንዱስትሪ ማቋቋማቸው ሂደት ሊሆን ይችላል፡፡ ከግብርና በሚመጣው አቅማቸውን አሳድገው ወደ ኢንዱስትሪ እንዲገቡ ያግዛል፡፡ ትስስርን በመፍጠር ለኢንዱስትሪ የሚኖረው ሂደት አዋጪ ነው፡፡ አገልግሎት፣ ኢንዱስትሪና ፋብሪካዎች ከግብርና ጋር የቀጥታና የኋልዮሽ ትስስር አላቸው፡፡ እንደ ግብዓት ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም ኢንዱስትሪን ይመራል የሚለው ይከብዳል፡፡ ካፒታል ይፈጥራል ለሚለው ግን አሁን እያደገ ለመጣው ኮንስትራክሽን ትልቁ ሚና የባንክ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በግብርና ላይ ያለው ትኩረት ምን ይመስላል?

ዶ/ር በዛብህ፡- ግብርናን ማሳደግ ግዴታችን ነው፡፡ ግብርና የማንደራደርበት ዘርፍ ነው፡፡ በበጀት ቀመር ስናይ፣ የግብርና ትምህርት ከጠቅላላ ትምህርት ያለው ድርሻ፣ ለምርምር የሚወጣውን ወጪ ስናይ ካለው ሕዝብ አንፃር የሚደረገው ድጋፍ ትንሽ ነው፡፡ በኤክስቴንሽን፣ ግብዓት፣ በሰው ኃይል ከሌሎች ሴክተሮች አንፃር ማየት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝብ ቁጥር በግብርና ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡ ወደ ሌላ ዘርፎች እንዲሸጋገሩ ምን ያስፈልጋል?

ዶ/ር በዛብህ፡- በገጠር ያሉ ግብርና ነክ ያልሆኑ ዘርፎችን ማጠናከር ከግብርና መውጣት አለባቸው፡፡ ለዚህም አቅም፣ እውቀትና እድል ማግኘት አለባቸው፡፡ ግብርና ላይ ያለው ጠንካራ ገበሬ ይኖራል፡፡ ወጣቱ ቦታ የለውም መውጣት አለበት፡፡ የገጠርና የከተማ ትስስርን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በቀላሉ ወደሌላ ምርት ሊቀየሩ በሚችሉ በሚደረጉ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ ማገዝ፣ ማድረግ የምርት ሂደቱን ማስተካከል የተሸላሚ አርሶ አደሮች ቁጥር መጨመር ያስፈልጋል፡፡

 
< Prev   Next >