Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 20th
Home arrow Sections arrow የባሕል ውዝዋዜ፡ እየተንፏቀቀ ያለ ጥበብ
የባሕል ውዝዋዜ፡ እየተንፏቀቀ ያለ ጥበብ Print E-mail
Wednesday, 16 January 2008

በየትኛውም አገር የሚኖር ዜጋ ባህልን የማንነቱ መገለጫ አድርጐ ይቆጥረዋል ሲሉ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ ከባህል መገለጫዎች አንዱ የሆነው ዘፈንና ውዝዋዜ ደግሞ ቀድሞ በሠዎች አዕምሮ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በአሁኑ ወቅት በስልጣኔ ጣራ ላይ የሚገኙ አገሮች ባህላዊ ሙዚቃዎቻቸውን በዩኒቨርሲቲዎቻቸው እያስተማሩ የሚገኙት፡፡ እንደነ ህንድ፣ ቻይና ጃፓንና ሜክሲኮ ያሉ አገሮችን በባህላዊ ሙዚቃዎቻቸውና በውዝዋዜያቸው ማንም ሊለያቸው ይችላል፡፡ ለምን ቢባል ዘፈናቸው በድርጊት በተሞላ ውዝዋዜ፣ በትርጉም በታጀበ አለባበስና በታሪክ በተዋቀረ ቀረፃ የተዋበ በመሆኑ ነው፡፡

ወደአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ ግን የተለያዩ አስተያየቶችን እንሰማለን፡፡ ገሚሱ ባህላዊ ውዝዋዜያችን ያደገው በቀረፃ ብዛት..ቁጥር) እንጅ በእውነተኛነትና በታሪክ አንፀባራቂነት አይደለም ይላል፡፡ የዚህ ጐራ ደጋፊዎች ውዝዋዜያችን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት እንኳን ስናነፃፅረው የእኛ መሠረቱን ለቋል እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በተሻለ እንቅስቃሴ ላይ እንዳለ ያምናሉ፤ ለዚህ እንደማስረጃ የሚያቀርቡት ደግሞ ብዙ ወጣት ዘፋኞች በክሊፖቻቸው ባህላዊ ውዝዋዜዎችን እየሰሩ ነው በማለት ነው፡፡ የተወሰነው ተመልካችና አንጋፋ ባለሞያዎች ግን ብዛት እንጅ ወጥነት የለውም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ይህንን ጉዳይ ይዘን የባህል ውዝዋዜያችን በምን ላይ ይገኛል? በማለት አንጋፋውን የባህል ውዝዋዜ አሰልጣኝ አርቲስት ታደለ ታምራትን አነጋግረነዋል፡፡ አርቲስት ታደለ ከ45 ዓመት በላይ ብሔራዊ ትያትርን ጨምሮ በሌሎች ቦታዎች የውዝዋዜ አሠልጣኝ ሆኖ ሠርቷል፡፡

ከአርቲስቱ ጋር የነበረንን ቆይታ የጀመርነው የመድረክ ውዝዋዜ አጀማመር ምን ይመስላል በሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ አርቲስቱ እንደሚለው በ1948 ዓ.ም አካባቢ ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሙዚቃና ቲያትር ማስፋፊያ ፅህፈት ቤት የተመለመሉ ከያንያን ወደ ብሔራዊ ትያትር ከተቀላቀሉ ጊዜ ጀምሮ ውዝዋዜ የተወሰነ ትኩረት አገኘ፡፡ ይሁን እንጅ የተመልካቹ ፍላጐትም ሆነ የተዋናዮች ፍላጐት ትያትር በመሆኑ ለትያትር ግብዓት ካልሆነ በቀር ውዝዋዜ አይሠራም ነበር፡፡

ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ የባህልና ዘመናዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ እንዲቋቋም ተደረገ፡፡ በ1953 ዓ.ም ደግሞ የባህል ቡድን ተቋቋመና ከብሔራዊ ትያትርና ከሐገር ፍቅር ትያትር ቤት የተውጣጡ ከያኒያን የባህል ሙዚቃና ውዝዋዜ ልምምድ ካደረጉ በኋላ ወደ ሱዳን አቀኑ፡፡ እንደ አርቲስት ታደለ ገለፃ የባህል ውዝዋዜና ዘፈን በመያዝ ከኢትዮጵያ ውጭ የሄደው ቀዳሚው የአርቲስቶች ቡድን ወደ ሱዳን የሄደው ነው፡፡ ባህልን ለማስተዋወቅ ይረዳ ዘንድም ወደ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ዩጋንዳና ሌሎችም ሀገራት ተዘዋውረው ዝግጅት አቅርበው ተመልሰዋል፡፡ ከአፍሪካ ውጭም ወደ ቻይና ከ40 የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ሄደዋል፡፡ ካናዳ፣ ሜክሲኮና ጀርመንም አፄ ኃይለስላሴ ጋር ተዘዋውረዋል፡፡

በ1966ቱ አበዮት አካባቢ ከውዝዋዜ ይልቅ ለመዝሙሮች የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ነበር፡፡ በ1968 ዓ.ም አካባቢ የባህል ተወዛዋዦችና ዘፋኞች አዝማሪ የሚለው አሉታዊ ስም እየተፋቀ መምጣት ለአርቲስቶች ሞራልና ጉልበት እየሆነ መጣ፡፡ እናም ከተለያዩ ቦታዎች ዘፋኞችንና አርቲስቶችን በማስመጣት የተለያዩ የብሔር ብሔረሰብ ዘፈኖችና ጭፈራዎች መስራት ጀመሩ፡፡

አርቲስት ታደለ እንደገለፀው የወቅቱ ባለሙያዎች እንደነ አውላቸው ደጀኔ ካሉ መሰል አርቲስቶች ጋር በመሆን የብሔረሰብ ዘፈኖችን በጥሩ ሁኔታ ለማቅረብ ቦታው ድረስ ሄደው አጥንተው ይመጡ ነበር፡፡ ከዚያ ባለፈም ከልምምድ በኋላ ሥራው ለሕዝብ እይታ ከመብቃቱ በፊት ስለብሔሩ የተሻለ እውቀት ያላቸውን ሰዎችና የአካባቢውን ተወላጆች በመጋበዝ ያስገመግማሉ፡፡ ከተሰጣቸው አስተያየት በመነሳት ማሻሻያዎችን ከወሰዱ በኋላ ለእይታ ያቀርባሉ፡፡ ይህም ቱባውን ባህል ያለምንም መዘበራረቅ ለማቅረብ ረድቷቸዋል፡፡

ከ1968 ዓ.ም በኋላ ውዝዋዜ ትልቅ ትኩረት ተሰጠው፡፡ በተለይ ከሜክሲኮ ሁለት ፈረንጆች መጥተው የአራት ወር ሥልጠና ከሰጡ በኋላ አሠራሩ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ተጀመረ፡፡ እንደ አርቲስቱ አባባል ከዚያ በፊት ለውዝዋዜ አሠልጣኝ ባለሙያው ያን ያክል ቦታ የሚሠጠው አልነበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ትኩረት እያገኘ የመጣው ውዝዋዜ በተለይ በደርግ ዘመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡

ለአብዮቱ ሲባል በየከፍተኛውና በየቀበሌው ተቋቁመው የነበሩ የኪነት ቡድኖች ህብረተሰቡን ከማዝናናት አልፈው ባህሉን ከማስተዋወቅ አንፃር ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡ ከደርግ መውደቅ በኋላ እንቅስቃሴው ቢኖርም ከእውነተኛው ባህል ግን የወጣ ነበር አርቲስቱ እንደሚለው፡፡

አርቲስቱ እንዳብራራው በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ውዝዋዜዎች ከአልባሳት አጠቃቀም አንፃር ሲታዩ ድክመት አለባቸው፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ የሚያቀርበው የኦሮሞ ባህልን ለመግለፅ ያን ጊዜ የተጠቀሙት ዘዴ ሌላ ነበር፡፡ የአርሲ ኦሮሞ ሴቶችን አለባበስ ለማሳየት ሽርጥና ካባ እንዲሁም ከውስጥ ያለ ጥብቆ ከአስመጡ በኋላ ያንን የሚመስል መርካቶ ገዝተው አሰፉ፣ ሹርባውንም በጥለት አክርረው ሠሩ፡፡ በእጅና በእግር የሚደረግ አምባርና በእጃቸው የሚይዙትን ከቅል የተሠራ ቀንድ ሁሉ አዘጋጅተው ይገለገሉ ነበር፡፡ ወንድ የብሔረሰቡን አባላት ለመግለፅም የሰላሌዎቹን አለባበስ መረጡ፡፡ እጀ ጠባብ ሱሪና የዝንጀሮ ጐፈር በጭንቅላታቸው ይደፋሉ፡፡ ሌሎቹን ጌጣጌጦችም አከማችተው ተጠቅመዋል፡፡ በአሁኖቹ ውዝዋዜዎች ግን የአንዱን አካባቢ ከአንዱ ጋር ማደበላለቅ ይስተዋላል ብሏል፡፡

በወላይትኛ ውዝዋዜም ችግሮች አሉ፡፡ ቀደም ሲሉ በነበሩ ውዝዋዜዎች የደስታ፣ የሠርግና የለቅሶ ጭፈራዎችን ለማሳየት ባህሉን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች እንዲያሰለጥኑና ራሳቸውም እንዲጫወቱ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የሠርጉም፣ የለቅሶውም የሚደበላለቅበት ጊዜ አለ፡፡

ከምንም በላይ የመደበላለቅ ሁኔታ የሚታይባቸው በጐንደር፣ በጐጃም፣ በወሎና በምንጃር ጭፈራዎች ነው፡፡ እነዚህ አካባቢያዊ መቀራረብ ስላላቸውና የውዝዋዜው ዓይነትም እንደ ወቅቱና ሁኔታው ስለሚለያይ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ተወዛዋዦች ከግምት አያስገቡትም፡፡ በጐንደር ውዝዋዜ ዝልያ ድስቅ የሚባል የሴቶቹ ጭፈራ አለ፣ የወንዶቹ ደግሞ መንጥቅ ይባላል፡፡ ሴቶቹ ዝልያ ድስቅ በሚጨፍሩበት ጊዜ በአንገታቸው የሚያጠልቁት ጌጥ ግንባራቸውን መትቶ ደረታቸው ላይ ያርፋል፡፡ አርቲስቱ እንደሚለው በአንገት ላይ የሚጠለቀው ትክክለኛ ጌጥ በአሁኑ ውዝዋዜዎች የለም፡፡ አንዳንዴ በሌሎቹ (ወይ በጐጃሙ ወይ በምንጃሩ) ያለ ቦታው ገብቶ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡

የትኛውም ባህል የየራሱ ጌጣጌጥ አለው ያለው አርቲስቱ በአሁኑ ጊዜ ያሳመሩ መስሏቸው አንዱን ከአንዱ የመቀየጥ አባዜ ይዟቸዋል ይላል፡፡ በአንገታቸው የጌጣጌጥ መዐት ሰብስበው ጭፈራ ሲከለክላቸው ይታያሉ፡፡ የሐረር ሴቶችን የአንገት ጌጥ ከጐጃም ጠልሰም ጋር እየደባለቁ አንገታቸው መሸከም ሲያቅተው የሚታዩበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ይህ ያሳዝናል ብሏል አርቲስቱ፡፡
በጭፈራ (ውዝዋዜ) ጊዜ ሴትና ወንድ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ አንዱ የጭንቅላት ውዝዋዜ ነው፡፡ የጭንቅላት ውዝዋዜ ሴቷ ወንዱን ወይም ወንዱ ሴቷን ለማሽኰርመም (ለመጥቀስ) ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን በቴስታ ሲማቱ እናያለን፡፡ የአንገት እንቅስቃሴያቸው ከባህል ውጭ ነው፡፡ ለምሳሌ በጐጃም አካባቢ አንገት የሚሰበርበት የሰጐን ጨዋታ የሚባል አለ፡፡ በዚህ ውዝዋዜ/ጭፈራ/ ጊዜ ሴቶች ቀና የሚሉት ወንድ ለማሽኮርመም ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን የሚታየው ጭፈራው ብቻ ነው፡፡ ወንዱ የሴቷን ሴቷም የወንዱን ሲጨፍሩ ማየት ጀምረናል፡፡

የጐጃሙ አታሞ ምትና የጐንደሩ ፈጣን ምት ያሁን ጊዜ ተዋዛዋዦች ትኩረት የሰጡት አይመስልም፡፡ በአታሞ ምት ጊዜ አጨፋፈሩ ዋና እንደምትዋኝ ወፍ ሲሆን የአሁኖቹ ተወዛዋዦች ግን እንዲሁ ይንፈራገጣሉ፡፡ በውዝዋዜ ጊዜ እግር፣ እጅና ፊት የሚሠሩት እንቅስቃሴዎች የተለያየ መልዕክትን ሊያስተላልፉ እንደሚገባ የጠቆመው አርቲስቱ የአሁን ዘመን ተወዛዋዦች መላ ሰውነታቸው በአንድ ዓይነት እንቅስቃሴ ላይ ይወዛወዛል ብሏል፡፡ 

ወጣቶቹ ባህሉን የማያውቁ በመሆኑ ለመፍረድ ይቻላል ወይ? ብለን ላነሳንለት ጥያቄ መች ይጠይቃሉ? ብሎ ነበር የመለሰልን፡፡ ብዙ ተወዛዋዦች ለማወቅ ከፈለጉ ታላላቆችን መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ቀደም ብሎ የተሠሩ ውዝዋዜዎችን ቢመለከቱ መልካም ነው ብሏል፡፡ ለዚህም በሕዝብ ለሕዝብ ጊዜ ተሠርተው የተቀመጡ ዶክመንተሪ ፊልሞችን እንደ አብነት ይጠቅሳል፡፡ እንደሱ እምነት በሕዝብ ለሕዝብ ጊዜ ተሠርተው የተቀመጡ ፊልሞች ታላቅ ማስተማሪያ መሆን ይችላሉ፡፡

አርቲስት ታደለ ለባህል ውዝዋዜ አለማደግ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሰፊው አለመንቀሳቀስ የበለጠ ተጠያቂ ነው ብሎ ያምናል፡፡ እሱ እንደሚለው በተለያዩ አገራት ተዘዋውሮ በነበረበት ጊዜ እንዳስተዋለው ባህል ሚኒስቴር በሰፊው በመንቀሳቀስ ወጣቶች ባህላቸውን እንዲያወቁ እያደረገ ይገኛል፡፡ የእኛ አገር ግን በዚህ ዙሪያ ብዙ አልሠራም፡፡

አርቲስቱ ሚዲያዎች በተለይም ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ያለምንም ገደብ ዘፈኖችን ማቅረብ ለውዝዋዜው መዳከም አስተዋፅኦ አድርገዋል ይላል፡፡ ከባህል ውዝዋዜና የሙዚቃ ስልት አንፃር ትክክለኛነታቸው ሳይመዘን /በተለይ ቴሌቪዥን/ ተቀብሎ ለአየር ማብቃት የለበትም፡፡

እንደመፍትሄ ካስቀመጣቸው ሃሳቦችም በዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደ ትምህርት ዘርፍ ቢታይ ጥሩ ነው፤ በሌሎቹ አገራት የሚስተዋለው ይህ የመጀመሪያው መፍትሄ ነው፡፡

የባህል ሙዚቃ ዘፋኞችም ሆኑ ተወዛዋዦች በአሁኑ ወቅት ያላቸው ፍላጐት የሚበረታታ መሆኑን የሚናገረው አርቲስቱ ከፍላጐታቸው ጐን ለጐንም ለሚሠሩት የባህል ውዝዋዜና ሙዚቃ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከታላላቅ አርቲስቶች ጠይቀው በመረዳትና ባህሉ ከሚገኝበት አካባቢ ድረስ በመሄድም ሆነ አልያም ቀደም ብሎ የተሠሩ ሥራዎችን አድኖ በመመልከት ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ ከምንም በላይ ግን የአንዱን ብሔር ውዝዋዜ ከአንዱ፣ የአንዱን ጌጥ ከሌላው ማቀላቀሉና ማደበላለቁ ይቅር በሚለው ላይ አስምሮበታል፡፡

በደመቀ ከበደ

 
< Prev   Next >