| ፍላጐትን ማስተናገድም ሆነ... |
|
|
| Wednesday, 23 July 2008 | |
![]() ግርማዊት ተረፈ ![]() ወጣት ተመስገን እንዳለው በምሕረት አስቻለው "ቀደም ሲል በነበረኝ አመለካከት ከተቃራኒ ፆታ ጋር በየትኛወም ጊዜ የፍቅር ግንኙነት መመስረት ችግር አለው ብዬ አላስብም ነበር፡፡ የፍቅር ግንኙነቱም ወሲብን መጨመር ይኖርበታል፣ ሴቶችም ለወንድ ጓደኞቻቸው ፍላጐት ተገዢ መሆን አለባቸው ብዬ አምን ነበር" ያለን በህይወት ኢትዮጵያ ያገኘነው የአሥራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት ነው፡፡ ወጣት ተመስገን ሲሳይ የአሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በህይወት ኢትዮጵያ የወንዶችና የሴቶች (Boys and Girls) ክለብ ተሳታፊ መሆን ከጀመረ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በክለቡ የሥርዓተ ፆታና የሥነ ተዋልዶ ስልጠናዎችን መውሰዱን እንዲሁም ስለኤች.አይ.ቪ መማሩን ገለፀልን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኮሚኒኬሽንና በድርድር ክህሎት ሥልጠና ወስዷል፡፡ ከላይ የገለፀው ደግሞ ወደ ክበቡ በመምጣት የተለያዩ ግንዛቤዎችን ከማግኘቱ በፊት የነበረውን አመለካከቱን ነው፡፡ አሁን ግን ማንኛውም ወጣት (ሴቶችም ወንዶችም) ቢሆኑ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ግንኙነት ከመመሰረታቸው በፊት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማዳበር እንደሚኖርባቸው ያምናል፡፡ በመልክ ወይም በሰውነት ቅርፅ ከመማረክ ባሻገር አመለካከትና ስብእና በሁለቱም ወገን ሊተኮርበት እንደሚገባ ይናገራል፡፡ ወጣት ተመስገን እንዳለው፣ ሌሎች ሊተኮርባቸው የሚገባ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው የቤተሰብ ተቀባይነትም (የልጆቻው ከተቃራኒ ፆታ ጋር ግንኙነት መመስረትን) አላስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም የማህበረሰብ የመጀመሪያ አካል የሆነው ቤተሰብ ያልተቀበለውን ህብረተሰቡ እንዴት ይቀበለዋል፡፡ ሙሉ በሙሉ ሕብረተሰቡ ከሚያምንበትና ከሚቀበለው ውጭ መሆን በተለይም ለታዳጊ ወይም ለወጣት ከባድ ይሆናል፡፡ የማይታሰብም ነው የሚሆነው፡፡ "በፊት የፍቅር ግንኙነት የማልመሰርተው ሴት ልጅን ቀርቦ ማነጋገር ስለሚያስፈራኝ፣ ከሴት ጋር መታየቱም ስለሚከብደኝ ነበር፡፡ አሁንም የሴት ጓደኛ የለኝም፡፡ ምክንያቴ ግን ሌላ ነው፡፡ ከትምህርቴ ውጭ የእኔ የምለው ነገር የለም፡፡ የራሴ የሆነ የገንዘብ ምንጭ የለኝም፡፡ በህይወቴ ቅድሚያ ልሰጣቸው ይገባኛል ለምላቸው ነገሮች ጊዜዬን መስጠት ስሜቴን ማስገዛት እንደለብኝ ይሰማኛል" በማለት ማንኛውም ወጣት የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ሲፈልግ ፍላጐቱን ለማስተናገድም ሆነ ለመግታት በቂ ምክንያት ሊኖረው እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ህብረተሰቡ ምንም እንኳ የሴት ወይም የወንድ እያለ ሥራዎችን የከፋፈለበት ሁኔታ ቢኖርም ማንኛውም ወንድ መሥራት የሚችለውን የቤት ውሰጥ ሥራ ሁሉ ሊሠራ እንደሚገባና እሱም የተወሰኑ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ገልፆልናል፡፡ በእርግጥ በአንድ ጊዜ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ወደ መሥራት መሄድ ከባድ መሆኑን አልደበቀም፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚያቀርበው ደግሞ ሕብረተሰቡ በባህልም ይሁን በሌሎች ተፅእኖዎች ለረዥም ዓመታት በጋራ ተስማምቶበት የኖረውን ነገር በቀላሉ መናድ ችግር መሆኑን ነው፡፡ የህይወት ኢትዮጵያ የወንዶችና የሴቶች ክለብ ለወጣቶች ከሚሰጣቸው የተለያዩ ስልጠናዎች በተጨማሪ ወላጆችና ወጣት ልጆቻቸው በጋራ የሚወያዩበት ተከታታይ ኘሮግራሞችን ያዘጋጃል፡፡ እኛም ከቤተሰቦቹ ጋር የሚያደርገው ውይይትን በማስመልከት ጠየቅነው፡፡ በክለቡ ውስጥ የተለያዩ ስልጠናዎች ካገኘና በበርካታ ውይይቶች ላይ ከተሳተፈ በኋላ በቤት ውስጥም ከእህተና ከወንድሞቹ እንዲሁም ከወላጆቹ ጋር ስለግንኙነት፣ ኤች.አይ.ቪና በአጠቃላይ ስለተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች በጋራ በግልፅ መወያየት መጀመራቸውን ነግሮናል፡፡ በእርግጥም ይህ በርሱ ጥረት ብቻ ሳይሆን የእሱ፣ የእህቶቹና የወንድሞቹ ለእድሜ ከፍ እያሉ መሄድና የተለያዩ ሚዲያዎች ተፅእኖ እንዳለበት ይናገራል፡፡ በሚዲያ የሚሰሙ የተለያዩ ጉዳዮች በተለይም ወጣቶችን ወይም ወላጆችን የማመልከቱና ስጋትን ወይም ፍራቻን የሚጭሩ ከሆኑ ተመስገንና ቤተሰቦቹ ይወያዩባቸዋል፡፡ "የእኔ ቤተሰቦች በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የፍቅር ግንኙነት ውስጥ እንድገባ አይፈልጉም፡፡ ይህን ዘወትር ይነግሩኛል፡፡ እኔም አምኜበታለሁ፡፡ ይህ ለእኔና ለቤተሰቦቼ የተዘጋ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ባለሁበት ሁኔታ የምወስናቸው ውሳኔዎች በነገው ህይወቴ ላይ ትልቅ ተፅእኖ እንደሚኖራቸው የህይወት መስመር አቅጣጫዬንም ሊቀይሩት እንደሚችሉ ተረድቻለሁ"ብሏል ወጣት ተመስገን፡፡ እዚያው አግኝተን ያነጋገርናት ታዳጊ ደግሞ ግርማዊት ተረፈ ትባላለች፡፡ የአሥራ ሰባት ዓመት ታዳጊ ስትሆን 10ቲ1 የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪ ነች፡፡ በህይወት ኢትዮጵያ የወንዶችና የሴቶች ክለብ አባል ከሆነች ሁለት ዓመት ሆኗታል፡፡ ሥርዓተ ፆታን በሚመለከት ያገኘችው ትምህርት ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ እንዳስገኘላት የምትናገረው ታዳጊ በማንኛወም ሁኔታ ውስጥ ግልፅነትና ውይይት አስፈላጊ መሆናቸውን አመልክታለች፡፡ ከወላጆች ጋር የሚደረግ ውይይት ቤተሰብ ስለልጆቹ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ከማስቻሉ ባሻገር ለልጆች አቅጣጫ እንደሚያስይዝ በመጠቆም ከእናቷ ይልቅ ከአባቷ ጋር በግልፅ በወጣትነት ሊገጥሙ ስለሚችሉ ነገሮች እንደሚወያዩ ገልፃልናለች፡፡ ቢሆንም እናቷም የራሳቸውን የህይወት ተሞክሮ ያካፍሏታል፡፡ ይህ የወጣቶች ኘሮግራም (የወንዶችና የሴቶች ክለብ) በሴቭ ዘችልድረን ሲውዲንና ኢፍሶ (IFSO) በተባሉ ድርጅት እንደተጀመረና፤ ሦስት ዓመት እንደሆነው እስካሁንም በጉለሌና በአራዳ ክፍለ ከተማ በሚገኙ ወጣቶች ላይ እንደሚያተኩር በህይወት ኢትዮጵያ የኘሮግራሙ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አበራ ገ/ሚካኤል ገልፀውልናል፡ በክለቡ ተሳታፊ ለመሆን ከ10 እስከ 24 የእድሜ ክልል ውስጥ መገኘት፣ በማንኛውም የበጐ ተግባር እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ፍቃደኛ መሆን እንደሚያስፈልግ ከንግግራቸው ለመረዳት ችለናል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |