Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Sep 07th
Home arrow Sections arrow በፍልውሃ ድርጅት አልተደሰትኩም
በፍልውሃ ድርጅት አልተደሰትኩም Print E-mail
Sunday, 27 July 2008
ሰሞኑን ወደ ፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት ጎራ በማለት በ2ኛ ማዕረግ አገልግሎት አግኝቻለሁ፡፡ ወደ ድርጅቱ ከሄድኩ በርካታ ወራትን ያሳለፍኩ በመሆኑ ስሄድ ወረፋው በጣም በዝቶ አገኘሁት፡፡ መታጠቢያ ክፍሎቹ ፅዳት የጎደላቸው፣ ለዓይን የሚቀፉ ሆነው ሳገኛቸው አዘንኩ፡፡

የምታጠብበት ክፍል በር ለመዝጋት መታገል ነበረብኝ፡፡ የመስኮቶቹ መስተዋት በመሰባበሩ ከውጪ ወደ ውስጥ እንዳይታይ ፎጣ ተጋርዷል፡፡ የግድግዳዎቹ ቀለም ለቀው ወይበዋል፡፡ የግድግዳ ሸክላዎቹ በመሰባበራቸው እዚያም እዚህም እንደ ቡትቶ ተለጣጥፈዋል፡፡ የውሀ ቧንቧዎቹ፣ የሻወሩን ጨምሮ በእርጅና የወላለቁ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ባለቤት የለውም ወይ ያሰኛል፡፡ የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት ማኔጅመንት ያለቅጥ እየጨመረ የመጣውን ተጠቃሚ በምን መልኩ ማስተናገድ እንዳለበት፣ በእርጅና ምክንያት ከጥቅም ውጪ የሆነውን ንብረቱን ለማደስ ትኩረት ይስጥ፡፡

(አበበ ጣሴ፣ ከአዲስ አበባ)

የስቃይ ሰለባዎች ጩኸት

ስለ የስቃይ ሰለባዎች መልሶ ማቋቋሚያ ማዕከልና ስለ ስቃይ ሰለባዎች በሪፖርተር ጋዜጣ የወጣውን ጽሑፍ አንብቤያለሁ፡፡

ኢንጅነር ታደለ ብጡል፣ በበላይነት የሚመሩት ማዕከል፣ በየመንደሩ ተበታትነው፣ የበይ ተመልካች ሆነው የሰብሳቢ ያለህ እያሉ የሚጮሁትን የጀግኖች ወላጆችና የስቃይ ሰለባዎችን እስከ ዛሬ ተረድተዋልና ዘለዓለም አይረዱም ማለታቸው ተገቢ አይደለም፡፡

የስቃይ ሰለባዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በእነሱ ስም የሚመጣ እርዳታም አያገኙም፡፡ ሰለባዎቹ አሁንም ጩኸታቸው አልተቋረጠምና አዳምጧቸው፡፡

 (ሐሰን ሁሴን፣ ከአዲስ አበባ)  

በኅልውናችን ላይ የመጣ ውሣኔ አንቀበልም

አስተያየት ለመስጠት ያነሳሳኝ፣ ..የኢትዮጵያ ድንበርና የሉዓላዊነት ጥያቄ.. በሚል ርዕስ በዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ተፅፎ በሪፖርተር ጋዜጣ ሐምሌ 13 ቀን 2000 ዓ.ም በፖለቲካ ገጽ የወጣውን ነው፡፡

"የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ኢሕአዴግ ወደደም ጠላም ኤርትራ በሌላ ሁኔታ እስካልተስማማች ድረስ ለኤርትራ የተፈረዱትን አካባቢዎች ከማስረከብ ሌላ አማራጭ የለውም"፡፡ አያይዘውም "የኮሚሽኑን ውሳኔ የማስፈፀም ኃላፊነት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ስለሆነ ይህንን እርምጃ ሊወስድ ይችላል" ብለዋል፡፡
እኔ እስከማውቀው አንድም አገር በሴክዩሪቲ ካውንስል ማዕቀብ ተደርጐበት መሬት ያስረከበ የለም፡፡ ዶ/ር ያዕቆብ አለ ካሉ እንዲጠቁሙን እጠብቃለሁ፡፡

ዶ/ር ያዕቆብ ፅሑፋቸውን ተአማኒ ለማድረግ በምሣሌነት ያቀረቡት የካሜሩንና የናይጄሪያን የወሰን ውዝግብ ነው፡፡ "ናይጄሪያና ካሜሩን በነበራቸው የወሰን ውዝግብ ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ለካሜሩን የፈረደውን የድንበር ከተሞችና በቤንዚንና በአሳ ሃብት የበለፀገችው ባካሲ ፔኒንሱላ ናይጄሪያ የዓለማቀፉን ግፊት መቋቋም ስላልቻለች ለካሜሩን ማስረከብ ግድ ሆነባት" ብለዋል፡፡

ናይጄሪያ ለካሜሩን እንዳስረከበች ተደርጐ የተገለፀው ጥናትና በቂ ማስረጃ ሳይደረግበት ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ባካሲ ከናይጄሪያ ለካሜሩን እንዲሰጥ መፈረዱ እውነት ነው፡፡ ናይጄሪያ ሃሳቡን በመርህ ደረጃ ብትቀበልም ቦታው ላይ የናይጄሪያ ዜጐች ሰፍረውበት ስለሚገኙ ውሳኔው ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ የናይጄሪያው ምክር ቤት ስለተቃወመውም ጉዳዩ በአጀንዳነት ተይዞ ውይይት ለማድረግ አቅደዋል፡፡

ባካሲ በነዳጅና በአሳ ምርቷ የምትታወቀውን ያህል ባድሜ በእብነ በረድ ይዞታዋ የታወቀች ናት፡፡ መንግሥት ፍርዱን ለመተግበር ያዳገተው ጥያቄው የንብረት (እብነበረድ) ሳይሆን በአካባቢው የሚኖሩ ወገኖች ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡

ሌላው የሚያስከፋው ጉዳይ ደግሞ "የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሣኔ የዓለማቀፍ ሕግ አካል እንደመሆኑ መጠን በዓለማቀፍ ሕግ ላይ ሸፍቶ ለዘላለም መኖር አይቻልም" የሚለው ነው፡፡

የዶ/ር ያዕቆብ አስተያየት የድንበሩና የአሰብ ጉዳይ አብቅቶለታል የምታደርጉትን ትግል አቁሙ፡፡ ይህ ካልሆነ በሴክዩሪቲ ካውንስል የኢኮኖሚ ማዕቀብ ተቀጥተን ቦታውን እናስረክባለን የሚል ነው፡፡

መሬት ስጡ ብሎ የሚያስገድደን ሃይል የለም፡፡ በኤርትራና በኢትየጵያ ስምምነት የድንበሩንም ሆነ የአሰብ ጉዳይ እንደገና ልንደራደርበት እንደምንችል ማወቅ ይገባል፡፡ ይህንን ከቻይናና ከመሳሰሉ አገራት ተሞክሮም የምናውቀው ነው፡፡

የድንበር ኮሚሽኑ ውሣኔ ተግባራዊ የሚሆነው በኅልውናችን ላይ ስለሆነ ለመቀበል እንቸገራለን፡፡

(ኃይለሚካኤል ገ/አናኒያ፣ ከአዲስ አባ)

ማዕከሉ ይስተካከል


ሐምሌ 7 ቀን 2000 ዓ.ም በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ በደርግ ጊዜ ስቃይ የደረሰባቸውንና የማዕከሉ አመራሮች የሰጡትን አስተያየት አንብቤያለሁ፡፡

በቦርዱ አመራር የተሰጠው መልስ አሳዝኖኛል፡፡ በደርግ ስቃይ ሰለባ ስም እርዳታ ሰበሰብን እንጂ ለእነሱ ብቻ አይደለም የሚለው ትክክል አይደለም፡፡ ኢንጅነር ታደለ ብጡል የሰጡት መልስ ከእሳቸው አይጠበቅም፡፡ ተረጂዎች ከ5 ዓመት በላይ ምንም እርዳታ አላገኘንም እያሉ በሰኔ ወር 2000 ፎቶአቸውን በኤግዚቢሽን አሳይተናል ማለት ወጪ ላወጡበት ማስረጃ የሚሆነው ፎቶ ግራፍ ሳይሆን ደረሰኝ መሆን ነበረበት፡፡ ይህ የግለሰብን መብት መጋፋት ነው፡፡

ሌላው በወፍጮ ግዢ ላይ ኢንጅነሩ 60 ሺህ ብር እርዳታ ተገኝቶ ነው ብለዋል፡፡ ለእህል መግዣ፣ ለሥልጠና፣ ለቤት ኪራይ፣ ለመብራት የወጣውን ወጪ ስደምረው ወፍጮው በስንት ተገዛ የሚል ጥያቄን ፈጠሮብኛል፡፡

ከምንም በላይ እየተጐዱ ያሉትን ወላጆች እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ማዕከሉ እድገት ሊያሳይ የሚችለው መልካም አመራር ሲኖረው ነውና ይህም መስተካከል ይኖርበታል፡፡

(ዘውዱ አበጋዝ፣ ከአዲስ አበባ)

አፍሪካዊያን እራሳችንን ብንመረምርስ?

ባለፈው ዘ አይሪሽ ኢንዲፐንደንት ጋዜጣ ያወጣውን ዕትም አስመልክቶ ያስነበባችሁትን ፅሑፍ ከተመለከትኩ በኋላ ይህንን ልፅፍላችሁ አሰብኩ፡፡ በመሠረቱ ጋዜጣው በዘረኝነት ላይ የተመረኰዘ ዘገባ ማውጣቱን የገለፃችሁ ሲሆን እኔ ግን ከፀሐፊው ጋር በመጠኑ የምስማማበት ነጥብ አለኝ፡፡

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅና በረሃብ እየተጠቃች መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በተፈጥሮ ከሚደርስብን የአየር መዛባትም ሆነ የዝናብ እጥረት ባሻገር እንደኔ በዋናነት እጅግ ኋላ ቀር የሆነው የሥራ ባህላችን ለድህነትና ለምግብ ችግር አጋልጦናል ባይ ነኝ፡፡ በብዛት እየተጐዳን የምንገኘው በስንፍናችን ነውና በዚህ ሐሳብ ከፀሐፊው ጋር እስማማለሁ፡፡

ሌላው ምንም እንኳ እንደ ጋዜጣው መረን የወጣ ነገር ለመናገር ባልፈልግም በአገራችን እየታየ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሰብዓዊ ፍጡር መሆናችንን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ አስባለሁ፡፡ ከዓመት በታች የሆነ ለጋ እና እምቦቅቅላ ህፃን ላይ የሚፈፀመው የአስገድዶ መድፈር ምን ይባላል? በየትኛው ትክክለኛ የሰው አእምሮ እንዲህ ያለው አሳዛኝ ድርጊት ሊፈፀም ይችላል? ፀሐፊው በነዚህ ጉዳዮች የተነሳ የአፍሪካ በተለይም የአገራችን ሰዎች ኃላፊነት እንደማይሰማን ቢገልፅ ምን ይገርማል?

የጋዜጣው ፀሐፊ በዋናነት የሳተው ነጥብ ቢኖር ሰዎች ሁሉ በተፈጥሮ አንድ መሆናቸውን በዛሬ ማንነታቸው የነገ ስብዕናቸውንም ያው እንደዛሬው ነው ብሎ መናገር ከተፈጥሮ ህግ ውጪ መሆንና ምሬትን እንደ ወረደ የመግለፅ አዝማሚያ በመሆኑ ፣ኃላፊነት የጐደለው፣ የሚለው አገላለፅ ይስማማዋል ባይ ነኝ፡፡

ገ/አምላክ ህሩይ ከ ጎላ ሠፈር
 
< Prev   Next >