| ያላለቁላቸው የቆዳ ምርቶች የሚልኩ... |
|
|
| Wednesday, 16 January 2008 | |
|
ያላለቁላቸው የቆዳ ምርቶች የሚልኩ ላይ ታክስ ሊጨመር ነው በኢትዮጵያ በቆዳ ሌጦ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ያለቀላቸውን ምርቶች እንዲልኩ ለማስቻል የተረቀቀው አዲስ ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ተገለፀ፡፡ ሕጉ ያላለቀላቸውን የቆዳና የሌጦ ምርቶች ላለቀላቸው ምርቶች በመተካት የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንዲያስቸል ታስቦ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ መንግሥት የአገር ውስጥ የቆዳና የሌጦ አምራሮች ያለቀላቸውን የቆዳና የቆዳ ውጤት የሆኑ ምርቶችን በብዛት ለመላክ እንዲችሉ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ሕግ እንደሆነ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ያነጋገርናቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሙያ እንደገለፁት በቆዳና በቀዳ ውጤቶች አምራች በሆኑ ኩባንያዎች ላይ ተግባራዊ የሚሆነው ይህ በዋናነት ያላለቀላቸው የቆዳና የሌጦ ምርቶችን ወደ ውጪ የሚልኩት ላይ የታክስ ክፍያን የሚያሳድግ እንደሆነ ታውቋል፡፡ እስካሁን ባለው አሰራር ያላለቀለት የቆዳ ምርቶችን የሚልኩት ፋብሪካዎች የሚጣልባቸው ቀረጥ አነስተኛ እንደነበር ያመለከተው መረጃ አሁን ግን ከዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያለቀላቸውን ምርቶች መላክ ተገቢ በመሆኑ መንግሥት ይህንን እርምጃ ሊወስድ መገደዱን ያመላክታል፡፡ መንግሥት ይህንን ሕግ ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት በከፊል ያለቀለትና ያላለቀለት የቆዳ ምርት ወደ ውጭ ለሚልኩ ኩባንያዎች ያለቀለት ምርት ወደውጭ እንዲልኩ ለማስቻል አቅማቸውን እንዲገነቡ ጊዜ ሰጥቷቸው እንደነበር ታውቋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ ያላለቀላቸው የቆዳ ምርቶች በሚልኩ ኩባንያዎች ላይ የሚጣለውን ታክስ ከፍ የሚያደርገው ረቂቅ ሕግ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲላክ የተደረገ መሆኑንና ረቂቁም ያዘጋጀው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ ማለት ግን ያላለቁላቸው የቆዳ ምርቶች ለውጭ ገበያ አይቀርቡም ማለት እንዳልሆነ እኚሁ ባለሙያ ገልፀዋል፡፡ የሕጉ ዋነኛ አላማ ያላለቀላቸውን የቆዳ ምርቶች ወደ ውጭ የሚልኩ ኩባንያዎች እንዳይበረታቱ ለማድረግና ትኩረታቸውን ወዳለቀለት የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲያደርጉ ለማድረግ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |