| "ፒር ሪቪው" |
|
|
| Sunday, 27 July 2008 | |
ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች! የአፍሪካ መንግሥታት በገዛ ፈቃዳቸውና በጋራ በተለያዩ መመዘኛዎች በየወቅቱ እንዲገመገም (PEER REVIEW) እንዲደረግ ተሰማምተው ተፈራርመዋል፡፡ ስራው ከተጀመረም ቆይቷል፡፡ በግልፅ በመመዘኛዎቹ ወይም በመገምገሚያ ነጥቦቹ ላይ መጨመር ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በአየገሪቱ ያለው የፕሬስ ነፃነት በሚመለከት፡፡ ሆኖም ጅምሩ ራሱ አበረታች ነው፡፡ በሂደት ግምገማው እያደገና እየተጠናከረ ሄዶ ውጤቱም ይበልጥ አመርቂ እንደሚሆን ተስፋ አለን፡፡ ይህ የየአገሩ ፒር ሪቪው በአገራችን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ብንጠቀምበትም ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡ ጠንክረውና ተጠንቅቀው እንዲሰሩና በመካከላቸው የውድድር መንፈስ ሰፍኖ ጥረታቸውም ብቃታቸው እንዲያድግ ይረዳል፡፡ ዋናው ኦዲተር፣ በበጀት አንፃር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት ያደርጋል፡፡ በባጀት አጠቃቀም ላይ ያለውን ጠንካራና ደካማ ጎን ይለያል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም ግን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መታየትና መገምገም ያለባቸው በባጀት አጠቃቀም ዙሪያ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ መሥሪያ ቤቶች የተቋቋሙበት አላማና የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚመለከት ሁሉ መገምገም አለባቸው፡፡ አሰራራቸውና አስተዋፅኦቸው መፈተሽ አለበት፡፡ በሕብረተሰቡ ተሳትፎም ሊኖር ይገባል፡፡ መሥሪያ ቤቶች የሚገመገሙበት ነጥብ፣ ብዙና ዝርዝር መሆን ያለበት ቢሆንም በአጠቃላይ ሲታይ የሚከተለውን ማካተት አለበት፡፡ - የሚሰሩት ሥራና የተፈቀደላቸው ባጀት ይመጣጠናል ወይ? በሚገባ ተጠቅመውበታል ወይ? - የተሰጣቸውን ዓላማና ኃላፊነት በሚገባ አሳክተዋል ወይ? ያስቀመጡትና የጸደቀላቸው እቅድ በሚገባ ተፈፅሟል ወይ? - አሰራራቸው ከሙስና የፀዳ ነው ወይ? ጨረታ፣ የዕቃ ግዢ፣ የሰው ሃይል ምደባና ዕድገት አሰጣጥ፣ ከሥራ ማዛወር ወይም ማስወገድ ሕግና ደንብ የተከተለ ነው ወይ? - ሕዝብን በሚገባ በፍጥነት፣ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያገለግላሉ ወይ? - ራሳቸውን ይገመግማሉ ወይ? በመሥሪያ ቤቱ ደረጃ፣ በመጥሪያ ደረጃ ወዘተ. ራሳቸውን ይፈትሻሉ ወይ? - ለመንግሥት፣ ለፖለቲካ የሚያቀርቡት ሪፖርት እውተኛ ነው ወይ? - የሰራተኛው ተሳትፎ ምን ይመስላል? - ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል የሚያመጣ መሥሪያ ቤት ነው ወይ? - ግልፅነት፣ የመረጃ አቅርቦት፣ ዶክመንቴሽን ምን ይመስላል? - በአገሪቱ አጠቃላይ ሂደት የመሥሪያ ቤቱ ድርሻ ምን ይመስላል? - የድርጅቱ አሰራር ምን ይመስላል? ቅሬታ መስማት የችግር አፈታት ወዘተ. እነዚህና እነዚህን በመሳሰሉት ነጥቦች መሥሪያ ቤቶች ሊፈተሹና ሊገመገሙ ይገባል፡፡ መፈተሽና መገምገም ብቻ ሳይሆንም እርስ በርስ ተወዳድረውም ደረጃ ሊወጣላቸው ይገባል፡፡ የቀደመው ሲመሰገን ኋላ የቀረው ሊወቀስ እንደሚገባ በግልፅ በደረጃ አመዳደብ መታየት ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ለፓርላማ የፈለጉትን ተናግረው ጠያቂ አጥተው የሚሄዱበት ሁኔታ መቆም አለበት፡፡ ለፓርላማ ሪፖርት ማቅረብ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ሆኖም ግን ብቸኛ አሰራር መሆን የለበትም፡፡ ይህ ስራ መንግሥት በሚያቋቁመው ቋሚ አካል ወይም በየጊዜው እየተገናኘ የሚሰራ የተውጣጣ የባለሙያዎች ሰራተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ቁም ነገሩ ግን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እየተከታተሉ እንደ ቀልድ እንደማይታዩ እንደማይታለፉ ግልፅ ማድረግ ነው፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች አሰራሩን እያሻሻሉና በተሻለ ሁኔታና ፍጥነት እያገለገሉ ሲጓዙ ሌላው ተኝቶና ወደኋላ እየተጓተተ ሲኖር ሁለቱም እኩል የሚታዩበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡ ደረጃ ወጥቶላቸው ለሕዝብ ይፋ መሆን አለበት፡፡ ይህ አሰራር በክልሎች እርስ በርስ ውድድርና በክልሎች ውስጥ የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ መደረግ ያለበት ነው፡፡ "ፒር ሪቪው" የትም ይሰራል፡፡ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችም በግል ዘርፎችም እንደዚሁ ሊደረግ ይገባል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ያተኮርንበት ምክንያት ሕዝብ የማገልገል ሕጋዊ ኃላፊነት ተሰጥቶአቸው የሕዝብ ገንዘብ ተመድቦላቸው የሚሰሩ ስለሆነ በዚህ አንጻር መፈተሽ ችላ ሊባል ስለማይገባው ነው፡፡ ስለ መልካም አስተዳድር ብዙ ተብሏል፡፡ ታቅዷል፤ ቃል ተገብቷል፡፡ እነዚህ መልካም መስተዳድር ያመጣል የተባሉት ሳያመጡ ሲቀሩስ? በአንፃሩ የመስተዳድሩ ብሉሽነት ያስፋፉ እንደሆነስ? የንቅዘትና የሙስና ማዕከል ሆነው ከሆነስ? ይህ "ፒር ሪቪው" አካሄድ በህዝብ ፊት የሰራና ያልሰራ፣ የጠራና የደፈረሰ፣ ታታሪና አልምጥ፣ መሥሪያ ቤት ለይቶ የሚያሳይ ስለሆነ ሁሉም ሕዝብ ምን ይለኛል? ወደሚል መንፈስ ሊያስገባ የሚችል ነው፡፡ የአፍሪካ አገሮች "ፒር ሪቪው" አገሮች በፈቃደኝት እኔን ገምግሙኝ፤ እያሉ የሚያወጡት ነው፡፡ ግዴታ የሚገባባቸው አይደሉም፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ሕጋዊ አሰራር አድርጎ መውሰድ የሚቻል ሆኖም አጀማመሩ ፈቃደኛ በሆኑ መሥሪያ ቤቶች ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ ደካማ ጎንና ጠንካራ ጎን የሚለይ ግምገማ ማካሄድ ነው፡፡ "ፒር ሪቪው" ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች! |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |