| በአለም አቀፍ የቆዳ ንግድ ትርዒት... |
|
| Wednesday, 16 January 2008 | |
|
በአለም አቀፍ የቆዳ ንግድ ትርዒት 58 የውጭ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የቆዳ ገበያ ማዕከል ለማድረግ ታቅዷል በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው አለም አቀፍ የቆዳ ንግድ ትርዒት ላይ ከ58 በላይ የሚሆኑ የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ተገለፀ፡፡ ኢትዮጵያን የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ገበያ ማዕከል ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ከጥር 15 እስከ 17 ቀን 2000 ዓ.ም በሚሌኒየም አዳራሽ የሚካሄደውን ይህንን የንግድ ትርዒት የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ አብዲሳ መሃመድ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ትርዒቱ እስከ ዛሬ በቆዳ ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ በተዘጋጁ የንግድ ትርዒቶች ሁሉ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡ እስካሁን ባለው መረጃም ከአውሮፓ፣ ከእስያ፣ ከላቲን አሜሪካና ከሰሜን አሜሪካ እንደሚመጡ ካረጋገጡት 58 በቆዳ ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ ከሚሰሩ ኩባንያዎች ሌላ ከ85 በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች በትርዒቱ እንደሚሳተፉ አቶ አብዲሳ ገልፀዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይከፈታል ተብሎ በሚጠበቀው በዚሁ የንግድ ትርዒት ላይ ተሳታፊ ከሚሆኑ ኩባንያዎች ባሻገር ከ500 በላይ የሚሆኑ ጎብኚዎች ከውጭ አገራት እንደሚመጡ ከአቶ አብዲሳ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የዚህ የንግድ ትርዒት ዋነኛ አላማ የኢትዮጵያ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች የሆኑ ምርቶች በተገቢው መንገድ ለማስተዋወቅና አገሪቱ ባላት ሰፊ ሃብት የአፍሪካ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ገበያ ማዕከል መሆን እንደምትችል ለማሳየት ጭምር እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ እቅድ ጎን ለጎን በቆዳና ሌጦ ምርቾች የሚታወቁ የአፍሪካ አገሮች ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ እና በኢትዮጵያ ማዕከልነት ምርቶቻቸውን እንዲሸጡ ለማስቻል ጥረቶች የሚደረጉ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በንግድ ትርዒቱ ላይ የአገር ውስጥ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በጥምረት ሊሰሩበት የሚያስችላቸውን እድል የሚያገኙ መሆኑን የገለፁት አቶ አብዲሳ ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ማሽነሪዎችን የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት እንደሆነም አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን የንግድ ትርዒት ከዚህ በኋላም በየዓመቱ የምታዘጋጅ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ይህም አገሪቱን የቆዳና የቆዳ ወጤቶች የገበያ ማዕከል ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያካሂድ አመልክተዋል፡፡ ከንግድ ትርዒቱ ጎን ለጎንም የኢንቨስትመንት ፎረም እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ገዥ ኩባንያዎች ከሻጮች ጋር ምክክር የሚያደርጉ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማህበሩ እስከ ፕሮግራሙ መክፋ ድረስ የሚጠብቃቸው የተሳታፊ ኩባንያዎች ቁጥር 200 ነው፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |