Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow 314 መወድስ
314 መወድስ Print E-mail
Wednesday, 16 January 2008
አኮ ቀሊል ለዘይጸውሮ
እብነ አድማስ ረኃብ እንተ ይሰብር ክሣደ፣
ወከመ ኢቀሊል ለጾር አጠየቀነ ገሃደ
ኤልያስ ሐመልማለ ከርሡ በረኃብ ዘነደ፤
አድባረ ብካይ አመ ፆደ
እስመ በዐይኑ ነጸረ እንተ ብእሲት እደ፡፡

ረኃብሂ ሐፂነ ከርሥ እመ ኢኮነ ክቡደ
ለፈርፆን ጸላኢሁ በከተማ በትሩ እምኢሰገደ፣
ወእምሀገሩ ከነዓን እምኢተሰደ
ያዕቆብ በሀገሩ ብዙኃ ዘለመደ፡፡

/በመምህር አካለወልድ/

ትርጉም

አንገትን የሚሰብር የአድማስ
ድንጋይ /ራብ ለሚሸከመው ቀላል አይደለም፣
ሆዱ/ ቅጠል በራብ /እሳት የነደደ ኤልያስም
ለሸክም ቀላል እንዳይደለ በግልፅ አስረዳን፤
የልቅሶ ተራራዎችን በዞረ ጊዜ
የሴትን እጅ በአይኑ አይቷልና፡፡
ራብ/ የሆድ ብረትም ከባድ ባይሆን ኖሮ
ለጠላቱ ፈርኦን በበትሩ ጫፍ ባልሰገደ ነበርና፤
በአገሩ ብዙን የለመደ ያእቆብም
ከአገሩ ከነአን ባልተሰደደ ነበርና፡፡

ምስጢር

የድንጋይ ሸክም አንገትን እንደሚጫነው (እንደሚከብደው) ሁሉ ራብ አንገትን ያስደፋል፡፡ ቅጠልም በእሳት እንደሚቃጠል የኤልያስም ሆድ በራብ ተሞረሞረ፡፡ ተራራዎችንም እንደመዞር ኤልያስ ተርቦ ልቅሶን አበዛ፤ በአይኑም የሴትዮቱን ስጦታ ከጀለ፡፡ ድንጋይንም ከክብደቱ የተነሳ ብርቱ ሰው እንኳ ሊሸከመው እንደማይችል ያእቆብ ክራብ ፅናት የተነሳ ወደግብፅ ተሰደደ፤ ለፈርኦንም ተገዛ ማለት በቅኔው ተመስጥሯል፡፡

/በመምህር አካለወልድ/


የበርሊን አይሁዶች

በ1933 አካባቢ 160..000 ገደማ አይሁዶች በርሊን ውስጥ ይኖሩ ነበር፡፡ አይሁዶች 1/3ኛውን የጀርመን አይሁዶችን ወይም አራት በመቶ ያህሉን የበርሊን ነዋሪ ድርሻ ይይዙ ነበር፡፡ ከነኚህ መሀል ሦስት እጆቹ በምሥራቅ አውሮፓ ስደተኞችም ናቸው፡፡ በነኚህ አይሁዳውያን ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ የተጀመረውም ከናዚዎች አገዛዝ ጋር አብሮ ነበር፡፡ መጋቢት ወር 1933 ሁሉም አይሁዳውያን ሀኪሞች የቻርቲ ሆስፒታልን እንዲለቁ ተደረገ፡፡ በሚያዚያ ወር የመጀመሪያው ሣምንት ላይም የናዚ አመራሮች የጀርመን ሕዝቦች ከአይሁዳውያን መደብሮች እቃዎችን እንዳይገዙ ትዕዛዝ አስተላልፉ፡፡
ምንም እንኳን በርሊን የ1963ቱን ኦሎምፒክ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ከ1933 በፊት ቢሆንም ናዚዎች የውጭ ሀገር ጎብኚዎቸቸውን ላለማጣት በሚል ለአይሁዶች የተከለከሉ የሚሉ ምልክቶችን ለጊዜው አንስተዋቸው ነበር፡፡

ናዚዎች ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ቁጥራቸው 160..000 የነበሩትን የጀርመን አይሁዶች ከምድረ በርሊን አጥፍተዋቸዋል፡፡ በ1938 ከተካሄደው የክሪስታለቻት ጅምላ ጭፍጨፋ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዶች ለእስር ተዳረጉ፡፡ ቢሆንም ግን 1939 አካባቢ 7500 ገደማ የሚጠጉ አይሁዶች በበርሊን ከተማ ይኖሩ ነበር፡፡ ይሁንና በበርሊን የነበሩት አብዛኞቹ የጀርመን አይሁዶች ወደ ግሩበዋልድ ባቡር ጣቢያ በ1943 ተወስደው ከዘያም በመኪናዎች እየተጫኑ አብዛኛቹ በጅምላ ወደተጨፈጨፉበት እንደ ኦሽዊትዝ ወዳሉት የሞት ጣቢያዎች ነበር የተጓጓዙት፤ ነዋሪዎችዋ እንደ ቅጠል የረገፉባት በርሊን 1200 አይሁዶችን ብቻ ነበር በጉያዋ ደብቃ ከናዚዎች የሞት በትር መታደግ የቻለችው፡፡

/ከተሞቻችን፣ ጥቅምት 2000 ዓ.ም/

ቴሌና ፖስታ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፖስታ አገልግሎት በአፄ ምኒልክ በ1887 ዓ.ም ሲጀመር አፄ ምኒልክ የዚህን ሥራ ኃላፊነት የሰጡት ለልዩ አማካሪያቸው ለስዊዙ መሐንዲስ ለሙሴ አልፍሬድ ኢልግ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮመኒኬሽን ከቀድሞው የፖስታ፣ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ሚኒስቴር ሥር ወጥቶ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ በሚል ስያሜ ጥቅምት 5 ቀን 1945 ዓ.ም ራሱን ችሎ በአዋጅ ቁጥር 131/45 ተቋቋመ፡፡

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ደጃች ውቤ ሠፈር ከሚገኘው ከአሁኑ የሰሜን አዲስ አበባ ዞን /አራዳ ቴሌ/ ጽሕፈት ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ ቦርዱ በ1945 ዓ.ም ሲቋቋም የቴሌፎን ደምበኞቹ ቁጥር 3640፣ የመሥመር አቅሙ ደግሞ 4606 ነበር፡፡ በአስረኛ ዓመቱ በ1955 ጠቅላላ የደምበኞቹ ቁጥር 14..181 የመሥመር አቅሙ ደግሞ 17..865 ደርሶ ነበር፡፡

/ቴሌ ነጋሪት፣ 2000/


መሽቷል ካሉማ

ወጣቱ ጋብሮቮዬ የግንበኝነት ዕውቀት ለመቅሰም ካንድ ግንበኛ ዘንድ ተቀጥሮ ይሠራ ነበር፡፡ ይሁንና ሽማግሌው ተለማማጆቹን ከማለዳ እስከ ምሽት ድረስ እንዲሠሩ ያስገድዷቸው ስለነበረ ወጣቶቹ በጣም ይደክማቸው ነበር፡፡

ታዲያ አንድ ቀን አመሻሹ ላይ ወጣቱ ጋብሮቮዬ ጮክ ብሎ ግድግዳ ላይ የምትሔደውን አይጥ ተመለከቱ ጋሼ? ሲል ጠየቃቸው፡፡

ሽማግሌውም በጨለማ ዐይኔ አያይም ልጄ.. ብለውት ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡
እርስዎ መሽቷል ካሉማ የዕለቱ ሥራችን አብቅቷላ.. ብሎ ጋብሮቮዬው እንደተናገረም ወጣቶቹ በፍጥነት ቱታቸውን አወላልቀው ተፈተለኩ፡፡

/ዐረፈ ዓይኔ ሐጐስ፣ ከጋብሮቮ ምድር/

አበዳሪና ተበዳሪን ማቆራኘት

ቀድሞ በየሰንሰለትም ሆነ በነጠላ ጫፎች ተቆራኝተው በየመንገዱ የሚዘዋወሩ ተበዳሪና አበዳሪን ማየት በአገራችን የተለመደ ነበር፡፡ እዳውን በጉልበት ሥራ ወይም በገንዘብ ለመክፈል እስከሚችልበት ጊዜ ድረስ እንዳይሰወር በሚል አስተሳሰብ የተበዳሪ ቀኝ እጅ ከአበዳሪው ግራ እጅ ጋር በሰንሰለት እንዲቆራኝ ይደረጋል፡፡ አልያም የነጠላዎቻቸውን ጫፎች በማያያዝ ብቻ ይኸው ድርጊት ይፈፀማል፡፡ ከዚያም ተበዳሪ ከአበዳሪ ጋር በዚሁ መልክ እንዲቆይ ይበየንበታል፡፡ ይህም የተበየነበት ሰው አበዳሪው የእለት ተእለት ተግባሩን በሚያከናውንባቸውና በሌሎችም ቦታዎች ሁሉ የግድ አብሮ መገኘት ነበረበት፡፡ በሥራ ቦታ፣ በአደባባይ፣ በገበያ፣ በመጠጥ ቤቶችና በመሳሰሉት ሁሉ ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜም እዳው ከፍ ያለበትና የመክፈል አቅሙም ዝቅተኛ የሆነ ሰው በዚሁ መልክ ከአበዳሪው ጋር ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ችግሩን ተመልክተው ለመርዳት ፈቃደኛ ከሆኑ ሰዎች እርዳታ በመጠየቅና በመሰብሰብ እዳውን ሸፍኖ ነፃነቱን ያረጋግጥ እንደነበረም ይነገራል፡፡

የማቆራኘቱ ጉዳይ ደሃና ሀብታምን ሳይለይ ሁሉንም በእኩልነት የሚመለከት እንደነበረም አባቶች ይናገራሉ፡፡ ህግ ዝተትና ጃኖ ያቆራኛል የሚለው ምሳሌያዊ አነጋገርም ይህንኑ የሚያጠናከር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በእርግጥ ይህ አባባል ማንኛውም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆኑንና ኅብረተሰቡም ስለ ፍትህ የነበረውን የዳበረ ስሜት የሚጠቁም ይሁን እንጂ፣ ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚነትን አግኝቷል ብሎ ለመገመት አዳጋች ይሆናል፡፡

/ሺበሺ ለማ፣ ተጠየቅ፣ 1985/


ገራገር
ከሞት የተመለሰው አሳ አጥማጅ


አሳ ለማጥመድ እንደወጣ ሞቷል የተባለ ፖላንዳዊ በህይወት እንዳለ ቢገልፅም የአካባቢው ባለስልጣኖች ሊያምኑት አልቻሉም፡፡

ፒተር ኩሲ የተባለ የ37 ዓመት ጐልማሳ ሁኔታውን በማስመልከት ሲናገር ከአካባቢው አስተዳዳሪዎች ፊት ለፊት ቆሜ ተመልከቱኝ በህይወት አለሁ ብላቸውም ሊቀበሉኝ አልቻሉም ብሏል፡፡

ስዊኖጅሲ ከተባለችው የወደብ ከተማ ተነስቶ ለሁለት ሣምንት ያህል አሳ ለማጥመድ የተጓዘው ፒተር ኩሲ የአሳ ማጥመድ ቆይታውን አጠናቅቆ ወደ መኖሪያ ከተማው ሲመለስ መሞቱ ተነግሮታል፡፡

የከተማዋ አስተዳዳሪዎች አሳ አጥማጁ እንደሞተ አድርገው የወሰዱት በወደቡ ዳርቻ ያገኙትን ሰው አስከሬን በስህተት የፒተር ኩሲ አድርገው በመውሰዳቸው ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶም የአካባቢው ባለስልጣኖች ኩሲ በህይወት እንዳለ እውቅና ለመስጠት አልፈለጉም፡፡

አሳ ማጥመዴን ጨርሼ ከሁለት ሣምንት በኋላ ወደ መኖሪያ ቤቴ ስመለስ ቤተሰቦቼ በድንጋጤ ፈዝዘው ቀሩ፡፡ ሞቷል ብለው የቀበሩትን ሰው በህይወት ሲያገኙት ለምን አይደነግጡ? እኔ ለአሳ ማጥመድ በወጣሁበት ጊዜ በባህር ዳርቻው የሞተ ሰው ያገኙት የአካባቢው ፖሊሶች የሟቹን ማንነት ሲጠይቁ አንድ ጓደኛየ ሟቹ እኔን እንደሚመስል ተናገረ፡፡ ፖሊሶችም ምንም ሳያጣሩ እኔ እንደሞትኩ አድርገው አወጁ በማለት ኩሲ የተፈጠረውን አጋጣሚ አብራርቷል፡፡

በካባቸው ኮኬይን የያዙት ቄስ ታሰሩ

የካቶሊክ ቄስ ነኝ ያሉ አንድ ግለሰብ በካባቸው ወስጥ ኮኬይን ይዘው በመገኘታቸው በአምስተርዳም አየር ማረፊያ ታሰሩ፡፡ የሆላንድ ፖሊስ እንደገለፀው ስማቸው ያልተጠቀሰው ተጠርጣሪ በሀይማኖታዊ ምክንያት ፍተሻ እንዳይደረግባቸው ተከላክለው ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ፖሊስ ብቻቸውን ወደ ሌላ ቦታ በመውሰድ ሲፈትሻቸው በካባቸው ውስጥ 7 ፓውንድ ኮኬይን ተገኝቷል፡፡

ኮኬይን በህገ ወጥ መንገድ የሚተላለፍባቸውን ብዙ ዓይነት ነገሮች አይተናል በቤዝቦል፣ በወይን ጠርሙስና በመሳሰሉት ኮኬይን ለማሳለፍ የሚሞክሩ ሰዎችን ይዘናል በካባ ውስጥ ኮኬይን የያዘ ሰው ስናገኝ ግን የአሁኑ የመጀመሪያ ነው በማለት የአምስተርዳም የፖሊስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል፡፡

ከቦሊቪያ ተነስተው ወደ አምስተርዳም የተጓዙት ግለሰብ እስከመጨረሻው ድረስ ቄስ መሆናቸውንና መብታቸውም እንደተጣሰ ገልፀዋል፡፡

የሮማው ጳጳስ የእግር ኳስ ጨዋታ ይደግፋሉ

እግር ኳስ የህይወትን ጠቀሜታ ለወጣቶች ለማስተማር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የሮማው ካቶሊክ ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ ገለፁ፡፡

ጳጳሱ እንዳሉት ውበት ያለው የእግር ኳስ ጨዋታ ለወጣቶች ታማኝነት፣ አንድነትንና ወንድማማችነትን ያስተምራል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት እየተስፋፋ ያለው ሙስና የእግር ኳስን ጥሩ ገፅታ እንዳያበላሸው ስጋት ያደረባቸው መሆኑን ቤኔዲክት 16ኛ ጠቁመዋል፡፡

የባየር ሙኒክ ቡድን ደጋፊ መሆናቸው የሚነገርላቸው የካቶሊኩ ጳጳስ ከጣሊያን እግር ኳስ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው በተነጋገሩበት ሰዓት እግር ኳስ ጨዋታ ወደ ታማኝነት አንድነትና ወንድማማችነት የሚመራ ድልድይ እንዲሆን እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡ የጣሊያን እግር ኳስ ከሙስና ጋር በተያያዘ ብዙ ውዝግብ ተከስቶበት መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ከእግር ኳስ ጋር በተያያዘ ብጥብጥም የሊጉ ውድድር ሁለት ጊዜ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ጳጳሱም ወደ ጣሊያን እግር ኳስ ትኩረታቸውን ሲያደርጉ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

ሟች ጓደኛቸውን በጐዳና ላይ ያዘዋወሩ ተያዙ

ሟች ጓደኛቸውን በቢሮ ወንበር ላይ አስቀምጠው በጐዳና ላይ እየገፉ ሲያዘዋውሩ የነበሩ ግለሰቦች ኒውዮርክ ውስጥ ታሰሩ፡፡ ሰዎቹ ሟቹን በጐዳና ላይ ሲገፉት የነበረው በህይወት ያለ አስመስለው የሰውየውን ገንዘብ ከባንክ ቤት ለማምጣት በማሰብ ነው፡፡

ዴቪድ ዳልያና ጀምስ ኦሀሬ የተባሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የሟች ጓደኛቸውን አስከሬን ከሚኖርበት አፓርትማ አውጥተው በአካባቢው ወደሚገኘው የቼክ መመንዘሪያ ሲወስዱት ነው በፖሊስ የተያዙት፡፡

የዓይን እማኞች እንደገለፁት ሟቹ ግለሰብ በወንበር ላይ ሆኖ ከአንድ ጐን ወደሌላው ጐን ሲያዘነብል ተጠርጣሪዎቹ እየተከታተሉ ያስተካክሉት ነበር፡፡

ግለሰቦቹ የጓደኛቸውን 180 ፓውንድ ቼክ ለመመንዘር ወደ ባንክ ሲሄዱ የባንኩ ሠራተኛ ሟቹን ግለሰብ ያውቃቸው ስለነበር ሰውየውስ? ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቸም ውጭ ነው ያለው እናመጣዋለን ብለው ሟቹን ወዳስቀመጡበት ቦታ ሲሄዱ አስከሬኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ አግኝተውታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ቼክ በማጭበርበር ወንጀል እንደሚከሰሱ ታውቋል፡፡

 
< Prev   Next >