| የወ/ት ብርቱካን ቅንጅት ውሳኔዎችን አሳለፈ |
|
|
| Sunday, 06 January 2008 | |
|
የአቶ ኃይሉ ቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባ ሊጠራ ነው በወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ሦስት ውሳኔዎችን ማሳለፉ ታወቀ፡፡ በውሳኔው መሠረት ለኘሬዚዳንቱ አቶ ኃይሉ ሻወል ደብዳቤ ይፃፋል፡፡ የአቶ ኃይሉ የሚመራው ቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባ ሊጠራነው፡፡ ባለፈው እሁድ ከሃያ በላይ አባላት የተሳተፉበት ስብሰባ የተጓደሉ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት በሌሎች እንዲተኩ መወሰኑን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ የማሟያ ምርጫ በአስቸኳይ እንዲካሄድ ኃላፊነቱ ለሥራ አስፈፃሚዎች ተሰጥቷል፡፡ ኘሬዚዳንቱ አቶ ኃይሉ ሻወልን በተመለከተ የቀረበው አጀንዳ ኘሬዚዳንቱ አምስት የፓርቲውን አመራሮች ያገዱበትና አቶ አባይነህ ብርሃኑን የወከሉበት አግባብ የፓርቲውን ህግና ደንብ ያልተከተለ፣ በደንቡ የተሰጣቸውን ሥልጣን የተላለፈ በመሆኑ ለሰሩት ጥፋት ምን ዓይነት ርምጃ ይወሰድ? የሚል ሲሆን አባላቱ በስፋት እንደተከራከሩበት ከእነዚሁ ምንጮች ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ..በሰሩት ጥፋት ለዲስፒሊን ኮሚቴ ቀርበው ይቀጡ.. በሚሉና ..በላዕላይ ኮሚቴው አማካይነት ይቀጡ.. በሚሉት ሁለት የቅጣት አማራጮች ተሰብሳቢዎቹ ተጨቀጭቀው እንደነበር የገለፁት ምንጮቻችን ..ኘሬዚዳንቱ ያጠፉት ጥፋት ከፍተኛ በመሆኑ በዲሲፒሊን ኮሚቴ ይቀጡ ማለት ጉዳዩን ማሳነስ ነው.. የሚል መከራከሪያ ቀርቦ ነበር፡፡ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን መቆጣጠርና ጥፋት ካጠፉ ርምጃ የመውሰድ ሥልጣን የተሰጠው የላዕላይ ምክር ቤቱ ኘሬዚዳንቱ ላይ ርምጃ እንዲወስድ የቀረበው ሀሳብ በመጨረሻ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በዚሁ መሠረት ኘሬዚዳንቱ የሰሩት ጥፋት ተጠቅሶ፣ ወደፊት ተመሳሳይ ጥፋት ከመስራት እንዲቆጠቡ የማጠይቅ ነገር ግን የሚወሰድባቸውን ርምጃ ወደፊት የማያሳውቅ ደብዳቤ እንዲደረሳቸው እንዲደረግ መወሰኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ ለጊዜው ኘሬዚዳንቱ ላይ ርምጃ የማይወሰደው የሚወስደው ርምጃ በላዕላይ ምክር ቤቱ አባላት 2/3 ድምፅ መደገፍ ስላለበት ነው፡፡ ..ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ኘሬዚዳንቱ ላይ የሚወሰን ማንኛውም የቅጣት ውሳኔ እሳቸው የሰሩትን ህግን የመተላለፍ ጥፋት መድገም ነው.. በሚል ተሰብሳቢዎቹ መስማማታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተወሰነው በቅርቡ በኘሬዘዳንቱ ውክልና የተሰጣቸው አቶ አባይነህ ብርሃኑን የሚመለከተው ጉዳይ ነበር፡፡ ምንጮቻችን እንዳስታወቁት ለአቶ አባይነህ የተሰጠው ውክልና ህገወጥ መሆኑና እሳቸውም ሆኑ በስራቸው ያሉ በቅንጅት ስም ማንኛውንም መግለጫ ከመስጠት እንዲቆጠቡ የሚያደርግ ውሳኔ ተወስኗል፡፡ ባለፈው እሁድ በወ/ት ብርቱካን ማደቅሳ የሚመራው ቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባውን ለሦስተኛ ጊዜ በማድረግ ባሉት አባላት የሚወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ እንደሚሆን አቶ ሙሉነህ ኢዮዌልን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ እንደ እሳቸው እምነት ውሳኔው ለቅንጅት ..ታሪካዊ ነው.. ተብሏል፡፡ በሌላ ዜና በኢንጅነር ኃይሉ ሻወል ውክልና የተሰጠውና በአቶ አባይነህ ብርሃኑ የሚመራው ቅንጅት በቅርቡ የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባ እንደሚጠራ አስታወቀ፡፡ አቶ አባይነህ ብርሃኑ በተሰጣቸው ውክልና መሠረት ፓርቲያቸው የተነሳለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ለሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ተገቢውን ሁሉ እንደሚያመቻቹ አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡም የላዕላይ ምክር ቤት ስብሰባ ለማካሄድ ጥሪ የሚደረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ፓርቲው በቀድሞው አንድነቱ ፀንቶ እንዳይቀጥል ጥቂት የአመራር አባላት አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ማካሄድ እንደጀመሩና አሁንም በስፋትና በጥልቀት የቀጠሉበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ አባይነህ እገዳ ከተጣለባቸው አምስት የአመራር አባላት በስተቀር ለማንኛውም የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ የላዕላይ ምክር ቤት አባላትና ደጋፊዎች የቅንጅቱ ፅህፈት ቤት ለፓርቲው መደበኛ ሥራና ለስብሰባ ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |